Tuesday, January 6, 2015

አያፍርባችሁም!



በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

ማክሰኞ ታኅሳስ 28 ቀን 2007 የምሕረት ዓመት

      ዓለማችን በብዙ የሚያሸማቅቁና የሚያሳፍሩ ታሪኮች የተሞላች ናት፡፡ ሰዎች በሚያፍሩባቸውና በሚታፈርበት ማንነታቸው መካከል ይኖራሉ፡፡ መቀባበል በሥጋ ለባሽ ዘንድ ቀላል ዋጋን የሚያስከፍል አይደለም፡፡ ሰዎች ሌሎች መሰል ወገኖቻቸው ለእነርሱና ለተግባራቸው አዎንታዊነትን እንዲያሳዩ እጅግ ዋጋን ይከፍላሉ፡፡

      በሰው ፊት ላለማፈር ወይም መታፈሪያ ላለመሆን አጊጠውና ደምቀው፤ አጥንተውና ደክመው ብዙዎች በአደባባይ ይቆማሉ፡፡ ብዙ ጓዳዎች የአገር ያህል ተቆጥረው ሰዎች ለሕዝብ እንደሚሆኑት ያህል ተጨንቀው በቤታቸው ይሆናሉ፡፡ በዚህ ሁሉ ግን ሰው ተቀባብቶ በጭንብል፤ ሸነጋግሎ በወሬ የማያልፈው ውስጣዊ መራቆት፤ የሕሊና ሃፍረት ይሰማዋል፡፡

      በሰው ታሪክ እፍረት የጀመረው በመጀመሪያው ሰው መኖሪያ ቤት ቅጥር ውስጥ ነው /ዘፍ. 3፡8/፡፡ አንድ አካል የነበሩት ባልና ሚስት እንደ ነበሩ ቀርቶ፤ ሁለት ሆኖ ለመቆም እንኳን አቅም አጡ፡፡ በደል ጉልበት ያሳጣል፡፡ ነውር አያስተያይም፡፡ ሐዋርያው ‹‹ስለዚህ እኔ ደግሞ በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ሁልጊዜ ነውር የሌለባት ሕሊና ትኖረኝ ዘንድ እተጋለሁ።›› /ሐዋ. 24፡16/ እንዳለ፤ በእግዚአብሔር ፊት ብቻ ሳይሆን ሰው በሰው ፊት ለመቆምም ንጽሕና ትልቅ አቅም ነው፡፡

      የኃጢአት የመጀመሪያው ውጤት መተፋፈርና መፍራት ነው፡፡ አዳም ከጎኑ የተገኘች እግዚአብሔር የፈጠረለትን ሚስቱን አፈረባት፡፡ ሔዋንም እንዲሁ፡፡ ሁሉም ሲገለጥ አንዳቸው በሌላቸው ፊት መቆም አቃታቸው፡፡ ዛሬም ብዙ ትዳሮች ስላልተገለጡ እንጂ ስንቱ በተፋፈረና ለመለያያት ባመረረ ነበር፡፡ ቅጠል ያገለደሙ፤ ግንዳቸውን የታመኑ በሰው ፊት ብዙ መወደድንና መሰማትን እንዳገኙ ቢመስላቸውም እውነተኛ ሰላም ግን የላቸውም፡፡ በራሳቸውና በሌሎች የሚያፍሩ ዛሬም በዙሪያችን አሉ፡፡

      ልጅ አምጣ በወለደችው እናቱ፤ አባት በአብራኩ ክፋይ በልጁ የሚያፍሩበትን ሁኔታ ስናይ እንገረማለን፡፡ ትምህርት ቤት ሳለሁ ስለ ወላጅ አባት ሲወራ ሁልጊዜ ርዕሱን ለማዳፈን የሚፍጨረጨር ልጅ አስታውሳለሁ፡፡ ለእርሱ ከየትኛውም ነገር በላይ ‹‹ወላጅ አምጣ›› ያስጨንቀው ነበር፡፡ ምክንያቱ ግልጽ ባይሆንልኝም በወላጆቹ በጣም ያፍር እንደ ነበር ግን አውቃለሁ፡፡ ምድራችን ሕዝባቸው በሚያፍሩባቸው መሪዎች፤ ቤተሰባቸው በማይደሰትባቸው ወላጆች፤ ለእናት ለአባታቸው ስቃይ በሆኑ ልጆች . . . የተጨናነቀች ናት፡፡

      አለመታዘዝ /ዘፍ. 2፡16/ በሰው ኑሮ ላይ መተፋፈርን ጨመረ፡፡ ሰው በገዛ ልቡ ዝንባሌ ወደ ራሱ መፍትሔ ዘወር ቢልም ከማባስ ባለፈ አንዳች አላተረፈም፡፡ እግዚአብሔር ግን ‹‹ወዴት ነህ?›› የሚል ድምጹን ሃፍረት በነገሠበት የሰው ኑሮ ላይ ያሰማ ነበር፡፡ የሸሸውን የተከተለ፤ ጀርባውን ለሰጠው ፊቱን ያልሰወረ፤ በድካሙ ላይ ደካማ ብልሃተኛውን ሰው የታገሠ፤ ርኅራኄና ፍቅሩን በተግባር የገለጠ እግዚአብሔር ነው፡፡ አዳም ከእግዚአብሔር ወዳነሰው ግንድ ሲያዘግም የሚበልጠው እግዚአብሔር ግን ድምጹን እያሰማ ይከተለው ነበር፡፡

      ነቢዩ ‹‹ቸርነትህና ምሕረትህ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ ይከተሉኛል›› /መዝ. 22፡6/ ይላል፡፡ የሚከተለንን ነገር ለማስተዋል ቆም ብሎ ዘወር ማለት ያስፈልጋል፡፡ ነውራቸው ፊት ፊት እየቀደመ የሚነዳቸው፤ ሥጋ እንዳሳዩት ሥጋ በል እንስሳ የራቃቸውን እየተከተሉ የሚኖሩ ሰዎች ቀዳሹን እግዚአብሔር መታዘዝ እንቢ ብለው ነው፡፡ የበለጠው እየተከተለን ባነሰው ላይ ሙጭጭ ካልን ያ ኑሮ ምርጫችን ነው፡፡ ቃሉ ግን ‹‹እናንተ የምድር ዳርቻ ሁሉ፥ እኔ አምላክ ነኝና፥ ከእኔም በቀር ሌላ የለምና ወደ እኔ ዘወር በሉ ትድኑማላችሁ።›› /ኢሳ. 45፡22/ ይላል፡፡ መዳን በእርሱ ብቻ ነው /ሐዋ. 4፡12/!

      ደግሞ በሌላ ስፍራ ‹‹ቃሉን ላከ ፈወሳቸውም፥ ከጥፋታቸውም አዳናቸው።›› /መዝ. 106፡20/ ተብሎ ተጽፎአል፡፡ ያ በዔደን ገነት ውስጥ የተሰማው ቃል ጸጋንና እውነትን ተመልቶ በእኛ አደረ /ዮሐ. 1፡14/፡፡ ከኃጢአትና ከበደል፤ ከውጤቱም ከሞት የሚያድን የእግዚአብሔር ልጅ /አካላዊ ቃል/ ከድንግል በበረት ተወለደ፡፡ በገነት ለሁለት ነፍሳት የተሰማው ድምጽ በቤተልሔም ለዓለም ሁሉ የምስራች ሆነ፡፡ አንዱ ስለ ሁሉ ይሞታልና /2 ቆሮ. 5፡14/ በአንዱ በክርስቶስ መወለድ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆነው መዳን በሰው መካከል ተገለጠ፡፡ ለዓለሙ ሁሉ ችግር፤ ለሁሉ የሚበቃ መፍትሔ መጣ፡፡

      እግዚአብሔር ከጥንት ጀምሮ በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት እንደተናገረ፤ ምሪቱን እንዳስታወቀ፤ ፈቃዱን እንዳስፈፀመ፤ በዚህ ዘመን መጨረሻ ግን ሁሉን ወራሽ ባደረገው ከነቢያትም እጅግ በሚልቀው በልጁ ተናገረን /ዕብ. 1፡1/፡፡ ‹‹እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ፥ እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፥ ይኸውም ዲያብሎስ ነው፥ በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ፥ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ።›› /ዕብ. 2፡14/ ተብሎ እንደተፃፈ፤ የእግዚአብሔር ልጅ የሰው ልጅ ሆነ፤ ፍፁም አምላክ ፍፁም ሰው ሆኖ ተገለጠ፡፡

      ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ ተገልጦአልና /ቲቶ. 2፡11/ ሰዎች ለዚህ የጸጋ አሠራር በእምነት ሲታዘዙ በክርስቶስ የእግዚአብሔር ጽድቅ ይቆጠርላቸዋል /ሮሜ 4፡23/፡፡ የሆነው ሁሉ እግዚአብሔር በልጁ በኩል ለእኛ ልጆቹ እንሆን ዘንደ ያደረገው ነውና ‹‹የማያፍርብን›› እንሆናለን፡፡ ሰዎች ታትረው የማያሳፍር ነገር ሊያቆሙ በምድሪቱ ላይ ይተጋሉ፡፡ የሚያሳፍረውን እያረሙና እያሻሻሉም ይኖራሉ፡፡ በክርስቶስ ካልሆነ በቀር ከሚያሳፍር ኑሮ መውጣት ከቶ አይቻልም፡፡ እርሱ ሰዎች ለመወለድ ቀርቶ ለመገኘት በሚያፍሩበት ቦታ በሥጋ ተወልዷል /ሉቃ. 2፡7/፡፡ በአብ ፊት የማይታፈርብን ልጆች ሆነን እንድንቀርብ ክርስቶስ በውርደት ተመላልሷል፡፡

      ልደቱ በረት ሞቱ መስቀል ላይ የሆነው ብዙ ልጆችን ወደ ክብር ለማምጣት የመዳናቸውንም ራስ በመከራ ይፈጽም ዘንድ ነው፡፡ ተወዳጆች ሆይ፤ ክርስቶስ ኃጢአትን ሊያስወግድ፤ የዲያብሎስን ሥራ እንዲያፈርስ ተገልጦ ሳለ፤ በተወለደ ሰበብ የዲያብሎስን ሥራ መገንባትና በኃጢአት ውስጥ መኖር አግባብ ነውን? ‹‹በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን፤ እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ እንደ ገናም በባርነት ቀንበር አትያዙ።›› /ገላ. 5፡1/ ተብለናልና እንደተወደዱ የእግዚአብሔር ልጆች ክርስቶስን በመምሰል ተመላለሱ፡፡


      ክርስቶስ በሥጋ ተዛምዶናል፡፡ ወንድሞቼ ሲለንም አላፈረብንም /ዕብ. 2፡13/፡፡ ከእኛ የሆነ ምንም ስለሌለ፤ ሁሉ ከእርሱና በእርሱ ለእርሱ ስለሆነ ጌታ በራሱ አያፍርም፡፡ የክርስቶስ የሆነው ሁሉ ለእኛ ከሆነ፤ የእኛ የሆነ ምን አለ? ሐዋርያው ስለ እምነት በፃፈበት ክፍል ‹‹አሁን ግን የሚበልጠውን እርሱም ሰማያዊ አገር ይናፍቃሉ። ስለዚህ እግዚአብሔር አምላካቸው ተብሎ ሊጠራ በእነርሱ አያፍርም፥ ከተማን አዘጋጅቶላቸዋልና።›› /ዕብ. 11፡16/እንዳለ፤ ለማያፍርብን አምላክና አባት የታመኑ ልጆች ሆነን በእምነት እንኑር!!
                                          ‹‹ . . . ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤›› /ቆላ. 4፡3/!

No comments:

Post a Comment