/ካለፈው የቀጠለ/
(መዝ. 123÷1-8)
መስከረም 16 ቀን 2007 የምሕረት ዓመት
ከእናንተ ጋር ያላችሁ ምንድነው? መቼም አንድ ነገር እያለን፤ ነገር
ግን እንዳለን ባናውቅ ይህ እጅግ ያሳዝናል፡፡ የፍቅር ሐዋርያው ዮሐንስ ‹‹የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ታውቁ ዘንድ በእግዚአብሔር
ልጅ ስም ለምታምኑ ይህን ጽፌላችኋለሁ›› /1 ዮሐ. 5÷13/ ሲል፤ የዘላለም ሕይወትን የተቀበሉ ግን ደግሞ ይህንን የተሰጣቸውን
ሕይወት ያላስተዋሉ ክርስቲያኖችን ልብ እንላለን፡፡ ተወዳጆች ሆይ፤ ይህንን አለመረዳት ትርጉሙ ቀላል አይሆንም፡፡ ኪሳራውም እጅግ
የከፋ ነው፡፡
የእግዚአብሔር ሰዎች ያላቸው ትልቁ ‹‹እግዚአብሔር›› ብቻ ነው፡፡
ነቢዩ ዳዊት እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር አለመሆኑ ምን ሊያመጣ እንደሚችል በተረዳው መጠን ይናገራል፡፡ በዚህ መዝሙር ውስጥ ያሉትን
አሳቦች በሁለት ከፍለን ልናያቸው እንችላለን፡፡ የመጀመሪያው ካለፈው ነገር ጋር የተያያዘ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ከመጪው ጋር የተያያዘ
ነው፡፡ ባለፈው ጊዜ ካለፈው ኑሮ ጋር የተያያዘውን አሳብ ማየት ጀምረን ነበር፡፡ በዚህም ክፍል አሳቦቹን በዝርዝር እናያለን፡፡