Saturday, April 11, 2015

ሞቶ መዋል


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ቅዳሜ ሚያዝያ 3 ቀን 2007 የምሕረት ዓመት
‹‹ . . እትቤዝወከ በመስቀልየ ወበሞትየ››
‹‹ . . በመስቀሌና በሞቴ አድንሃለሁ።››
(ኪዳነ አዳም ፫፡፫-፮፤ ዘፍ.፫።፲፭)
     ‹‹ቀደምት የኢትዮጵያ ነገሥታት ስመ መንግሥታቸው ከመስቀል ጋር የተጣመረ ነበር፣ የቅዱስ ንጉሥ ላሊበላ (፩ሺህ፩፻፶፮ - ፩ሺህ፩፻፺፯ ዓ.ም) ስመ መንግሥቱ ገብረ መስቀል ሲሆን የእቴጌይቱ ስመ መንግሥት መስቀል ክብራ ነበር፤ የዐፄ ይስሐቅም (፩ሺህ ፬፻፲፬ - ሺህ፩፬፻፳፱ ዓ.ም) ስመ መንግሥታቸው ገብረ መስቀል ነበር። የደብዳቤያቸውም ርእስ ትእምርተ መስቀልና ኢየሱስ የሚል ነበር።
ኢ            የ
   +      
ሱ            ስ  ››             /መጋቤ ብሉይ ሠይፈ ሥላሴ ዮሐንስ/

          በኢትዮጵያ ታሪክ የክርስትና እምነት ከቤተ መንግሥት ወደ ሕዝቡ እየወረደ እንደተስፋፋ ይነገራል፡፡ ለዚህም ከመጽሐፍ ቅዱስ እንደ ዋና ማሳያ የሚጠቀሰው ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ነው /ሐዋ. 8፡26-39/፡፡ በአገራችን ወንጌል እንዲሰበክ፤ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲገለጥ፤ ክርስቶስ ትውልዱን እንዲገዛው ሕዝባችን ሰፊ እድል እንደነበረውና እንዳለው አመላካች ታሪኮችን ከመዛግብት ልንረዳ እንችላለን፡፡ ዳሩ ግን ለእውነት የማይታዘዝ ኑሮ፤ የእግዚአብሔርን አሳብ የሚቃወም አመጽ፤ ከቃሉ በተቃራኒ የሆኑ ሥርዓቶች ሕዝቡን ያሰከሩ ጉሽ ወይን ጠጆች ሆነው በየዘመናቱ ዘልቀዋል፡፡

          መስቀል የስም መጠሪያ፤ ኢየሱስ የነገር ሁሉ ማረጋገጫ ማኅተም ሆኖ በታየባት አገር ላይ ሰዎች እውነትን በአደባባይ ጥለው፤ መልክ ለሆነው ግን ኃይል ለሌለው ነገር ልባቸው ቀልጦ፤ ኑሮአቸው ክርስቶስን ሲክድ እዚህ እንደደረስንም ታሪክ አይሸሽገንም፡፡ ነገሥታቱ ከክርስትናው አሳብ ጋር አሳባቸውን፤ ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር ፈቃዳቸውን አስከብረው የኖሩበት ሥርዓት ተጽእኖ ዘመነኛው ትውልድ ላይ አብለጭልጮ ይስተዋላል፡፡
           የአመጽና የነውር ኑሮ፤ እንዲሁም አሰቃቂ ታሪኮች መንፈሳዊ መልክና ስሙን ብቻ በያዙ ጌቶችና ሎሌዎች ተፈጽመዋል፡፡ እግዚአብሔር እየተጠራ፤ ቃሉ እየተጠቀሰ ከእውነት ያልሆኑ ልምምዶች ተስተውለዋል፡፡ እግዚአብሔርን ጭምር ለውጊያ የሚፈልግ ሽለላና ፉከራ ከጓዳ እስከ አደባባይ ታይቷል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ነው የሚሉ እነሱ ለሕዝቡ የጣዖት ያህል ሆነው ኖረዋል፡፡ እግዚአብሔር እየተጠራ በተግባር ተክዶ መኖር የሚቻልበትን የኑሮ ውርስ ሰዎች በሰው ልብ ተክለዋል፡፡   
           የቃል ውርስና የኑሮ ቅብብሎሽ ቀጣዩን የማቅናትም ሆነ የማበላሸት ብርታት አላቸው፡፡ ታሪክ የማያነቡ፤ የቀደመውን ልማድ ያልመረመሩ ሰዎች ቢሆኑም እንዳለፈው የመኖር እድላቸው ሰፊ ነው፡፡ ልክ ያልሆነውን ደፍሮ የሚገስጽ፤ የተበላሸውን ዋጋ ከፍሎ የሚያቀና፤ ለትውልዱ ሸክም ያለበት ሰው ከሌለ፤ በእውነት ስም ያለ እውነት መሟሟቁ ቀጣይ ይሆናል፡፡ በአል እያደረጉ መርከሱም ይኖራል፡፡ ኑሮን የማያንጹና ሕሊናን የማያነጹ ልምዶች እንደገዙም ለቀጣይ ይሻገራሉ፡፡
           የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት መነሣት የክርስትናችን ብርቱ መሠረት ነው፡፡ ‹‹ክርስቶስም ካልተነሣ እንግዲያስ ስብከታችን ከንቱ ነው እምነታችሁም ደግሞ ከንቱ ናት›› /1 ቆሮ. 15፡14/ ተብሎ እንደተፃፈ፤ በእርሱ መነሣት ጽድቃችን ተረጋግጧል /ሮሜ 4፡24/፡፡ እምነትና አገልግሎት ትርጉማቸው በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ሞት የያዘውን ልናምነው፤ ያልተነሣውንም ልንሰብከው እንዴት ይቻለናል?
           ሞት ብዙ ታላላቅ ሰዎችን ውጦ አስቀርቷል፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ ግን ይህንን ብርታት ሽሮታል፡፡ ‹‹እርሱ ሞትን ሽሮአልና እኔ ሰባኪና ሐዋርያ አሕዛብንም አስተማሪ እንድሆን በተሾምሁበት በወንጌል ሕይወትንና አለመጥፋትን ወደ ብርሃን አውጥቶአል።›› /2 ጢሞ. 1፡11/፤ ደግሞ ‹‹እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ፥ እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፥ ይኸውም ዲያብሎስ ነው፥ በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ፥ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ።›› /ዕብ. 2፡14/፡፡
            ጴጥሮስ በበዓለ ሃምሳ፤ መንፈስ ቅዱስ በወረደበት ዕለት በሰበከው ስብከት፤ ‹‹ወንድሞች ሆይ፥ ስለ አባቶች አለቃ ስለ ዳዊት እንደ ሞተም እንደ ተቀበረም ለእናንተ በግልጥ እናገር ዘንድ ፍቀዱልኝ፤ መቃብሩም እስከ ዛሬ በእኛ ዘንድ ነው።›› /ሐዋ. 2፡29/ ብሏል፡፡ ነቢዩ ዳዊት በእስራኤል ታሪክ እጅግ የሚወደድ የእግዚአብሔር ሰው ነው፡፡ አንድ አይሁዳዊ ስለ እርሱ በደስታ ይናገራል፡፡ ዳሩ ግን ይህ ታላቅ ሰው ዛሬ ድረስ መቃብሩ አለ፡፡ ከሞትም ሊነሣ አልተቻለውም፡፡
            በአገራችንም ብዙ እንደሠሩ የምናወራላቸው፤ በጀግንነት የምንጠቅሳቸው፤ በሥጋ ለባሽ ፊት ብዙ ሞገስ የነበራቸው ወደ መቃብር ወርደዋል፡፡ ስማቸውም ደብዝዞአል፡፡ ታሪካቸውም በሚበልጥ ተዘንግቷል፡፡ በአመጽ ያስከበሩት በሌላ አመጽ ፈርሶባቸዋል፡፡ የናዝሬቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ትናንትና ዛሬ እስከ ለዘላለምም ያው ነው።›› /ዕብ. 13፡8/፡፡ 
            ነቢዩ ዳዊት ‹‹ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ አስቀድሞ አይቶ፥ ነፍሱ በሲኦል እንዳልቀረች ሥጋውም መበስበስን እንዳላየ ተናገረ።››፡፡ ጴጥሮስም ሲናገር ‹‹ይህን ኢየሱስን እግዚአብሔር አስነሣው ለዚህም ነገር እኛ ሁላችን ምስክሮች ነን›› ይለናል፡፡ ሕያው ለሆነው፤ ከሙታንም መካከል ስለማይፈለገው ጌታ እኛ በምድር ላይ ሕያዋን ምስክሮች ነን፡፡ ይህም በየዘመናቱ በቃልና በኑሮ የምንገልጠው እውነት ነው፡፡
            የክርስቲያኖች ሕይወት በትንሣኤው ኃይል የሚገለጥ ነው፡፡ እንደ ቅድስና መንፈስ ከሙታን መነሣት የተነሣው ኢየሱስ /ሮሜ 1፡3/፤ ሰዎች ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ይቀድሱ ዘንድ፤ ከሚታየው ባለፈ ያለውን እንዲያስተውሉ ጉልበት ነው፡፡ ሐዋርያቱ የኢየሱስ መነሣት በሕይወታቸው ላይ ያመጣውን ከፍተኛ ለውጥ እንመለከትባቸዋለን፡፡ በሞቱ የዛሉት እነርሱ በትንሣኤው ግን የእምነት ድፍረትን አግኝተዋል፡፡ በእርግጥም እርሱ ክርስቶስ የዓለም መድኃኒት ነው፡፡
            በመቃብር ያለ ቤዛ የለንም፡፡ ከሞት የተነሣ ብቸኛው ቤዛችን ክርስቶስ ነው /ኤፌ. 1፡7/፡፡ ለሰው ሁሉ መድኃኒት፤ ወጥመድን የሚሰብር አሻጋሪ፤ ወደ ሰማይ የሚያደርስ መሪ እርሱ ነው፡፡ ሕይወትንና አለመጥፋትን ያገኘንበት የዘላለም ዋስትናም ነው፡፡ ከሞት በተነሣው በእርሱ ክርስትናን እንደ ጀመርን፤ ከሞት ተነሥተን ደግሞ ገና ከእርሱ ጋር ዘላለምን እንኖራለን፡፡
            ተወዳጆች ወዳጆቼ ሆይ፤ ክርስቶስ ከሞት የተነሣው ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር ነው፡፡ ‹‹ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር፥ እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ›› /2 ጴጥ. 2፡24/ ተብሎ እንደተፃፈ፤ በጽድቅ መኖር ያስፈልጋል፡፡ ትንሣኤውንም ተግባራዊ በሆነ ኑሮ ማብራራት ካመኑቱ ይጠበቃል፡፡
            በትንሣኤ ሽፋን ሰዎች በብዙ አመጽ ውስጥ ያልፋሉ፡፡ ዋጋ ከፍለው ነውርን የሚያደርጉ፤ ስለ እነርሱ መስቀል ላይ የተከፈለውን ዋጋ አምኖ ለመቀበል ይፈተናሉ፡፡ ኢየሱስ ተነሥቷል እያሉ፤ ሞተው ውለው ሞተው ያድራሉ፡፡ በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት እንዳወጣን እየተነገረ፤ ፈቅደው በባርነት ይያዛሉ፡፡ ክርስቶስ ከሞት እንደተነሣ እየተናገሩ ሞቶ መዋል ምን ይሉታል?


ምን ያለ አክባሪ
ትንሣኤን ዘካሪ
ጌታ ተነሣልኝ ስለኔ እያለ
እርሱ በኃጢአት ደክሞ
ምነው ሞቶ ዋለ? 

            የእግዚአብሔር ልጅ ከሙታን መካከል ተለይቶ መነሣቱን ኑሮ በተግባር ሊናገር ይገባል /ሉቃ. 24፡5/፡፡ ስለ እርሱ ‹‹ሕያውን ከሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጋላችሁ?›› እንደተባለ፤ ክርስቲያን በክርስቶስ ሕያው ነውና ከሙታን መካከል አይገኝም /1ዮሐ. 5፡12/፡፡ ሞትና መቃብር ስላልያዘው ጌታ መመስከር ከባርነት ቀንበር ተላቆ ነው፡፡ ኢየሱስ ተነሥቷልና ሞታችሁ አትኑሩ፡፡

‹‹ስምከ ሕያው ዘኢይመውት››
ስምህ የማይሞት ሕያው ነው!
                                      ‹‹ . . . ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤›› /ቆላ. 4፡3/!

No comments:

Post a Comment