Monday, January 4, 2016

በተረገመች ምድር፡ ዕረፍታችን!

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!


                                                                           

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

ሰኞ ታኅሣሥ 25 ቀን 2008 የምሕረት ዓመት

          ‹‹ላሜሕም መቶ ሰማንያ ሁለት ዓመት ኖረ፥ ልጅንም ወለደ። ስሙንም፦ እግዚአብሔር በረገማት ምድር ከተግባራችንና ከእጅ ሥራችን ይህ ያሳርፈናል ሲል ኖኅ ብሎ ጠራው።›› /ዘፍ. 5፡28-29/!

         የመጽሐፍ ቅዱሳችን የመጀመሪያ ክፍል የሆነው የዘፍጥረት (የልደት) መጽሐፍ የትውልዶችን ጅማሬ የሚያስረዳን መጽሐፍ ነው፡፡ ስለ ተፈጥሮ ጅማሬ፤ ግሩምና ድንቅ ሆኖ ስለ ተፈጠረው የሰው ልጅ፤ ውድቀት ስላስከተለው ኪሳራ፤ ያንን ተከትሎ ለሰው ስለተሰጠው የመዳን ተስፋ የምናውቅበት ክፍል ነው፡፡ ምእራፍ አምስት ‹‹የአዳም የትውልዱ መጽሐፍ ይህ ነው›› በሚል ርእስ ይጀምራል፡፡

         በምእራፉ ውስጥ

1.     አዳም (5፡1-5)፡- ሰው ማለት ነው፡፡
2.    ሴት (5፡6-8)፡- ምትክ ማለት ነው፡፡
3.    ሄኖስ (5፡9-11)፡- ደካማ ማለት ነው፡፡
4.    ቃይናን (5፡12-14)፡- አሳዛኝ ማለት ነው፡፡
5.    መላልኤል (5፡15-17)፡- በእግዚአብሔር የተባረከ ማለት ነው፡፡
6.    ያሬድ (5፡18-20)፡- ቀጣይ ትውልድ ማለት ነው፡፡
7.    ሄኖክ (5፡21-24)፡- ትምህርት ማለት ነው፡፡
8.    ማቱሳላ (5፡25-27)፡- ሲሞት ይመጣል ማለት ነው፡፡
9.    ላሜሕ (5፡28-31)፡- ኃይለኛ ማለት ነው፡፡
10.  ኖኅ (5፡32)፡- ዕረፍትና ምቾት ማለት ነው፤ (ዝርዝሩ እስከ ዘፍ. 6፡8 ድረስ ይቀጥላል)፡፡

         ከላይ ከተዘረዘሩት ትውልዶች መካከል ኃይለኛና ብርቱ የሚል የስም ትርጉም ያለው ላሜሕ ለልጁ ለኖኅ ያወጣለትን የስም ትርጉም በተነሣንበት ርእስ ለማየት እንሞክራለን፡፡ ስሙንም፦ እግዚአብሔር በረገማት ምድር ከተግባራችንና ከእጅ ሥራችን ‹‹ይህ ያሳርፈናል›› ሲል ኖኅ ብሎ ጠራው፤ ተብሎ ተጽፎልናል፡፡ በላሜሕ ልብ ውስጥ ያለውን ታላቅ ምኞት አስተውላችሁ ከሆነ በአጭር ቃል ‹‹ዕረፍት›› መሆኑን ትደርሱበታላችሁ፡፡    

         ‹‹ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትሁን›› /ዘፍ. 3፡17/ የተባለውን አዳምን ስናስታውስ፤ ‹‹ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፥ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ፤›› /ሮሜ 5፡12/ የሚለውን ግልጽ ታሪካችንን ልብ እንላለን፡፡ እግዚአብሔር በሰው ውድቀት ላይ ፍርድን ሲያስተላልፍ አብሮ የመዳን ተስፋን ስለሰጠ (እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፥ አንተም ሰኰናውን ትቀጠቅጣለህ)፤ አዳምና ሔዋን የሰሙትን ተስፋ በማመን አዳኙን እንደጠበቁ እናስባለን፡፡

        ትውልድ በቀጠለ ቁጥር ‹‹ራስህን ይቀጠቅጣል›› የተባለለትን ከወለዱት መካከል ተስፋ ያደርጋሉ፡፡ ሔዋን የመጀመሪያ ልጇን በወለደች ጊዜ ‹‹ወንድ ልጅ ከእግዚአብሔር አገኘሁ›› /ዘፍ. 4፡1/ በማለት ተናግራለች፡፡ ሔዋን በወለደችው በቃየን ውስጥ የእባቡን ራስ የሚቀጠቅጥ ማንነትን ተስፋ አድርጋ ይሆናል፤ ዳሩ ግን አምጣ የወለደችው የወንድሙን ራስ የሚቀጠቅጥ እባብ ሆነባት፡፡ ‹‹የምትዘገይ ተስፋ ልብን ታሳዝናለች›› /ምሳ. 13፡12/ ተብሎ እንደ ተጻፈ፤ የሔዋን (የሕያዋን ሁሉ እናት) ልብ ምን ያህል ያዝን ይሆን፡፡

        አዳምና ሔዋን የበደላቸውን ውጤት ምድር ላይ አይተዋል፡፡ የመርገሙንም ቀጣይነት ተገንዝበዋል፡፡ አቤል (እስትንፋስ ማለት ነው) በወንድሙ ጭካኔ ወዲያው ታይቶ ሲጠፋ፤ ከእግዚአብሔር መለየት የሚያስከፍለው ዋጋ ለአዳምና ለሔዋን ግልጽ ነበረ፡፡ ሞት ምን እንደ ሆነ የማያውቁት አዳምና ሔዋን እግዚአብሔር አንድ እንስሳ ሠውቶ ባለበሳቸው በቁርበቱ በኩል፤ አቤል ደግሞ በእምነት ባቀረበው በመሥዋዕቱ (በበጉ) በኩል ከዘላለም ሞት የሚመለጥበትን አስተዋሉ (ዮሐ. 1፡29)፡፡

         ብሉይ ኪዳን ትውልድ ይቆጥራል፡፡ ለመጀመሪያው ሰው የተሰጠውን ተስፋ ወደ ፍጻሜ መምጣት  በሚወልዷቸው ልጆች መካከል በብርቱ ይፈልጋሉ፡፡ ስማቸውንም ሲያወጡ በአብዛኛው የተሰጠውን ተስፋ ባገናዘበ መልኩ ነበር፡፡ ይመጣል የተባለው መሲሕ መምጣቱ በእጅጉ ይናፈቅ ነበርና፡፡ አዳም ‹‹ሰኮናው የሚነከስ ክርስቶስ›› ከሔዋን እንደሚወለድና የእባቡ ራስ እንደሚቀጠቀጥ እግዚአብሔር የተናገረውን ሰምቶ (እምነት ከመስማት ነው) አምኗል፡፡ ከእርሱ ከሚወለደው የአብራኩ ክፋይ ‹‹ዕረፍትን›› እንዴት ሊናፍቅ እንደሚችል እንረዳለን፡፡

          ኖኅ የስሙ ትርጉም እግዚአብሔር በረገማት ምድር እረፍት ወይም ምቾት የሚል ነው፡፡ አባቱ ላሜሕ በልጁ ላይ ምን ያህል ተስፋ እንዳደረገ እናስተውላለን፡፡ እረፍትን የሚፈልግ የተበላሸ የሰው ታሪክ ዛሬም የምድሪቱ ሸክም ነው፡፡ ላሜሕ ኃይለኛ (ብርቱ) የሚል ስም ቢኖረውም ለተረገመችየረቱ ምድር ግን እረፍት መሆን አልቻለም፡፡ ስለዚህ በእርሱ በኩል ያልመጣውን ምቾት በልጁ በኩል እንደሚሆን አሰበ፡፡

          በእምነት የሚገኘውን ጽድቅ ወራሽ የሆነው ኖኅ፤ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር በማድረግ ዓለምን የኮነነ፤ የእግዚአብሔርን ማስጠንቀቂያ በመቀበል ስለማይታየው፤ ነገር ግን በተቀጠረው ጊዜ የሚሆነውን ፍርድ የተረዳና መርከብን በእምነት ያዘጋጀ ነበር (ዕብ. 11፡ 7)፡፡ በኃጢአተኞች ዓለም ላይ የጥፋትን ውኃ ያወረደው እግዚአብሔር፤ የጽድቅ ሰባኪ የነበረውን ኖኅን ግን ከሌሎች ሰባት ጋር እንዳዳነው ቅዱሱ መጽሐፍ ይነግረናል (2 ጴጥ. 2፡5-6)፡፡

           የደኅንነት አምላክ አምላካችን እግዚአብሔር ነው፤ ከሞት መውጣትም ከእርሱ ብቻ ነው (መዝ. 67፡20፤ ሮሜ 1፡16)፡፡ እግዚአብሔር ከመጣው የጥፋት ውኃ ያዳነው ኖኅ፤ ገበሬ መሆን በጀመረና ወይን በተከለ ጊዜ ከዚያው ጠጥቶ እንደሰከረና እንደተራቆተ እንመለከታለን (ዘፍ. 9፡20)፡፡ በመጀመሪያው ሰው የታየው መራቆት ቀጣይነቱን እንዴት እንዳስጠበቀ አስተውሉ፡፡ ያ በእባብ ምክር ይኼ በሥጋው ምኞት ሁሉም እግሮች ወደ ሞት ይፈጥኑ ነበር፡፡

          በቀደመው ኪዳን ‹‹ሰማዮችን ቀድደህ ምነው ብትወርድ›› /ኢሳ. 64፡1/ የተረገመችይቱ ምድር ብርቱ ጩኸት ነበር፡፡ ለሰው እረፍትና ምቾትን ሊያመጣ የሚችል ከሰው መካከል አንድ ስንኳ አልተገኘም (ሮሜ 3፡9-23)፡፡ ‹‹አቤቱ፤ እባክህ አሁን አድን፤ አቤቱ እባክህ አሁን አቅና፡፡›› /መዝ. 117፡25/ ጽድቁ እንደ መርገም ጨርቅ የሆነው /ኢሳ. 64፡6/ የሰው ዘር የጋራ ጸሎት ርእስ ነው፡፡ ላሜሕ ኃይለኛውን፤ ኖኅ እረፍት አልሆነውም፡፡ በእርግጥም ‹‹ይህ ያሳርፈናል›› የተባለው እውነተኛ የዘላለም እረፍት ሊሆን አልተቻለውም፡፡

          ‹‹እግዚአብሔርም አየ . . ሰውም እንደሌለ አየ . . ስለዚህ የገዛ ክንዱ መድኃኒት አመጣለት ጽድቁም አገዘው›› /ኢሳ. 59፡16/ ተብሎ እንደተጻፈ፤ ‹‹ . . የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ፤ እንደ ልጆች እንሆን ዘንድ ከሕግ በታች ያሉትን ይዋጅ ዘንድ፡፡›› /ገላ. 4፡4/፡፡ ሔዋን ከእግዚአብሔር አገኘሁ ያለችው ወንድ ልጅ በእባቡ መስመር የሄደ ቢሆንም፤ አለቅነት በጫንቃው ላይ የሚሆን፣ ስሙም ድንቅ መካር ኃያል አምላክ የዘላለም አባት የሰላም አለቃ ተብሎ የሚጠራ፤ የእባቡን ራስ የሚቀጠቅጠው ከእግዚአብሔር የተሰጠን ወንድ ልጅ ተወለደ (ኢሳ. 9፡6፤ ሉቃ. 2፡11)፡፡ ‹‹ይህ አሳርፎናል››!

          ኖኅ ድካሙ ያመጣበትን ራቁትነት እናይበታለን፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ጸጋ ስለ ሁላችን ኃጢአት እርቃኑን በመስቀል ላይ የተሰቀለ ነው (ዕብ. 2፡9)፡፡ እርሱ ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ? (አምላኬ አምላኬ ለምን ተውኸኝ?) በማለት ራሱን ከእኛ ጋር በመቁጠር (ማር. 15፡34)፤ ‹‹በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ ከሕግ እርግማን ዋጀን›› /ገላ. 3፡13/፡፡ በተረገመችይቱ ምድር ስለ እኛ እርግማን የሆነው፤ በቤተልሔም በበረት የተወለደው ኢየሱስ ነው፡፡

          እግዚአብሔር ‹‹ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋል›› ያለው ኢየሱስ ብቸኛው እረፍት ነው፡፡ እርሱ ብቻ ‹‹እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ።›› /ማቴ. 11፡28/ ማለት ተችሎታል፡፡ ተወዳጆች ሆይ፤ እረፍትና ምቾት በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለን የእምነት መደገፍ የሚሆን ነው፡፡                                                    -      ይቀጥላል
                                                    ‹‹ . . . ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤›› /ቆላ. 4፡3/!

No comments:

Post a Comment