በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
ቅዳሜ መስከረም 8 ቀን 2008 የምሕረት ዓመት
‹‹ነገር ግን ለእርሱ ስለ ሆኑት ይልቁንም ስለ ቤተ ሰዎቹ የማያስብ ማንም
ቢሆን፥ ሃይማኖትን የካደ ከማያምንም ሰው ይልቅ የሚከፋ ነው።›› /1 ጢሞ. 5፡8/፡፡
ቤተ፡ ሰብ፤ የብዙ ነገሮች መሠረት እንደ ሆነ በብዙዎች ዘንድ ይነገራል፡፡
መጽሐፍ ቅዱስም እንዲሁ ለቤተ፡ ሰዎች ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣል፡፡ በብሉይ ኪዳን ቤተ፡ ሰብ የሚለው፤ በአዲስ ኪዳን ቤተ ሰዎች በማለት
ተጽፎ እናነባለን፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ትኩረት ከሰጣቸው ነገሮች አንዱ በቤተ፡ ሰዎች መካከል ያለው ግንኙነት ተጠቃሽ ነው፡፡
የመጽሐፍ
ቅዱሳችን የመጀመሪያ ክፍል የዘፍጥረት መጽሐፍ ስለ ስድስት ቤተ፡ ሰዎች ማለትም አዳም፤ ኖኅ፤ አብርሃም፤ ይስሐቅ፤ ያዕቆብና ዮሴፍን
ቤተሰባዊ ኑሮ የሚተርክና ለኪዳኑ ታማኝ የሆነውን እግዚአብሔር የሚያሳየን ድንቅ መጽሐፍ ነው፡፡ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ እንደ አቤል
ያለውን የእምነት ሰው፤ ደግሞም እንደ ቃየል ያለውን የሞት ልጅ የምናገኝበት ብዙ ትኩረትና ማስተዋላችንን የሚጠይቅም ክፍልም እንደሆነ
ልብ እንላለን፡፡