Monday, November 4, 2013

ለፍቅር የተከፈለ


                             ሰኞ ጥቅምት 25/2006 የምሕረት ዓመት

      በገጠሪቱ የአገራችን ክፍል የሆነ ነው፡፡ አብዝተው የሚዋደዱ ሁለት ጓደኛማቾች ሾላ ለመልቀም ዱር ይወጣሉ፡፡ በዚያም አንደኛው ከላይ አውራጅ  ሌላው ደግሞ ከታች ለቃሚ /ተቀባይ/ ለመሆን በቃል ተስማምተው የድርሻቸውን ማከናወን ጀመሩ፡፡ ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኋላ ግን በሁለቱ ወዳጆች ፍቅር፣ በጓደኛማቾቹ የዘወትር መተጋገዝ ይፈነድቅ የነበረው ቀዬ ወደ ሀዘን ተቀየረ፡፡ ሕልውናን ሞት፣ ደስታንም እንባ ተካው፡፡ ከሁለቱ ጓደኛማቾች መሀል አንደኛው የስንብት ያህል አጣጥሮ ላይመለስ በዚያው አንቀላፋ፡፡ ባልንጀራ የጎዳችሁ፣ የወዳጅ ፍላፃ ያለፈባችሁ፣ አምኖ መከዳት፣ አጉርሶ መነከስ ቀለብ የሆናችሁ፣ አዝናችሁ የተጨከነባችሁ፣ በወርቅ ፈንታ ጠጠር፣ በፍቅር ፈንታ ጥላቻ የተመዘነላችሁ ቃየል በወንድሙ አቤል ላይ እንዳደረገው ያለ የሆነ ነገር ሊኖር እንደሚችል ትጠረጥሩ ይሆናል፡፡

     እነዚህ ጓደኛማቾች ለጸብ ተሰናዝረው፣ ቂም በቀል አሳድረው፣ ልዩነት አክርመው፣ በውል ተጣልተው አያውቁም፡፡ ሾላ ለመልቀም ብቻ ሳይሆን እውቀት ለመገብየትም ተነጣጥለው ሄደው አያውቁም፡፡ የአፋቸው ብቻ ሳይሆን የልባቸውም የጋራ ነው፡፡ አንዱ የሚናገረው ሌላውን የሚደግፍ፣ መተናነጽ የሞላበት ነው፡፡ ቁራሿን እየተካፈሉ፣ ዝግን ጥሬ እየተዘጋገኑ፣ በአንድ ዋንጫ እየተጎነጫጩ፣ ትንሽ አጎዛ ላይ እየተላፉ ያደጉ የሁለት ቤት ልጆች ናቸው፡፡ አብሮህ የሳቀውን ትረሳዋለህ፡፡ አብሮህ ያለቀሰውን ግን ፈጽሞ አትረሳውም እንደሚባለው አብሮ መጫወት ብቻ ሳይሆን አብሮ የማንባትንም ወራት በፍቅርና በደስታ አሳልፈዋል፡፡

     ታዲያ አሁን ምን ክፉ ገጠማቸው፣ መሀላቸው ምን ገባ ትሉ ይሆናል፡፡ ሾላ በመልቀሙ ሂደት ከላይ የነበረው ልጅ ድልጠት ይገጥመውና ተንሸራቶ ከሾላው ላይ ሲወድቅ አጎንብሶ ይለቅም የነበረው ጓደኛው ላይ በሙሉ አካሉ ይወድቅበታል፡፡ በአጋጣሚና በጓደኛው መሥዋዕትነት የተረፈው ልጅ በሕይወት መኖሩ መደነቅ ሞልቶት እያጣጣረ እጁ ላይ ያሸለበውን ጓደኛውን እየተመለከተው ወደ ውስጥ አለቀሰ፡፡ እጁ ላይ የያዘው ሬሳ ለእርሱ የሰጠውን ሕይወት፣ የተጨፈኑ ዓይኖቹ የሰጡትን ማየት፣ በድን አካሉ ለእርሱ የሰጠውን ሙቀት፣ የተሰበሰቡ እግሮቹ ለእርሱ የተዉለትን ትጋት እያሰበ አለቀሰ፡፡ ለእርሱ የመጣውን ሞት የወሰደለትን ጓደኛውን በስስት እያያየ ወደ ውጪ ጮሆ አለቀሰ፡፡ አንድ እናት ለአንድ ልጇ እንደምታለቅሰው ያለ አለቀሰ፡፡

    አውቀው ያልከፈሉት ዋጋ እንኳ ይህንን ያህል ልብ ይነካል፡፡ በእርግጥ ተወዳጆች ሆይ ለፍቅር፣ ለይቅርታ፣ ለጽድቅ፣ ለቅድስና፣ ለወንጌል የከፈላችሁት ዋጋ እየቆጫችሁ ይሆን? የኃጢአትን ግብዣ እረግጣችሁ የወጣችሁበት፣ ወደ ዘላለም እቅፍ ጌታ የቀረባችሁበት፣ እንደ ቀድሞው ላትሆኑ እግዚአብሔርን ያወቃችሁበት ቀን እየቆጫችሁ ይሆን? ሰጥታችሁ መስጠታችሁ ባልገባቸው፣ ታግሳችሁ መታገሳችሁን ባልተረዱ፣ ዝምታችሁን እንደ ሞኝነት፣ ማለፋችሁን እንደ ውርደት በቆጠሩባችሁ ወገኖች ተመራችሁ ይሆን? በዘመናችን ሁሉ የማንቆጭበት ነገር ቢኖር ለፍቅር የምንከፍለው ነው፡፡ ፍቅር አውቀን ብቻ ሳይሆን ሳናውቅም የምንታዘዝበት፣ የማናዘው ግን የሚያዝዘን ኃይል ነው፡፡ ሊገድሉ ወጥተው ለወጡለት ሞተው፣ ሊቀሙ ተሰማርተው ያላቸውን ገፈው፣ ሊረግሙ ተንደርድረው ምርቃት ጨርሰው፣ ላለመተያየት ቆርጠው የቁርጥ ተቃቅፈው የተመለሱ ብዙ ናቸው፡፡

    ፍቅር የማይቆጥረው ለዚህ ነው፡፡ በፍቅር ውስጥ የሚቆጠረው ጉዳቱ ሳይሆን ራሱ ፍቅር ነው፡፡ የደረሰብን ሳይሆን በፍቅር የደረስናቸውን የምንቆጥርበት ሂደት ነው፡፡ ከጌታ የተማርነው ይህንንም አይደል? የዚያ ወጣት ሞት ለዚህኛው ጓደኛው ሕይወት ሆነው፡፡ ዳሩ ግን ሟች ይህንን የሚያስተውልበት እድሜ አልነበረውም፡፡ ጣሩ ለመኖር ያደረገው ትግል እንጂ ሞቶ ሕይወት የሰጠበትን ሂደት ያስተዋለበት አልነበረም፡፡ ግን ባይረዳውም፣ ፈቅዶ ባያደርገውም ለጓደኛው የፍቅር ዕዳ ነበር፡፡ ይህ ምንኛ እፁብ ድንቅ ነው? እንኳን በሞታቸው ቀርቶ በሕይወታቸው መልካም መተው የማይሆንላቸው ብዙ ሳሉ ይህ ግሩም ነው፡፡ ኖረውም ሞተውም የሚያዋጉ ሰዎችን ምድሪቱ ከስርም እንደተሸከመች እናውቃለንና፡፡

     ወዳጃችን ኢየሱስ ምንኛ ይልቃል? ሁሉን የሚያውቅ ከሆነውም ያለ እርሱ የሆነ አንድ ስንኳ የሌለ ሊወለድ በረትን ሊሞት መስቀልን መረጠ፡፡ በጊዜው ውስጥ ተንገላትቶ ለዘላለም ወለደን፣ የምድሩን ተቀላቅሎ ከሰማዩ ተካፋይ አደረገን፡፡ ዛሬም ከሾላው ላይ የሚወርዱትን ኃጢአተኞች የሚሸከም ትከሻ ያለው እርሱ ብቻ ነው፡፡ ዘኬዎስን የተሸከመው ውረድ ያለው ጌታ ነው፡፡ ማኅበረሰቡ ዓይንህን ለአፈር ያለውን፣ በነውርና በግፍ የፈረጀውን ቤትህ እገባለሁ! ከማለት የዘለለ ምን መሸከም አለ፡፡ ሰው ስለ ዘኬዎስ ላወራው ኃጢአት ብቻ ሳይሆን ራሱ ዘኬዎስ ለሚያውቀውም ኃጢአት የሞተው ክርስቶስ ነው፡፡ ሰዎች ለምናውቀው በደል እንጂ እነርሱ ለሚያወሩብንና ለሚያሶሩብን ኃጢአት ጌታ እንደሞተልን አይገባቸውም፡፡ ግን እያደር ይረዱታል፡፡ መውረድን ሰው ይፈራል፡፡ ብቻ ምንም ይሁን ሰው ለከፍታው ክብር ይሰጣል፡፡ ከፍ ከፍ ያለው ጌታ ግን ውረዱ ይላል፡፡ የእኛ ጥረት፣ በስንት መቧጠጥና መጫጫር ከወጣንበት ላይ ውረዱ የሚል የከፍታ ሁሉ ወሰን እርሱ ነው፡፡

    ከእውነት ተንሸራተን፣ ኃጢአት አዳልጦን ለወደቅነው በዚህ ፈራጅ ዓለም ውስጥ ክርስቶስ ኢየሱስ ትከሻ ነው፡፡ ክርስቲያን ክርስቲያንን በተጸየፈበት፣ መሸካከም እንደ ጉዳት በተቆጠረበት በዚህ ጊዜ ጌታ ከመቼውም ጊዜ በላይ ታዳጊያችን ነው፡፡ እናንት ደካሞች የራሳችሁን ሸክም ተሸክማችሁት እንኳ እረፍት ያላገኛችሁ እባካችሁ ወደ እግዚአብሔር ኑ፡፡ ሁሉን በሚችል በእርሱ ፊት ሸክም ይቅለልላችሁ፡፡ እርሱ ክርስቶስ ሞቶ ሕይወት፣ ተዋርዶ ክብር፣ ተጥሎ ትንሣኤ የሆነን ነው፡፡ እንደ እርሱ የሚሸከም ሸክሙ ከሞት የሚታደግ ከቶ ማን ነው? በየዕለቱ እኛን የሚያስመልጥ፣ ወጥመድ የሚሰብር፣ ከሰማይ የሆነ ረድኤታችን ስሙ ይቀደስ፡፡

     ወደ ጓደኛማቾቹ ታሪክ እንመለስ የለቅሶውን ጩኸት ተከትሎ ከምስራች ይልቅ መርዶ የሚያሻትተው ማኅበረሰብ ግልብጥ ብሎ ወጣ፡፡ እልልታ ከሚጠራውና እሪታ ከሚሰበስበው የቱ ይበልጣል? ተወለደ ከሚያስደግሰውና ሞተ ከሚያስደግሰው የቱ ይበዛል? ተገላብጦብን የምንገላበጥ ሰነፎች ነንና ጌታ ያስበን፡፡ ሾላው ስር የተሰበሰበው ሰው አንዳንዱ ድሮም አላማረኝም፣ ሌላው ምን ሰይጣን መሐላቸው ገባ?፣ ደግሞ ሌላው ሲያልቅ አያምር እያሉ ወሬ ተቀባበሉ፡፡ ከቁንጫ መላላጫ እንዲሉ ሁሉም የቻለውን ያህል ቦጨቁ፡፡ ያ እንዴት እንደወደቀና እንዴት እንደተረፈ የማያውቅ ምስኪን እንደ ነፍሰ ገዳይ ተቆጠረ፡፡

     መስጠት ብቻ ሳይሆን የለገስነው፣ መመገብ ብቻ ሳይሆን ያበላነው፣ መናገር ብቻ ሳይሆን ያወራነው ለጥፋት እንዳይሆን የምንጸልይ ስንቶቻችን ነን? ወጣቱ አስቦና አቅዶ፣ አውጥቶና አውርዶ፣ አድፍጦና ሸምቆ ጓደኛውን ለመግደል ያደረገው አንዳች ጥረት የለም፡፡ ሟችም በዓላማ አልሞተም፡፡ ታዲያ እንደ ዳኛ ምን ትፈርዳላችሁ?    
-      ይቀጥላል  -    



No comments:

Post a Comment