Friday, April 13, 2012

የጌልገላው ባልጩት



            የእስራኤል ልጆች ዮርዳኖስን ከተሻገሩ በኋላ እግዚአብሔር ኢያሱን አንድ ነገር አዘዘው፡፡ ይኸውም የእስራኤልን ልጆች ሁለተኛ ጊዜ በባልጩት እንዲገርዛቸው ነው፡፡ (ኢያ. 5÷2-10) እስራኤላውያን ከግብጽ ከወጡ በኋላ እንደተገረዙ ነገር ግን በምድረ በዳው ጉዞ ባለመታዘዛቸው ጠንቅ እንደተቀሰፉ እንረዳለን፡፡ በዚህም እግዚአብሔር ጉዳዩ ከሥጋቸው ሸለፈት ጋር ሳይሆን ከልብ መገረዝና ስነ ምግባራዊ ከሆነው ነገር ጋር እንደሆነ መረዳት እንችላለን፡፡ ምክንያቱም ያ ሕዝብ ግብጽን ጥሎ ቢወጣም መገረዝን ቢፈጽሙም የግብፅ ነውርና እርም ግን ከልባቸው አልወጣም ነበር፡፡ ስፍራውን ለቀው ነበር የግብጽ ጠባይ ግን ከልባቸው ላይ ስፍራ አለቀቀም ነበር፡፡ ስለዚህ ሕዝቡ ከሕጉ አንፃር ይዳኝ ስለነበር ደግሞም እግዚአብሔር መንግስት በመሆኑና ኃጢአትን መቅጣት ስላለበት ሕዝቡ ምድረ በዳ ቀርተዋል፡፡ አሁን ግን እንደምናየው እግዚአብሔር ልጆቻቸው በጌልገላ ተራራ ላይ በባልጩት እንዲገርኣቸው ኢያሱን ያዛል፡፡ ጌልገላ በኢያሪኮና በዮርዳኖስ መካከል ያለ ስፍራ ሲሆን የስያሜው ትርጉም ማንከባለያ ማለት ነው፡፡ የእስራኤል ልጆች በመንገድ ሳሉ ሸለፈታሞች ስለነበሩ ፈጽመው መገረዝ ነበረባቸው፡፡ ስለዚህ ኢያሱ የተባለውን ሁሉ አደረገ፡፡ እግዚአብሔርም ኢያሱን፡-ዛሬ የግብፅን ነውር ከእናንተ ላይ አንከባልያለሁ አለው፡፡
            የእስራኤል ልጆች በጌልገላ የግብፅን ሸለፈት በመገረዝ ኮረብታ በባልጩት (ስለታም ድንጋይ ሲሆን በአገራችን የሰማይ ድንጋይ ይባላል) ካሶገዱ በኋላ በኢያሪኮ ሜዳ ላይ ፋሲካ አደረጉ፡፡ የእስራኤል ልጆች አባቶቻቸው ከግብፅ ሲወጡ በቤታቸው መቃንና ጉበን ላይ የበጉን ደም ከመቀባታቸው የተነሣ ሞት በደጃቸው አለፈ፡፡ ከእያንዳንዱ ግብፃዊ ቤት ሬሣ ሲጎተት የእስራኤል ቤቶች ግን በሕይወት ነበሩ፡፡ ለጠላቶቻቸው ሲጨልም ለእነርሱ ግን ብርሃን ነበር፡፡ በጠላቶቻቸው ደጅ እንባ እንደ ጅረት ሲፈስ በእነርሱ ቤት ግን ሰላምና ደስታ ነበር፡፡ የእስራኤል ልጆች እንዲህ ያለውን በዋጋ የማይተመን የሕያው እግዚአብሔር ውለታ የዘከሩት የግብፅን ነውርና ሸለፈት በማስወገድ ነው፡፡ ወላጆቻቸው ከግብፅ ሲወጡ ተገርዘው ነበር፡፡ ነገር ግን የእግዚአብሔርን ቃል ባለመስማታቸው ለአባቶቻቸው የማለላቸውን ምድር እንዳያሳያቸው እግዚአብሔር ማለ፡፡ አሁን ግን እግዚአብሔር በጌልገላው ባልጩት የልጆቻቸውን ሸለፈት ጣለ ከግብፅ ተጽእኖና ነውር አሳረፋቸው፡፡ በዚህም ሸክም መቅለልና ዕረፍት ውስጥ ሆነው ፋሲካውን አከበሩ፡፡
           በአዲስ ኪዳን የእግዚአብሔር ቃል “ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዷልና እንግዲህ ያለ እርሾ እንዳላችሁ አዲሱን ሊጥ ትሆኑ ዘንድ አሮጌውን እርሾ አስወግዱ” ይላል፡፡ ከላይ ለማየት ከሞከርነው የብሉይ ኪዳን ታሪክ አንፃር እኛስ ፋሲካችን ክርስቶስን እንዴት ነው የምናከብረው? የማለፍን በዓል፣ ከድቅድቅ ጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃን የመምጣትን በዓል፣ ከሰማያዊው ጥሪ ተካፋይ የመሆንን በዓል፣ የመንግስት ልጆች የመባልን በዓል እንዴት ነው የምናስበው? ቃሉ ግን “እንግዲህ በምድር ያሉ ብልቶቻችሁን ግደሉ÷ እነዚህም ዝሙትና ርኩሰት ፍትወትም ክፉ ምኞትም ጣዖትንም ማምለክ የሆነ መጎምጀት ነው” (ቆላ. 3÷5-11) ይላል፡፡
           ከፋሲካው በፊት በአንድ እውነተኛ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ሊታሰብበትና ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ይህ ነው፡፡ የመድኃኒዓለም ፈቃድና ደስታም በዚህ ይፈፀማል፡፡ በምድራዊ ብልቶቻችን ላይ የሰለጠነውን የግብፅን ነውርና ሸለፈት በቃሉ ባልጩትነት (የመንፈስ ሰይፍ) ቆርጠን ፋሲካውን ውስጣዊ በሆነ እርካታና ዕረፍት ብናከብረው ለነፍሳችን ትርጉም ይኖረዋል፡፡ ጎሎጎታ ኃጢአታችንን የምንጥልበት፣ ሸክም የሚቀልበት ነው፡፡ እርሱ ደዌያችንን ስለ ተቀበለ፣ ስለ መተላለፋችን ስለ ቆሰለ፣ ስለ በደላችን ስለደቀቀ በእርሱ መቁሰል ተፈውሰናል፡፡ ተወዳጆች ሆይ በምድር ያሉ ብልቶቻችንን ማለትም ዝሙትና ፍትወት፣ ክፉ ምኞትና ርኩሰት እነዚህን የመሳሰሉትን ለማሶገድ ምን ያህል ቆራጦች ነን? ምክንያቱም ሸለፈት ላይ ባልጩት ማሳረፍ መጨከንን ይጠይቃል፡፡ የክርስቶስ መከራና መስቀል ለዚህ ብርቱ ኃይል ነው፡፡ ኃጢአት የእግዚአብሔርን አንድያ ልጅ ለሞት ተላልፎ እንዲሰጥ ያደረገ መሆኑን ከተረዳን በእኛ አመለካከት ጥቂት የምንላት በደል እንኳን ክርስቶስን መስቀል ላይ እንዲቸነከር እንዳደረገው ከገባን በእርግጥም ፋሲካችን ነውርን በማከባለል ይሆናል፡፡ “አጥፊው የበኩሮችን ልጆች እንዳይነካ ፋሲካንና ደምን መርጨትን በእምነት አደረገ” (ዕብ. 11÷28)፡፡ ጌታ ሆይ ሞት ከደምህ የተነሣ አልፎናልና መንግስትህ ይባረክ!!

2 comments:

  1. Ye kiristos mekera ena sikay wede ersu endankerb enkifat behonubin gudayoch lay endichekin yirdan! Egziabher yibarkachu!

    ReplyDelete
  2. ጌታ ይባርካችሁ ሞት አፍቃሪያችን በሆነው በኢየሱስ ሞት አልፎናልና መንግስቱ ይባረክ

    ReplyDelete