Tuesday, February 14, 2012

የወዳጅ ወጣ ገባ



    ሰው በሰው ብቻ ሳይሆን በራሱም ማዘዝ ይቸግረዋል፡፡ መሄድ እየፈለግን የምንቆምበት፣ መሥራት እየፈለግን የምንሰንፍበት፣ መስጠት እየፈለግን የምንነፍግበት፣ በጎ መናገር ሽተን ክፉ ስናወራ የምንውልበት ጊዜ የእድሜያችንን አብላጫ ይወስዳል፡፡ የእኔ ነው ያልነው የሰው የሆነብን፣ አቋሜ ነው ያልነው የተንሸራተተብን፣ ጨበጥኩት ያስኩት ያልነው ነፋስ መዝገን የሆነብን፣ አለ ያልነውን አለመኖር የለም ያልነውን ሕልውና እየተፈራረቀው የተቸገርን፣ ገባ ያልነውን ወጥቶ ወጣ ያልነውን ገብቶ እያገኘነው ግራ የገባን ብዙ ነን፡፡ ወዳጅ የልባችንን እልፍኝ ብቻ ሳይሆን ጓዳ ጎድጓዳውን የሚያውቅ፣ መልካሙን ብቻ ሳይሆን መጥፎውንም የሚረዳ፣ በደስታ ቀን ከብቦ የሚስቅ ብቻ ሳይሆን በሀዘንም ቀን ታጥቆ የሚያለቅስ ነው፡፡ ወዳጅ በጆሮ ሳይሆን በልብ የሚሰማ፣ ከአፍ ሳይሆን ከልብ የሚያደምጥ፣ ከሚደርሱ በፊት ቀድሞ የሚደርስ፣ ከሚቀርቡ በላይ አብዝቶ የሚቀርብ፣ ከሚያውቁ በላይ በጥልቀት የሚያውቅ፣ የማይነገር ያለስስት የሚነገረው፣ የማይታይ ያለመሽኮርመም የሚገለጥለት የማይካፈልን የሚያካፍሉት የልብ ነው፡፡

    ወዳጄ ነው! ማለት የቃሉን ያህል የሚቀል ኃላፊነትን ያዘለ አይደለም፡፡ ለዚህም ነው ጠላቴ በምንለው ከሚደርስብን ጉዳት በላይ የወዳጅ ማቁሰል የሚያንዘፈዝፈን፤ የአፍቃሪ መክዳት አቅል የሚያስተን፡፡ ወጡ ስንል በረንዳ ላይ፤ ገቡ ስንል በር ስር ገብተው አይገቡ ወጥተው አይወጡ ነገር በጉጉት የሚንጡ “አለ የለም፣ ገባ ወጣ፣ ሄደት መለስ፣ ሞቅ ቀዝቀዝ፣ በተን ስብስብ ” ግን ወዳጅ የምንላቸው የየእለቱ የቤት ሥራ ናቸው፡፡ እንዲህ ያለውን ሕመም ዘመናዊ ሐኪም፣ የባሕል መድኃኒት፣ የሥጋ ዘመድ፣ የሀብት ብዛት፣ የስልጣን ከፍታ፣ የእውቀት ጥልቀት አይረዳውም አይፈውሰውምም፡፡

ሰውየው ሚስቱ በመግቢያ ሰዓት እየወጣች በመውጫ ሰዓት እየገባች፤ እንተኛ ሲል እየተሰማራች፣ እንሥራ ሲል እየተጋደመች መከራውን አይኑ ፈጦ ታበላዋለች፡፡ እራት በመብያ ሰዓት ጉሊት ለመሸመት ትወጣለች አንዱን ጥላ ሌላውን አንጠልጥላ በዋል ፈሰስ በያዝ ለቀቅ በሩ ክፍቱን ያመሻል፡፡ ታዲያ ባል ቢቸግረው “ገብተሽ አልቀሽ እንደሆን በሩን ልዝጋው ወይ?” ማለት ጀመረ፡፡ አንዳንዴ ወደ ልባችን አልገባ ካሉን በላይ መግባት ጀምረው ገብተው ያላለቁት ዋጋ ያስከፍሉናል፡፡ በተናጉ ትዳሮች በተበተኑ ጋብቻዎች ላይ ከምናስተውለው የችግር ምክንያት አንዱ ገብቶ አለማለቅ ነው፡፡ አንዳንዶች በቸልተኝነት ሌሎች ደግሞ በብልጣብልጥነት እንዲህ ያለውን ስህተት ይፈጽማሉ፡፡ ብልጦቹ ገብተን ካለቅን ፍቅር ይቀዘቅዛል፣ መዋደድ ይሰለቻል፣ አብሮነትም ይታክታል ይላሉ፡፡ ስለዚህ ለእነርሱ ትዳርን የሚያቆመው ምሰሶ፤ የእድሜውም ዋስትና እንደ ቀብድ እየተሸራረፉ መግባት ነው፡፡ ዛሬ ስለ አይናቸው ያስጠኑናል እሱን አጣጥመን ስንጨርስ ደግሞ ተከታይ አፍንጫን ያብራሩልናል፡፡ አምስቱን የስሜት ሕዋሳት ሲያስጠኑን ብቻ ዐሥር ልደታችንን እናከብራለን፡፡ እንደነዚህ ያሉ ሰዎች በአንዴ የምንናገርለት ሙሉ ነገር የላቸውም፡፡ ስለ ልባቸው ስንጠየቅ እኛ ገና የምላሳቸው አልገባንም፡፡ ስለዚህ ልባቸው ወደ ልባችን ገብቶ እስኪያልቅ ድረስ የምንናገርላቸው አይኖረንም፡፡ በእርግጥም ገብተው ካላለቁ ምን ማውራት ይቻላል? ያለ በቂ መጠናናት የሚፈጸም ትዳርም ሆነ የዓላማ ወዳጅነት የማይጠግ ቁስል ሲያክሙ መኖር ነው፡፡

አዎ! የወዳጅ ወጣ ገባ ማለት ደስታም ሀዘንም፤ ማጣት ማግኘትም ነው፡፡ የወደዳችሁት እንደወጣ የተሰማችሁ መግባትም አለና የሻከረው ልባችሁ በዚህ ተስፋ ይለስልስ፡፡ ወዳጅ በሕይወታችሁ እልፍኝ እንደተሰበሰበ የተሰማችሁም መበተን አለና በዚህ አትመኩ፡፡ ብትወዱ ግን ብዙ ነገሬ ስለሆነው ወዳጄ ጥቂት ልንገራችሁ፡፡ ከገባ የማይወጣ ከያዘ የማይለቅ ካቀፈ የማይገፋ ከሳመ የማይነክስ ቃል ከሰጠ ቃሉን የማያጥፍ ፍቅሩን በቃል ሳይሆን በተግባር እያብራራ የሚደግፍ መታማት መነቀፋችሁ መሰደብ መሰደዳችሁ የማያሸሸው እግራችሁን ሊያጥብ የታጠቀ ሊያቆማችሁ የወደቀ ሊፈውሳችሁ የደቀቀ ሊያከብራችሁ የተዋረደ ለአርነታችሁ የታሠረ መለያው መስቀል የሆነ በአባቱ ቤት ብዙ መኖሪያ ያለው በዚያም ሥፍራን ያዘጋጀላችሁ ትንሣኤና ሕይወት መንገድና እውነት ክርስቶስ ኢየሱስ ነው! በእርሱ ዘንድ ብቻ ገባ ወጣ የለምና በደጅ ቆሞ ለሚያንኳኳው እንቢ እንዳትሉ ተጠንቀቁ!

ተወዳጆች ሆይ በእንባ መጥታችሁ ከነሀዘን፣ በድካም መጥታችሁ ከነመዛል፣ በሕመም መጥታችሁ ከነበሽታችሁ፣ በጥያቄ መጥታችሁ ያለ እረፍት፣ የማትመለሱበት ፊትና ዙፋን የጌታ ነው! መዋደድ ይብዛላችሁ፡፡

2 comments:

  1. በዚህ ምድር ላይ ከእናት እና ልጅ በላይ መወዳጀት ያለበት ሕይወት የለም:: ያም ቢሆን ጥሩ ልብ ያላት እናት ወይም ጥሩ ልብ ያለው ልጅ ከሆኑ ነው:: ግን ምንም ያህል ቢወዳጁ እውነተኛ ፍቅር በመካከላቸው ቢኖር በኃዘን ከመጎስቆል ባለፈ እናት ስትሞት ተከትሎ መቃብር የሚገባ ልጅ፤ ልጅም ሲሞት ተከትሎ መቃብር የምትገባ እናት አለች ወይ?? እኔ እንጃ!! ነገር ግን የእኛ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ለዚያውም እንደ ልጅነታችን ለእናታችን የምንሆነውን ያህል ፍቅር ሳንለግሰው እርሱ ግን እንደ አባትነቱ (ከእናትም በላይ ሆኖ)ከምንም የማይወዳደር ፍቅር ለግሶን በኃጢአት መቃብር ውስጥ ተቀብረን ለነበርነው ለእኛ ሞታችን ሞቶ ከመቃብር አወጣን፤ ታዲያ እስከ መቃብር የማያደርስ ወዳጅነት ወዳጅነት ልንለው እንዴት ይቻለናል? እውነተኛ ወዳጅነትስ ያለው ክርስቶስ ኢየሱስ ጋር መሆኑን ተረዳሁ!! ቃለ ሕይወት ያሰማልን ቤተፍቅር!!

    ReplyDelete
  2. በምድር ላይ እንደ እናት እና ልጅ ያለ ጥሩ የወዳጅነት ሕይወት የለም:: ለዚያውም ጥሩ ልብ ያላት እናት ወይም ጥሩ ልብ ያለው ልጅ ከሆነ:: በመካከላቸው ምንም ያህል ወዳጅነት ወዳጅነት ቢኖር በኃዘን ከመጎስቆል ባለፈ እናት ብትሞት ተከትሎ ወደ መቃብር የሚወርድ ልጅ ወይም ልጅ ቢሞት ተከትሎ መቃብር የምትገባ እናት ትኖር ይሆን?? እንጃ!! የእኛ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ለዚያውም ልጆቹ እንደመሆናችን ለእናታችን የምንሆነውን ያህል ፍቅር እንኳ ሳንለግሰው፤ አባት እንደመሆኑ (ከእናትም በላይ ሆኖ)ከሚገባን በላይ ፍቅር ለግሶን ሞታችንን ሞቶ ከኃጢአት መቃብር ያወጣን ታማኝ ወዳጅ መሆኑን የተረዳን ስንቶቻችን እንሆን? ቃለ ሕይወት ያሰማልን ቤተ ፍቅር!!

    ReplyDelete