Thursday, February 16, 2012

የምስጋና ዋጋ



   ጥንታዊ በሆነ አንድ ገዳም ውስጥ የነበረን ሃይማኖታዊ ስርዓት በምሳሌነት እናንሣ። የዚህ ስነ ስርዓት አንዱ መሰረታዊ ነገር በውስጡ የሚኖሩ ባህታውያን ዝም ማለት አለባቸው የሚል ሲሆን የመናገር እድል የሚዘጋጅላቸውም በሁለት ዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ በዚያን ጊዜ ታዲያ ሁለት ቃላቶችን እንዲናገሩ ይፈቀድላቸው ነበር፡፡
     አንድ ወጣት ይህን ስርዓት ከጀመረ በኋላ የሁለት ዓመቱን የአመክሮ ጊዜ ሲያጠናቅቅ አበምኔቱ ሁለት ቃላትን ይናገር ዘንድ ጋበዙት፡፡ እርሱም “የምግቡ መጥፎነት” ሲል ተናገረ። ከሁለት ተጨማሪ ዓመታት በኋላ እንደገና ሁለት ቃላት የመናገሩን እድል አገኘ። ታዲያ ይህንን አጋጣሚ “የመኝታው መቆርቆር” ለማለት ተጠቀመበት፡፡
    ከሁለት ዓመታት በኋላ ለሦስተኛ ጊዜ የገዳሙ መሪ ጋር ሲደርስ ተስፋ መቁረጥ በሚታይበት መንፈስ ውስጥ ሆኖ እንዲህ ሲል ተናገረ፡- “እኔ ለቅቄያለሁ”፤ የገዳሙም አበምኔት ወደ ወጣቱ እየተመለከቱ፡- “ታውቃለህ! ያልከው ሁሉ እኔን ትንሽ እንኳን አልደነቀኝም፡፡ እዚህ ከደረስክበት ጊዜ አንስቶ እያደረክ ያለኸው ማማረር፣ ማማረር፣ ማማረር . . . . ብቻ ነው” አሉት። ወደእኛ ሕይወት እንምጣና ኑሮን በሁለት ቃላቶች እንድንገልጸው እድሉ ቢሰጠን ምላሻችን ምን ይሆን ነበር? ትኩረትህ በአሜኬላዎቹ በጉብታዎቹና ፍትሃዊ ባለመሆን ላይ ይሆን ነበር? ወይስ መልካም ትክክልና ተወዳጅ በነበሩት ሁኔታዎች ውስጥ ለመኖር ቆርጠህ ትነሣ ነበር?
    ለልባችን ከጣፋጩ ይልቅ የመረረው ቅርብ የሆነበት ምስጢር አለማመስገን ነው፡፡ አእምሮን ከሚያልፍ ሰላም ርቀን የሕሊናችን ትኩሳት አልበርድ ያለውም ብዙ ተቀብሎ ጥቂት ከማያመሰግን ሰብእናችን የተነሣ ነው፡፡ ኑሮ ከምግብ መጣፈጥ፣ ከመኝታ መመቸት፣ ከቦታ መደላደል፣ ከሥጋ መቀማጠል የዘለለ ቁም ነገር አለው፡፡ በዚህም ምድር ሳለን ከዚህ ከፍ ያለ ዓላማና ጉዞ ከሌለን እጅግ ምስኪኖች ነን!  
    እግዚአብሔርን በማመስገን፣ ስሙን በማክበር፣ ቃል ኪዳኑን በማመን፣ ጌትነቱን በማምለክ፣ ተስፋውን በመጠባበቅ የኖሩ በእሳት ውስጥ እንኳን ለአምላካችን አምልኮ ለንጉሣችን ውዳሴ ነበራቸው፡፡ የሁኔታ ለውጥ፣ የምቾት መጓደል፣ የጨካኞች ዛቻ፣ የሐሰተኞች ተንኮል የማያቀልጠው ልብ፣ የማያቆሽሸው ሕሊና እርሱ አመስጋኝ ነው፡፡ እግዚአብሔርን ለማመስገን ፈቃዱንም ላለማማረር ከበቂ በላይ ምክንያት አለን፡፡ የምናስወጣውና የምናስገባው አየር፣ ያለፈልን ሌሊት የተቀበልነው ማለዳ፣ ለዘላለም ኑሮ የተያዘልን ቀጠሮ . . . . የተባረከ ጥቂት ምክንያታችን ነው፡፡ ዛሬ ለመቀበል ትላንት የተደረገልንን በማሰብ ማመስገን ጤናማነት ነው፡፡ የሰጭውን ልብ ከሚያራሩ ነገሮች አንዱ ያለፈውን ውለታውን ማሰብ መቻላችን ነው፡፡ ተወዳጆች ሆይ የምስጋና ዋጋው የሚብራራው ባመሰገንበት መጠን ነውና አመስግኑ!
    አንድ ጊዜ የሰማሁትን ሌላ ምሳሌ ላካፍላችሁ፡፡ ሁለት ሰዎች እግዚአብሔርን ተመሳሳይ ነገር ለመኑት፡፡ እግዚአብሔርም ለአንዱ ሰጥቶ ሌላውን ከለከለው፡፡ ያልተቀበለውም ሰው በአምላኩ ፊት ቆሞ “ለባልንጀራዬ ሰጥተህ እኔን የነሳኸኝ ስለምንድነው” በማለት ሞገተ፡፡ ጌታም አምላክም የሆነው ሲመልስ “እርሱን ብከለክለው ኖሮ ከእኔ ይርቅ ነበር ስለዚህ በመስጠት በእቅፌ እንዲቆይ አደረኩት፡፡ አንተ ደግሞ ብሰጥህ ኖሮ በሰጠሁህ ረክተህ ሰጭውን እኔን ትተህ ትለየኝ ነበር፡፡ ስለዚህ አንተን በመከልከል የእኔ አደረኩህ፡፡” አለው፡፡ እግዚአብሔር ሲሰጠን ልክ የሚሆነውን ያህል ሲከለክለንም እውነተኛ ነው፡፡ እርሱ የሚሰጠንን ማንም መልአክ እንኳን እንደማይሰጠን እርሱ የከለከለንንም ከማንም አናገኘውም፡፡ “በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ሁሉ ከላይ ናቸው÷ መለወጥም በእርሱ ዘንድ ከሌለ በመዞርም የተደረገ ጥላ በእርሱ ዘንድ ከሌለ ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ፡፡” (ያዕ. 1÷17)፡፡ አሜን!

No comments:

Post a Comment