የእግዚአብሔርን ሕልውና የተቀበልንበት መንገድ እምነት ነው፡፡
እርሱን ያየውና የዳሰሰው የለም፡፡ ስለ እርሱ ከሰማነው ቃል የተነሣ ግን ወደ ማመን ከፍታ መምጣ ሆኖልናል፡፡ በእርሱና በእኛ መካከል
ያለው መግባባት የተመሰረተው በእምነት ላይ እንደሆነ ለልባችን ማስረገጥ እንችላለን፡፡ እግዚአብሔርን ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሔር
የሆነውን ሁሉ በረከት የምንቀበለው የእግዚአብሔርን ሕልውና በተቀበልንበት መንገድ ነው፡፡ ራሱን በማመን ሰጥቶን የእርሱ የሆነውን
እንደ ትጋታችን መጠን ሊሰጠን አይችልም፡፡ ምክንያቱም ስጦታው ጸጋ (የማይገባ) ነው!
ሐዋርያው ለገላትያ ሰዎች በፃፈው መልእክት “የማታስተውሉ የገላትያ
ሰዎች ሆይ በአይናችሁ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ተሥሎ
ነበር ለእውነት እንዳትታዘዙ አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው? (ገላ. 3÷1)” በማለት መጠይቃዊ ተግሳጽ ሲያስተላልፍ እናስተውላለን፡፡
የገላትያ ሰዎች ከሚያስመካው የእግዚአብሔር ጽድቅ ይልቅ በራሳቸው ጥረት የተመኩ ነበሩ፡፡ በሕግና በነቢያት የተመሰከረለትን ነገር
ግን ያለ ሕግ የተገለጠውን የመለኮት ጽድቅ በሥጋቸው ውስጥ ካለው ትምክህት የተነሣ ገፍተውት ነበር፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እንግዲያማ
ክርስቶስ በከንቱ ሞቶአል? እስኪል ድረስ የሕዝቡ ድንዛዜ የክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ ዋጋ ያሳጣ ነበር፡፡ ከዚህም የተነሣ ለእውነት
እንዳይታዘዙ ልባቸው ደነደነ፡፡
ለእነርሱም የእግዚአብሔር ምሳሌ የሆነ የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል
ብርሃን እንዳያበራላቸው የዚህ ዓለም አምላክ የማያምኑትን አሳብ አሳወረ (2 ቆሮ. 4÷4) ተብሎ እንደተፃፈ የዲያብሎስ ውጊያ ከአሳባችን
ጋር ነው፡፡ አሳባችንን ማሳወር! ሰው ደግሞ ልቡ (አሳብ) ካላየ አይኑ አያስተውልም፡፡ በተለይ በእምነት ውስጥ ስንኖር የዚህ እውነት
ተግባራዊነት ግልጽ ይሆናል፡፡ በአንድ ሰው ውስጥ ያለው ትልቁ ሐብት አሳቡ ነው፡፡ ለዚህም ነው በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ
የተባለው፡፡ ጉብዝናችንን እግዚአብሔርን ካላሰብንበት ሽምግልናችን የጸጸት ይሆናል፡፡ የምድሪቱ ጩኸት ምንድነው ካልን መልሱ “የአስተሳሰብ
ለውጥ” የሚል ነው፡፡ ሐዋርያው የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች ሲል አእምሮ የሌላችሁ ማለቱ አይደለም፡፡ እየሰማችሁ የማትረዱ፣ እያያችሁ
የማትቀበሉ፣ በተገለጠው እውነት የማታምኑ ማለቱ ነው፡፡
ተግባራዊ ወደሆነው ሕይወታችን ስንመጣ የገላትያ አዚም በግልጥ
ይስተዋላል፡፡ አዚም መፍዘዝንና መደብዘዝን የሚያመለክት ቃል ሲሆን ይህም ከድግምት ኃይል ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ የሥራ ብዛት፣ የጤና
መቃወስ፣ የእድሜ ሕፃንነት ያመጣው መንፈሳዊ ችግር ሳይሆን እግዚአብሔር በልጁ የሠራውን ማዳን ባለማስተዋል፣ ከመንፈሳዊ ጤና ማጣትና
በቃሉ ካለማደግ ጨቅላነት የሚመጣ ድንዛዜ ነው፡፡ ይህም የዚህ ዓለም አምላክ በተባለው ሰይጣን አጋዥነት የሚከወን ድርጊት ነው፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ እንድናስታውሰው ያዘዘን ሞቱንና ውርደቱን ነው፡፡
ምክንያቱም የእኛ ታሪክ መቀየር ያለው እርሱ በመስቀል ላይ ኃጢአታችንን ተሸክሞ የሕግ እርግማን ሆኖ በመሞቱ ነው (ዘዳ.
21÷23)፡፡ እኛ የተዋረድንበትን ቀን ሌሎች አይደሉም እኛው ራሳችን እንኳን ልናስበው አንፈልግም፡፡ ቤታችን ላይ የሚሰቀለው ፎቶ
እንኳ ምቾታችንን የሚያሳየው ተመርጦ ነው፡፡ ከስተን ጠቁረን የተነሣነው የት ነው የሚቀመጠው? ጌታ ግን በእጅና በእግሮቹ ላይ ችንካር
እንዳለፈ፣ ፊቱ ላይ ምራቅ እንደተተፋ፣ ራሱ ላይ የእሾህ አክሊል እንደደፋ፣ ጀርባው በጅራፍ እንደተገረፈ፣ በየሸንጎው እንደተንገላታ፣
እርጥብ እንጨት ተሸክሞ ተራራው ላይ ደፋ ቀና እንዳለ አስቡት ሲል አላፈረም፡፡
ለጠፋው መልካችን መልክ የሆነን ባየነው ጊዜ እንወድደው ዘንድ
ደምግባት የለውም ተብሎለት ነው (ኢሳ. 53÷2)፡፡ የተናቀ ከሰውም የተጠላ የሕማም ሰው ደዌንም የሚያውቅ ስለ መተላለፋችን የቆሰለ
ስለ በደላችን የደቀቀ እርሱ ነው፡፡ ከመስቀሉ ጋር የተያያዘው ሕይወት ሕይወቱን ለእኛ አሳልፎ የሰጠው ጌታ ነው፡፡ የምናከብረውም
እንደ ወንበዴ የተሰቀለልንን ፃድቅ ክርስቶስን ነው፡፡ በኃጢአት ምክንያት ያጣነው መልካችን ጽድቅ፣ ቅድስና እና እውቀት የተመለሰው
ክርስቶስ መልክ ሆኖልን ነው፡፡ እርሱ ደምግባት የለውም ቢባልለትም መልካችን ነውና አናፍርበትም፡፡ በመልኩ የሚያፍር የለምና፡፡
በኃጢአት ምክንያት በእኛና በእግዚአብሔር መካከል የነበረው የጥል
ግድግዳ (ኤፌ. 2÷14) የፈረሰው እርሱን እግዚአብሔር በእምነት የሚገኝ በደሙም የሆነ ማስተስሪያ አድርጎ ስላቆመው ነው (ሮሜ.
3÷25)፡፡ ሁላችንም እንደሚገባን በሁለት ሰዎች መሐል ለረጅም ጊዜ ጸብ ቆሞ ከነበረ የሚፈርሰው እርቅ በመካከላቸው ሲቆም ነው፡፡
አለዚያ ቦታው ባዶ ሊሆን አይችልም፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት ያገኘነው በልጁ በክርስቶስ ክርስቲያን በሆንበት መታወቅ ነው፡፡
ሁላችንም ዳግም የእግዚአብሔር የሆነው በልጁ በክርስቶስ ቤዛነት በኩል ነው፡፡ ስለዚህም ክርስቶስ መታወቂያችን ነው፡፡ ታዲያ ልጁ
የሌለው ሕይወት የለውም ቢባል ምን ይደንቃል?
ዳሩ ግን ይህንን ሁሉ የእግዚአብሔር ባለ ጠግነት እንዳናስተውል ደግሞም ለእውነቱ
እንዳንታዘዝ በኑሮአችን ውስጥ ልዩ ልዩ አዚም ጋርዶን ይስተዋላል፡፡ ሐዋርያው በፊታችሁ እንደተሰቀለ ሆኖ ይላል፡፡ እለት እለት
በፊታችን እናስተውለው ዘንድ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ያደረገልን ውለታ በግልጥ ተስሏል፡፡ የእግዚአብሔር ውለታ ደግሞ ወቅት እየጠበቅን
የምንዘክረው ሳይሆን በየጊዜው የምናከብረውና ልባችን ላይ ትልቁን ስፍራ የያዘ ሐቅ ሊሆን አግባብ ነው፡፡
እርሱ ስለ እኛ በመስቀል ላይ እንዴት ራሱን እንዳዋረደ ስናስተውል
ክብሬ ብለን አንሟገትም፡፡ እርሱ ሕማማችንን እንዴት እንደተሸከመ ስናስተውል ሕመማችንን ቆጥረን አንማረርም፡፡ እርሱ በመከራ እንዴት
እንደደቀቀ ስንረዳ የሰዎች ማሳዘን፣ የኑሮ ውጣ ውረድ፣ የሕይወት ፈተናችን ሁሉ ይፈወሳል፡፡ ተወዳጆች ሆይ የተሰቀለውን እዩ! ደግሞም
ስላደረገው ሁሉ ልባዊ በሆነ መንገድ ስሙን አክብሩ፡፡ በገላትያ ምእመናን ላይ የተስተዋለው አዚም ግን ለዘላለም አይግዛን!!