Saturday, August 16, 2014

ፍቅርም እንደዚህ ነው!

                       Please Read in PDF: Fikirm Endezih New
                             
                                ነሐሴ 10 ቀን 2006 የምሕረት ዓመት

      ‹‹የሕይወታችን ምስጢር በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የተገለጠ መጽሐፍ ከሆነ ከሁለት ሺህ ዓመታት በላይ ሆኖታል፡፡ ያለፈው፤ የአሁኑ እና የወደፊቱ ሕይወታችን ሁሉ በእርሱ ተገልጧል፡፡ ያለፈው ሕይወታችን በእርሱ ስቃይና መከራ፤ የአሁኑ በእርሱ ጸጋ እና ምሕረት የተገለጠ ሲሆን፤ የወደፊቱ ደግሞ በዘላለማዊው ሕይወት ይገለጣል›› (ቶማስ አኩይናስ)፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በማመናችን የምናገኘውን ትልቅ ነገር ሲናገር ‹‹ሕይወት›› በማለት ይገልጸዋል፡፡ የፍቅር ሐዋርያው ‹‹የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ታውቁ ዘንድ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ለምታምኑ ይህን ጽፌላችኋለሁ›› (1 ዮሐ. 5÷13) ሲል፤ የዘላለም ሕይወት ያላቸው ግን ያንን ያገኙትን የዘላለም ሕይወት የማያውቁትን ሰዎች እያስታወሰ ነው፡፡ እራሳችንን መርዳት በማንችልበት ‹‹ሙታን›› የተሰኘ ኑሮ ውስጥ ስንኖር ሳለ፤ ሕይወት እንዲሆንልን እንዲበዛልንም (ዮሐ. 10÷10) የእግዚአብሔር ልጅ በሥጋ ተገለጠ፡፡

     ተወዳጆች ሆይ፤ የዘላለምን ሕይወት እንዳገኛችሁ፤ ይህም ለእናንተ በክርስቶስ ክርስቲያን በመሆናችሁ እንደ ተሰጠ ታውቃላችሁን? ይህንን አለማወቅ አጉል ነዋሪ ያደርጋል፤ ተስፋ መቁረጥንና ለሞት ባርያ መሆንን ያመጣል፡፡ አዲስ ኪዳንን በደንብ ስናጠና ከምናስተውለው ነገር አንዱ ‹‹እግዚአብሔር ለእኛ የዘላለም ነገር እንዳለው›› ነው፡፡ ከእርሱ ጋር ሊኖረን የሚችለው ግንኙነት ከዚህ ባነሠ ነገር ላይ የተመሠረተ አይደለም፡፡ ሰው ኃጢአትን በማድረጉ፤ ተከትሎ የመጣው ደመወዝ ‹‹የዘላለም ሞት›› ነው (ሮሜ. 6÷23)፡፡ የዘላለም አባት እግዚአብሔር (ሮሜ. 16÷25)፤ የዘላለም ልጁን (ሮሜ. 9÷5)፤ በዘላለም መንፈስ (ዕብ. 9÷14) ለእኛ ምትክ አድርጎ በመስጠቱ የዘላለም ሕይወትን በጸጋ ተቀበልን (ኤፌ. 2÷5)፡፡ ይህም እግዚአብሔር ለእኛ ያለው የዘላለም አሳቡ ነው (ኤፌ. 3÷12)፡፡ እግዚአብሔር ለእኛ የማይቆጠር ነገር ማድረጉ ምንኛ ድንቅ ነው?

      ልባችንን ዝቅ ከሚያደርገው፤ ዓይናችንን በዕንባ ከሚሞላው፤ ፊታችንንም ከሚያጠቁረው ነገር መካከል፤ ከሚቆጠር ነገር ጋር ያለን ትስስር ተጠቃሽ ነው፡፡ በዚህ ዓለም እንደ ሰው ኑሮ ባልተከናወነልን ነገር የመለኮትን ፈቃድ በምሬት እንቃወማለን፡፡ እርሱ ግን ከዘላለም ባነሠ ነገር ሊያረካን ጊዜያዊ አምላክ አይደለም፡፡ የዘላለም አምላክ፤ የዳርቻዎች ፈጣሪ፤ የምድር የሰማያት ጌታ ሕሊናችንን በዘላለም ሊሞላው ታምኖ ያለ ነው፡፡ ‹‹በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ እኔም አውቃቸዋለሁ ይከተሉኝማል፤ እኔም የዘላለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፥ ለዘላለምም አይጠፉም፥ ከእጄም ማንም አይነጥቃቸውም።›› (ዮሐ. 10÷27-28) ተብሎ እንደ ተፃፈ፤ በእምነት ሕይወትንና አለመጥፋትን አግኝተናል (2 ጢሞ. 1÷11)፡፡ የሰጠን እግዚአብሔር ለተቀበልነው ነገር ከበቂ በላይ ዋስትና ነው፡፡

        ቤተክርስቲያን በወልድ ያላመነ የዘላለም ሕይወት እንደሌለው ታስተምራለች (በቅዳሴ መካከል ወንጌል ሲነበበብ)፡፡ ይህ በክርስቶስ ያመነ የዘላለም ሕይወት አለው ማለት ነው፡፡ ያገኘነው ሕይወት የማይጠፋ ነው፡፡ ሕይወትን ብቻ ሳይሆን አለመጥፋትንም ወደ ብርሃን ያወጣ ጌታ ስሙ ብሩክ ይሁን፡፡ ከእርሱ ጋር ለዘላለም አብረን እንድንኖር በሰማይ ቀጠሮ የያዘልን አምላክ ስሙ ይቀደስ፡፡ በእግዚአብሔር የተወደዳችሁ ሆይ፤ አባት ሕይወትን ከልጁ ጋር ከሰጠን፤ ያለ ድንግል ማርያም ልጅ ሰው ለዘላለም ሞት የተቀጠረ ነው፡፡ እግዚአብሔር እንዴት እንደወደደን ልብ በሉ፡፡ ሐዋርያው ‹‹ፍቅርም እንደዚህ ነው፤ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም›› (1 ዮሐ. 4÷10) በማለት የፍቅርን ልኬት ያስረዳናል፡፡ ‹‹ፍቅር እንዴት ነው?››

        ሁሉም ሰው ስለ ፍቅር የተለያየ ትርጉምና መግለጫ ይሰጣል፡፡ ለአንዳንዶች ፍቅር እንደ ወደዱ መጠን ሲሆን፤ ለሌሎች ደግሞ እንደመወደዳቸው ልክ ነው፡፡ ባሏን አጥብቃ የምትወድ ሚስት ፍቅር ልክ እንደ አባወራው እንደ ሆነ ልታስብ ትችላለች፤ ደግሞ ሚስቱን አጥብቆ የሚወድም ባል እንዲሁ ፍቅር እንደ ትዳር አጋሩ እንደ ሆነ ታጥቆ ያስረዳናል፡፡ ለቤተሰቡ መለወጥ፤ ለተቀሩት አባላት መሻሻል የሚደክም ወንድም በቤት ውስጥ ካለ ‹‹ያለ እርሱ›› እየተባለ ፍቅሩ ይተረካል፡፡ እህትም ከሆነች እንደዚያው፡፡ ለተለያዩ ሰዎች ፍቅር የተለያየ ነው፡፡ ከትርጉሙ ጀምሮ ማወዳደሪያው ለየቅል ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ትክክለኛውን የፍቅር ትርጉም፤ የልዕልና ዳርቻ፤ የማወዳደሪያ ፍፃሜን የሆነውን መውደድ ወደ ፊታችን ያቀርብልናል፡፡ የፍቅር ሐዋርያው ‹‹ፍቅር እናንተ እግዚአብሔርን እንደ ወደዳችሁት ሳይሆን እርሱ እናንተን እንደ ወደደ ነው›› ይለናል፡፡ ተወዳጆች እናንተ፤ እግዚአብሔርን ምን ያህል ትወዱታላችሁ? ፍቅር እንደዚያ አይደለም፡፡ እግዚአብሔርን ለበዓል የገዙትን ጫማ ያህል፤ አልያም የሚያሽከረክሩትን መኪና በሚተካከል ፍቅር እንኳ መውደድ ያልቻሉ፤ ግን ክርስቲያኖችን መመልከት እንችላለን፡፡   

         ፍቅር እግዚአብሔር እኛን እንደ ወደደን መሆኑ ደስ ያሰኛል፡፡ ይህም እኛ ለእርሱ ያለንን ሳይሆን እርሱ ለእኛ ያለውን ነገር እያከበርንና በዚያ እየተደነቅን እንድንኖር ያደርገናል፡፡ በዚህ ዓለም ላይ በተለያየ ጊዜ የተፈጸሙ የሰው የፍቅር ታሪኮችን እንደ እውነተኛ ፍቅር ማሳያ እናጣቅሳለን፡፡ በቅርብም በሩቅም የሰማናቸውን ለፍቅር መርኅ አድርገን እንይዛለን፡፡ ቃሉ በማያሻማ ሁኔታ ‹‹ፍቅርም እንደዚህ ነው›› ይለናል፡፡ እንዴት? እንደ ወላጆቻችን ነውን? ወይስ እንደ ባልንጀሮቻችን? የለም! ምናልባት ፍቅር፤ ታሪካቸውን እንደ ሰማንላቸው ታላላቅ ሰዎች ይሆንን? ተወዳጆች ሆይ፤ ፍቅር እንደ ማንም አይደለም፡፡ እርሱ ራሱ እግዚአብሔር እኛን እንደ ወደደን እንጂ፡፡ ይህ ፍቅር ተግባራዊ በሆነ መንገድ የተገለጠው እንዴት ነው? ‹‹ስለ ኃጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ››፤ እግዚአብሔር ብዙ ነገር አድርጎልናል፡፡ ስለ ኃጢአታችን ያደረገውን ያህል ግን ምንም አላደረገም፡፡ ‹‹ልጁን ላከ›› (ገላ. 4÷4)፡፡ ፍቅር እግዚአብሔር ስለ ኃጢአታችን ማስተስርያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደላከው እንደዚህ ነው፡፡ ስለ ኃጢአታችን ማስተስርያ የሚሆን ሌላ የለምና የእግዚአብሔር የብቻው ፍቅር (አጋፔ) እንደዚህ ነው፡፡

         የፍቅር ሐዋርያው በወንጌሉ ክፍል ላይ ‹‹በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።›› (ዮሐ. 3÷16) ይለናል፡፡ በብዙዎች ዘንድ እውቅና ያለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ነው፡፡ ከመልእክቱ ጋር አገናዝበን የወንጌሉን ክፍል ስናጤነው የእግዚአብሔርን ፍቅር እንረዳለን፡፡ በዚህ ክፍል ብዙውን ጊዜ እንደምንሰማው ‹‹እንዲሁ›› የሚለው አገላለጽ ‹‹በባዶ›› ማለት አይደለም፡፡ እግዚአብሔር እኛን የወደደን ትልቅ ዋጋ ከፍሎ ነው፡፡ ‹‹ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና››፤ እንዴት? ‹‹አንድያ ልጁን እስኪሰጥ››፡፡ እንዴት ያለ ፍቅር ነው፡፡ እንግዲህ የእግዚአብሔር የስጦታው ጥግ ይህ ነው፡፡ ለኃጢአታችን ማስተስሪያ /ይቅርታ ማግኛ/ ይሆን ዘንድ ልጁን ላከ፡፡ እንዲሁ ወዶናል፤ አንድያ ልጁን እስኪሰጥ፡፡ ተወዳጆች ሆይ፤ ፍቅርም እንደዚህ ነው፡፡ እግዚአብሔር እኛን በዚህ መንገድ እንደ ወደደን!

3 comments:

  1. ‹ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና››፤ እንዴት? ‹‹አንድያ ልጁን እስኪሰጥ››፡፡ እንዴት ያለ ፍቅር ነው፡፡ Semu yetebareke yehun!

    ReplyDelete
  2. ፍቅር እንደማንም አይደለም እርሱ እራሱ እግዚአብሔር እኛን እንደ ወደደን እንጂ!!!
    ፀጋህ ይብዛ በብዙ ተባረክ!!!

    ReplyDelete
  3. Ebakachihu bedenbee safu, geta yistachihu

    ReplyDelete