የእግዚአብሔር ፍትሃዊነት በኑሮ ከምናልፍባቸው ፈተናዎች ጋር ያለው ተዛምዶ አልገባ ሲለን ከምንናገራቸው ብሶት ወለድ አባባሎች አንዱ “ኑሮ ካሉት መቃብር ይሞቃል” የሚል ነው:: ከዚህ እድሜ ጠገብ ብሂል በ'እኛ' ውስጥ የምናስተውለው ልዩ ልዩ ቢሆንም በ'እኔ' ውስጥ ብቻ ሆኜ ስረዳው ግን በመኖር ውስጥ ካለው ቅዝቃዜ በመሞት ውስጥ ሊኖር የሚችለውን ሙቀት ያስበለጠ ይመስለኛል:: ምንም እንኳን በድንን ሙቀት ሳይሆን ቅዝቃዜ ቢገልፀውም የሰው ምሬት ግን ይህንን በመሻል እና በመሞቅ ደረጃ አስቀምጦታል::
የመስጴጦሚያ ጥንታዊያን ህዝቦች የአንድን ሰው መጨረሻ አሊያም ተስፋ ቢስ እጣ ፈንታ ለመግለፅ ይጠቀሙበት የነበረው አገላለፅ “ትቢያ ውስጥ መጋደም” የሚል ነበር:: ይህም ህይወት እንዳከተመች ለሚሰማቸው ሁሉ ከመሬት በታች የቀረላቸው እረፍት ነው::
ፃድቁም ኢዮብ የመከራው እንቆቅልሽ፣ እግዚአብሔርም በእርሱ መፈተን ላይ ያለው ዓላማ አልረዳ ሲለው “አሁን በምድር ውስጥ እተኛለሁ ማለዳ ትፈልገኛለህ አታገኘኝም” (ኢዮ 7፥21) በማለት በምሬት ተናግሯል:: እንዲህ ያሉ አነጋገሮች ሕይወት ብርቱ ሰልፍ በሆነባት ቁሳዊ ዓለም ውስጥ አዲስ ነገር አይደሉም:: ሰዎች በመንፈሳቸው ጭንቀት፣ በነፍሳቸው ምሬት፣ በቀን ሁከት በሌሊት ቅዠት ውስጥ ሲያልፉ፤ ዓይን የመክደኛ ምራቅ የመዋጫን ያህል እረፍት ከልባቸው መዝገብ ሲርቅ ከመከራ ወደላቀ መከራ መገላበጥ የግዴታ ትጋት ሲሆንባቸው ከዚህም በላይ ሲናገሩ አልፎም ተርፎ ሲያደርጉ እናያለን:: ሕይወት ግን አንድ ጎን ብቻ አይደለችም። መደሰት እንዳለ ሁሉ ማዘን፣ የምስራች እንዳለ ሁሉ መርዶ መስማት ዓለሙ የተዋቀረበት ሀቅ ነው፡፡
ለማግኘት በምናደርገው ጥረት ውስጥ የማጣት ሥጋት፣ ዕረፍትን በመናፈቅ ውስጥ የሕመም ፍርሃት፣ ክብርን በመሻት ውስጥ የውድቀት ሥጋት፣ ሕይወትን በማፍቀር ውስጥ የሞት ፍርሃት፣ ድልን በመጠበቅ ውስጥ የሽንፈት ውጥረት በብርቱ ይታገለናል:: ንቁ አእምሮ ያለው ሰው በራስ የመርካትም ሆነ ተስፋ የመቁረጥ ሁኔታ አይታይበትም:: የዘመኑን መርዶ አዘል ዜናዎች ቢሰማም ለመኖር ከሚያሳየው ጉጉትና ጥረት አይቦዝንም:: የሕይወትን አስቸጋሪ ገጽታዎች ቢጋፈጥም “አበቃልኝ” አይልም:: የቱንም ያህል ፈተና ቢጋፈጥ የትቢያ ውስጥ ሙቀትን አይመኝም:: ይልቁንም የወደፊት ተስፋው በእግዚአብሔር አስተማማኝ እጆች ውስጥ ፍጻሜ እንዳለው ስለሚያውቅ እያንዳንዱን ዕለት በብልሃት በጭምትነትና በመታዘዝ ያሳልፋል:: አመለካከት የሕይወትን ስኬትና ውጤት ይወስናልና አስተሳሰባችን የቀና ከሆነ ስኬታማነታችንም የተረጋገጠ ነው:: ማናኛችንም ብንሆን መታወክ የሌለበት ከፈተናና ከውጣ ውረድ የጸዳ መሻታችን ሁሉ የተሟላበት ኑሮ ቢኖረን እንፈልጋለን:: ዳሩ ግን ሕይወት ሙሉ ጣዕም የሚኖራት ሁለቱንም ጫፍ (ማግኘትና ማጣት) በመንካት መሐሉ ላይ ስንኖራት ነው::
ማኅበራዊ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት በምቾት ውስጥ አልፈው ለስኬት ከበቁት ይልቅ በፈተና ውስጥ እንደ ወርቅ ነጥረው በድል ያብረቀረቁ ታታሪ ሰዎች አብላጫውን ቁጥር ይወስዳሉ:: ለምናምን ለእኛ ከሕያው እግዚአብሔር እቅፍ ባለፈ የሚሞቅ ቦታ የለም:: ያም በሚያስፈልገን ሁሉ በእምነት የምንቀርብበት የጸጋ ዙፋን ነው:: የእግዚአብሔር ልጅ ከመቃብር ኑሮ የታደገን እስከ መስቀል ሞት ታዝዞ ነው:: ስለዚህ እግዚአብሔር ያለው ሰው ኑሮ የሸክሞቹ ስብስብ፣ ሕይወት የእንቆቅልሾች አደባባይ ብቻ እንደሆነ አያስብም:: ፈረንሳውያን “ክፉን አላይም ብለህ ዐይንህን አትጨፍን ደግ ሲያልፍ ያመልጥሃልና” ይላሉ:: ኑሮን የሚያጣፍጠው ሁሉን በልኩና በሚዛናዊነት ማስተዋል ነው:: ተወዳጆች ሆይ መቃብር አይሞቅም!!
ይቀጥላል