Sunday, April 19, 2015

በዚያ አይፈልጓችሁ


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
እሁድ ሚያዝያ 11 ቀን 2007 የምሕረት ዓመት
‹‹ሕያውን ከሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጋላችሁ? ተነሥቶአል እንጂ በዚህ የለም።››
 /ሉቃ. 24፡5/
         የብሉይ ኪዳን መጻሕፍ የሚጀምረው የእግዚአብሔርን ሉዓላዊነት በማወጅ ነው፡፡ ‹‹በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ።›› /ዘፍ. 1፡1/፤ እግዚአብሔር የበላይ የሌለበት ሉዓላዊ አምላክ ነው፡፡ እርሱ እንደሚያይ የሚመለከት ሌላ፤ እርሱ እንደሚያውቅ የሚረዳ ሌላ፤ እርሱ እንደሆነው የሚገኝ ሌላ የለም፡፡
         ‹‹ብቻውን ተአምራትን የሚያደርግ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ›› /መዝ. 71፡18/፤ ‹‹እርሱ ብቻውን ታላቅ ተአምራትን ያደረገ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና›› /መዝ. 135፡7/፤ ‹‹እርሱ ግን ብቻውን ነው፤ እርሱንስ የሚመስለው ማን ነው? ነፍሱም የወደደችውን ያደርጋል።›› /ኢዮ. 23፡13/፤ የሚሉት መዝሙራት እግዚአብሔር ብቻውን የበላይ ገዥ አምላክ መሆኑን ያስረዱናል፡፡
         ነቢዩ በሌላ ስፍራ ‹‹እግዚአብሔር ታላቅ ነው፤ እጅግም የተመሰገነ ነው፤ ለታላቅነቱም ፍፃሜ የለውም፡፡ ትውልደ ትውልድ ሥራህን ያመሰግናሉ፤ ይልህንም ያወራሉ፡፡ የቅድስናህን ግርማ ክብር ይነጋገራሉተአምራትህንም ይነጋገራሉ፡፡ የግርማህንም ኃይል ይናገራሉታላቅነትህንም ይነጋገራሉብርታትህንም ይነጋገራሉ፡፡›› /መዝ. 144፡3-6/ ይላል፡፡ ስለ እግዚአብሔር ከተነጋገርን ብርታትና ታላቅነቱን እንነጋገራለን እንጂ እርሱ ድካም የለበትም፡፡ በዘመናት የማይቀያየር፤ በሁኔታዎች የማይዝል ግርማ የእግዚአብሔር ነው፡፡ ይታጣል ይሞታል ተብሎ ለእርሱ አይሠጋም፡፡

         ‹‹አቤቱ፥ በኃይልህ ከፍ ከፍ በል፤ ጽናትህንም እናመሰግናለን እንዘምርማለን።›› /መዝ. 20፡13/ ተብሎ እንደተፃፈ፤ እግዚአብሔር በራሱ ኃይል ከፍ ከፍ የሚል የዘላለም አምላክ ነው፡፡ በዚህ ዓለም የሰዎች ከፍታ ውስጥ ብዙ በጎም ክፉም አስተዋጽዖ አለበት፡፡ በዚህ ዓለም ባለ ሀብትነት ውስጥ ብዙ መንጠቅ፤ በዚህ ዓለም ሥልጣን ውስጥ ብዙ አመጽ፤ በዚህ ዓለም ክብር ውስጥ ብዙ ሸር አለ፡፡
         የሰዎች ልዩ ልዩ ብልጥግና በብዙዎች ግልጽና ስውር ተሳትፎ የመጣ ነው፡፡ ጌታ እግዚአብሔር ድጋፍ በሌለው ብርታት፤ ምክር በሌለበት ጽናት፤ ሕልፈት ባልተቀጠረበት ሕያውነት ያለና የሚኖር ያህዌ ኤሎሂም ነው፡፡ እርሱ ዘመናትን ይሰፍራል ዘመኑ ግን አይሰፈርም፤ እርሱ ዳርቻዎችን ያበጃል ነገር ግን ዳርቻና ወሰን የለውም፡፡ በእግዚአብሔር የማይዳኝ እርሱን የሚዳኘው ማን ነው? ኤል-ሻዲ ባራህ፤ ኤል-ዖላም ባራህ፤ ኤል-ሆሲም ባራህ፤ ኤል-ዔልዮን ባራህ!
         እግዚአብሔርን ስለ ጽናቱ አመስግኑት፡፡ በኃይል በክብር የጸና፤ በመግቦቱ በቸርነቱ የጸና፤ በፍቅር በምሕረቱ የጸና እንደ እርሱ ያለ ማን ነው? በላይ በመላእክቱ ዓለም ሳጥናኤል እንደ ወደቀ፤ የሚጋርድ ኪሩብ የነበረው እንደተዋረደ እናውቃለን /ኢሳ. 14፡12-23/፡፡ በታች በሰው ዓለም አዳምና ሔዋን እንደበደሉ፤ ከጽድቅም እንደጎደሉ እንዲሁ እናውቃለን /ዘፍ. 3፡4-6/፡፡ በመለኮት ጉባኤ ግን አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በማይለያይ ፈቃድ፤ በማይበላለጥ ሥልጣን አንድ አምላክ በጽናት አለ፡፡ እርሱ ብቻ ለመጽናቱ ምስጋናና ዝማሬ ይገባዋል፡፡
         ድካም የሌለበት ብርቱ እግዚአብሔር ኃይሉን፤ የቅድስናውን ግርማ ክብር፤ ተአምራቱንም እናወራለታለን፡፡ ስለ እርሱ ስንነጋገር ብቻ ከብርታት ወደ ብርታት ይሆናል፡፡ የንግግራችን ርዕሱ፤ የወሬአችን ማዕከሉ ታላቅነቱና ብርታቱ እንዲሁም የግርማው ኃይል ይሆናል፡፡ ስለ ሥጋ ለባሽ ስናወራ ዝለቱም ይወራል፤ አቅም እንደ ከዳው፤ ቀን እንደጣለው፤ ስንፍና እንደያዘው፤ ምክሩ እንደጠፋ ይተረካል፡፡ አምላካችን ግን የኃይል አምላክ ነው፤ ምስጋናና ዝማሬም ለእርሱ ነው፡፡
        በአዲስ ኪዳን ‹‹ሞት ሆይ፥ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ፥ ድል መንሣትህ የት አለ?›› /1 ቆሮ. 15፡55/፤ ብለን ስለዘመርንበት የትንሣኤው ኃይል እናስተውላለን /ፊል. 3፡10/፡፡ ከሙታን መካከል የማይፈለገው የናዝሬቱ ኢየሱስ ከሙታን መካከል ተለይቶ ተነሥቶአል፡፡
        ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በአቴና የኢየሱስንና የትንሣኤውን ወንጌል ስለሰበከ አዲሶችን አማልክት የሚያወራ ይመስላል እንዳሉት እናነባለን /ሐዋ. 17፡18/፡፡ በአርዮስፋጎስ  አደባባይ ዘወትር መሰብሰብ ልማዳቸው ለነበሩት ፈላስፎች የትንሣኤው ነገር ለጆሮአቸው እንግዳ ነው፡፡ እንደ ለፍላፊ በቆጠሩት የጳውሎስ አንደበት ላይ ከሞት የመነሣትን ዜና የሚያበስር የምስራች ነበረ፡፡
        በማኅበረሰቡ መካከል እንደ መፍትሔ የሚሰሙት ምሁራን፤ ስለ ክርስቶስ ሰምተው አዲስን ነገር አስተናገዱ፡፡ ሞትን ከባርነት ነፃ መውጫ መንገድ አድርገው የሚቆጥሩት የግሪክ ፈላስፎች የሚሰበከውን ክርስቶስን ሊሰሙት ፈቀዱ፡፡ ለፍላፊ እያሉ ካፌዙበት ጳውሎስ የዘላለም የምስራችን ሰሙ፡፡ ፍልስፍናቸው ያልደረሰበትን እምነት አብራራላቸው፡፡  
        ተወዳጆች ወዳጆቼ ሆይ፤ ወንጌል ስለ ልጁ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው /ሮሜ 1፡3/፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን ኡፉ ኡፉ እየተባለ የኖረ የሚመስለው ሕዝብ እጁ ላይ ያለውን መጽሐፍ ቅዱስ የአዲስ ኪዳን ክፍል ቢገልጠው ‹‹የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ፡ አዲስ ኪዳን›› እንዲሁም በየወንጌላቱ የላይ ክፍል ‹‹የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል፡ ቅዱስ ማቴዎስ/ ማርቆስ/ ሉቃስ/ ዮሐንስ እንደ ጻፈው›› የሚል ንባብ በግልጽ ተጽፎአል፡፡
        ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን መነሣት፤ በኃይል የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ መገለጥ ሲሰበክ፤ ይህ የትንሣኤው ወንጌል ይባላል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በአቴና የተናገረው የምስራች ‹‹ኢየሱስ ተነሥቶአል›› የሚል ነው፡፡ በክርስትና ስለ ኃይል የምናወራበት፤ እንዲሁም የምንነጋገርበት ርዕስ የክርስቶስ መነሣት ነው፡፡ ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን ሲባል በዐቢይ ኃይል ወሥልጣን . . . የምንለው የብርታታችን ምንጭና መሠረት ክርስቶስ ከሙታን መነሣቱ ስለሆነ ነው፡፡
        ከክርስቶስ መነሣት ጋር በተያያዘ ለክርስትናችን ተግባራዊ የሆነ ትምህርት የምናገኝባት የቆሮንቶስ ቤተክርስቲያን ናት፡፡ የቆሮንቶስ ቤተክርስቲያን በክርስትናው እድገት ጅማሬ ውድቀትን ካስተናገዱ አብያተ ክርስቲያናት ከፍተኛውን ቦታ ትይዛለች፡፡ በክርስቲያኖቹና በጉባኤው መካከል በአህዛብ ዘንድ እንኳን የማይስተዋል ነውርና በደል ባመኑት ዘንድ ነበረ፡፡ መከፋፈል፤ የዘመዳሞች ጋብቻ፤ እርስ በርስ መፈራረድ፤ በዓለም የችሎት አደባባዮች መካሰስ፤ ዓለማዊነትና በዝሙት መርከስ፤ በጸጋና በእውቀት መታበይ . . . ይታዩባት ነበር፡፡
        በቤተክርስቲያኒቱ ከታዩት ችግሮች አንዱ፤ ትንሣኤ ሙታን የለም የሚሉ ክርስቲያኖች መኖራቸው ነው፡፡ ‹‹ክርስቶስ ከሙታን እንደ ተነሣ የሚሰበክ ከሆነ ግን ከእናንተ አንዳንዶቹ፡- ትንሣኤ ሙታን የለም እንዴት ይላሉ?›› /1 ቆሮ. 15፡12/፡፡ በቆሮንቶስ ቤተክርስቲያን ክርስቶስ እንደተነሣ ይሰበካል፤ ዳሩ ግን ሙታን ትንሣኤ እንዳላቸው የሚክዱ ክርስቲያኖች ነበሩ፡፡ በክርስቶስ ስም ከክርስቶስ ጋር አለመቆ፤ በእምነት ሽፋን ታማኙን ጌታ የመካድ ልምምዶች ከክርስትና ጅማሪ አንሥቶ ዘመን ጠገብ ችግርና ፈተና ነው፡፡
        ሐዋርያው በትንሣኤ ሙታን አለማመን፤ ክርስቶስ አልተነሣም ማለት እንደ ሆነ፤ ክርስቶስ ካልተነሣ ደግሞ ስብከት ከንቱ እንደ ሆነ፤ ስብከቱ ከንቱ ከሆነ ደግሞ እምነታቸውም ከንቱ እንደ ሆነ፤ እምነታቸው ከንቱ ከሆነ ደግሞ ከኃጢአትና ከውጤቱ ከሞት አርነት እንዳልወጡ ያስረዳቸዋል፡፡ የክርስቶስ መነሣት የክርስትናው ዋጋና መሠረት ነውና፡፡ እርሱ ባይነሣ ኖሮ እርስትና በሕይወት ሳይሆን በሞት መሠረት ላይ ይቆም ነበር፡፡ ይህም ደግሞ ክንቱ የከንቱ ከንቱ ነው፡፡
        በዘመናችን በምናየው ክርስትና ውስጥ ትንሣኤ ሙታን የለም ብለው በግልጽ የሚናገሩ ክርስቲያኖችን አንመለከት ይሆናል፡፡ ዳሩ ግን የሉም ማለት አይደለም፡፡ በቆሮንቶስ አንዳንዶች የለም ሲሉ፤ ዛሬ ግን ‹‹የለምን›› በኑሮ የሚኖሩትን ብዙ ልንመለከት እንችላለን፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ለቲቶ ሲጽፍለት ‹‹እግዚአብሔርን እንዲያውቁ በግልጥ ይናገራሉ፥ ዳሩ ግን የሚያስጸይፉና የማይታዘዙ ለበጎ ሥራም ሁሉ የማይበቁ ስለ ሆኑ፥ በሥራቸው ይክዱታል።›› /ቲቶ 1፡16/ ይለዋል፡፡
        ቃላት ከካደው ይልቅ ኑሮ የሚክደው ይከፋል፡፡ የኑሮን ውድቀት የቃላት ውበት አያቆመውም፡፡ የቃላትን አለመዋቀር ግን ኑሮ ያቀናዋል፡፡ በቆሮንቶስ ቤተክርስቲያን የትንሣኤ ሙታንን አለመኖር የማያምኑት ድነዋል ተብለው በቤተክርስቲያን ያሉ ምዕመናን ነበሩ፡፡ በጌታ የተወደዳችሁ ወዳጆቼ ሆይ፤ በዙሪያችሁ ያለውን ልብ በሉ፡፡ በእርግጥ ኑሮአችን ትንሣኤ ሙታን መኖሩን ያብራራልን?
       ለማታቀው ዓለም አታስብ ብላ፤ጠጣ፤ የወደድከውን አድርግ እያለ ትንሣኤ ሙታን መኖሩን በተግባር የሚክደው ማነው? የኀዘን ስርዓታችን፤ የመቃብር ቦታዎቻችን ትንሣኤ እንዳለን ያሳያሉን? የአንዳንዶችን የቀብር ስፍራ ሳስተውል፤ ለረጅም ጊዜ በድን ማቆያ ስለተጠቀሙ ክርስቲያኖች ስሰማ፤ በእርግጥ ክርስትናው በመቃብር የሚቀር፤ ክርስቲያኖችም ከሙታን መካከል የሚፈለጉ ይመስሉኛል፡፡
       ክርስቶስ በታላቅ ኃይልና ሥልጣን እንደተነሣ የሚናገረው ማንነታችን ለምን ኃይል ራቀው? ተነሣ የሚሉ ወድቀው ለምን ቀሩ? ማራናታ እንኳን አፋቸው ላይ ሊመጣ፤ ለጆሯቸውም እርቁ የሆነባቸው ስንቶች ናቸው? መሄድና ከክርስቶስ ጋር መኖርን ኑሮአቸው አብዝቶ የሚናፍቀው ምን ያህል ክርስቲያኖች ናቸው? ምድሪቱን በግድ ለቅቀው የሚሄዱት ክርስቲያኖች ጭምር አይደሉምን?
       ጌታ እግዚአብሔር ቀኝና ግራውን መለየት ላልቻለው ምስኪን ወገን፤ በምላሱ የሚናገረው ኑሮ አልሆንለት ያለውን ሕዝብ፤ ውሻም አሻንጉሊትም ሰውም የታሠረባቸውን የቼቼ ቤቶች ትንሣኤ ያድርግላቸው፡፡ በቆሮንቶስ የነበረው ውድቀት የዘመናችን አብያተ ክርስቲያናትም ውድቀት ነውና የጌታን ስም የምትጠሩ ልባችሁ ከዚህ አመጽ ይራቅ /2 ጢሞ. 2፡19/፡፡ ሐዋርያው ‹‹በዚች ሕይወት ብቻ ክርስቶስን ተስፋ ያደረግን ከሆነ፥ ከሰው ሁሉ ይልቅ ምስኪኖች ነን።›› /1 ቆሮ. 15፡19/ ይላል፡፡
       በክርስቶስ ክርስቲያን የሆነው በመቃብር ለሚቀር ኑሮ አይደለም፡፡ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ እንደተነሣ እኛም ከእርሱ ጋር ተነሥተናል /ኤፌ. 2፡6/፡፡ እርሱን ከሙታን መካከል መፈለግ እንደማይቻል ሁሉ እኛም ከእርሱ የተነሣ ሕያዋን ሆነናልና በዚያ አንፈለግም፡፡ በበደላችንና በኃጢአታችን ሙታን ከሆንበት ታሪክ በሞቱና በትንሣኤው አርነት ያወጣን ክርስቶስ ስሙ ቡሩክ ይሁን /ገላ. 5፡1/፡፡ እግዚአብሔር ከሞት ያስነሣልና ኤል-ያቄም እንላለን /ሮሜ 4፡24/፡፡   
       ትንሣኤ ሙታን መኖሩን የማያምን አድራሻው ከሙታን መካከል ነው /ዮሐ. 3፡36/፡፡ አበባው እንደደረቀ፤ ሻማው እንደቀለጠ፤ ሽቶው እንደተነነ እርሱም እንደዚያው ነው፡፡ ተስፋውን ከፀሐይ በታች መስርቷልና ለእርሱ የተባረከ ተስፋ የለውም፡፡ የሁሉ ዓይን ተስፋ የሚያደርገውን በክርስቶስ ተስፋ አላደረገውምና እርሱ ትንሣኤና ሕይወት /ዮሐ. 11፡25/ ከሆነው ኢየሱስ ጋር እድል ፈንታ የለውም፡፡

       ተወዳጆች ሆይ፤ በዚያ አይፈልጓችሁ፡፡ አመጽና ክፋት፤ ስስትና ንጥቂያ፤ ነውርና ሞት ባለበት በዚያ ኑሮ ውስጥ አትፈለጉ፡፡ አባትህን ሂድና ጠጅ ቤት ፈልገው /ለድሀው/፤ አባትህን ሂድና ውስኪና ቁማር ቤት ፈልገው /ለሀብታም/፤ እናትህን ሂድና ከጫቱ መደብ ላይ ቀስቅሳት፤ ወንድምህን ሂድና ነጋባችሁ በለው በሚባልበት ማኅበረሰው ትንሣኤ በድምቀት መባሉ ‹‹በድርቀት›› አልሆነባችሁምን? እናንተን ግን በዚያ አይፈልጓችሁ!!
                             ‹‹ . . . ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤›› /ቆላ. 4፡3/!

No comments:

Post a Comment