Friday, May 2, 2014

ተቤዢዬ ሕያው ነው!

                            Please Read in PDF: Tebeziye Heyaw New
 
                          አርብ ሚያዝያ 24 ቀን 2006 የምሕረት ዓመት
 
           ‹‹ምነው አሁን ቃሌ ቢጻፍ! ምነው በመጽሐፍ ውስጥ ቢታተም! ምነው በብረት ብዕርና በእርሳስ በዓለቱ ላይ ለዘላለም ቢቀረጽ! እኔን ግን የሚቤዠኝ ሕያው እንደ ሆነ፥ በመጨረሻም ዘመን በምድር ላይ እንዲቆም፥ ይህ ቁርበቴም ከጠፋ በኋላ፥ በዚያን ጊዜ ከሥጋዬ ተለይቼ እግዚአብሔርን እንዳይ አውቃለሁ። እኔ ራሴ አየዋለሁ፥ ዓይኖቼም ይመለከቱታል፥ ከእኔም ሌላ አይደለም። ልቤ በመናፈቅ ዝሎአል።››
(ኢዮ. 19÷23-27)፡፡

           ስለ ቃል ብርታት፤ የሚናገርና የሚሰማ ሁሉ ልብ ይለዋል፡፡ በቃል የቀኑ፤ በቃል የወደቁ፤ በቃል የተጽናኑ፤ በቃል የተሰበሩ፤ በቃል የተሰበሰቡ፤ በቃል የተበተኑ፤ በቃል የጸኑ፤ ቃል ኪዳን ያፈረሱ፤ በቃል ያመለጡ፤ በቃል የተያዙ ምድሪቱ ላይ እንደ ትቢያ ናቸው፡፡ የመጽሐፉ ኢዮብ መልካምንና ክፉን፣ ደስታና ሀዘንን፣ ማግኘትና ማጣትን፣ መክበርና ውርደትን ያየ፤ ሁለቱንም የኑሮ ጽንፍ የነካ ነው፡፡ እንዲህ ያለው ኢዮብ በአሥራ ዘጠነኛው ምዕራፍ ላይ አንዳች እንዲፃፍለት የፈለገውን ቃል በተማጽኖ ጭምር ይነግረናል፡፡ ብዙ ሰው የግል ማስታወሻ ወይም ዲያሪ እንዳለው ልብ እንላለን፡፡ እንደዚህ ያሉ የግል ማስታወሻዎች ዕንባና ፈገግታ፤ መከፋትና ቡርቅታ፤ ተስፋና ሥጋት የሰፈረባቸው ዥንጉርጉር ናቸው፡፡ ለዚህ ጽሑፍ ዝግጅት የተጠና ነገር ለማቅረብ ጊዜው ባይኖረኝም አብዛኛው የጽሑፍ ይዘት መከፋትንና ቅዝቃዜን ማዕከል ያደረገ እንደ ሆነ ይሰማኛል፡፡ በተለይ ለመፃፍ እንደ ሰበብ የሚሆነው ነገር፤ ከሌላው ወደ እኛ የሚመጡ ስብራትና ተስፋ አስቆራጭ ነገሮች ናቸው፡፡

         ኢዮብ ወደዚህ ምድር መምጣቱን የኮነነ፤ የመቃብር ሙቀትን የተመኘ፤ ሥጋውን በጥርሱ ነክሶ ያዘነ፤ በገዛ ወዳጆቹ ግብዝነት የተከበበ፤ ከአምላኩ ጋር ሙግት የገጠመ የመከራ ሰው ነው፡፡ በሕይወቱ ከገጠመው ብርቱ ፈተና የተነሣ የሚናገራቸው እያዳንዱ ቃል በስቃይና ሮሮ የተለወሱ ናቸው፡፡ በመጽሐፉ የተለያዩ ምእራፎች ውስጥ ጠንካራ ጩኸቱንና ያልተቋረጠ ክርክሩን እናነባለን፡፡ እንደዚያ ባለ ስቃይ ውስጥ፤ የወዳጆቹ ፍርደ ገምድልነት፤ የሚስቱ ስንፍና ተጨምሮ ኑዛዜ በሚመስለው ቃሉ ውስጥ ለሥጋ ለባሽ ሁሉ መፍትሔ የሆነ ነገርን ሲናገር ልብ እንላለን፡፡


         ኢዮብ በጨለማው ዘመን (በጨለማ የሔደ ሕዝብ እንዲል መጽሐፍ)፤ በሞት አገልግሎት መካከል፤ ‹‹አቤቱ እባክህን አሁን አድን፤ እባክህን አሁን አቅና›› የሚል ድምጽ የእግዚአብሔርን ዙፋን በከበበት ሁኔታ፤ በግል ሕይወትና በቤተሰቦቹ ላይ ሕይወትን ያሳለፈ መከራ በተቀበለበት ወቅት እሮሮው ሳይሆን ቤዛው፤ የአሁኑ ሳይሆን የሚመጣው፤ ሞቱ ሳይሆን ትንሣኤው እንዲፃፍ በጽናት ተመኘ፡፡ ‹‹ምነው በብረት ብእርና በእርሳስ በዐለት ላይ ለዘላለም ቢቀረጽ›› ኢዮብ በጊዜ ውስጥ ሆኖ የዘላለሙን፤ በምድር ሆኖ የሰማዩን፤ ሥጋው ቆስሎ መንፈሳዊውን አስተዋለ፡፡ ስለ ቤዛውና ከሞት በኋላ ስለ መነሣቱ እርግጠኛነት እምነቱን በገለጠበት በዚህ ክፍል ልቡ የዛለበት ናፍቆቱንም ገለጠ፡፡

         ከመከራው በፊት የነበረው ምቾት አልያም ማጣቱን ተከትሎ የመጣው ሥቃይ፤ በእግዚአብሔር ፊት  የሠራው መንፈሳዊ ትሩፋት ወይም ሁሉን በሚችል አምላክ ላይ የተናገረው ክርክር፤ የሚስቱና የባልንጀሮቹ የስንፍና ቃል አልያም የግሉ ምሬት እንዲፃፍ ሳይሆን ሕያው የሆነ ቤዛው አንድ ቀን በምድር ላይ እንደሚቆምና እንደሚቤዠው ይፃፍለት ዘንድ ጠየቀ፡፡ ይህም ‹‹ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ›› (ገላ. 4÷4) የሚለውን ቃል ወደ አእምሮአችን ያመጣልናል፡፡ ለሁሉ የሞተው አንዱ ቤዛ ኢየሱስ ክርስቶስ በሰው መካከል ሰው ሆኖ በምድር ላይ የተመላለሰበትን የሥጋውን ወራት ልብ ይሏል፡፡ የእኛ ቤዛ በቀደመው ኪዳን ውስጥ ለኖረው ለኢዮብም ቤዛው ነው፡፡ የአብርሃም፣ የይሳቅና የያዕቆብ ቤዛ የእኛም ቤዛ ነው (መዝሙራችን ‹‹የይስሐቅ ቤዛ፤ ወገኖቹን በደሙ ገዛ›› እንዲል)፡፡ እነርሱን ሌላ፤ እኛን ደግሞ ሌላ ቤዛ አልተቤዠንም፡፡ ቅዱሳት መጻህፍት በግልጥ እንደሚናገሩት ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት የሞተ የሕማም ሰው፤ ደዌንም የሚያውቅ ‹‹አንድ ቤዛ›› አለ፤ እርሱም ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፡፡

        የተቤዠንበት መንገድም ልዩ ልዩ አይደለም፡፡ በክርስቶስ ደም መፍሰስ፤ ስርየትን ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግስት ፈልሰናል (ቆላ. 1÷13)፡፡ ‹‹ደም ሳይፈስ ስርየት የለም›› በሚለው መርኅ መሰረት በቀደመው ኪዳን ለኃጢአተኞች የእንስሳት ደም ሲፈስ ቆይቷል፡፡ ያ ግን ኃጢአትን ከመክደን ባለፈ ወደ ማንፃት ሊያደርስ አልቻለም፡፡ በደሙ የሆነ የክርስቶስ ቤዛነት ግን ከኃጢአት ሁሉ የሚያነፃን ሆኖልናል፡፡ ኃጢአተኛ ሁሉ በእርሱና በእግዚአብሔር መካከል መካከለኛ መሥዋዕት ባልቆመበት ሁኔታ ሁሉን የሚችል አምላክን ፊት ማየት አይችልም፡፡ አቤልና ቃየልን ስንመለከት በእነርሱና በእግዚአብሔር መካከል መሠዊያን ሲያደርጉ መሥዋዕት ሲያቀርቡ እናያቸዋለን፡፡ አቤል ደም ሳይፈስ ስርየት የለም! የሚለውን መመሪያ ተግባራዊ በማድረግ ከበጎቹ በኩራትና ከስቡ ለእግዚአብሔር መሥዋዕትን አቀረበ (ዘፍ. 4)፡፡ ‹‹ስለዚህም የፊተኛው ኪዳን ሲጸና ሕግን የተላለፉትን የሚቤዥ ሞት ስለ ሆነ፥ የተጠሩት የዘላለምን ርስት የተስፋ ቃል እንዲቀበሉ እርሱ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ነው›› (ዕብ. 9÷15)፡፡     

        እግዚአብሔር በዚያ መሥዋዕት ውስጥ እንደተወደደ የመዓዛ ሽታ መባንና መሥዋዕትን አድርጎ  ስለ እኛ ራሱን ቤዛ አድርጎ ያቀረበውን ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ያይ ነበር (ኤፌ. 5÷2)፡፡ የብሉይ ኪዳን መሥዋዕቶች ኢየሱስ ክርስቶስን የማሳየታቸው አስተምህሮም በዚህ የተደላደለ እውነት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡  ኢዮብን በተመለከተ ‹‹ማልዶ ተነሣ፥ እንደ ቍጥራቸውም ሁሉ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ። እንዲሁ ኢዮብ ሁልጊዜ ያደርግ ነበር›› (ኢዮ. 1÷5) ተብሎ ተጽፎአል፡፡ ነገር ግን በሌላ ስፍራ ደግሞ ኢዮብ ‹‹እኔን ግን የሚቤዠኝ ሕያው እንደ ሆነ›› በማለት ሊመጣ ያለውን እውነተኛ ቤዛ ይነግረናል፡፡ ዕለት ዕለት ያቀርበው የነበረው መሥዋዕት እርሱንና ልጆቹን ለእግዚአብሔር ከመቀደስ (ከመለየት) ባለፈ ፍጹም የኃጢአትን ሥርየት ማምጣትና መዳንን መፈጸም አልተቻለውም፡፡

       ተወዳጆች ሆይ፤ ቅዱሳት መጻህፍትን በተመለከተ ሚዛናው መሆንና አጥርቶ መመልከት ያስፈልጋል፡፡ ብዙ ሰዎች መጽሐፈ ኢዮብን በተመለከተ ከመከራና ከፈተና ጋር በተያያዘ ካልሆነ በቀር የተለየ የመለኮት ጥልቅ አሳብና ጠንካራ ትምህርት ያለው መጽሐፍ አይመስላቸውም፡፡ እውነትን መሰረት አድርገን ባልታየበት በኩል ለማየት ብንሞክር ለሕይወት የሚሆኑ ታላላቅ ቁም ነገሮችን እንረዳለን፡፡ የእግዚአብሔር አሳብ ከአሳባችን፤ መንገዱ ከመንገዳችን ልዩ (ኢሳ. 55÷8) እንደ ሆነ ከተነገረን፤ አሳባችን ላይ ሙጭጭ ማለት ስንፍና ነው፡፡ ወደ እግዚአብሔር አሳብ ለመጠጋት፤ ፍለጋውንም ለመከተል ብርታትን ማሳየት ግን ጽድቅ ነው፡፡

       በዓለማችን ላይ የብዙ ሰዎች ቃል ተጽፎአል፡፡ በመጽሐፍም ታትሞአል፡፡ አልፎም ተርፎ በዐለት ላይ ተቀርጸው የሚጎበኙ፤ የሚነበቡ ጽሑፎችንም ማስተዋል እንችላለን፡፡ አብዛኛዎቹ ለትምህርትና ለጥናት ጥቅም ላይ የዋሉ ማጣቀሻዎች ጭምር ናቸው፡፡ ዳሩ ግን ማንም ሰው ከእነዚህ ጽሑፎች ጋር መቃብርን ስለ መሻገር፣ ሞትን ድል ስለ መንሣት፤ ጽድቅን ስለ ማግኘት፤ አንድ አዲስ ዓለምን ስለ መውረስ አያወጋም፤ እነርሱም አያወሩትም፡፡ ከጊዜያዊ ሞቅታ፤ ሥጋን አድራሻ ካደረገ ደስታ፤ አሁንም አምጣ አምጣ ከሚል መጠማት፤ ማብቂያ ከሌለው የአሳብ ዙረት አያሳርፉም፡፡

       እናንተ ሆይ፤ ምን ቢፃፍላችሁ ትወዳላችሁ? ምርጫችሁ የወለደው ቋሚ ሥቃይ፤ ሰዎች ሰፍተው ያለበሷችሁ ማቅ፤ በደጃችሁ የሚያደባው የዲያብሎስ ወጥመድ፤ ወደ እናንተ ስለሚወረወር ቀስትና ፍላፃ፤ ልባችሁ ስለደማበት፤ አካላችሁ ስለቆሰለበት አጋጣሚ፤ ደጃፋችሁን ቆልፋችሁ፤ አንገታችሁን ጭናችሁ ስር ቀብራችሁ ዓይናችሁ ፍም እስኪመስል ስላለቀሳችሁበት ጊዜ፤ እመጣለሁ! እያለ የውኃ ሽታ ስለ ሆነው ተስፋችሁ አልያስ እንቁልልጭ ስለሆነባችሁ ነገር፤ ስለ ምን ይፃፍላችሁ? ስለ ስኬታችሁ ነውን? ሮጣችሁ ስላመለጣችሁበት፤ ጨብጣችሁ ስላስጨነቃችሁበት፤ ተናግራችሁ ስላስደሰታችሁበት፤ ሠርታችሁ ስላደማችሁበት ቀን፤ ስለ ምን ይፃፍላችሁ? ስለከበባችሁ ምቾት ነውን? ስላጠናችሁት እውቀት፤ ስለደረሳችሁበት ጥበብ፤ ስለከበቧችሁ ወዳጆች፤ ገንዘባችሁ ስለገዛቸው ባሪያዎች፤ ደግሳችሁ ስላበላችሁት ወገን፤ መጽውታችሁ ስለሞላችሁት ጓዳ፤ ቤታችሁ ስላስተናገደው ፈገግታ፤ ስለተቀበላችኋቸው እንግዶች፤ ምን ይፃፍላችሁ?

       ስለዘረጋችሁት ጉባኤ፤ ስላስተማራችሁት ምዕመን፤ ልብ ስላረፈበት ዝማሬአችሁ፤ ሰዎች ስለተመሰጡበት ቅዳሴ፤ ዓይን ስላማለለው ዝማሜ፤ ሙገሣን ስለተቀበለው ቅኔያችን፤ እልልታና ጭብጨባ ስለተቸረው አገልግሎታችን፤ አንቱ ስላሰኘን መጽሐፍ፤ በሰዎች እጅ ላይ ስለምናየው ድጉስ፤ ተወዳጆች ሆይ፤ ስለ ምን ይፃፍላችሁ? ቃላችሁ ቢፃፍ ምን ትላላችሁ፤ በመጽሐፍ ቢታተም ምን ታስነብባላችሁ፤ በብረት ብዕርና እርሳስ በዐለት ላይ ለዘላለም ብታስቀርጹ ምን ታስቀርጻላችሁ?

       ምቾት ቢሆን ሥቃይ ቢሆን፤ ማግኘት ቢሆን ማጣት ቢሆን፤ ስኬት ቢሆን ውድቀት ቢሆን፤ ክብራችን ቢሆን ውርደታችን ቢሆን በእግዚአብሔር ጽድቅ ፊት አያቆመንም፡፡ ሰው የትኛውንም መልካምነት ቢያጽፍ፤ በጎነት ቢያስቆጥር ጽድቅ የእግዚአብሔር፤ ማዳን የመለኮት ነው፡፡ ኢዮብ ብልጥግናዬ ምነው በተፃፈ? አላለም፡፡ ደግሞ ሥቃይና እንግልቴ በዐለት ላይ ተቀርፆ ለመጪው ትውልድ ምነው በቀረልኝም አላለም፡፡ ዕለት ዕለት በእግዚአብሔር ፊት ያቀርብ ስለነበረው መሥዋዕት፤ ለሌሎች ስላሳየው ርኅራኄ፤ ለሚስቱ ስለመለሰው የብርታት ቃል፤ ልጆቹን በእግዚአብሔር አሳብ ታጥቆ እንዳሳደገ፤ በሰዎች ላይ ግፍ እንዳልሠራ፤ የማንም ዕዳ እንዳላለፈበት ይፃፍልኝ አላለም፡፡ ዳሩ ግን የሚቤዠው ሕያው እንደ ሆነ፤ በመጨረሻም ዘመን በምድር ላይ እንዲቆም፤ ቁርበቱም ከጠፋ በኋላ፥ በዚያን ጊዜ ከሥጋው ተለይቶ እግዚአብሔርን እንዲያይ ማወቁን፤ ይፃፍልኝ አለ። ይህ ምንኛ አስደናቂ ትምህርት ነው?

       ሐዋርያው ‹‹ልጆቼ ሆይ፥ ክርስቶስ በእናንተ እስኪሣል ድረስ ዳግመኛ ስለ እናንተ ምጥ ይዞኛል›› (ገላ. 4÷19) እንዳለ፤ በክርስቶስ ክርስቲያን ለተሰኘን ሁሉ የተቤዠን ጌታ፤ የተፃፈ ቃል፤ በመጽሐፍ የታተመ ጽሑፍ፤ በዐለትም ላይ የተቀረጸ ምስል ሳይሆን ‹‹በእኛ የተሣለ›› ነው፡፡ የክርስቶስን ፍኖት የተከተሉ ቀደምት አባቶች ‹‹ምጣቸው /መከራቸው/›› አንድ ነበር፡፡ እርሱም ክርስቶስን በሰዎች ሕይወት ላይ መሣል፤ በልብ ላይ መቅረጽ፤ በሕሊና ላይ መፃፍ፡፡ ወረቀት ላይ ቢሆን ውኃ ያጥበዋል፤ የተፃፈበት ቀለም ይለቃል፡፡ ዐለቱ ላይ ቢሆን የዘመናት ርዝማኔ፤ የመሬት መንቀጥቀጥ ይፈረካክሰዋል፤ ይሰነጣጠቃል፡፡ በእናንተ ሕይወት ላይ የተቀረጸው ኢየሱስ ግን ብትሞቱም እንኳን ሕያው ያደርጋችኋል (ዮሐ. 11÷25)፡፡ ከሙታን ተለይቶ፤ በዝግ መቃብር የተነሣው፤ የትንሣኤያችን በኩር በትውልዱ ላይ እስኪሳል ድረስ ዛሬም እኛ ምጥ ላይ ነን፡፡ ‹‹ልናገር እንደሚገባኝ ያህል እገልጠው ዘንድ ጸልዩልኝ።›› (ቆላ. 4÷4)!

በክፍሉ ላይ ተጨማሪ ጥናት ለማድረግ ለምትፈልጉ፡
·        ኢዮ. 33÷19-28፤ ኢሳ. 44÷1-6

·        ሉቃ. 2÷25-32፤ 2÷36-38 ብሉይ ኪዳን ጥቅሱን ከአዲስ ኪዳን አካሉ ክርስቶስን በሚገልጥበት አውድ ውስጥ ሆናችሁ ለማስተዋል ሞክሩ፡፡ ጸጋ ይብዛላችሁ!

6 comments:

  1. ቃለ ሕይወት ያሰማልን!!! በእውነት የሁልጊዜ ጥማቴ ፍፁም ወደ ሆነው እግዚአብሔርን የመምሰል ሕይወት ማደግ ነው። እግዚአብሔር ሁላችንንም ይርዳን።

    ReplyDelete
  2. ‹‹ስለዚህም የፊተኛው ኪዳን ሲጸና ሕግን የተላለፉትን የሚቤዥ ሞት ስለ ሆነ፥ የተጠሩት የዘላለምን ርስት የተስፋ ቃል እንዲቀበሉ እርሱ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ነው›› (ዕብ. 9÷15)፡፡

    ReplyDelete
  3. ‹‹ልጆቼ ሆይ፥ ክርስቶስ በእናንተ እስኪሣል ድረስ ዳግመኛ ስለ እናንተ ምጥ ይዞኛል›› (ገላ. 4÷19) kale hiwot yasemalen!

    ReplyDelete
  4. ወረቀት ላይ ቢሆን ውኃ ያጥበዋል፤ የተፃፈበት ቀለም ይለቃል፡፡ ዐለቱ ላይ ቢሆን የዘመናት ርዝማኔ፤ የመሬት መንቀጥቀጥ ይፈረካክሰዋል፤ ይሰነጣጠቃል፡፡ በእናንተ ሕይወት ላይ የተቀረጸው ኢየሱስ ግን ብትሞቱም እንኳን ሕያው ያደርጋችኋል ፡፡

    ReplyDelete
  5. ወረቀት ላይ ቢሆን ውኃ ያጥበዋል፤ የተፃፈበት ቀለም ይለቃል፡፡ ዐለቱ ላይ ቢሆን የዘመናት ርዝማኔ፤ የመሬት መንቀጥቀጥ ይፈረካክሰዋል፤ ይሰነጣጠቃል፡፡ በእናንተ ሕይወት ላይ የተቀረጸው ኢየሱስ ግን ብትሞቱም እንኳን ሕያው ያደርጋችኋል Amen!!!!!!!!!!!!

    ReplyDelete
  6. ወረቀት ላይ ቢሆን ውኃ ያጥበዋል፤ የተፃፈበት ቀለም ይለቃል፡፡ ዐለቱ ላይ ቢሆን የዘመናት ርዝማኔ፤ የመሬት መንቀጥቀጥ ይፈረካክሰዋል፤ ይሰነጣጠቃል፡፡ በእናንተ ሕይወት ላይ የተቀረጸው ኢየሱስ ግን ብትሞቱም እንኳን ሕያው ያደርጋችኋል Amen!!!!!!!!!!!!

    ReplyDelete