በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
እሁድ ሚያዝያ 11 ቀን 2007 የምሕረት ዓመት
‹‹ሕያውን ከሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጋላችሁ? ተነሥቶአል እንጂ በዚህ የለም።››
/ሉቃ. 24፡5/
‹‹ሕያውን ከሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጋላችሁ? ተነሥቶአል እንጂ በዚህ የለም።››
/ሉቃ. 24፡5/
የብሉይ
ኪዳን መጻሕፍ የሚጀምረው የእግዚአብሔርን ሉዓላዊነት በማወጅ ነው፡፡ ‹‹በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ።›› /ዘፍ.
1፡1/፤ እግዚአብሔር የበላይ የሌለበት ሉዓላዊ አምላክ ነው፡፡ እርሱ እንደሚያይ የሚመለከት ሌላ፤ እርሱ እንደሚያውቅ የሚረዳ ሌላ፤
እርሱ እንደሆነው የሚገኝ ሌላ የለም፡፡
‹‹ብቻውን
ተአምራትን የሚያደርግ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ›› /መዝ. 71፡18/፤ ‹‹እርሱ ብቻውን ታላቅ ተአምራትን ያደረገ
ምሕረቱ ለዘላለም ነውና›› /መዝ. 135፡7/፤ ‹‹እርሱ ግን ብቻውን ነው፤ እርሱንስ የሚመስለው ማን ነው? ነፍሱም የወደደችውን
ያደርጋል።›› /ኢዮ. 23፡13/፤ የሚሉት መዝሙራት እግዚአብሔር ብቻውን የበላይ ገዥ አምላክ መሆኑን ያስረዱናል፡፡
ነቢዩ
በሌላ ስፍራ ‹‹እግዚአብሔር ታላቅ ነው፤ እጅግም የተመሰገነ ነው፤ ለታላቅነቱም ፍፃሜ የለውም፡፡ ትውልደ ትውልድ ሥራህን ያመሰግናሉ፤
ኃይልህንም ያወራሉ፡፡ የቅድስናህን
ግርማ ክብር ይነጋገራሉ፤ ተአምራትህንም ይነጋገራሉ፡፡
የግርማህንም ኃይል ይናገራሉ፤ ታላቅነትህንም ይነጋገራሉ፤ ብርታትህንም ይነጋገራሉ፡፡›› /መዝ. 144፡3-6/ ይላል፡፡ ስለ እግዚአብሔር ከተነጋገርን ብርታትና ታላቅነቱን
እንነጋገራለን እንጂ እርሱ ድካም የለበትም፡፡ በዘመናት የማይቀያየር፤ በሁኔታዎች የማይዝል ግርማ የእግዚአብሔር ነው፡፡ ይታጣል
ይሞታል ተብሎ ለእርሱ አይሠጋም፡፡