Thursday, September 11, 2014

እግዚአብሔር ከእኛ ጋር፡

                 (መዝ. 123÷1-8)

                           መስከረም 1 ቀን 2007 የምሕረት ዓመት

     ስላልተሳኩልን ነገሮች ማስታወስ ለሰው እያደር የሚመረቅዝ ቁስል ነው፡፡ ምስጋናችንን ምሬት፤ እልልታችንን ጩኸት፤ ደስታችንን ዕንባ እየቀደመው የምንቸገርበትም ርዕስ ይህ ነው፡፡ ተወዳጆች ሆይ፤ ወደ ኋላ መለስ ብላችሁ ያለፈውን ስታስቡ ለልባችሁ የቀረው ነገር ምንድነው? ያጣችሁት ወይስ ያገኛችሁት? የተደረገላችሁ ወይስ የተወሰደባችሁ? ምሬት ወይስ ሐሴት? የትኛው ሚዛን ይደፋል? ‹‹ዘመን መለወጡ፤ በእድሜ መባረኩ፤ ተጨማሪ ዕድል ማግኘቱ ልባችንን በደስታ ያጠግባልን?›› ብለን እንደ ክርስቲያን ብንጠይቅ ጥያቄያችን ጥያቄን፤ ጥማታችን የበለጠ መጠማትን ያገናኘናል፡፡ ያለ እግዚአብሔር ሕልውና አለመኖር ነው፡፡ ብዙ ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር አለመሆናቸውን ሲወቅሱ፤ እግዚአብሔር በዚያም ውስጥ ከእነርሱ ጋር በመሆኑ ግን አይደነቁም፡፡ የተዋችሁት ከያዛችሁ፤ ቸል ያላችሁት ካልረሳችሁ ከዚህ የሚበልጥ ምን የምስጋና ርዕስ አለ?

          ከላይ የተነሣንበት የዳዊት መዝሙር፤ ነቢዩ ለእግዚአብሔር ክንድ ክብርን የሰጠበት ነው፡፡ በእስራኤል ላይ ንጉሥና ሹም ሆኖ ሳለ ‹‹እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ባይሆን ኖሮ›› ይላል፡፡ ባለንና በደረስንበት ነገር ውስጥ እግዚአብሔርን ማየት መባረክ ነው፡፡ ብዙዎቻችን ሕይወት ለሁለት የተከፈለብን ነን፡፡ የሥጋና የመንፈስ! እንዲህ ያለውን አመለካከት በተሳሳተ መንገድ የተረዱ ክርስቲያኖች፤ እግዚአብሔር የሚገዛው በተወሰነ ነገራቸው ላይ ብቻ ነው፡፡

    በኅብረት ሲገኙ እግዚአብሔር የተናገራቸው ነገር፤ በግል የዕለት ከዕለት ሥራቸው ላይ ሲሆኑ አይታሰብም፡፡ እንዲያውም ‹‹ይህ ዓለማዊ ሥራ ነው፤ ያ ደግሞ መንፈሳዊ ቦታ ነው›› ይላሉ፡፡ እንደነዚህ ያሉቱ እግዚአብሔርን እየመረጡ የሚከተሉ ናቸው፡፡ እግዚአብሔርን ከእያንዳንዱ የኑሮአቸው ተግባር ጋር ስለማያያይዙት እውነት ከሐሰት፤ ጽድቅ ከአመጽ፤ ቅድስና ከርኩሰት ጋር በፈረቃ ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር የሌለው ምንም የለውም፤ እርሱ ያለው ግን ሁሉም አለው፡፡ ያለፈውን ዘመን ስናስብ ያለፍናቸውን ብዙ ነገሮች እናስታውሳለን፡፡

        በእርግጥ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ባይሆን ባለፈው ኑሮና ዘመን ውስጥ ምን ይሆን ነበር? ነቢዩ አጽንዖት ለመስጠት በድጋሚ ‹‹እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ባይሆን›› ይላል፡፡ ተወዳጆች ሆይ፤ ከዚህ የበለጠ አጽንዖት የምንሰጠው ምንም የለም፡፡ ሕልውና ከዚህ አምላካችን ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ድልንም የምንለማመደው በዚህ ትምክህታችን ነው፡፡ እንደ እርሱ አሳዳሪ፤ ለኪዳኑ ታምኖ ኗሪ ማንም የለም፡፡ ዛሬን የተቀበልነው ትላንትን አልፈን ነው፡፡ የነገ ዋስትናችንም ያሳለፈን ጌታ ነው፡፡

         በእስራኤል ምድር ንጉሥ፤ በጠላት ፊትም የሚዘምት ሠራዊት ነበረ፡፡ ዳሩ ግን እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ባይሆን ኖሮ ይህ ሁሉ ምን ይረባል፡፡ በእስራኤል ታሪክ ሕዝቡ ታቦት ተሸክመው እንኳን ሽንፈትና ሐፍረትን ተከናንበዋል (1 ሳሙ 4)፡፡ ክብር ከሕዝቡ በለቀቀበት ሁኔታ ጠላቶቻቸው ምርኮን በዝብዘዋል፡፡ እርሱ ጌታ ከእኛ ጋር በሆነበት አንዱ እልፍ ነው፡፡

         አዎ! ‹‹እስራኤል እንዲህ ይበል፡-›› በተባለበት፤ እኛም የምንለው ብዙ አለን፡፡ ነቢዩ በዘመረበት በዚያው ቅኝት ብንዘምር እንኳን እንዲህ ይዜማል፡

1. የሰዎች መነሣት፡ የተነሡ ሁሉ ሊረዱን አይደለም፡፡ ከጓደኞቻችን፤ ከወዳጆቻችን፤ ከቤተሰቦቻችን የተነሡብን ይኖሩ ይሆናል፡፡ ባለፈው ዓመት በዚህ መንገድ ስለ ሞቱ ሰዎች እናውቃለን፡፡ ሰው ለሰው ጥቅሙ የሆነውን ያህል ጉዳቱም ይሆናል፡፡ በር ዘግተን የምንተኛው ጎረቤት ስለማይመከር አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ምክሩን ከንቱ ስለሚያደርግ እንጂ፡፡ ገና ኖረን የምንሰማው ያመለጥንበት ነገር ይኖራል፡፡ ያኔ አንተ ሳታውቅ . . በዚያን ጊዜ አንቺ አልገባሽም እንጂ . . ብዙ የሥጋና የደም ብልሃት፤ እልህ አስጨራሽ ትጋት፡፡ በመቃብር ያሉት ቢነሡ ብላችሁ አስቡ፡፡ የሚነሡባቸውን ብዙ ወገኖች ከመፈለግ አይታክቱም፡፡ ክርስቶስ ከሙታን መካከል ተለይቶ ቢነሣ፤ ለዘላለም ሕይወት አስነሣን፡፡ መነሣቱ ያነሣን ጌታ ስሙ ብሩክ ይሁን፡፡ በዚህ መንገድ የተጎዳችሁና ጌታ ያሳለፋችሁ ክብርን ስጡ!

2. የሚነድ ቁጣ፡ ነቢዩ ‹‹ቁጣቸው በላያችንን በነደደ ጊዜ›› ይለናል፡፡ ቁጣ አንዳች የሚቻኮል ሰበቃ ውስጥ ያለን ስሜት ያሳያል፡፡ ከቁጣቸው ጽናት የተነሣ ራሳቸውን እስከ መሳት የሚደርሱ ሰዎች አሉ፡፡ ነቢዩ ወላጆች በልጆቻቸው ላይ እንደሚቆጡት ያለ መቆጣትን እየተናገረ አይደለም፡፡ ወደ ከፋ እርምጃ የሚቸኩል የሥጋ መንገድን እየነገረን ነው፡፡ ይህም ‹‹የሚነድ›› ተብሎ ተብራርቷል፡፡ በብዙ ሰዎች ፊት ላይ በግልጽ እናስተውላለን፡፡ በምድሪቱ ብዙ ወንበሮች ላይ ቁጣቸው የሚባላ፤ ፊታቸው የሚጋረፍ ሰዎች አሉ፡፡ ጭካኔያቸው የሚቆላመጥላቸው፤ ድሆች የተጣዱባቸው ብዙ የሰው ምድጃዎች በእርግጥ አፍንጫችን ስር ናቸው፡፡ የእግዚአብሔር ዙፋን ግን የጸጋ ዙፋን ነው (ዕብ 4÷16)፡፡ ሰው ትኩረት የነፈጋቸውን እግዚአብሔር ይንከባከባል፡፡

3. በቁም የሚውጡ፡ የሚውጠውን ተብሎ የተነገረው ለዲያቢሎስ እንደ ሆነ እናስታውሳለን ‹‹ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና›› /1 ጴጥ 5÷8/፡፡ ለሰዎች ‹‹ሕያዋን ሳለን በዋጡን ነበር›› መባሉ፤ ጠላትነቱ ምን ያህል የተካረረ እንደ ነበር ያስረዳናል፡፡ እጅግ ጠንካራ አገላለጽ ነው፡፡ ‹‹በዋጡን ነበር›› ሲል ብዜትን ያስረዳናል፡፡ እንዲሁ ሊናጠቁን የሚተጉ በበዙበት ሁኔታ ወደ እቅፉ የነጠቀን ጌታ ክብርን ሊወስድ ይገባዋል፡፡ እግዚአብሔር ያስመልጣል፡፡

       ካልገቡንና ካልተረዳናቸው ክፋቶች ሸሽጎ በፊቱ ምስክሮቹ ያደረገን፤ ታማኝ አገልጋይ አድርጎ የቆጠረን ጌታ ስሙ ይቀደስ፡፡ በሕይወት ያለን ነገር መዋጥ እንዴት ያለ ጭካኔ ሊሆን እንደሚችል ልብ በሉ፡፡ የምንኖርበት ዓለም እንዲህ ዓይነት መልክና ጠባይ እንዳለው እናያለን፡፡ ሰይጣን እንደ እባብ ከቀረበ በኋላ ቀጣዩ እንደ አንበሳ መገለጥ ነው፡፡ እንደ መጀመሪያው ያታልላል፡፡ እንደ ሁለተኛው ደግሞ ይከሳል፡፡ እንዲህ ላለው ባላጋራ መሳሪያ የሆነ ሥጋ ለባሽ ‹‹ይውጣል›› ተብሎአል፡፡


                                         - ይቀጥላል -    

2 comments:

  1. ካልገቡንና ካልተረዳናቸው ክፋቶች ሸሽጎ በፊቱ ምስክሮቹ ያደረገን፤ ታማኝ አገልጋይ አድርጎ የቆጠረን ጌታ ስሙ ይቀደስ፡፡

    ReplyDelete
  2. ዘመን ለጽድቅ ይሁንላችሁ!

    ReplyDelete