Friday, September 26, 2014

እግዚአብሔር ከእኛ ጋር፡


/ካለፈው የቀጠለ/
                  (መዝ. 123÷1-8)
                          መስከረም 16 ቀን 2007 የምሕረት ዓመት

        ከእናንተ ጋር ያላችሁ ምንድነው? መቼም አንድ ነገር እያለን፤ ነገር ግን እንዳለን ባናውቅ ይህ እጅግ ያሳዝናል፡፡ የፍቅር ሐዋርያው ዮሐንስ ‹‹የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ታውቁ ዘንድ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ለምታምኑ ይህን ጽፌላችኋለሁ›› /1 ዮሐ. 5÷13/ ሲል፤ የዘላለም ሕይወትን የተቀበሉ ግን ደግሞ ይህንን የተሰጣቸውን ሕይወት ያላስተዋሉ ክርስቲያኖችን ልብ እንላለን፡፡ ተወዳጆች ሆይ፤ ይህንን አለመረዳት ትርጉሙ ቀላል አይሆንም፡፡ ኪሳራውም እጅግ የከፋ ነው፡፡

       የእግዚአብሔር ሰዎች ያላቸው ትልቁ ‹‹እግዚአብሔር›› ብቻ ነው፡፡ ነቢዩ ዳዊት እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር አለመሆኑ ምን ሊያመጣ እንደሚችል በተረዳው መጠን ይናገራል፡፡ በዚህ መዝሙር ውስጥ ያሉትን አሳቦች በሁለት ከፍለን ልናያቸው እንችላለን፡፡ የመጀመሪያው ካለፈው ነገር ጋር የተያያዘ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ከመጪው ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ባለፈው ጊዜ ካለፈው ኑሮ ጋር የተያያዘውን አሳብ ማየት ጀምረን ነበር፡፡ በዚህም ክፍል አሳቦቹን በዝርዝር እናያለን፡፡

4. የሚያሰጥም ውኃ፡- ነቢዩ ይህንን ውኃ ከሥጋ ጋር ሳይሆን ከነፍስ ጋር እንዳያያዘው ልብ እንላለን፡፡ ውኃ እያሳሳቀ እንዲወስድ እንዲሁ መንፈሳዊ አቋማችንን የሚሸረሽሩ ጠላትነቶች እጅግ ብልሃት የተሞላባቸው ናቸው፡፡ የትልልቅ ውድቀቶች መነሻ የተናቁ ጥቂት ተግባራት ናቸው፡፡ ክፍሉ ‹‹ፈሳሽ ባለፈ ነበር›› ካለን በኋላ ቀጥሎ ደግሞ ‹‹የጎርፍ ውኃ ባለፈ ነበር›› ይለናል፡፡ ፈሳሹን ጎርፍ ሲከተለው ማየት የተለመደ ነው፡፡

        ተወዳጆች ሆይ፤ የሶምሶንን ሕይወት እንድታጠኑ እመክራችኋለሁ፡፡ ሶምሶን የውድቀት ታሪኩ የሚጀምረው እዚህ ግባ በማይባል ዝለት ነው፡፡ መንፈሳዊ የሆነው ነገሩ ተገዝግዞ ውድቀት ሙሉ ማንነቱን እስኪወርሰው ድረስ በሂደቱ ላይ መንቃት አልቻለም፡፡ ከዚህ የተነሣ መጨረሻው እንደ ጎርፍ ነበር፡፡ ነቢዩ ‹‹እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ውኃ ከሰሜን ይነሣል፤ የሚያጥለቀልቅም ፈሳሽ ይሆናል፤ በአገሪቱና በመላዋ ሁሉ፥ በከተማይቱና በሚኖሩባት ላይ ይጐርፋል፤ ሰዎቹም ይጮኻሉ፥ በምድርም የሚኖሩ ሁሉ ያለቅሳሉ›› /ኤር 47፥2/ በማለት የተናገረውን ትንቢት እዚህ ጋር እናስተውላለን፡፡ ከሰሜን የተነሣው ፈሳሽ ከተማን ሁሉ የሚያጥለቀልቅ ነበር፡፡ ውኃው ከኃይለኞች ፈረሶች፤ ከኮቴያቸው መጠብጠብ ድምፅ፤ ከሰረገሎች መሽከርከር፤ ከመንኮራኩሮች መትመም ጋር የተያያዘ ነው፡፡ 

        ነቢዩ እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር መሆኑ በውኃ ከመስጠም እንደታደጋቸው ያስረግጥልናል፡፡ በመንፈሳዊው ኑሮ ውስጥም ልክ በነቢዩ በኤርምያስ እንደተነገረው ያለ ጠላትነትና ውጊያ እንጋፈጣለን፡፡ እግዚአብሔር ግን ያስመልጣል፤ ከክፉ ይታደጋል፡፡ ‹‹እግዚአብሔር በወጀብና በዐውሎ ነፋስ ውስጥ መንገድ አለው፥ ደመናም የእግሩ ትቢያ ነው።›› /ናሆ 1፥3/ እንደተባለ፤ እግዚአብሔር ሊያልፍብን የመጣውን ያሳልፋል፡፡ የማናልፍ በመሰለን ነገር ውስጥም መንገድን ይሰጣል፡፡

         በእስራኤል ታሪክ በግልጥ የምናውቀው ከውኃ ማምለጥ አለ፡፡ በኤርትራ ባህርና በዮርዳኖስ ወንዝ ፊት እግዚአብሔር በኪዳን አብሮት ላለው ሕዝብ ደግሞ ያደረገውንም ድንቅ እናውቃለን፡፡ ታሪኩ ምድራዊ ተስፋና በረከት ላለው ለዚያ ሕዝብ እጅግ አስፈላጊ ከነበረ፤ በሰማያዊ ስፍራና በመንፈሳዊ በረከት ለተባረክነው ለእኛ፤ መንፈሳዊ ውጊያ ላለብን እግዚአብሔር ከእኛ ጋር መሆኑ ምንኛ ያስደንቃል? ጌታ የሚወዳችሁ እናንተ፤ እንደ ተደረገለት አብዝታችሁ አመስግኑ፡፡ ብዙ የተቀበልን እኛ፤ እጅግ የተጠበቅን እኛ አብዝተን ልናመሰግን ይገባናል፡፡ ነቢዩ ለእስራኤል ‹‹እንዲህ ይበል›› ያለው ከእግዚአብሔር መሆን ጋር በተያያዘ እንጂ ሕዝቡ ከእግዚአብሔር ጋር ከመሆኑ ጋር በተያያዘ አይደለም፡፡ ያለፍነውና ያለፈልን እኛ ከእግዚአብሔር ጋር ሆነን ሳይሆን እርሱ ከእኛ ጋር ሆኖ ነው፡፡ የታመነ እርሱ ነው!

         እንደተደረገለት አመስግኑ፡፡ በሌሎች ያየነው ውድቀት የእኛ ውድቀት ያልሆነው፤ እዚያ ቤት ያንኳኳው ሀዘን የእኛ ሀዘን ያልሆነው፤ በሌሎች ላይ ያስተዋልነው ነውር የእኛ ነውር ያልሆነው ከእግዚአብሔር ጸጋና ክንድ የተነሣ ነው፡፡ እስራኤል ኤርትራን ያለፉት ውኃ ስላልነበረ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ስለ ነበረ ነው፡፡ ምድሪቱ በብዙ የሚያሰጥሙ ነገሮች የተሞላች ናት፡፡ በሰሙት ሰጥመው፤ በተመለከቱት ሰጥመው፤ በደረሱበት ማስተዋል ሰጥመው፤ በሰበሰቡት ሀብትና ንብረት ሰጥመው፤ ከፀሐይ በታች ባለው ጥበብ ሰጥመው የቀሩ ብዙ ናቸው፡፡ አዎ! እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ባይሆን ነፍሳችን ለስጥመት በሆነች ነበር፡፡

5. የጥርስ ንክሻ፡- ‹‹በዋጡን ነበር›› የሚለውን አሳብ ካነበብን በኋላ ተከትሎ የምናገኘው ቃል ነው፡፡ የሚውጡ አኝከው መሆኑ የስቃዩን ርዝማኔ ያስረዳናል፡፡ በክፉዎች አፍ ውስጥ መላወስና መገላበጥን ፊታችን ላይ ይስልብናል፡፡ ነቢዩ ግን ‹‹ያላደረገን›› በማለት እግዚአብሔርን ይባርካል፡፡ ያላደረገን ስሙ ብሩክ ይሁን፡፡ የሥጋ ለባሽ መጫወቻ፤ የምቾታቸው አጫዋች፤ ለልባቸው መሻት ባሪያ፤ በትምክህታቸው ግዞት ስር ያላደረገን እግዚአብሔር ይባረክ፡፡ እስራኤል በግብፅ እጅ ብትወድቅ፤ የአብራካቸውን ክፋይ ከጡብ ጋር አብኩተዋል፡፡ ግብፅ ዓለም ናት፡፡ የእግዚአብሔር ባልሆነው መዳፍ ውስጥ ከዚህ የተለየ ምንም የለም፡፡ ከእጁ ዘወር ብትሉ የማትለምዱት እጅ ይጠብቃችኋል፡፡

         ተወዳጆች ሆይ፤ ለእውነተኛ ክርስቲያኖች፤ የአፍ ሳይሆን ለልብ አማኞች በዚህ ምድር ላይ መኖር አይቀልም፡፡ ለአመፀኞች አልጋ ባልጋ የሚሆኑ ነገሮች ለአማኝ እንደዚያ አይሆኑም፡፡ እንኳን ኩራታችሁ ልመናችሁ የማያገኘው ብዙ ነገር በዚህ ዓለም አለ፡፡ የዚህ ዓለም አምላክ የማያምኑትን አሳብ አሳውሮ የሚያስተዳድርበት መልክዓ ምድር ላይ እንዳለን አንስተውም /2 ቆሮ 4፥4/፡፡ መኖራችን ምስጢር ነው፡፡ እንደ ወፍ በአዳኞች መካከል የምንወጣና የምንገባ ነን፡፡ በዙሪያችሁ ዛፍ የለም፤ ዱር የለም፤ ተራራ ቁልቁለት የለም፤ ዳሩ ግን አዳኝ /የሚያሳድድ/ አለ፡፡ ነፍሳችንን ያስመለጠ ደግሞም የሚያስመልጥ እግዚአብሔር ስሙ ብሩክ ይሁን፡፡ ማምለጣችን ወጥመድ እየተሰበረ ነው፡፡ እግዚአብሔር ብዙ ነገር ሰብሮልናል፡፡ ሰባሪው ቀድሞ እኛ ተከትለናል፡፡

         ወዳጆቼ ሆይ፤ ማለፍ ቀሎ አያውቅም፡፡ ሰው ያዘጋጀውን የወረቀት ፈተና በጥሩ ውጤት አጠናቀን የቦረቅንበትን ጊዜ አስቡት፡፡ የሕይወት ፈተና ለደቂቃዎች የተካፈለ የክፍል ውስጥ ትግል አይደለም፡፡ ጌታ ስንቱን አሳለፈን? የማያልፍ የመሰለንን ብዙ፤ የማያልፉ የመሰሉንን እንኳን ስንቱን አሰናበተ? ቢያኖር ቢያሳልፍ፤ ቢሰጥ ቢነሳ፤ ቢያጸድቅ ቢኮንን እርሱ እግዚአብሔር እውነተኛ ነው፡፡ እንደ ተሻገረ እናመሰግነዋለን፡፡ ወጥመድ እንደተሰበረለት እናከብረዋለን፡፡ ከሞት እንደቀረ እናመሰግነዋለን፡፡ እስራት እንደተፈታለት፤ ሰንሰለት እንደተበጠሰለት ስሙን እንቀድሳለን፡፡ ጌታ እግዚአብሔር በእርግጥም ከእኛ ጋር ባይሆን ታሪካችን ምን ያህል ይከፋ ነበር? ስሙ ይቀደስ!

         ነቢዩ ዳዊት እስራኤልን ስላለፈው ብቻ ሳይሆን ለመጪውም እግዚአብሔር የታመነ ዋስትና እንደ ሆነ ያስረዳቸዋል፡፡ እግዚአብሔርን ካሳለፍነው ጋር ብቻ ሳይሆን ከመጪውም ጋር የምናያይዘው ‹‹ያለና የነበረ፤ የሚኖርም›› ገዥ ነው፡፡ በትላንት ታሪካችን ውስጥ ድንቅ የነበረ ብቻ አይደለም፤ የሆነና እንደ ሆነ የሚዘልቅ አምላክ ነው፡፡ ያሳለፈን ገና የሚያሳልፈንም ነው፡፡ የታደገን ገና ወደፊትም ታዳጊያችን ነው፡፡ የፈወሰን ለመጪውም ፈዋሽ ነው፡፡ መድኃኒትነቱ የአገልግሎት ማብቂያ ጊዜ የሌለው ጌታ ስሙ ይቀደስ፡፡ ‹‹ረድኤታችን ሰማይንና ምድርን በሠራ በእግዚአብሔር ስም ነው››፤ እግዚአብሔር ለመኖር የሚያስፈልገንን ሁሉ በእኛና በሰው እጅ ላይ አላስቀመጠውም፡፡

        ሰው ሳይደርስ አስቀድሞ ‹‹እደርስ ይሆን?››፤ ሲደርስ ደግሞ ‹‹አልፈው ይሆንን?›› ብሎ ይጨነቃል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ከመጣው ይልቅ ገና ለሚመጣ የምንጨነቀው ይበረታል፡፡ ዳሩ ግን ‹‹ይሹሩን ሆይ፥ በሰማያት ላይ ለረድኤትህ፥ በደመናትም ላይ በታላቅነት እንደሚሄድ እንደ እግዚአብሔር ያለ ማንም የለም።›› /ዘዳ 33፥26/ ተብሎ እንደ ተፃፈ፤ ረድኤታችን ሰማይንና ምድርን በሠራ በእርሱ ስም ነው፡፡ ሰዎች በስማቸው የበሉት እንጀራ አላጠግብ፤ የጠጡት አላረካ፤ በስማቸው የለበሱት አላደምቅ፤ የሰበሰቡት አላሳርፍ ብሏቸው ተቸግረዋል፡፡ በስሙ መደገፍ ያስፈልገናል፡፡

        በክርስቶስ የምወዳችሁ፤ አሁን ወደ ልባችሁ ተመለሱ፡፡ ደግሞ በስሙ ረድኤትን ተለማመዱ፡፡ መጽሐፍ ‹‹በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ሁሉ ከላይ ናቸው፥ መለወጥም በእርሱ ዘንድ ከሌለ በመዞርም የተደረገ ጥላ በእርሱ ዘንድ ከሌለ ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ።›› /ያዕ 1፥17/ እንዲል፤ የብርሃናት አባት የመጪውም /የተቀበልነው/ ዘመን ዋስትና ነው፡፡ ምድሪቱ ላይ ብዙ ነገሮች በተለያየ ስም የሚጠሩ ናቸው፡፡ ለንግዳቸው ስያሜ የእግዚአብሔርን ስሞች የሚጠቀሙ ሰዎች በእነርሱ ቀርቶ በሸቀጣቸው እንኳን እግዚአብሔር እንዲያዝበት የዚያን ያህል ትንሽ መታዘዝ የላቸውም፡፡ ብዙ ነገሮች በሰው ስም መሽጎ ሰይጣን የሚረካባቸው ናቸው፡፡

        የእግዚአብሔርን ስም ከምንቀድስበት ነገር አንዱ ማንኛውንም ነገር ‹‹በስሙ›› ማድረግና ከእርሱ ‹‹በስሙ›› መቀበላችን ነው፡፡ የተወደዳችሁ፤ እንደሚቀበል አመስግኑ፡፡ ገና ጌታ እንደሚረዳው ሰው፤ የጠመመ እንደሚቀናለት፤ ጉብታ እንደሚናድለት፤ መንገድ እንደሚቀናለት ሰው አምናችሁ አመስግኑ፡፡ ገና በብዙ እንደሚባረክ፤ እጅግ እንደሚበዛ ሆናችሁ ስሙን ቀድሱ፡፡ ዘመን ለጽድቅ ይሁንላችሁ!  

                     

2 comments: