Tuesday, December 3, 2013

ለፍቅር የተከፈለ(ካለፈው የቀጠለ)


           
                            እሮብ ህዳር 25/2006 የምሕረት ዓመት
    ሚስቱን በሞት ያጣ አንድ ወጣት ከብዙ መፍትሔ ፍለጋ በኋላ ወደ አንድ የስነ ልቦና አጥኚ ዘንድ ሄዶ በሕይወት ላይ ተስፋ እንደቆረጠ፣ የሚስቱ ሀዘን ለመኖር ምክንያት እንዳሳጣው በእንባ ጭምር ይነግረዋል፡፡ የስነ ልቦና አማካሪውም ወደ ወጣቱ እየተመለከተ “ሚስትህ በሕይወት ብትኖርና አንተ ብትሞት ኖሮ ሚስትህ ምን የምትሆን ይመስልሃል?” ሲል ጠየቀው፡፡ ወጣቱ ፍም የመሰለ ፊቱን በእጁ እያሻሸ “በቁሟ ጨርቋን ጥላ፣ ሚዛኗን ትስታለች እንጂ በጤና የምትሆን አይመስለኝም” በማለት ጥርሱን ነክሶ መለሰለት፡፡

         አማካሪውም ይናገር ቀጠለ “አየህ! አሁን እየሆነ ያለው አንተ ሞተህ ሚስትህ በሕይወት ብትኖር ኖሮ ሊሆንባት የሚችለው ነገር ነው፡፡ እናም አንተ ለእሷ ያለህ ፍቅር አጠገብህ በሌለችበት በዚህ ጊዜ እንኳ ውድ ዋጋ እንድትከፍል አስገድዶሃል፡፡ በአንተ የሆነው ለፍቅር የተከፈለ ነው” አለው፡፡ የወጣቱ ፊት ላይ ወዝ ድፍት አለ፡፡ ከመቀመጫው ተነሥቶ ለሰላምታ እጁን ዘረጋ፤ እየወዘወዘውም “ችግሬ የምለውን ነገር በዚህ መንገድ እንዳየው የረዳኝ ሰው አልነበረም፡፡ ለመኖር እንድጓጓ፣ የምወዳትን ሚስቴን አጥቻት እንኳ ይበልጥ እንድወዳት፣ ለእሷ ሳይሆን ለፍቅር በደስታ እንድኖር አድርገኸኛልና ከልብ አመሰግናለሁ፡፡” በማለት አፉን ደስታ ሞልቶት፣ በደቂቃዎች ጥያቄው ተመልሶለት ወጣ፡፡

‹‹በፍቅር ዓለም ተጀመረች፡፡ ዓለም በፍቅር ውስጥ አደገች፡፡ ፍቅር በዓለም ውስጥ የጥንካሬ ምንጭ ነው፡፡ ፍቅር እውነት ነው፡፡ ፍቅር እውነት ካልሆነ እውነት በራሱ እውነት አይደለም፡፡ ሕይወት ከሞት ይልቅ ደካማ ናት፡፡ ሞት ደግሞ ከፍቅር ይልቅ ደካማ ነው፡፡ ከሞት ቀጥሎ ሰው የማይመርጥ ረቂቅ ኃይል ቢኖር ፍቅር ነው፡፡ ፍቅር የሁሉ የጋራ አካፋይ ነውና፡፡ የፍቅር ዋናው ነገር ለሌሎች የምናስበው፣ የምናደርግላቸውና የምንለግሳቸው ሳይሆን ከእኛነታችን የምንሰጣቸው መጠን ነው፡፡ ተወዳጁ የፍቅር ስጦታ የተከበሩ ማዕድናት (አልማዝ፣ ወርቅ፣ እንቁ)፣ አበባና ቸኮሌት ሳይሆን ራስን መስጠት ነው፡

ሕይወት ያለ ፍቅር ባዶ ናት፡፡ ጣዕሟንም ታጣለች፡፡ ብዙ ጉድለት በፍቅር ይካካሳል፡፡ ብዙ ኃጢአት በፍቅር ይሸፈናል፡፡ ያለ ፍቅር ሕይወት ትርጉም የላትም፡፡ ያለ ፍቅር እምነትና ተስፋን አናስተውልም፡፡ በዚህ ግራ አጋቢና አልጫ በሆነው ዓለም ሕይወትን ጣፋጭ የሚያደርጋት ፍቅር ነው፡፡    እውነተኛ ፍቅር የራሱን ገደብ ያውቃል፡፡ የሰውን ገደብ ያከብራል፡፡ ነገሮችን በጥንቃቄ ያከናውናል፡፡ ከመተው ይልቅ ይታገሣል፡፡ ስሜትን ከመጉዳት ይቆጠባል፡፡ በመከራ ይጸናል፡፡ በተስፋ ያጽናናል፡፣ እውነተኛ ፍቅር ‹‹ከእኔነት›› ወደ ‹‹እኛነት›› የምንሸጋገርበት መንገድ ነው፡፡ በችግሩ ላይ ሳይሆን በመፍትሔው ላይ እንድናተኩር ይረዳናል፡፡›› /ዳንኤል ዓለሙ፣ ስኬታማ የፍቅር ሕይወት፣ 2004 ዓ.ም/

        እንደ ፍቅር ዋጋ ከመክፈል ጋር የተያያዘ ነገር የለም፡፡ ለያዝነው ብቻ ሳይሆን ላጣነውም ጭምር ፍቅራችንን የምናሳይበት የሚኖር አጋጣሚ ቢኖር እራሱ ፍቅር ነው፡፡ እውነተኛ አፍቃሪዎች ስንሆን በእጃቸው የበላነውን እያሉ ብቻ ሳይሆን አጥተናቸውም፤ የተዘረጋ እጅ በሌለበት ሁኔታ ውስጥም ፍቅራችን ዋጋ ይከፍላል፡፡ የወደድነው መውደዳችንን፣ የዋልንለት ውለታችንን፣ ያቀረብነው ቅንነታችንን በማይረዳበት ሁኔታ ውስጥም ሆነን እንወድዳለን፡፡ በውድ ብቻ ሳይሆን አንዳች ብርቱ ኃይል ዐለት ልባችንን ሠነጣጥቆት፣ የኩራት ጉብታውን ንዶት፣ የእልህን እሾህና አሜኬላ መነጣጥሮት በሙሉ አቅማችን እንወድዳለን፡፡ የማናዘው የሚያዘን፣ የማንታገለው የሚያሸንፈን፣ የማንቋቋመው የሚረታን ፍቅር ይገዛናል፡፡ ከእንባ ጋር ቢቀላቀል፣ ከስቃይ ጋር ቢለወስ፣ ከመከራ ጋር ቢዋሀድ፣ ከፈተና ጋር ቢቀየጥ ፍቅር አድራሻውን አይስትም፡፡ የትኛውንም መራራ የሚያጣፍጥ ጣእም አለው፡፡

         በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ሁኔታዎችን የምናይበት አተያየት በእጅጉ ጠቃሚ ነው፡፡ በተለይ በመከራና በፈተና ውስጥ ስናልፍ ነገሮችን በተደጋጋሚ አጥርተን ለማየት መሞከር ከተጨማሪ ጭንቀትና ተስፋ ከመቁረጥ ይታደገናል፡፡ ከፍቅር ጋር የተያያዙ ፈተናዎች ጉዳታቸው ያየለ ነው፡፡ ምክንያቱም የምንጋፈጠው የወዳጅን ፍላፃ፣ የባልንጀራን ማመም፣ “የእኔ” የምንለውን ሸክም ነውና፡፡ እንዲህ ባለው ጊዜ ማጽናኛዎች ሁሉ ወደ እኛ የሚደርሱት ከነማርከሻቸው ነው፡፡ ሰዎች ለሚመክሩን ሁሉ ማጣፊያ እንመዝዛለን፡፡ ወድደን በምንከፍለው የፍቅር ዋጋ ውስጥ ደግሞ ከዚህ ይከፋል፡፡ ምክንያቱም የእኛ መስማማት የታከለበት እንደመሆኑ ለሰው የማናስነካው ቁስል፣ የማናካፍለው እንቆቅልሽ፣ እዩልኝ የማንለው ገመና ይሆናል፡፡

          ስለ ኢየሱስ “ተጨነቀ ተሠቃየም አፉንም አልከፈተም ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት፥ በሸላቾቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም።” ተብሎ አልተፃፈምን? ለፍቅር በተከፈሉ ዋጋዎች ውስጥ መጨነቅ - ስለሚወድዱት ማውጣትና ማውረድ፣ ማሰብ ማብሰልሰል፣ ለመፍትሔ መጠበብ ይኖራል፡፡ ከመከራና ከወጀቡ ማየል የተነሣ መጨነቅ ይኖራል፡፡ ወዝ ጠፍ ሊል፣ ጉልበት ሊብረከረክ፣ አቅም ሊከዳ ይችላል፡፡ በጠላት ፍጥጫ፣ በክፉዎች ጡጫ፣ በሸንጎ እርግጫ ወዲያ ወዲህ ማለት ሊኖር ይችላል፡፡ በችንካር መወጠር፣ አክሊለ እሾህ መድፋት ይኖራል፡፡

          ተሠቃየ - ፍቅር የሌሎችን ችግር የሚታዘብ ሳይሆን ራሱን ከሌሎች መከራ ጋር አብሮ የሚቆጥር ነው፡፡ እስሮችን እንደታሰረ፣ ሀዘንተኞችን ልክ እንደቀበረ፣ ድሆችንም ልክ እንደተቸገረ ሆኖ ማሰብ መከራን መካፈል ነው፡፡ ፍቅር ሚዛናዊ ነውና የሕይወትን አሉታዊ ክፍልም እንድናይ ግድ ነው፡፡ በመውደድ ውስጥ ደስታ ብቻ እንዳለ ማሰብ ጤናማነት አይደለም፡፡ ዋጋ የምንከፍልለት ፍቅር ስቃዩ ግልጽ ነው፡፡ ልክ በፍም ላይ እንደሚራመድ ሰው መርገጫ የመፈለግን ያህል ሥቃይ ይበረታል፡፡ ዝምታ - እንደ ፍቅር በዝምታ ውስጥ የሚጮህ ነገር የለም፡፡ ዕይታው ብቻ ይቀጣል፡፡ መታገሱ ብቻ ያሸብራል፡፡ ማለፉ ብቻ አንገት ያስደፋል፡፡ የእግዚአብሔር ቃል የሚያቀርብልን ትልቁ ቅጣት መውደድ ነው፡፡ በክፉዎች ራስ ላይ የፍርድን እሳት የሚከምር መውደድ ምን ያህል ጠንካራ ነው? እጅግ ስንወድድ የሚታይ ኑሮ እንጂ የቃላት ድሪቶ ስፍራ አይኖረውም፡፡ ከቃላችን በላይ ዝምታችን ሞገስ አለው፡፡ አፍን አለመክፈት - ፍቅር ሸላቾቹ ፊት እንኳ እንደዚህ ነው፡፡ እስቲ ስለ ፍቅር ምን እንደከፈላችሁ ልብ በሉ? ትቆጫላችሁ? በእርግጥ በአግባቡ ገብቶአችኋል? ለፍቅር የምትከፍሉት ዋጋ የትህትናው ጥግ ይህ ነው፡፡         
         ምድራችን ላይ ሰዎች እስከ ሞት ድረስ ዋጋ የሚከፍሉባቸው ብዙ ርእሶች አሉ፡፡ ከመቀያየም እስከ መጠፋፋት የሚደርሱ ልዩነቶች በጀት አላቸው፡፡ ታዲያ እንዲህ ባለው ጊዜ ዓለማችን ለፍቅር ዋጋ የሚከፍሉ ሰዎችን ትሻለች፡፡ ለማስተራረቅ ዋጋ የሚከፍሉ፣ ሕብረትን ለመጠበቅ ዋጋ የሚከፍሉ፣ ትዳር እንዲጸና ዋጋ የሚከፍሉ፣ ልጆች እንዳይበተኑ ዋጋ የሚከፍሉ፣ በሰዎች መካከል ፍትህ እንዲሰፍን ዋጋ የሚከፍሉ፣ ለመታገስ ዋጋ የሚከፍሉ፣ ለሰላም ዋጋ የሚከፍሉ፣ ለእውነት ዋጋ የሚከፍሉ . . . የምድሪቱ ብርቱ ጥማት! ለሰዎች የመኖር ቅመሙ ፍቅር ነው፡፡ ከፍቅር የተነሣ የቸሩ፣ ከመውደድ የተነሣ የራሩ፣ ለሰው ሳይሆን ለፍቅራቸው የኖሩ ልብ ሁሉ በደስታ ያስባቸዋል፡፡ አለመረሳት ትሻላችሁን? በፍቅር ኑሩ!
                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                  


No comments:

Post a Comment