Wednesday, July 31, 2013

ካፈርኩ አይመልሰኝ (ካለፈው የቀጠለ)


                                እሮብ ሐምሌ 24/2005 የምሕረት ዓመት

“ቃየንም ወንድሙን አቤልን፡- ና ወደ ሜዳ እንሂድ አለው። በሜዳም ሳሉ ቃየን በወንድሙ በአቤል ላይ ተነሣበት፥ ገደለውም” (ዘፍ. 4÷8)፡፡

        ግንኙነትን አስመልክቶ የሚያሻክሩ ምክንያቶችን ከአንድ እስከ አምስት ነጥቦች ባለፈው ንባባችን ለማየት የሞከርን ሲሆን በዚህ ክፍል ደግሞ ቀሪ ምክንያቶችን የምንዘረዝርና ርእሳችንን በደንብ የምናብራራ ይሆናል፡፡

6. ሁሉም ጥሩ ወይም ሁሉም መጥፎ፡- እንደዚህ ያሉ ሰዎች ማንኛውንም ነገር ነጭ ነው አልያም ጥቁር ነው፣ መልካም ነው አልያም መጥፎ ነው ከማለት ውጪ ነገሮችን በሚዛናዊነት ለመዳኘትና ከተለያየ አቅጣጫ ለማየት ጥረት አያደርጉም፡፡ ሁሉም ነገር ለእነርሱ ከሁለት አንዱ ነው፡፡ እንዲህ ያለው አመለካከት ግንኙነትን ሚዛን ያሳጣል፡፡ ሁሉም መጥፎ እንደ ሆነ በምናስብበት ሁኔታ ውስጥ ስንሆን ደጉን ነገር ለመመልከት ጭፍኖች እንሆናለን፡፡ ሁሉም ጥሩ እንደ ሆነ በምናስብበት ሁኔታ ደግሞ ኑሮአችን ጥንቃቄ የጎደለው “በሬ ከአራጁ ጋር ይውላል” አይነት ይሆንብናል፡፡ ተወዳጆች ሆይ ሚዛናዊ ሁኑ!

7. ለፍርድ መቸኮል፡- በሰው የመፍረድ ዝንባሌ ግንኙነትን ጉዳት ላይ ይጥለዋል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ በዚህ መንገድ የመተያየት ልማዳዊ አለማስተዋል ይስተዋላል፡፡ ነገር ግን በዚህ መንገድ ሰዎችን ማስተካከል አይቻልም፡፡ ደግሞ አብዝተን በምንፈርድባቸው ነገሮች ዘግይቶም ቢሆን ራሳችንን እናገኘዋለን፡፡ ታዲያ እውነተኛነት እኛ በደከምን ጊዜ ለድካማችን የምናሳየውን ርኅራኄ ለሌሎችም ውድቀት እንዲሁ ማሳየት ማለት ነው፡፡ ለመፍረድ አለመቸኮል ያበላሸ እንዲያስተካክል እድል መስጠት ነው፡፡ አለመፍረድ የወደቀ እንዲቆም መደገፍ ነው፡፡ እስቲ በዛላችሁባቸው ወራቶች በቁስላችሁ ላይ እንጨት የሰደዱባችሁን አስቡ፡፡ ምን ያህል ከባድ ነበር? እናንተ ግን ፈጽማችሁ እንዲህ አታድርጉ፡፡ ፍርድን ለጌታ ስጡ!     

8. አሳብ ማንበብ፡- ብዙ ሰዎች የሌሎችን አሳብ ማንበብ እንደሚችሉ ይሰማቸዋል፡፡ ነገር ግን እንዲህ ያለው ሁኔታ በእለት ከእለት ግንኙነቶቻችን ላይ ተጽእኖው ከፍተኛ ነው፡፡ ልትል የፈለከው ገብቶኛል . . . ገና ሳትናገር ሁኔታህ ይነግረኛል . . . ብዙ አትድከም አሳብህን መቼ አጣሁት . . . የሚሉት ቃላቶች ባይሰሙንም ግንኙነቶቻችንን እንደ ብል በልተው ለጉዳት የሚዳርጉ ልማዶች ናቸው፡፡ ማንም ሰው የሌላውን አእምሮ (አሳብ) የማንበብ አቅም የለውም፡፡ ባልተገለጠ አሳብ ውስጥ ያለው መብት የአሳቢው ብቻ ነው፡፡ በቃል አልያም በአካል እንቅስቃሴ (በተግባር) መገለጥ ያልቻለ አመለካከት ምስጢር ነው፡፡ አፍ ሲከፈት ጭንቅላት ይታያል እንዲሉ የሰዎች አሳብ ሲገለጥ ብቻ የምናየው ነገር ይኖራል፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን ያውም አቅማችን ባልሆነ ነገር ግንኙነቶቻችንን መጉዳት አይኖርብንም፡፡


        ሰዎችን የማዳመጥ ዝንባሌ ማዳበር ጥሩ ነው፡፡ እግዚአብሔር አንድ ምላስ ሁለት ጆሮ የሰጠን “ጥቂት አውሩ፤ ብዙ አድምጡ” ብሎ ነው እንደሚባለው በማያወሩ ሰዎች ፊት እንኳ ትንፋሻቸውን አድምጡ፡፡ ብዙ ጊዜ እርሱ ዓይን አፋር ነው አያወራም . . . እሷ የቤት ልጅ ናት አትናገርም . . . የሚሉ አባባሎችን እንሰማለን፡፡ የቤት ልጅ መገለጫው አለመናገር ሳይሆን ክፉ አለመናገር ነው፡፡ በመጠን ማውራት የሚቸገሩ ሰዎችን እንዲያወሩ በመገፋፋት ልንረዳቸው ይገባል፡፡ ይህ እነርሱን በቀላሉ ከሰው ጋር ለመግባባትና አሳባቸውን ከትክክለኛ ስሜቱ ጋር እንዲያካፍሉ ሲረዳቸው እኛን ደግሞ ስለ እነርሱ በቂ መረጃና መረዳት እንዲኖረን ይጠቅመናል፡፡ ምን ጊዜም ስለ ሰዎች ከዝምታቸው ተነሥቶ መናገር ከባድ ነው፡፡ ስለዚህ እንዲናገሩ እድል ስጧቸው፡፡ የሚቸገሩትን ደግሞ እርዷቸው በዚህም ግንኙነቶችን ማስጌጥ እንችላለን፡፡ የመሰማት ፍላጎታችንን የምንቆጣጠረው እንዲሁ ሌሎችን በመስማት ነው፡፡

         ስለ ግንኙነት እንድናወራ ምክንያት የሆነን በገዛ ወንድሙ የተገደለው የመጀመሪያው ሟች ቃየል ነው፡፡ ይህ በቤተሰብ ውስጥ ቀዳሚውና ምናልባትም ከፍተኛው ዓመጽ ይሆናል፡፡ የአንድ እናትና የአንድ አባት ልጆች ቢለዋና ሥጋ፣ በግና ተኩላ፣ ስንዴና እንክርዳድ፣ ለሲዖልና ለገነት፣ ለክብርና ለውርደት የሆኑበት ታሪክ ነው፡፡ ዲያቢሎስ በወንድማማቾች መካከል ጠብን የዘራበት የታሪክ መጀመሪያ! በዚህ ታሪክ ውስጥ አቤል መሥዋዕቱ በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት ማግኘቱን ተከትሎ በወንድሙ በኩል ጠላትነት ተነሣበት፡፡ የምስክርነት፣ የምሥጋና፣ የጸሎት፣ የምሕረት፣ የልግስና እንዲሁም የሰውነታችንን መሥዋዕትነት ከሁሉ በላይ እነዚህን ሁሉ ይዘን ከምንቀርብበት መሥዋዕት ከክርስቶስ የተነሣ ጠላት በልቡ እኩይ፣ በእጁ ድንጋይ ይዞ ይነሣል፡፡ ከበጉ የተነሣ ሕይወት እንዳለ ሁሉ ከእርሱ የተነሣ ሞትንም እንቀምስ ዘንድ አለን፡፡ እስጢፋኖስ በድንጋይ የተወገረው በሥጋ ከእስራኤል ስለ ተወለደው የእግዚአብሔር ልጅ እየመሰከረ ነው (የሐዋ. 7)፡፡ የእውነተኛው መሥዋዕት ምስክርነት ያላቸው ሁሉ የመከራው እውነተኛ ተካፋይ ናቸው፡፡ ራሳቸውን በማዋረድ ብቻ ሳይሆን በሞቱ እንኳ ይመስሉታል፡፡

         ከሥጋ ወንድምነት ውስጥ ከዚህ የተሻለ ምንም አይወጣም፡፡ እንደ ሥጋ ያለው መንፈስ ከሆነው ጋር ይጣጣም ዘንድ ተፈጥሮአዊ አይደለም፡፡ የእናት ማኅፀን አንድ ያደረጋቸውን መሠዊያ ለያቸው፡፡ ቀራንዮ ላይ ግብር እኩይ ለዘመናት ያስተዋደዳቸውን መሠዊያና መሥዋዕቱ ለዘላለም ለያቸው፡፡ በቀኝ የነበረው ወንበዴ ከጊዜው ተፋቶ ከዘላለሙ ተጋባ፡፡ ከዛሬው ተጣልቶ ከዘላቂው ጋር ኅብረት መሰረተ፡፡ እውነት እላችኋለሁ ክርስቶስ ይለያል፡፡ ቃየል ፊቱ ጠቆረ እጅግም ተቆጣ፡፡ እግዚአብሔር የቃየልን መንገድ ተመለከተ፡፡ አካሄዱ መልካም እንዳይደለ፣ ኃጢአት በደጁ እንደምታደባ፣ እርሱ ለጽድቅ ካልተሸነፈ ኃጢአት በላዩ ላይ እንደምትነግስበት ነገረው፡፡ በአጭር ቋንቋ ከመንገዱ እንዲመለስ አስጠነቀቀው፡፡ ፊታችን ገደል ካለ መፍትሔው መመለስ ነው፡፡ ቃየል ግን ካፈርኩ አይመልሰኝ አለ፡፡ እናም ወንድሙን አቤልን ወደ ሜዳ ወስዶ ገደለው፡፡ ይህም በመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ አሳዛኝ ታሪክ ሆኖ ለትምህርት ተፃፈልን፡፡

        ብዙ ጊዜ ለስህተቶቻችን አቅም የሚሆነው ካፈርኩ አይመልሰኝ አይነት አካሄድ ነው፡፡ እንደዚህ የመሰለው ሂደት እልከኝነትንና አለመሸነፍን ያስከትላል፡፡ እንደነዚህ ያሉቱ የጀመሩት አመጽ ካሰቡበት ካልደረሰ፣ የስህተታቸውን ጽዋ ካፍ ከገደፉ ካልሞሉት በስተቀር ሰላም የላቸውም፡፡ በትንሽ አሳፋሪ ነገር የጀመሩትን በዚያው ደረጃ ላይ ሊተዉት ፈቃደኝነት አያሳዩም፡፡ የሰው ቀርቶ የአምላክ ማስጠንቀቂያ አይመልሳቸውም፡፡ ለእነርሱ ልክ የጀመሩት እንጂ ጌታ የሚለው አይደለም፡፡ በደል በተዋረደው ማንነታችን ምክንያት ለሞት ከተሰጠ ሰውነታችን ጋር ዘወትር ሙግት የምንገጥምበት ነው፡፡ ዳሩ ግን በቁርጥ ልንታገለው፣ እዚህ ጋር በቃ ብለን ልንፈርድበት የተገባ ነው፡፡ አጥፍተናልና እንዳጠፋን፣ በድለናልና እንደ በደልን፣ ስተናልና እንደ ሳትን መዝለቅ ጤና አይደለም፡፡ መመለስ፣ መጸጸት፣ መካስና ንስሐ የሚባልም ነገር አለ፡፡ ዓመጽ ሲጨርሱት አያምርም፡፡ ተወዶም ተገዶም የተጀመረ ኃጢአት ሳያልቅ መጨናገፍ አለበት፡፡ ቃየል እግዚአብሔርን ቢሰማው ኖሮ ሕሊናውን፣ ወንድሙንና አምላኩን ባተረፈ ነበር፡፡ መከሩ ከተዘራው የተትረፈረፈ ነውና ቃየል አንድ ወንድሙን ገድሎ ለዘላለም ሞተ፡፡

       በዘጠነኛ ደረጃ ግንኙነትን ጉዳት ላይ የሚጥለው “እንደ ቀድሞው” የሚል አስተሳሰብ ነው፡፡ ጉዞ ካለ ለውጥና እድገት አለ፡፡ ሰው በዚህ ጊዜያዊ ዓለም ውስጥ መንገደኛ ነው፡፡ ትክክለኛ ነዋሪዎች ከትላንት ስህተታቸው ይማራሉ፡፡ በመከራና በወጀብ ውስጥ ራሳቸውን የተሻለ ያደርጋሉ፡፡ ጤፍ እንጀራ ለመሆን መበጠር፣ መፈጨት፣ መቦካት፣ በፈላ ውኃ (አብሲት) ውስጥ ማለፍ ይኖርበታል፡፡ በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ ለውጡን ማስተዋል ይኖርብናል፡፡ ሰውም እንዲሁ ነው! ለምን ተለወጥክ ልክ የማይሆነው በክፉ ብቻ ሲሆን ነው፡፡ የሥጋን አሳብ ትቶ ለነፍሱ ካደረ፣ ሱሱን እርግፍ አድርጎ ገቢውን ከቆጠበ፣ ዋዛ ፈዛዛውን ንቃ ለቁም ነገር ከተሸነፈች፣ ከስህተት መንገድ ጨክና ከተመለሰች ይህ ደግ እንጂ ወግድ የሚያሰኝ አይደለም፡፡ አውግስጢኖስ እውነተኛ ክርስቲያን ሳይሆን በፊት በዝሙት የምታውቀው ሴት ለጌታ አገልጋይ ከሆነ በኋላ በመንገድ አገኘችው፡፡ እርሷ ስትከተለው እርሱ እየሸሸ እንደ ምንም ደረሰችበት፡፡ በእርሷ ጊዜ እንደምታውቀው ስሙን እየጠራች አንተ አይደለህምን? አለችው፡፡ እርሱም አይደለሁም! አሁን አዲስ ሰው ነኝ አላት፡፡ ተወዳጆች ሆይ በመልካም ተለወጡ፡፡ ከትላንት ዛሬ በርቱ፡፡ እየሆነ ያለውን ሰዎች ባይረዱትም፣ ወዳጆቻችሁ ወዳጅ እንደሆኗችሁ ባይቀጥሉም፣ የማይታየውን እያተረፋችሁ የሚታየውን ብትከስሩም እውነት አርነት ያወጣችኋል፡፡  

       በአዲስ ኪዳን ከቃየል ታሪክ ጋር በተወሰነ ደረጃ መመሳሰል የምናይበትን አንድ ታሪክ ማየት ርእሳችንን ይበልጥ ግልጽ ያደርግልናል፡፡ የጠርሴሱ ሳውል የጌታን ደቀ መዛሙርት ሊገድላቸው እየዛተ ወደ ሊቀ ካህናቱ የሄደበት ክፍል (የሐዋ. 9)፡፡ ወደ ደማስቆ በቀረበ ጊዜ ግን ሊያስረው በማይችለው አንዳች ኃይል ታሰረ፡፡ ሊቋቋም በማይችለው የብርሃን ኃይል ዓይኑ ጨለመ፡፡ ለጊዜው መረዳት ባልቻለው ብርቱ ክንድ ወደቀ፡፡ ታዲያ ሞቶ የነበረው ሕያውም የሆነው ድምጽ መጣ፡-“ሳውል ሳውል ስለ ምን ታሳድደኛለህ? አለው” እርሱም “ጌታ ሆይ ማን ነህ? አለው” ጌታም “አንተ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ የመውጊያውን ብረት ብትቃወም ለአንተ ይብስብሃል” አለው፡፡ ሳውል ጌታ ለተናገረው ብርቱ ማስጠንቀቂያ የሰጠው ምላሽ “ጌታ ሆይ ምን አደርግ ዘንድ ትወዳለህ” የሚል ነበር፡፡


       በቃየልና በሳውል መካከል ያለውን ልዩነት ስንመለከት በጣም የሚደንቅ ነው፡፡ ያ እንደ ልቡ በእግዚአብሔር ፊት ሲሄድ የጀመረውን ዓመጽ ሲፈጽም፤ ይህ ደግሞ ለክርስቶስ ልብ ተሸነፈ መንገዱን አቋረጠ፡፡ ለእውነት ብላችሁ የምታቋርጡት ከእውነት ጋር የዘላለም ወዳጅነት የምትመሰርቱበት ነው፡፡ ተወዳጆች ሆይ ሳውል ካፈርኩ አይመልሰኝ! ቢል ኖሮ ዛሬ የምናጠናቸውን መልእክታት እንዲሁም እኔን ምሰሉ የማለት መንፈሳዊ ድፍረት ያገኘበትን ልምምድ ባልተጋራነው ነበር፡፡ በእርግጥስ የመውጊያውን ብረት ማለትም የኢየሱስን ስም ተቃውሞ ለእርሱ የማይብስበት ማን አለ? በዚህ ዓመጽ ውስጥ ያላችሁ ንስሐ ግቡ፡፡ ማስተዋል ይብዛላችሁ!!

2 comments:

  1. በእርግጥስ የመውጊያውን ብረት ማለትም የኢየሱስን ስም ተቃውሞ ለእርሱ የማይብስበት ማን አለ?..........Amen mastewal yebzalin!

    ReplyDelete
  2. በቃየልና በሳውል መካከል ያለውን ልዩነት ስንመለከት በጣም የሚደንቅ ነው፡፡ ያ እንደ ልቡ በእግዚአብሔር ፊት ሲሄድ የጀመረውን ዓመጽ ሲፈጽም፤ ይህ ደግሞ ለክርስቶስ ልብ ተሸነፈ መንገዱን አቋረጠ፡፡ ለእውነት ብላችሁ የምታቋርጡት ከእውነት ጋር የዘላለም ወዳጅነት የምትመሰርቱበት ነው፡፡

    ReplyDelete