Saturday, September 19, 2015

ከማያምንም የከፋ፡

                 በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

ቅዳሜ መስከረም 8 ቀን 2008 የምሕረት ዓመት 

         ‹‹ነገር ግን ለእርሱ ስለ ሆኑት ይልቁንም ስለ ቤተ ሰዎቹ የማያስብ ማንም ቢሆን፥ ሃይማኖትን የካደ ከማያምንም ሰው ይልቅ የሚከፋ ነው።›› /1 ጢሞ. 5፡8/፡፡

        ቤተ፡ ሰብ፤ የብዙ ነገሮች መሠረት እንደ ሆነ በብዙዎች ዘንድ ይነገራል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም እንዲሁ ለቤተ፡ ሰዎች ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣል፡፡ በብሉይ ኪዳን ቤተ፡ ሰብ የሚለው፤ በአዲስ ኪዳን ቤተ ሰዎች በማለት ተጽፎ እናነባለን፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ትኩረት ከሰጣቸው ነገሮች አንዱ በቤተ፡ ሰዎች መካከል ያለው ግንኙነት ተጠቃሽ ነው፡፡

        የመጽሐፍ ቅዱሳችን የመጀመሪያ ክፍል የዘፍጥረት መጽሐፍ ስለ ስድስት ቤተ፡ ሰዎች ማለትም አዳም፤ ኖኅ፤ አብርሃም፤ ይስሐቅ፤ ያዕቆብና ዮሴፍን ቤተሰባዊ ኑሮ የሚተርክና ለኪዳኑ ታማኝ የሆነውን እግዚአብሔር የሚያሳየን ድንቅ መጽሐፍ ነው፡፡ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ እንደ አቤል ያለውን የእምነት ሰው፤ ደግሞም እንደ ቃየል ያለውን የሞት ልጅ የምናገኝበት ብዙ ትኩረትና ማስተዋላችንን የሚጠይቅም ክፍልም እንደሆነ ልብ እንላለን፡፡

         በአዲስ ኪዳንም ቤተሰባዊነት በብዙ መንገድ ተገልጧል፡፡ ከመንፈሳዊ አስተዳደር ጋር በተያያዘ ‹‹ሰው ግን የራሱን ቤት እንዲያስተዳድር ባያውቅ፥ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን እንዴት ይጠብቃታል?›› /1 ጢሞ. 3፡5/ ተብሎ ስናነብ፤ ቤተሰብን አስመልክቶ ደግሞ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የእምነት ልጁ ለሆነው ጢሞቴዎስ ‹‹ስለ ቤተ፡ ሰዎቹ የማያስብ ከማያምን ሰው ይልቅ የከፋ ነው›› ይለዋል፡፡

         ሐዋርያው እንደነገረን የጢሞቴዎስ አያት ሎይድና እናቱ ኤውንቄ ግብዝነት የሌለበት እምነት ነበራቸው /2 ጢሞ. 1፡5/፤ አባቱ ግን የግሪክ ሰው ነበረ /ሐዋ. 16፡1/፡፡ ስለ ጢሞቴዎስም ሲመሰክር ‹‹በአንተ ያለውን ግብዝነት የሌለበትን እምነትህን አስባለሁ›› ይላል፡፡ ከሚያምኑ ክርስቲያን ቤተ፡ ሰዎች መወለድ ወደ እውነተኛው መንገድ ለመድረስ ምን ያህል አስተዋጽዖ እንዳለው ማንም ልብ ይለዋል፡፡ እንደ አገልጋይ ባላመኑ ሰዎች መካከል ያሉትን ወደ እምነት ለማምጣት ምን ያህል ጭንቅ እንደ ሆነ ይገባናል፡፡    

         ለቁሳቁስ ውርስ ብቻ የሚጨነቁ ወላጆችን በጢሞቴዎስ ቤተ፡ ሰዎች ፊት ስናቆማቸው ምስኪኖች እንደ ሆኑ እናያለን፡፡ ቤተሰብ በአንድ ሰው እድገት ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳል፡፡ በትምህርትና በቅጣት አልስተካከል የሚሉ አመሎች ከልጅነት ጀምሮ ስንከሳ አብረው የከሱ፤ ስንወፍርም አብረው የወፈሩ፤ ስንረዝም እንደዚያው የተላመዱን ናቸው፡፡
         ሰው ካደገ በኋላ ወደ ፊት ላመጣቸው፤ ወደ ኋላ ደግሞ ለመጣባቸው ቤተ ሰዎቹ ኃላፊነት የሚሰማው ይሆናል፡፡ ወላጆቹ ያለፈበትን፤ ውላጆቹ ደግሞ የሚሄድበትን ያሳስቡታል፡፡ እኔ በዚህ ክፍል ለማሳየት የምሞክረው ሁላችንም አልፈን ስለመጣንበት ቤተሰብ ነው፡፡ የነገሥታትን ታሪክ በመጽሐፈ ነገሥት ውስጥ ስንመለከት፤ ወላጆቻቸው ቅን ሆነው ልጆቻቸው ክፉ ስለነበሩ፤ ልጆቻቸው መልካም የሆኑ ነገር ግን አመፀኛ ስለነበሩ ወላጆች እናነባለን፡፡
         በእግዚአብሔር አሠራር ውስጥ ሰው ከየትኛውም ቤተሰብ ቢገኝ እግዚአብሔር እርሱን ይጠቀምበት ዘንድ፤ እንደ ቅድመ ሁኔታ አይወሰድም፡፡ የእርሱ ጸጋ በሰው አተያይ የተጨከነባቸውን ወደ ክብር ሲያመጣ፤ ደግሞ ከፍ ከፍ ያሉትን ሲያዋድር እናውቃለን፡፡ ፈቃዱንም የእሽታ ልብ ባላቸው ውስጥ ሲፈጽም እንመለከታለን፡፡ በመጽሐፈ ነገሥት ውስጥ የምንረዳው እንዲህ ያለውን እውነታ ነው፡፡ ወላጆቻቸው በእግዚአብሔር ፊት በአመጽ ሄደው እነርሱ ግን ቅን የሆነውን ያደረጉ፤ እውነተኛውን ለመናገርና ለማድረግ የጨከኑ ልጆችንን እናገኛለን፡፡
        ይልቁንም እግዚአብሔርን ወደ ማወቅ ያልደረሱ ወላጆቻቸውን በማስተማርና መንፈሳዊውን ልምምድ በማሳየት የተባረኩ የእግዚአብሔር ጸጋ የረዳቸው ናቸው፡፡ ወላጅነት ሁሉን አዋቂነት ሆኖ በሚቆጠርበት፤ ከልጆች የተሻለ ነገር እንደማይገኝ በተደመደመበት፤ ማድመጥ ሳይሆን መደመጥ ብቻ ክብር ሆኖ በሚታይበት ማኅበረሰባችን ዘንድ በእድሜ በቀደሙን ዘንድ ሞገስን ማግኘት ፈታኝ ነው፡፡
         ብዙ ክርስቲያን ልጆች በቤተ፡ ሰዎቻቸው ሲፈተኑ አስተውያለሁ፡፡ አንዳንዶችም ተስፋ ቆርጠው በጎውን ከመናገር፤ እውነትን ከመግለጥ ሲለግሙና ቸል ሲሉ ታዝቤአለሁ፡፡ የበረታ ልጅ የሰነፈ አባቱን ቢያነቃ፤ ልጅ እናቷን ወደ ንስሐ ብትመራ፤ ልክ ባልሆነ መንገዳቸው ላይ የአብራካቸው ክፋዮች ቢገሩአቸው ችግሩ ምን ላይ ነው? በወላጆቻቸው መካከል እንደ ሽማግሌ ተቀምጠው የቤታቸውን ገመና የሸፈኑ፤ ቤተሰብ ከመበተን የታደጉ፤ ትዳርን መሳለቂያ ከመሆን ያተረፉ በጎ ሕሊና ያላቸው ብዙ ልጆች እንዳሉ እናውቃለን፡፡
          ተወዳጆች ሆይ፤ ቤተ ሰዎቻችሁን ስለ መጦር፤ ቁሳዊ በሆነ ነገር ስለመርዳት ከምትጨነቁላቸው በላይ አብልጣችሁ ልታስቡላቸው የሚገባበት ነገር እንዳለ ላስታውሳችሁ እወዳለሁ፡፡ የእግዚአብሔርን አሳብና ምክር እንዲረዱ፤ ሕሊናቸው በሚወቀስበት ኃጢአት ላይ በንስሐ እንዲንበረከኩ፤ በክርስቶስ የተደረገውን መዳን እንዲያገኙ፤ ከእምነት የሚነሣ መታዘዝን እያሳዩ እንዲኖሩ በጸሎትና በተግባር ልትተጉ ያስፈልጋችኋል፡፡
          መልካምነት ከቤት እንዲጀምር አውቃችሁ፤ ለቤተ ሰዎቻችሁ መልካሙን አድርጉ፡፡ ባሎቻቸውን ቸል ያሉ ሚስቶች ለእግዚአብሔር እንዲቀኑለት ቢናገሩ ግብዝነት ነው፡፡ ሚስቶቻቸውን እንደሚገባ የማያስተዳድሩ ባሎች ራሳቸውን ከእውነት ጋር ቢቆጥሩ ምስኪኖች ናቸው፡፡ ለወላጆቻቸው በጌታ የማይገዙ አመፀኛ ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ትጋትን ቢያሳዩ ይህ ከፊል መታዘዝ ነው፡፡ ‹‹ውጪ ውጪ ያላችሁ፤ ዙሩ ወደ ቤታችሁ›› ያለውን ገጣሚ እዚህ ጋር አስታወስኩት፡፡
         ላላበው የሚያዝኑ በቤት ደም ካፈሰሱ፤ አደባባይ የለሰለሱ በውስጥ ከሻከሩ፤ በሰው ፊት አንቱ የተባሉ በቤተ ሰዎቻቸው ፊት ከቀለሉ፤ የወጪቱን ውጪ አጥርተው በውስጥ ንጥቂያና አመፅ ከሞላባቸው፤ ላያቸው ኖራ ተለስኖ በውስጥ መቃብር ከሆኑ ምን ይረባል? ጌታ ከማያምን የከፋ ክርስቲያን ከመሆን ይጠብቀን፡፡ ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን!!   
                                       ‹‹ . . . ስለ እኛ ደግሞ ጸልዩ፤›› /ቆላ. 4፡3/!

No comments:

Post a Comment