Sunday, September 13, 2015

ዘመን እንደ ዮሐንስ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

ቅዳሜ መስከረም 1 ቀን 2008 የምሕረት ዓመት  

           በቤተ፡ ክርስቲያን 2008 የምሕረት ዓመት ‹‹ዘመነ ዮሐንስ›› ይባላል፡፡ በአዲስ ኪዳን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ወንጌላቱ በተቀመጡበት ቅደም ተከተል በአራት ዓመት አንድ ጊዜ አንዱ ወንጌላዊ ዘመኑ ይሰየምበታል፡፡ ብዙ ሰዎች ልብ ባይሉትም ዘመን በተፈራረቀ ቁጥር አንዱ ወንጌላዊ ለሌላው እየተቀባበለ ዓመቱ በወንጌል ጸሐፊዎቹ ስም ይጠራል፡፡

          የሐዲስ ኪዳን ክፍል ሲጀምር ‹‹የጌታችንና፡ የመድኃኒታችን፡ የኢየሱስ፡ ክርስቶስ፡ አዲስ፡ ኪዳን፡፡›› በማለት ሲሆን፤ የወንጌላቱም ክፍል ‹‹የጌታችን፡ የኢየሱስ፡ ክርስቶስ፡ ወንጌል፡ ቅዱስ፡ ___________ እንደ፡ ጻፈው፡፡›› በማለት ነው፡፡ ሐዋርያው ‹‹ይህም ወንጌል በሥጋ ከዳዊት ዘር ስለ ተወለደ እንደ ቅድስና መንፈስ ግን ከሙታን መነሣት የተነሣ በኃይል የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ ስለ ተገለጠ ስለ ልጁ ነው፤ እርሱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው›› /ሮሜ 1፡3/ እንዳለ፤ በቅዱሱ መጽሐፍ ውስጥ እውነተኛው የምስራች ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፡፡
          መልአኩ ‹‹እነሆ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምስራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና፡፡›› /ሉቃ. 2፡10/ እንዳለ፤ አዲስ ኪዳን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ምስራች ነው፡፡ ወንጌላውያኑ የጌታችንን ወንጌል እንደ ጻፉ መጽሐፍ እርግጥ ያደርግልናልና፡፡ ስለዚህ ዓመቱ በአንድ ወንጌላዊ ስም ሲሰየም የጌታችን የኢየሱስ ዘመን መሆኑን ያስረግጥልናል፡፡ አዲስ ኪዳን የጌታችን የኢየሱስ ነው!
          ዮሐንስ ማለት ‹‹እግዚአብሔር ጸጋ ነው›› የሚል ትርጉም ይሰጠናል /የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፤ 9ኛ እትም 2002 ዓ.ም፤ ገጽ 222፤ የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር እንዳሳተመው/፡፡ ዓመተ ምሕረት ብለን ዘመን ስንቆጥር ‹‹የጸጋ ዘመን›› መሆኑን እናስተውላለን፡፡ በምሕረቱ ባለ ጠጋ /ኤፌ. 2፡4/ የሆነው እግዚአብሔር፤ ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ የምንድንበትን ለእኛ እንዳደረገ መጽሐፍ ይነግረናል፡፡ ‹‹ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ ተገልጦአልና . . ›› /ቲቶ 2፡11/ እንደተባለ፤ በመለኮት ዘንድ ሥጋን የለበሰ ሁሉ ተቀባይነት እንዲያገኝ እግዚአብሔር ልጁን ለሞት አሳልፎ ሰጥቶአል /ዮሐ. 3፡16፤ ሮሜ 8፡31/፡፡
          ‹‹ቃልም ሥጋ ሆነ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ . . . ሕግ በሙሴ ተሰጥቶ ነበርና ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ›› /ዮሐ. 1፡14፤16/ ተብሎ እንደ ተጻፈ፤ የእግዚአብሔር ልጅ የሰው ልጅ በመሆን በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ /ዕብ. 2፡14/፤ ከኃጢአትም በቀር በነገር ሁሉ እኛን መሰለ፡፡ ተወዳጆች ሆይ፤ ዘመነ ዮሐንስ፡-
1/ ‹‹እግዚአብሔር ጸጋ ነው›› ይላል፡
         እግዚአብሔር ሰው ሁሉ ኃጢአተኛ ለመሆኑ የሰው ምስክር አያስፈልገውም፡፡ ‹‹ . . መጽሐፍ ከኃጢአት በታች ሁሉን ዘግቶታል፡፡›› /ገላ. 3፡22/ እንደተባለ፤ ሰው ኃጢአት የለብኝም ቢል ራሱን ያስታል /1 ዮሐ. 1፡8/ እንጂ ‹‹ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋል›› /ሮሜ 3፡23/፤ የኃጢአት ደመወዝ ደግሞ ሞት ነው /ሮሜ 6፡23/፡፡
         ዘመነ ዮሐንስ ‹‹እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ›› /ዮሐ. 1፡29/ በማለት የሰውን ሳይሆን የእግዚአብሔርን በግ ያሳየናል፡፡ ሰው ለራሱ ቤዛ ሊያዘጋጅ ስለማይችል፤ እግዚአብሔር ለሰው ምትክ የሚሆን ቤዛ አዘጋጅቶአል፡፡ ‹‹አንዱ ስለ ሁሉ ሞተ›› /2 ቆሮ. 5፡14/ እንደተባለ የሁላችን ቤዛ ክርስቶስ ነው፡፡ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ጻፈው ‹‹እንዲሁም የሰው ልጅ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም›› /ማቴ. 20፡28/ በማለት ያስረዳናል፡፡
       ከእግዚአብሔር ደኅንነትን ሊቀበሉ የሚያስፈልጋቸው ሁሉ ሁለት መሠረታዊ ጥያቄዎችን ለእግዚአብሔር ያቀርባሉ፡፡
      ሀ/ እግዚአብሔርን እኔን እንዴት ታየኛለህ? ብለን መጠየቅ አለብን፡፡
·        እርሱም ‹‹መሞት የሚገባህ ኃጢአተኛ ነህ››፤ ማለት የሞት ልጅ ነህ ይለናል፡፡
      ለ/ እግዚአብሔርን ‹‹ምን አደርግ ዘንድ ትወዳለህ?›› ብለን መጠየቅም ይኖርብናል፡፡
·        እርሱም ‹‹ምንም ልታደርግ አትችልም የማደርግልህ እኔ ብቻ ነኝ›› ይለናል፡፡
      እግዚአብሔር ኃጢአተኛ ለሆነው የሰው ማንነት መሥዋዕት በማዘጋጀት፤ የእኛን ኃጢአት ባዘጋጀው መሥዋዕት ላይ በማድረግ ከሞት አድኖናል /ቆላ. 1፡13/፡፡ ሰው እግዚአብሔር ለእርሱ ባደረገለት (በሠራለት) በማመን የእግዚአብሔር ይሆናል፡፡
      ወንጌላዊው እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከ መስጠት ዓለሙን እንደወደደ ይነግረናል /ዮሐ. 3፡16/፤ ዓለም የምንለው ሁለት ዓይነት ገጽታ አለው፡፡ አንዱ ዲያቢሎስና መልእክተኞቹ የሚገዙበት በሐሰተኛው አባት የተደራጀው ሲሆን ሌላው ግን የሰውን ዘር የሚያመለክት ነው፡፡ እግዚአብሔር ኃጢአተኛ የሆነውን ሰው ለማዳን ‹‹መፍትሔውን ሰጪ›› ነው፡፡ እርሱ እኛን መውደድ ብቻ ሳይሆን ልጁንም መስጠት ነበረበት፡፡ ያለ ክርስቶስ ደም ዓለም አይድንምና፡፡     
2/ ‹‹ኢየሱስ እንደ ሆነ ባታምኑ በኃጢአታችሁ ትሞታላችሁ›› ይላል፡
        መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ የተገለጠው ኃጢአተኞች እንዲድኑበት ነው፡፡ ‹‹ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው›› /1 ጢሞ. 1፡15/፤ ዓለም ሁሉ እንዲቀበለው ግድ የሆነ መፍትሔ በሰው መካከል ተገልጧል፡፡
          ሐዋርያው ‹‹ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና›› /ኤፌ. 2፡8/ እንዳለ፤ የተገለጠው የእግዚአብሔር ጸጋ በሰው ዘንድ የሚሆነው ሰው እንደ እግዚአብሔር ቃል ሲያምን (የተደረገለትን ሲቀበል) ነው፡፡ ‹‹ታምኑ ዘንድ›› /ዮሐ. 20፡31/ ተብሎ እንደተጻፈ፤ ክርስቶስ ኢየሱስን ማመን የተገለጠውን የእግዚአብሔር ጸጋ ማመን ነው፡፡ ይህም ሰውን ያድነዋል፡፡
        መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሕግ ሥራ የሚመኩትን አይሁድ ‹‹እንግዲህ፡- በኃጢአታችሁ ትሞታላችሁ አልኋችሁ እኔ እንደ ሆንሁ ባታምኑ በኃጢአታችሁ ትሞታላችሁና አላቸው›› /ዮሐ. 8፡24/፤ እንዳላቸው ተጽፎ እናነባለን፡፡ ወንጌላዊው ዮሐንስ ‹‹እኔ›› የሚለውን ኢየሱስ በወንጌሉ ክፍል ሰባት ጊዜ በቀጥታ አብራርቶልን እናገኛለን፡፡
          የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ቅዱስ ዮሐንስ እንደ ጻፈው፡ (6፡35) የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ (8፡12) እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ (10፡7) እኔ የበጎች በር ነኝ፤ (10፡11) መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ (11፡25) ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ (14፡6) እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም፡፡
          በብሉይ ኪዳን ‹‹ያለና የሚኖር እኔ ነኝ›› /ዘፀ. 3፡14/ በማለት በምድያም ምድረ በዳ ሙሴን ወደ ግብጽ መልሶ የላከው መለኮታዊ ማንነት በእግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ እንመለከተዋለን፡፡ የእግዚአብሔርን መልክና ምሳሌ በሥጋው ምድር ላይ የገለጠ ኃጢአት የሌለበት፤ ስለ ኃጢአታችን ግን የሞተ ክርስቶስ ነው፡፡ ‹‹አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ›› /ማቴ. 16፡16/ ተብሎ በሰማያት ያለው አባቱ በጴጥሮስ እንደ ገለጠው ዛሬም ሥጋና ደም የማይገልጠው የእግዚአብሔር መገለጥ ሕይወት እንዲሆንልን እመኑ ይለናል፡፡
         ‹‹እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው›› /ሮሜ 10፡17/ ተብሎ እንደተጻፈ፤ በቅዱሱ ቃል ውስጥ ኃጢአተኛ ለሆነው የሰው ዘር ሁሉ መፍትሔ የሆነውን ኢየሱስ እንደ ቃሉ በማስተዋል ወደ ትክክለኛ እምነት መድረስ ይቻላል፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል የማይሰማ ሰው እውነትን መሰረት ያደረገ እምነት ሊኖረው አይችልም፡፡ የዚህም ውጤቱ ‹‹በኃጢአታችሁ ትሞታላችሁ›› የሚል ነው፡፡ ኢየሱስ ‹‹እኔ መጥቼ ባልነገርኋቸውስ ኃጢአት ባልሆነባቸውም ነበር›› /ዮሐ. 15፡22/ እንደተባለ መድኃኒት ተገኝቶአል፤ ባታምኑት በኃጢአታችሁ ትሞታላችሁ፡፡
3/ ‹‹በእግዚአብሔር ልጅ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው›› ይላል፡
       አለማመን ዋጋ እንደሚያስከፍል ሁሉ እምነትም ዋጋ አለው፡፡ ወንጌላዊው ዮሐንስ ወንጌሉ ለምን እንደተጻፈ ባስረዳበት ክፍል ‹‹ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ታምኑ ዘንድ አምናችሁም በስሙ ሕይወት ይሆንላችሁ ዘንድ ይህ ተጽፎአል›› /ዮሐ. 20፡31/ ይለናል፡፡ ሕይወት የመጽሐፍ ቅዱስ ትልቅ ርእስ ነው፡፡ ‹‹በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ›› /ኤፌ. 2፡1/ እንደተባለ፤ ሙታን ለሆነው ሰው ሕይወት ታላቅ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው /ኤፌ. 2፡5/፡፡
       የዘላለም ሕይወት የእግዚአብሔር ስጦታ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ አስረግጦ ይነግረናል፡፡ ‹‹የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው›› /ሮሜ 6፡23/ ተብለናል፡፡ ወንጌላዊውም ‹‹በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቁጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም›› /ዮሐ. 3፡36/ እንዳለ፤ የዘላለም ሕይወትን ማየት የሚችለው በክርስቶስ እንደ ቃሉ ያመነ ብቻ ነው፡፡
        በእምነት የሚገኘው የእግዚአብሔር ሕይወት ባለቤት መሆን የምንችለው ለኃጢአታችን ሕይወቱን በከፈለው በኢየሱስ ነው፡፡ ቃሌ ከሚያልፍ ያለው ጌታ ‹‹ . . . እኔም የዘላለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ ለዘላለምም አይጠፉም›› /ዮሐ. 10፡28/ እንዳለን፤ ሕይወትና አለመጥፋት /2 ጢሞ. 1፡11/ በወንጌል በማመን አግኝተናል፡፡ ዋስትናችንንም ‹‹ከእጄ ማንም አይነጥቃቸውም . . ከአባቴም እጅ ሊነጥቃቸው ማንም አይችልም፡፡ እኔና አብ አንድ ነን›› በማለት አረጋግጦልናል፡፡
       ተወዳጆች ሆይ፤ 2008 ዓመተ ምሕረት ዘመነ ዮሐንስ እንደ ሆነ ከተቀበላችሁ፤ ወንጌላዊው ለሰዎች ሁሉ መዳን የመጣውን ‹‹የዓለም ቤዛ›› በማመን የሚገኘውን የዘላለም ሕይወት እንደምናገኝ ይናገራል፤ ወንጌሉን እንደሚገባ አጥኑት፡፡ የእግዚአብሔር መንግሥት ልጆች ለሆናችሁ /1 ዮሐ. 5፡13/ መጽናት ይብዛላችሁ፤ በቃሉ እንዲህ እንደተጻፈው ላላመናችሁ ግን ‹‹ . . የሚያምንም የዘላለም ሕይወት አለው፤ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሸገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣምሐሕሐሕሐሕሐሀከጀበሀጀከከሀጀ›› /ዮሐ. 5፡24/፤ ‹‹ . . በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል›› /ዮሐ. 3፡18/፡፡
                                       ‹‹ . . . ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤›› /ቆላ. 4፡3/!
           

No comments:

Post a Comment