Friday, July 18, 2014

ከፍ ብሎ መቀመጥን፤ ዝቅ ብሎ በመቀመጥ ሞክረው!

                             
                   ሐምሌ 11 ቀን 2006 የምሕረት ዓመት

      እውነተኛ ወዳጅ የሚታወቀው፤ የወዳጅነት መፈታተኛ በሆነው በጭንቅና በመከራ ጊዜ ነው፡፡ ቁጣ የአዋቂውን ሰው ዕውቀት ያጠፋል፡፡ ቁጣና ትውኪያ ካሰቡት አያደርስም የሚባለው ስለዚህ ነው፡፡ ራሱን በራሱ የሚያመሰግን ሰው ራሱን ባይታመንና ሰው የማያመሰግነው መሆኑን ስለሚያውቅ ነው፡፡ እንዲሁም እርሱ የሚሠራው ሥራ ሁሉ በሰዎች ዘንድ የማይመሰገን መሆኑን ስለሚያምን ነው፡፡ በተድላ ደስታ መኖር ከተፈለገ ከወንድም ቅናትና ከጠላት ሽንገላ መጠንቀቅ ነው፡፡ ጊዜ ሳለው አለሁልህ ማለትን ለማያውቅ ጊዜ ሲከዳው አለሁልህ የሚለው አይገኝም፡፡ ጠባየ ክፉ ለሆነ ሰው ፍቅር አይስማማውም፡፡ ወዳጁ የሚከብደው ሰው ሸክሙ የቀለለ ነው፡፡

      አንድ ፈላስፋ ከወንድምህና ከወዳጅህ ማናቸውን ትወዳለህ? ቢሉት ወዳጄ ከሆነ ወንድሜ ነው አለ፡፡ ሆኖም ከበጎ ባልንጀራ መልካም ጠባይ ይበልጣል አለ፡፡ ያልያዘውንና የማያገኘውን የሚመኝ ሰው የያዘውንና ያለውን እስከ ማጣት ይደርሳል፡፡ ጥቂት ገንዘብ ከምስጋና ጋር ታላቅ ሃብት ነው፡፡ የማይችለውን እሸከማለሁ የሚል ሰው ለመሸከም የሚችለውንም ያጣል፡፡ በሐሰት ከመናገር በእውነት ድዳ መሆን በዓመፅ በሰበሰቡት ገንዘብ ሃብታም ከመሆን ጽሮ ግሮ ባገኙት ገንዘብ ድኻ መሆን ይሻላል፡፡ ሃብት በማያውቅበት ሰው ዘንድ በሞተ ሰው መቃብር ላይ ምግብን እንደ ማስቀመጥ ያለ ነው፡፡

       በመሥራት ካልሆነ አንዳችም ነገር በምኞት የሚፈጸምና የሚከናወን የለም፡፡ ምኞት የኀዘንና የትካዜ እናት ስለ ሆነች ምን ጊዜም ኃዘንና ትካዜን ትወልዳለች፡፡ ራሱን በራሱ የናቀ ሰው የዚህ ዓለም ተድላ ደስታ አያስደስተውም፤ ድህነትም አያጨናንቀውም፡፡ ራሱን ከበርቴ አድርጎ የሚመለከታት ሰው ግን ዓለሙ ሁሉ ለዓይኑ አይበቃውም፡፡ ነገርህ ሊሰማልህ ከወደድህ አንደበትህን ቀልድ መናገርን አታስለምድ፤ እንዲሁም ሰዎች ሊያከብሩህ ከፈለግህ ሌላውን አክባሪ ሁን፤ ከፍ ብሎ መቀመጥን ዝቅ ብሎ በመቀመጥ ሞክረው፡፡

      ራሱ የማይሠራውንና የማይወደውን የሚመክርና የሚያስተምር ሰው በጣም ክፉና አደገኛም ነው፡፡ ራስህን ኃጢአት ከማድረግ ካልገታህ ሌላውን ኃጢአት እንዳይሠራ ለመግታት መብት የለህም፡፡ አንድ ሰው ምኞቱንና መሻቱን እስኪያሸንፍ ድረስ ብልህና ታላቅ ሰው ተብሎ ሊጠራ አይገባውም፡፡ አቅሙንና መጠኑን አውቆ ሥራውን የሚሠራ ሰው፤ የዕውቀት ዕውቀት ያለው ነው፡፡ ሰው የሚገመተው በአዋቂነቱ እንጂ በግዝፍነቱ አይደለም፡፡ የልብ ዕረፍት ፍጹም የሚሆነው ከአቅም በላይ እሠራለሁ አለማለትና በዚያው ጸንቶ መኖር ነው፡፡ አሳቡን የቃኘና ምኞቱን የሚያሸንፍ ሰው ከሁሉ ይበልጣል፡፡ ገንዘብን መውደድ ፍቅርን ያጠፋል ሃይማኖትን ያስክዳል፤ ሞትን ያስረሳል፤ ኃጢአትን ያስጨርሳል፡፡ ንፍገት ችግርን ይስባል፤ አልጠግብ ማለትን ያስከትላል፤ ያስገበግባል፡፡ አስተዋይና ብልህ ካልሆነ ባለ ጸጋ ብልህና አስተዋይ ድኻ ይሻላል፡፡

      ደመና ያልጋረደው ፀሐይ ደስ እንደሚያሰኝ ብርሃኑም መሬቱን እንደሚያለብሰው መልካም ጠባይ ያላትም ሴት ባሏን ታስደስታለች፤ ተወዳጅነቷ በቤቷ ውስጥ ያበራል፡፡ ቤት ከመሥራትህ በፊት ደኅና ጎረቤት ፈልግ፤ መንገድም ከመሄድህ በፊት ደኅና ጓደኛን አግኝ፡፡ ከባለጌ ሰው ጋር ጠጅ ከመጠጣት ከብልህ ሰው ጋር ደንጊያን መሸከም ይሻላል፡፡ ደግነት ከተፈጥሮ ባሕርይ ነው፤ ሃይማኖት ግን ከትምህርት ነው፡፡ ሆኖም ጠላቶቼን ፈጥኖ ያላጠፋልኝ ብለህ እግዚአብሔርን አታማርር ይልቁንስ ስትበድል እያየ አንተን ፈጥኖ ባለመበቀሉ ቸርነቱንና ትዕግሥቱን ማድነቅ ይገባሃል፡፡

       ዓለም ሦስት ናት አንድ ቀን ላንተ፤ አንድ ቀን ባንተ፤ አንድ ቀን ለሌላ ናትና ስለ እገሌ ብለህ መኖር የለብህም፡፡ ጥንድ ካልሆኑ የማይረቡ ነገሮችም አራት ናቸው፤ ተወዳጅነት የሌለው መልክ፣ ቸርነት የሌለው ሃብት፣ ጉልበት የሌለው መመካት፣ ስምምነት የሌለው መትጋት ናቸው፡፡ ንብና ሸረሪት ሌት ተቀን ተግተው ይሠራሉ፤ ነገር ግን የንብ ሥራ ጠቃሚና ቁምነገር ሲሆን የሸረሪቷ ሥራ ጥቅም የለውም፡፡ ሰው የወደደውን ሊመኝ ይገባዋል፤ ግን የሚወደው በጎና አስፈላጊ መሆን አለበት፡፡ ሆነ ብሎ ለመዋሸት ካልሆነ በእውነተኛው ነገር ማመካኘት ሊኖር ባልተገባም ነበር፤ ምክንያት የሐሰት መሸፈኛ ናትና፡፡ ወፎች የሚያዙ በወጥመዱ አይደለም፤ ከወጥመዱ በታች ያለውን በመሻት ነው፡፡

      መልካም ወሬ ማለት ምን ጊዜም እግዚአብሔርን ማሰብና ማስታወስ ነው፡፡ የሕይወት መገኛ የጥበብ መጀመሪያ የመጨረሻ አለኝታ እሱ ነውና፡፡ አንድ ፈላስፋ የዚህ ዓለም ዘመኑ ሦስት ነው፤ ይኸውም ያለፈው ቀን፣ ያለው ቀን፣ የሚመጣው ቀን ነው፡፡ ያለፈው ቀን ተመልሶ አይመጣልህም፤ ያለህበት ቀን ላንተ ብሎ አይኖርም፤ የሚመጣውም ቀን ለማን እንደሚሆን አታውቅም አለ፡፡ የቤትህ በራፍ ምንም እንኳ ከፍታው ሰባት ክንድ ቢሆንም ራስህን ዝቅ አድርገህ ብትገባበት ይሻልሃል፡፡ ብልህ ሰው አጥፊ ሲፈረድበት አይቶ ይታረማል፤ ሰነፍ ግን የብልሁ ማስተማሪያ ይሆናል፡፡ ምሥጢርህን አንተ እሠረው ካላሰርከው ግን እሱ ያስርሃል፡፡

      ከትልቅ ሰው ተወልጄ ብሎ ከመንደላቀቅ ይልቅ ተሠርቶ ተቀጥቶ ማደግ የበለጠ ነው፡፡ ከሰነፍ ሽማግሌ ብልህ ወጣት፤ ከሰነፍ ረዳት ብልህ ጠላት ይባላል፡፡ ከወደቀ በኋላ ከሚጠነቀቅ ይልቅ ከመውደቁ አስቀድሞ የሚጠነቀቅ ይበልጣል፡፡ ዘመንን የሚቃወም ሰው ራሱን ይጎዳል፤ እንደዚህ ያለው ሰው ዓይኑ እያየ ከጎርፍ ጋር የሚጋፋውን ይመስላል፡፡ ችኮላ ሰውን ከታላቅ ጥፋትና ውድቀት ታደርሰዋለች፡፡ ከንቱ ውዳሴን የሚወድ ሰው ባላሰበው መንገድ እንደሚሄድ ያለ ነው፡፡ ዛሬ የምታደርገውን ለነገ አደርገዋለሁ አትበል፤ የነገውን ነገ ታደርገዋለህና፡፡ ሶቅራጥስ እንዲህ አለ ‹‹ልጄ ዓለምና ጣዕሟ እንዳያስትህ ተጠንቀቅ›› እሷ ካንተ በፊት ለነበሩት አልኖረችላቸውም፤ ዛሬም ላንተ አትኖርልህም፤ ካንተ በኋላ ለሚመጡትም አትኖርላቸውምና፡፡  

                                  ሊቀ መዘምራን ሞገስ ዕቁበ ጊዮርጊስ            

5 comments:

  1. አስተማሪ መልዕክት

    ReplyDelete
  2. Interesting be blessed.Thanks PS keep posting it been long time.

    ReplyDelete
  3. ሆኖም ጠላቶቼን ፈጥኖ ያላጠፋልኝ ብለህ እግዚአብሔርን አታማርር ይልቁንስ ስትበድል እያየ አንተን ፈጥኖ ባለመበቀሉ ቸርነቱንና ትዕግሥቱን ማድነቅ ይገባሃል፡፡

    ReplyDelete
  4. ከትልቅ ሰው ተወልጄ ብሎ ከመንደላቀቅ ይልቅ ተሠርቶ ተቀጥቶ ማደግ የበለጠ ነው፡፡ Great!

    ReplyDelete
  5. ሰዎች ሊያከብሩህ ከፈለግህ ሌላውን አክባሪ ሁን፤ ከፍ ብሎ መቀመጥን ዝቅ ብሎ በመቀመጥ ሞክረው፡፡

    ReplyDelete