Friday, October 2, 2015

‹‹የመጽናናት ሁሉ አምላክ››


      (2 ቆሮ. 1፡3)
 
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

አርብ መስከረም 21 ቀን 2008 የምሕረት ዓመት

          በቅዱሱ መጽሐፋችን ‹‹አጽናኑ፤ ሕዝቤን አጽናኑ፡ ይላል አምላካችሁ፡፡›› /ኢሳ. ፡1/ ተብሎ እንደተጻፈ፤ ክርስቲያኖች በፈተናና በመከራቸው እርስ በእርስ የሚጽናኑበት ‹‹የርኅራኄ አባትና የመጽናናት ሁሉ አምላክ›› እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ 
          እርሱ አምላካችን የዘላለም አምላክ፤ የምድር ዳርቻ ፈጣሪ፤ የማይደክም የማይታክት፤ ማስተዋሉም የማይመረመር፤ ሰማያትን የፈጠረ የዘረጋቸው፤ ምድርንና በውስጥዋ ያለውን ያጸና፤ በእርስዋ ላይ ለሚኖሩ ሕዝብ እስትንፋስን፣ ለሚሄዱባትም መንፈስን የሚሰጥ ነው፡፡   

          ተወዳጆች ሆይ፤ ያላችሁበትን መከራ ጎናችሁ ካለው ሌላው መከረኛ /ተፈታኝ/ በላይ ጌታ በቅርበት የሆነባችሁን ያውቃል፡፡ ‹‹ጌታ ቅርብ ነው›› /ፊልጵ. 4፡6/ እንደተባለ፤ እርሱ ለአካላችሁ ብቻ ሳይሆን ለውስጥ ሰውነታችሁም የተጠጋ ነው፡፡ ከከንፈሮቻችሁ መንቀሳቀስ ሳይሆን ከልባችሁ የሚያደምጥ አምላክ ነው፡፡ 
          ሁኔታዎች ይለወጣሉ፤ እርሱ ግን ለዘላለም ያው ነው /ዕብ. 13፡8/፡፡ ሐዋርያው ‹‹በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ሁሉ ከላይ ናቸው፥ መለወጥም በእርሱ ዘንድ ከሌለ በመዞርም የተደረገ ጥላ በእርሱ ዘንድ ከሌለ ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ።›› /ያዕ. 1፡17/ እንዳለ፤ በእግዚአብሔር ዘንድ መለወጥ የለም /ሚል. 3፡6/፡፡ 
          አምላካችሁ እንደወደዷችሁ አልያም እንደጠሉአችሁ እንደነርሱ አይደለም፡፡ እርሱ ብቻውን መጽናናትና መታመኛችሁ ነው፡፡ ካላችሁበት ፈተና ባለፈ አስተውሉ፤ በደረሳችሁበት ሁሉንም በእምነት ዓይን ተመልከቱ፤ እግዚአብሔር በእናንተ ዘንድም ነው፡፡
          እርሱ በዚህ አለ ወይም በዚያ የለም አይባልም፡፡ ከፀሐይ መውጣት በላይ ምድርን ያካለለ፤ በክበብዋ ላይ የተቀመጠ፤ ሰማያትን እንደ መጋረጃ የሚዘረጋቸው፤ እንደ ድንኳንም ለመኖርያ የሚዘረጋቸው አምላካችሁ እርሱ እግዚአብሔር ብቻ ነው /1 ጢሞ. 1፡17/፡፡
 
          እግዚአብሔር የሁሉ ዓይን የሚያርፍበት ብቸኛ ተስፋ ነው /መዝ. 144፡15/፡፡ ተስፋና እምነታችሁን ከእግዚአብሔር ባነሰ ነገር ላይ አታድርጉ /መዝ. 24፡3/፡፡ አምላካችሁ እንደ ባለ ጠግነቱ መጠን በክብር በክርስቶስ ኢየሱስ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ ይሞላባችኋል /ፊል. 4፡19/፡፡ 
          አምላካችሁ ለደካማ ኃይልን ይሰጣል፤ ጉልበት ለሌለውም ብርታትን ይጨምራል፤ እርሱን በመተማመን ብትጠባበቁ ኃይላችሁ ይታደሳል፡፡ ሕይወት ብርቱ ሰልፍ ብትሆንባችሁም፤ እግዚአብሔር ብርቱ ተዋጊ ነው /ዘፀ. 15፡3/፡፡ ከምታዩትም ከማታዩትም፤ ከገባችሁም ካልተረዳችሁትም ፈተና ታዳጊያችሁ እርሱ የዘላለም አምላክ፤ የርኅራኄ አባት እግዚአብሔር ነው፡፡
          ‹‹እግዚአብሔር በወጀብና በዐውሎ ነፋስ ውስጥ መንገድ አለው፥ ደመናም የእግሩ ትቢያ ነው።›› /ናሆ. 1፡3/ እንደተባለ፤ እርሱ በመከራችሁ መውጫ ነው፡፡ በየትኛውም መናወጥና መናጥ ውስጥ ብትሆኑ ደመና እንደ እግሩ ትቢያ የሆነለት እግዚአብሔር ታዳጊያችሁ ነው፡፡ 
          ሐዋርያው ለሰው ሁሉ ከሚሆነው በቀር ምንም ፈተና አልደረሰባችሁም ካለ በኋላ ‹‹ነገር ግን ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፥ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል።›› /1 ቆሮ. 10፡13/ በማለት ለክርስቲያን እግዚአብሔር የሰጠውን ዋስትና ያስረዳናል፡፡
          የቅዱሱ የእግዚአብሔር ቃል ለልባችን ብዙ መጽናናትን በምናገኝባቸው አሳቦች የደመቀ ነው፡፡ ችግራችሁን አታጉሉ፡፡ በችግሮቻችሁ ላይ ግን የእውነትን አዋጅ በእምነት ድፍረት ተናገሩ፤ የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ /ኤፌ. 6፡17/፡፡ መከራችሁ ከሚናገረው የሚበልጠውን ቃሉ ይናገራል፡፡ ከእግዚአብሔር የሆነውንም መፍትሔ ወደ ልባችሁ ያደርሳል፡፡ 
          እምነት ከመስማት ነውና /ሮሜ 10፡17/ ስለ ፈተናዎቻችሁ ያላችሁ መረዳት እምነት እንዳይሆንባችሁ ተጠንቀቁ፡፡ ችግሩን ለመላመድ ትከሻችሁን ከማስፋት ለቃሉ ልባችሁን ማስፋት ጥበብ ነውና በዚህ እንዳትሞኙ፡፡ በፈተናችሁ ውስጥ ከእግዚአብሔር የሆነውን ትምህርት በትህትና ተማሩ፡፡ የሚያልፈው ላይ ስታፈጡ የማያልፈው እንዳያመልጣችሁ ልብ አድርጉ፡፡ 
          እንግዲህ ‹‹ልባችሁ አይታወክ፤ በእግዚአብሔር እመኑ በእኔም ደግሞ እመኑ፡፡›› /ዮሐ. 14፡1/ ተብሎ እንደተጻፈ፤ በማዕበል ውስጥ ጸጥታ፣ በበረሃው ዘንድ ጥላ፤ በሠልፍም መካከል ድል፤ በስደትና መከራ ጽናት ያለው በእምነት ነው፡፡ ያላችሁበት ሁኔታ ሞትንም የምታስተናግዱበት ሊሆን ይችላል፤ ያመናችሁበት ጌታ ግን ሞትንም ያሻግራል /ዮሐ. 11፡25/፡፡

          አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ ብሎ ማመን፤ ደግሞ በእኔ እመኑ እንደተባለ፤ የእግዚአብሔር ልጅ ከድንግል ተወልዶ በሥጋ በመገለጥ ስለ ኃጢአታችን እንደ ሞተልን፤ ስለ ጽድቃችንም ከሙታን ተለይቶ እንደ ተነሣ /ሮሜ 4፡24/፤ ስፍራ ሊያዘጋጅልን ወደ አባቱ እንደሄደ፤ ወዳዘጋጀልንም ስፍራ ሊወስደን ዳግም ተመልሶ እንደሚመጣ /1 ተሰ. 4፡17/ ማመን እና በመታመን መኖር ያስፈልጋችኋል /ዕብ. 10፡35/፡፡ ተወዳጆች ሆይ፤ ያለ መታወክ ምስጢር ያለው ‹‹ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ›› ከልብ በማመን ነው /ዮሐ. 20፡31/፡፡
          እግዚአብሔር የሚወዳችሁ ሆይ፤ ሰማያት በእናንተ ትይዩ ይከፈቱ፤ ሥጋና ደም የማይሰጠው ኃይልና ብርታት ከመለኮት ዙፋን ይጎብኛችሁ፡፡ የማይለቁት የአምላካችን ክንዶች ይያዙአችሁ፤ የማይከደኑት የእግዚአብሔር ዓይኖች በፍቅር ይመልከቷችሁ፤ በምትመለከቱት ከዓይናችሁ፣ በስውር ከልባችሁ የሚፈሰውን የሀዘን ዕንባ የማይሰወረው እግዚአብሔር ያብስላችሁ፤ ዮሴፍን በምድረበዳ በባዕድ አገር ሞገስ የሆነው አምላክ ጥበቃ ይክበባችሁ፤ ብዙ መጽናናት ለእናንተ ይሁን! 
‹‹ . . . ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤›› /ቆላ. 4፡3/!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!                           
/በስደት ላይ ላሉ ኢትዮጵያውያን የደረሰ የመጽናናት ቃል/

No comments:

Post a Comment