የወደደንን መውደድ፣ የጠላንን መጥላት፣ ለዋለልን መስጠት፣ ለነፈገን መንሣት፣
ላሰበልን መራራት፣ ለዘነጋን መክፋት የብዙኃኑ የሰው ልጅ የአኗኗር መመሪያ ነው፡፡ ምንም እንኳን በጸጋ ዘመን ላይ ብንገኝም ዓለም
ገና ዓይን ስለ ዓይን፣ ጥርስ ስለ ጥርስ፣ እጅ ስለ እጅ ከሚለው ምላሽ አልጸዳችም፡፡ እንዲያውም በዚህ ሕግ ግልጽ ሆኖ ከሚስተዋለው
ለጠሉኝ እሬት አይነት አካሄድ በበለጠና በረቀቀ መንገድ ሰዎች የልባቸውን ፈቃድ እያረኩ ነው፡፡ ለብዙ ክርስቲያኖች እንዲህ ያለውን
እሾህን በእሾህ፣ ደምን በደም የመመለስ ኑሮ ከእምነት ጋር አቻችሎ ማስኬድ አልከበዳቸውም፡፡ ክፉውም ጋር ደጉም ጋር ቋሚ ተሰላፊ
የሆኑ ጥቂት ሆድ ሲብሳቸው “ያስቀመጥኩትን ቆንጨራ እንዳላመጣው?” በማለት የሚዝቱ ሁሉን ትተው ሳይሆን ሁሉን ለክፉ ቀን አስቀምጠው
የተከተሉት አይናችን ስር ናቸው፡፡
አብዛኞቻችን
ሰው በሚለውና ክርስቲያን በሚለው መጠሪያ መካከል ያለውን ልዩነት ልብ አንለውም፡፡ ሰው ከምድራዊው ጥሪ ተካፋይ የሆንበት መንገድ
ሲሆን፤ ክርስቲያን የሚለው ደግሞ ከሰማያዊው ጥሪ ተካፋይ የሆንበት መንገድ ነው፡፡ ሰው በመሆን ውስጥ በምድራዊ ስፍራና በሥጋዊ
በረከት መርካት ሲስተዋልበት፡፡ (ማለትም በዚህ ምድር የምንሰበስበው ሁሉ ከፀሐይ በታች ሲሆን) ክርስቲያን በመሆን ውስጥ ደግሞ
በሰማያዊ ስፍራና በመንፈሳዊ በረከት መባረክን እናስተውላለን (ኤፌ. 1÷3)፡፡
ሰው በመሆን ልደት ይህንን ዓለም በሥጋና በደም አቋም ሆነን እንቀላቀላለን፡፡
ክርስቲያን በመሆን (ዳግም በመወለድ) ደግሞ የዘላለም ሕይወትን መቀላቀል ደግሞም የተዋረደው ሥጋችን የጌታን ክቡር ሰውነት መስሎ
በሰማይ ከእርሱ ጋር እንነግሳለን፡፡ ስለዚህ ክርስቲያን ሁሉ ሰው መሆንን ቢጋራም ሰው ሁሉ ግን ክርስቲያን አይደለም፡፡ በዚህም
ክርስቲያን መሆን ሰው ከመሆን በእጅጉ ከፍ ያለ እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡
“ቀኝ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሁሉ ሁለተኛውን ደግሞ አዙርለት፣ እንዲከስህም እጀ ጠባብህን እንዲወስድ
ለሚወድ መጎናጸፊያህን ደግሞ ተውለት፣ ማንም ሰው አንድ ምእራፍ
ትሄድ ዘንድ ቢያስገድድህ ሁለተኛውን ከእርሱ ጋር ሂድ” (ማቴ.
5÷38-42)፡፡ ጌታ በዚህ ክፍል ላይ ያስተማረው ትምህርት ሰው
በሚለውና ክርስቲያን በሚለው ስያሜ መካከል ያለውን ተግባራዊ ልዩነት ግልጽ ያደርግልናል፡፡ በመጀመሪያ እግዚአብሔር ለሚያዘን ነገር
ሁሉ የምንፈጽምበትን ኃይል እንደሚሰጠን መተማመን በዚህ ክፍል የተገለጸውን ትምህርት በቅንነት ለመረዳት ወሳኝ ነገር ነው፡፡ ቀኝ
ጉንጭን በጥፊ መመታት ውስጥ ያለው ክርስትና ሳይሆን ሰው መሆን ነው፡፡
እጀ ጠባብን ለሚወስድ ያንኑ መተው ሰው በመሆን ደረጃ የሚከናወን
ተግባር እንጂ ክርስቲያን መሆንን አይጠይቅም፡፡ አንድ ምእራፍ በመሄድ ውስጥም እንዲሁ ከክርስትና ይልቅ ያለው ሰው መሆን ነው፡፡
የክርስትናው የአኗኗር ልኬት የሚጀምረው ታዲያ የቱ ጋር ነው? ካልን ሁለተኛውን ጉንጭ በመስጠት፣ መጎናጸፊያን በመጨመር፣ ሁለተኛውን
ምእራፍ በመሄድ የሚል ይሆናል፡፡ ከዚህ ያነሰው ግን ማንም ሰው ከሰብአዊ ርኅራኄ በመነሣት አልያም ከሥጋ ሕግ በመነጨ ሁኔታ የሚከውነው
ነው፡፡ “የሚወዱአችሁን ብትወዱ ምን ዋጋ አላችሁ? ቀራጮችስ ያንኑ ያደርጉ የለምን? ወንድሞቻችሁንም ብቻ እጅ ብትነሡ ምን ብልጫ
ታደርጋላችሁ? አሕዛብስ ያንኑ ያደርጉ የለምን?” (ማቴ. 5÷46)፡፡
የነከሰንን ማጉረስ፣ የበደለንን መካስ፣ የተጣላንን ገፍቶ መታረቅ፣ የረገመንን
ከልብ መመረቅ ተወግቶ እንደ መርሳት ነው፡፡ ጉዳቱ እያለ በደልን አለመቁጠር፣ ስቃዩ እየታየ ጥፋትን መተው፣ ጉድለቱ እየተስተዋለ
ኪሳራን አለማስላት መንፈሳዊ የኑሮ ልዕልናን ይጠይቃል፡፡ ክርስትና የተወጋ ሲረሳ ነው!
ከብሉይ ኪዳን በዳዊትና በሳኦል መካከል የነበረው የገፊና ተገፊ፣
ያሳዳጅና ተሰዳጅ፣ የጠዪና ተጠይ ታሪክ ለተነሣንበት ርእስ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ የመጀመሪያው የእስራኤል ንጉሥ ሳኦል ወደ ንግሥና
የመጣበትን መንገድ የስነ መለኮት አዋቂዎች ሲያስረዱ “እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር የተስማማበት ሂደት ነው” ይላሉ፡፡ ለዚህም ምክንያቱ
ሳኦል የእስራኤል ንጉስ የሆነው እንደ እግዚአብሔር ፍላጎት ሳይሆን በሕዝቡ ፍላጎት ተመርጦ በእግዚአብሔር አጽዳቂነት መሆኑ ነው፡፡
እግዚአብሔር ሳሙኤልን “እንደጠየቁ ቀባላቸው” በማለት ከሕዝቡ
አሳብ ጋር ተስማማ፡፡ ይህም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብቸኛው ክፍል እንደሆነ ይነገራል (1 ሳሙ. 15)፡፡ ምን ጊዜም ቢሆን እግዚአብሔር
ከአሳባችን ጋር ከተስማማ ኪሳራው የሰው ነው፡፡ ወደኋላ መለስ ብለን ያለፈውን ፍላጎታችንን እና ዛሬ በዚያ ፍላጎት ላይ ያለንን
አተያየት ብንመለከተው ለየቅል ነው፡፡ ያኔ እግዚአብሔር በፊቱ ካቀረብነው አሳብ ጋር ተስማምቶ ቢሆን፤ እንደጠየቅነው ሁሉን ቢሰጠን
ኖሮ ዛሬ ከምናፍርበት ነገር ጋር ለመኖር በተገደድን ነበር፡፡
እግዚአብሔር ሲሰጥ ብቻ ሳይሆን ሲከለክል፣ ሲመልስ ብቻ ሳይሆን
ዝም ሲል፣ ሲያኖር ብቻ ሳይሆን ሲገድልም አይሳሳትም፡፡ የእርሱ ጌትነት ምቾትን ብቻ ሳይሆን ጉስቁልናንም ያጠቃልላል፡፡ ክርስትና
መብዛትን ብቻ ሳይሆን መዋረድን፣ መጥገብን ብቻ ሳይሆን መራብን፣ ከፍታን ብቻ ሳይሆን መጉደልንም ማወቅ ጭምር ነው (ፊል. 4÷12)፡፡
ስለዚህም አሳቡን እንስማማበት፣ መንገዱን እንጓዝበት ዘንድ እግዚአብሔር ከእኛ አሳብና መንገድ እጅግ የራቀ ነው፡፡ እርሱ ከፍላጎቶቻችን
ጋር ሳይሆን እኛ ከእርሱ ፍላጎት ጋር፤ ከምርጫዎቻችን ጋር ሳይሆን እኛ ከእርሱ ፈቃድ ጋር፣ ከልባችን ጋር ሳይሆን እኛ ከልቡ ምክር
ጋር እንስማማ ዘንድ አግባብ ነው፡፡
ዳዊት እግዚአብሔር በጠላቶቹ ፊት ለፊት በዘይት የቀባው፣ ከወንድሞቹ
መካከል ለይቶ በአባቱ ንቀት ፊት ያከበረው ሰው ነው፡፡ ትልቁ እግዚአብሔር በብላቴናው ሕይወት ኃይሉንና ክብሩን ይገልጥ ዘንድ ስለወደደ
ከበጎች ጥበቃ ወደ ንግሥና አመጣው፡፡ ሰው እኛን ወደተሻለ ነገር ለማምጣት ደረጃ በደረጃ ይሠራ ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር ግን ከትቢያ
አንስቶ ወደ ልዕልና ለማምጣት እርከን አያስፈልገውም፡፡ ዳዊት በሳኦል መንግሥት ዘመን ለሕዝቡ ፍርሃት፤ ለመንግስቱ ሥጋት የሆነውን
ጎልያድ በእግዚአብሔር ስም በማሸነፍ ባለ ውለታ ነው፡፡ ከድሉ በኋላም ቤተ መንግሥት ውስጥ በገና በመደርደር የሳኦልን ርኩስ መንፈስ
በማውጣት ለሳኦል ባለ ውለታ ነው፡፡ የሳኦል ምላሽ ግን ዳዊት ካደረገው ቅንነት ፍፁም ተቃራኒ ነበር፡፡ ሳኦልን ሊቀበል የወጣው
ሕዝብ ለዳዊት በመዘመሩ (እልፍ ገደለ) እጅግ ተቆጣ፡፡ በገናምም እየደረደረ ሳለ ከግንቡ ጋር አጣብቀዋለሁ በማለት በእጁ የያዘውን
ጦር ወረወረበት፡፡
በክፉዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን የሚያወጣ እግዚአብሔር ሁሉ
በፊቱ የተራቆተለት አምላክ ነው፡፡ የአመፀኛውን አመጽና የትሁቱን ትህትና የእርሱ ጽድቅ በእውነት ይዳኛል፡፡ ዳዊት እንዲህ ባለው
ጌታ ፊት አንደኛ ሳኦል የሚያደርግበትን ክፉ፤ ሁለተኛ ለሳኦል
የሚያደርግለትን መልካም ነገር አይቆጥርም ነበር፡፡ ለዳዊት
ጤና ይህ ነበር!
በሕይወታችን ውስጥ ከሚስተዋለው ድካም መካከል ያደረግነውን መልካም
መተሳሰብና የተደረገብንን ክፉ መቁጠር በጉልህ የሚስተዋል ነው፡፡ የእግዚአብሔር ሰው ዳዊት የወንድሞቹን ጥላቻ፣ የአባቱን መናቅ፣
የሳኦልን ማሳደድ የተበቀለበት ትልቁ መንገድ መርሳት (አለመቁጠር) ነው፡፡ ሰው በቀል የተጠማ ልቡን የሚያረካበት መንገድ በደልን
መቁጠር እንዲሁም ለበደሉ ተመጣጣኝ ምላሽ በመስጠት ነው፡፡ ነቢዩ ግን ሁሉን ማድረግ በሚችል እግዚአብሔር ፊት የተደረገበትን ይተወው
ነበር፡፡ ሳኦል ጦርን ያህል ነገር ወርውሮበት ምድረበዳ ለምድረበዳ ሲያሳድደው የሚያደርገውን እንደማያውቅ ምስኪን ሰው ይቆጥርለት
ነበር፡፡ እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ነው! ብሎ ጉልበቱን ለማጥፋት አልተጠቀመበትም፡፡ ለሚያምኑ ሁሉ የእግዚአብሔር ኃይል ለማዳን ነው
(ሮሜ. 1÷16) ተብሎ እንደተፃፈ የእግዚአብሔር የሆኑቱ ጉልበታቸውን በደልን ለመርሳት እንጂ ለመቁጠር አያውሉትም፡፡
- ይቀጥላል -
ውድ የቤተ ፍቅር ብሎግ ተከታታዮች
በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስና በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ሞት የተሰማንን ሀዘን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡ ጌታ እግዚአብሔር ምድሪቱንና
ሕዝቡን ይባርክ!!