Tuesday, July 31, 2012

የቃየን መንገድ (ካለፈው የቀጠለ)



1. ቤተ ፍቅር በየጊዜው የምታነሷቸው ርእሶች ጠንካራነትና አመራማሪነት በእጅጉ ይማርከኛል፡፡ በተለይ ከመጽሐፍ ቅዱስ ለመወያያነት የምታቀርቡት ትምህርት ከአሁን በፊት ከነበረኝ እይታና የመረዳት መንገድ በተሻለና በላቀ መንገድ እንዳስተውል ረድቶኛል፡፡ እግዚአብሔር በጥበብና በማስተዋል ጸጋውን ያብዛላችሁ፡፡ እኔ በፊት ስረዳው የቃየልን መንገድ ወንድምን ከመግደል አንፃር ብቻ ነበር፡፡ ለካስ ትውልድንም በመንፈሳዊው መንገድ ከመግደል አንፃር ይታይ ኖሮአል? ደጋግሜ ሳነበው የቃየል መንገድ የራሱ የቃየል ብቻ ችግር ሆኖ አልቀረም፡፡ በሺህ የሚቆጠሩ ዘመናትንም ተሻግሮ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ዘልቆአል፡፡ ችግሩ ከአምልኮ ጋር የተያያዘ መሆኑ ደግሞ ጉዳዩን ይበልጥ ያንረዋል፡፡
        በመጀመሪያ ቃየልና አቤል መካከል ልዩነት የፈጠረው መሥዋዕቱ እንደሆነ አስተውያለው፡፡ በቀጥታ ትዝ ያለኝ ደም ሳይፈስ ስርየት የለም የሚለው ብቸኛ መፍትሔ ነው፡፡ የቃየል መሥዋዕት ግን ደም አልባ በመሆኑ ሥርየት ሊያመጣ አልቻለም፡፡ አቤል እንደዚህ ያለውን መሰረታዊ ትምህርት ከቤተሰቦቹ የተማረ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም አዳምና ሔዋን ከበደሉ በኋላ በእግዚአብሔር ፊት መቆም ስላልቻሉ ቅጠል ሰፉ ይህም የሰው ምስኪን መፍትሔ ከመሆን ባለፈ ያሰቡትን ውጤት ሊያመጣ አልቻለም፡፡ ስለዚህ ያዘነላቸው እግዚአብሔር ቁርበት ሰፍቶ አለበሳቸው፡፡ ቁርበት የእንስሳ ቆዳ እንደመሆኑ በቀጥታ አንድ መሥዋዕት እንደተሰዋ እንድናስብ ይጋብዘናል፡፡ እንግዲህ ቀዳማዊ ቤተሰቦቻችን ከእግዚአብሔር ይህንን ትምህርት ተምረዋል ማለት ነው፡፡
         እኔ እንደተረዳሁት የአቤልን መሥዋዕት አቀራረብ ስመለከተው ከመስማት በሆነ እውቀት የተከናወነ እንጂ በዘፈቀደ የተሠራ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም አቤል መሥዋዕት ያቀረበው ከበጉ በኩራት፣ ከበኩራቱ ስቡን ነው፡፡ ይኼ ደግሞ መንፈሳዊ ትምህርትን መሰረት ባደረገ መንገድ የተፈፀመ እንደሆነ ያስረዳናል፡፡ በተጨማሪም አቤል እንደ እግዚአብሔር ልብ በሆነ መንገድ ለእግዚአብሔር መሥዋዕትን ሲያቀርብ ቃየል ግን እንደ ልቡ በሆነ መንገድ በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት ለማግኘት እንደሞከረ እናያለን፡፡
        ከሁሉም በላይ የተገረምኩት ደግሞ በቃየል ውስጥ እምነት አለመኖሩ በአቤል ውስጥ ደግሞ እምነት የመገኘቱ ነገር ነው፡፡ ዳሩ ግን ሁለቱም መሥዋዕት አቅርበዋል፡፡ አንድ ሰው ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ማቅረቡ ብቻ እምነት አለው ለመባል ብቸኛ ማረጋገጫ ሊሆን አይችልም፡፡ መንፈስ ቅዱስ ግን የሰውን ልብና ኩላሊት ይመረምር ዘንድ አዋቂ ነው፡፡ አቤል ከቃየል ይልቅ የሚበልጥን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር በእምነት አቀረበ (ዕብ. 11÷4) የሚለውን ምስክርነት ስናነብ መበላለጡን ያመጣው መሥዋዕቱ እንደሆነ ደግሞም በእምነት አቀረበ የሚለው ገለፃ ቃየል እምነት እንዳልነበረው ያረጋግጥልናል፡፡
        መሥዋዕትን ስናስብ ትልቁ አገልግሎቱ ምትክነት ነው፡፡ ማለትም ኃጢአተኛው በእርሱና በኃጢአት ደመወዙ ሞት መካከል ሌላ በመሞት ቤዛ የሚሆነው ማቆም አለበት፡፡ በእኛና በእግዚአብሔር መካከል ኃጢአታችን ስለለየች የጠብ ግድግዳ ቆሞ ነበር፡፡ እግዚአብሔር አብ ይህንን የጠብ ግድግዳ ለማፍረስ ደግሞ ማስተሰርያ ማቆም ነበረበት፡፡ ስለዚህም ልጁን ማስተሰሪያ አድርጎ አቆመው (ሮሜ. 3÷25)፡፡
        ሌላው ሳነብ የተረዳሁት አቤል በስጦታውና በስጦታው ላይ በነበረው ሙሉ እምነት በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነትን ሲያገኝ ቃየል ደግሞ በኃጢአቱ ምክንያት ተቀባይነትን አጣ፡፡ ቃየል በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት ያገኝ ዘንድ የተጠቀመበት መንገድ ዛሬም ድረስ ወዮታ አለበት፡፡
       በመጨረሻ ያስተዋልኩት ከመሠዊያው በኋላ በሁለቱ ሕይወት ውስጥ የታየውን ግልጽ ልዩነት ነው፡፡ መሥዋዕት ይዘው እግዚአብሔር ፊት ከመቅረባቸው አስቀድሞ ስለ ሁለቱ ጠባይና የአኗኗር ሁኔታ የተገለፀ ነገር የለም፡፡ ከመሠዊያው በኋላ ግን የሁለቱም መከር አስቀድሞ እንደዘሩት አይነት ሆነ፡፡ በእርግጥ ሁለቱን የሚያመሳስላቸው ባሕርይ አለ፡፡ ይኸውም ከዔደን ገነት ውጪ መወለዳቸው ደግሞም ከመጀመሪያው አዳም በልደት የኃጢአቱ ተካፋይ መሆናቸው ሁለቱንም በእኩል በደለኛ ማንነት ያስይዛቸዋል፡፡ በዚህ መንገድ ከሄድን ሁለቱንም በእግዚአብሔር ፊት የሚያበላልጣቸው ነገር አይኖርም፡፡ ዳሩ ግን መሥዋዕታቸው በወንድማማቾቹ ሕይወት ላይ ይህ ነው የማይባል ልዩነት ፈጥሮአል፡፡ እኔ በፊት ያለ ማስተዋል መጽሐፍ ቅዱስን አነብ በነበረበት ጊዜ በአቤል ውስጥ ጽድቅ ያለ ይመስለኝ ነበር፡፡ ነገር ግን አሁን ኃጢአተኛው አቤል ቅንና ፃድቅ በሆነው እግዚአብሔር ፊት ሞገስን ያስገኘለት ይዞ የቀረበው መሥዋዕት ነው፡፡
      ከመሠዋት በኋላ አቤል ለስደት ቃየል ለማሳደድ፤ አቤል ለሞት ቃየል ደግሞ ለነፍሰ ገዳይነት በቁ፡፡ ቃየል በራሱ ተቀባይነት አለማግኘት ሳይሆን በወንድሙ ሞገስ ማግኘት ቀና፡፡ ቃየል ፊቱ ጠቁሮ ሳለ እግዚአብሔር መልካም ብታደርግ ፊትህ የሚበራ አይደለምን? (ዘፍ. 4÷6) ባለው ጊዜ ዳግመኛ ከስህተቱ የመመለስና የመታረም እድል አግኝቶ ነበር፡፡ ግን በመንገዱ እንደጸና ዘለቀ፡፡ ለክፋትም ትልቅ ምሳሌ ለመሆን አገለገለ፡፡ መጨረሻውም ዓለምን ያስጌጠና ለሥጋው ብቻ በትጋት የኖረ ምስኪን ተቅበዝባዥ ሆኖ አለፈ፡፡ ከመሥዋዕቱ ጋር መታየት ምን ያህል ዋጋ አስከፋይ እንደሆነ የአቤል ኑሮ ያስረዳል፡፡ እኔ በትንሿ አእምሮዬ ይህንን ታክል ታይቶኛል፡፡ እናንተም በሰፋና በተረጋጋ አእምሮ ሆናችሁ ብትመረምሩት  ለእምነት ሰው የሚረባ ትምህርት እንዳለው አስባለሁ፡፡ ይህንን አሳቤን ለንባብ በማቅረብ ለሌሎችም እንደምታካፍሉልኝ በመማፀን ጨረስኩ፡፡
                                                            ዮርዳኖስ ወ/ትንሣኤ

2. በቤተ ክርስቲያን ብዙ ጊዜ ሲሰበክና ትምህርት ሲሰጥበት አስታውሳለሁ፡፡ ነገር ግን የአቤልና የቃየል ጉዳይ ይሁዳ መልእክት ድረስ እንደደረሰ ግን ሳውቅ የመጀመሪያዬ ነው፡፡ ታሪኩን እንድናይ ፍንጭ የሰጣችሁበት መንገድም በጣም ደስ ይላል፡፡ ብዙ ሰው ለመልኩ፣ ለቁመናው፣ ለኑሮው ልዩነት ደፋ ቀና ይላል፡፡ ነገር ግን ዘላለማዊ ልዩነት ስለሚፈጥረው መሥዋዕት ግድ የለውም፡፡ የወንድማማቾቹን ታሪክ ሳነበው የቃየል ትምክህት ያስገርመኛል፡፡ እንደውም እግዚአብሔርን እንደ እግዚአብሔርነቱ የተረዳው አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ማንና ምን እንደሆነ የተረዳ ሰው “የወንድሜ ጠባቂው ነኝን?” የሚል ስንፍና ሁሉን ለሚችል አምላክ አይመልስም፡፡
         እንደ እኔ አስተያየት ታሪኩን ወቅታዊ ከሆነው ታሪካችን ጋር አገናዝበን ማየቱ ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡ የይሁዳ መልእክት ለክርስቲያኖች እንደ መፃፉ ወዮላቸው የሚለው የፍርድ ቃል በመካከላችን እንደሆነ መረዳት ይገባል፡፡ እኛ የቆምነው በየትኛው መንገድ ነው፡፡ ቃየል ወንድሙን ሲገድል መሥዋዕቱንም እየተቃወመ ነው፡፡ በዚህ ታሪክ ውስጥ ግን አንድ ነገር ተረዳሁ አምልኮ በእግዚአብሔር ፊት ምን ያህል ከባድ ትርጉምና ከፍታ እንዳለው፡፡ እርሱ ባለቤቱ እንዲህ ካለው መንገድ ይጠብቀን፡፡
                                                                ገ/ኢየሱስ ኃይሌ

3. ቤተ ፍቅር በርቱ ጌታ ኃይሉን ይስጣችሁ፡፡ እኔ በስደት አገር የምኖር ክርስቲያን ነኝ፡፡ ጽሑፎቻችሁን በመከታተልም ብዙ አሳልፌአለሁ፡፡ ነገር ግን የምታነሷቸው አሳቦች ትንሽ ጠጠር ይላሉ፡፡ ስለዚህ በተቻለ መጠን ቀለል ማድረግ ብትችሉ፤ በተለይ እንደ እኔ ላሉ በቂ አማራጭ ማብራሪያና ተጠያቂ ሰው ለማያገኙ ወገኖች እጅግ ጥሩ ይመስለኛል፡፡ ምድራችን በቃየል መንገድ ተጨናንቃለች፡፡ የመንገዱም ፍሬ በግልጥ እየታየና ከእለት ወደ እለት ተባባሪዎችን እያከማቸ ነው፡፡ ብልህ ሰው ግን ወድቆ ሳይሆን ቆሞ ይማራል፡፡ወገኖቼ አምልጡ!
                                                                  ሶስና ተወልደ
       

No comments:

Post a Comment