Tuesday, September 18, 2012

የተወጋ ሲረሳ (ክፍል አራት)


                    
“ዮፍታሔም የገለዓድን ሽማግሌዎች፡- የጠላችሁኝ ከአባቴም ቤት ያሳደዳችሁኝ እናንተ አይደላችሁምን? አሁን በተጨነቃችሁ ጊዜ ለምን ወደ እኔ መጣችሁ? አላቸው” (መ. መሳ. 11÷7)፡፡
        ተስፋ መቁረጥ ማለት ከጨለማ ቀጥሎ ብርሃን፣ ከመጨነቅ ቀጥሎ ሰላም፣ ከድካም ቀጥሎ ድል፣ ከርሀብ ቀጥሎ ጥጋብ፣ ከስደት ቀጥሎ እረፍት እንደሚመጣ አለማስተዋል ነው፡፡ የጠሉን እንደጠሉን፣ ያሳደዱን እንዳሳደዱን፣ የናቁን እንደናቁን፣ ያሳዘኑን እንዳስነቡን፣ ያስቸገረን እንዳማረረን አለመቀጠሉ ለመኖር የምንናፍቅበት ጥቂቱ ምክንያታችን ነው፡፡ ያስጨነቁን አንድ ቀን ይጨነቃሉ፣ ያሳደዱን አንድ ቀን ይሰደዳሉ፣ ያስቸገሩን አንድ ቀን ይቸገራሉ፡፡ ያን ጊዜ እኛን እግዚአብሔር መፍትሔ ያደርገናል፡፡ ያስከፉን ተከፍተው ይመጣሉ፡፡ ያን ጊዜ እኛ መጽናናት ነን፡፡ ያቆሰሉን ታመው ይመጣሉ፡፡ ያን ጊዜ መፈለግንም ማድረግንም በእኛ ከሚሠራው ጌታ የተነሣ ፈውስ ነን፡፡ የነቢዩ የዳዊት ታላቅ ወንድም ኤልያብ ዳዊትን እንደ ችግር ቢቆጥረውም እግዚአብሔር ግን እርሱን ለእስራኤል መፍትሔ አድርጎት ነበር (1 ሳሙ. 17÷28)፡፡  
        የዮፍታሔ ሕይወት ተወግቶ መርሳትን፣ ተበድሎ መማርን፣ ተንቆ ማክበርን የምንማርበት ነው፡፡ የልዩ ሴት ልጅ መሆኑ በአባቱ ቤት ካለው ሀብት እንዳይካፈል አደረገው፡፡ ከዚህም በላይ ከአካባቢው እንዲሰደድ ሆነ፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ ከአንድ አባት በተወለዱ ወንድሞቹ ነው፡፡ እንዲህ ያለው መወጋት ሕመሙ ምን ያህል እንደሆነ በዚህ ያለፉ ሁሉ አይስቱትም፡፡ የሰው ፊት ለጠቆረብን፣ ጥላቻቸው እንደ ሳማ ቅጠል ለሚለበልበን፣ ወድደን መከዳት፣ ፈልገን መገፋት፣ ተጠንቅቀን መረሳት ለገጠመን ይህም ዘመን አልፎ የመወደድ ጊዜ ይመጣልና በዚህ ቃል ተጽናኑ፡፡
        የመጣል ዘመን አልፎ የመፈለግ ጊዜ ይመጣል፡፡ ገፍተው ያባረሩን ለምነው ይገናኙናል፡፡ አዋርደው የሰደዱን አክብረው ይቀበሉናል፡፡ በዮፍታሔ የሆነው ልክ እንደዚህ ነው! ከአባቱ ቤት ያሳደዱት፣ ከጋለሞታ ሴት በመወለዱ የናቁት፣ በእግዚአብሔር ዘንድ ያለውን ሞገስ ሳያስተውሉ ቁሳዊውን ነገር የከለከሉት ሰዎች የዮፍታሔን ጽናትና ኃይል የሚፈልጉበትና የሚያስተውሉበት ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ እግዚአብሔር ሲገልጠን የትኛውም የሰው አሳብ ሊሸፍነን አይችልም፡፡ ጸጋው በድካማችን ይገለጣልና በዚህ እንመካለን፡፡
        ለሰው ከባዱ ነገር መጠበቅ ነው፡፡ በተለይ በጭንቀትና በብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ እያለፍን የእግዚአብሔርን ምላሽ በእምነት መታገስ ጭንቅ ይሆንብናል፡፡ በማርቆስ ወንጌል ምእራፍ አምስት ላይ ኢያኢሮስ የተባለ የምኩራብ አለቃ ልጁ ታማበት ጌታ እንዲፈውስለት ተማጸነው በመንገድም ሳሉ አሥራ ሁለት ዓመት ደም የሚፈስሳት ሴት ጌታን አዘገየችው፡፡ ኢየሱስም ቆመ! የነካውም ማን እንደሆነ ጠየቀ፡፡ እንዲህ ያለው ሁኔታ የአለቃውን እምነት ምን ያህል እንደሚፈትነው አስቡ፡፡ በቤቱ ውስጥ በሞትና በሕይወት መካከል ያለች ልጁን እያሰበ በተመሳሳይ ሁኔታ ደግሞ ጌታን ቆሞ መጠበቅ ነበረበት፡፡ ይህ ምንኛ የሚያስደንቅ እምነት ነው?
          ከቤቱ ሰዎች መርዶ ይዘው ሲመጡ እርሱ ያመነ እንጂ የፈራ አልነበረም፡፡ ክርስቶስ እስኪመጣ ድረስ ታሪካችን በበደልና በኃጢአት ምክንያት የዘላለም ሙታን የሚል ነበር፡፡ በየትኛውም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የምናልፈው እርሱ በአስቸጋሪ ሁኔታዎቻችን ላይ በኃይልና በብርታት እስኪገለጥ ድረስ ነው፡፡ የሚያምኑ ሁሉ የሚያስመካውን ጌታ ታምነው ይጠብቁታል፡፡ ጨለማ ቢያስፈራችሁ እርሱ የማይጠፋ ብርሃን ነው፡፡ የእንጀራ ዋስትና ቢያሻችሁ እርሱ የሕይወት እንጀራ ነው፡፡ መከዳት ቢሰብራችሁ እርሱ የእስከ መጨረሻ ወዳጅ ነው፡፡ የጠላት ፍላፃ ቢከብባችሁ እርሱ የማይደፈር የበጎች በር ነው፡፡ የሞት ጣር ቢያስጨንቃችሁ እርሱ ትንሣኤና ሕይወት ነው፡፡ በእርግጥም ጌታ ለሚጠብቁት ከግምት በላይ ይሠራል፡፡ በእኛም ሕይወት ጌታ ከዚህ በላይ ይሠራል፡፡ በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ የእርሱን አሠራርና ጊዜ በጽናት መጠበቅን መለማመድ ይኖርብናል፡፡ ቢዘገይም የእግዚአብሔር ይበልጣል፡፡
          ተወዳጆች ሆይ ከፍርሃቶቻችሁ ጋር ሳይሆን ከተስፋዎቻችሁ ጋር ተወያዩ፡፡ ስለ ሰዎች ማሳደድ ሳይሆን ተቀባይ ስለሆነው የእግዚአብሔር ብርቱ ክንድ አስቡ፡፡ በአጣችሁት ነገር መብሰልሰሉን ትታችሁ በምሕረቱ ባለ ጠጋ የሆነውን ጌታ ታመኑት፡፡ አስተዋይ ሰው በፊቱ ያለውን መከራ ሳይሆን በልቡ ያለውን ራዕይ እየተከተለ በትዕግስት ይጓዛል፡፡ ተስፋ የሕይወት ዘመናችን ብቸኛው ወዳጅ ነው፡፡ የሚበልጠው ተስፋችን ደግሞ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው!
          በፈተና ውስጥ ስትሆኑ ከሁሉም ነገር በላይ የልባችሁን ሰላም ጠብቁ፡፡ ከማንኛውም ሀብት ይልቅ የከበረ ነውና፡፡ ዛሬ ያጣነው ነገር ነገ በተሻለ ይኖረን ይሆናል፡፡ ዛሬ ራሳችንን ከከሰርን ግን ነገ ባዶአችንን ነን፡፡ ስለዚህ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር ስጡ፡፡ ሰዎች ከሚበድሉን በላይ እኛ በደሉን በማሰላሰል የምንከፍለው ዋጋ ይከፋል፡፡ ለራሳችንና ለሌሎች ምሕረት ስናደርግ ግን ተወግቶ የመርሳትን በረከት እንለማመዳለን፡፡
          ዮፍታሔ የጠሉት ሰዎች በጠላት እጅ ሲወድቁ “የዘሩትን ይጨዱ” በማለት በተማጽኗቸው ላይ አልጨከነም፡፡ የገዛ ወገኖቹ ወግተውት ቢረሱም እርሱ ግን ተወግቶ አላስታወሰውም፡፡ የእርሱ ወደ ሆነው መጣ÷ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም (ዮሐ. 1÷11) ተብሎ እንደተፃፈ ክርስቶስ በገዛ ወገኖቹ ተቀባይነትን አጥቶአል፡፡ እስከ መስቀል ሞትም አሳድደውታል፡፡ እርሱ የናዝሬቱ ኢየሱስ ቢሆንም በዚያው ልክ ደግሞ የነገሥታት ንጉስ የጌቶችም ጌታ ነው፡፡ መልካም ነገር አይወጣብሽም ከተባለችው ከተማ የመልካምነት ልክ፣ የደግነት ዳርቻ፣ የሕግ ሁሉ ፍፃሜ የሆነው ክርስቶስ ተገኝቶአል፡፡ ከዚህ ጌታ ጽናትና ኃይል መካፈል የሚፈልጉ ሁሉ ነቀፋውን ተሸክመው ዮፍታሔን እንደተከተሉት ምናምንቴ ሰዎች ከሰፈር ውጪ (ከሥጋ አሳብ) እርሱን መከተል አለባቸው፡፡ ተወግቶ መርሳት ቀላል አይደለም፡፡ ግን ደግሞ በዚህ ውስጥ ያለው ትርፍም ቀላል አይደለም፡፡ ለዚህ ያለ ልክ ከፍ ከፍ ያለው፣ ከአለቅነትና ከሥልጣንም ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይ ከዚህና ከሚመጣው ዓለም የሚልቅን ስም የያዘው ጌታ ሕያው ትምህርት ነው፡፡   
                                                              - ይቀጥላል -


1 comment:

  1. ክርስቶስ እስኪመጣ ድረስ ታሪካችን በበደልና በኃጢአት ምክንያት የዘላለም ሙታን የሚል ነበር፡፡ በየትኛውም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የምናልፈው እርሱ በአስቸጋሪ ሁኔታዎቻችን ላይ በኃይልና በብርታት እስኪገለጥ ድረስ ነው፡፡ የሚያምኑ ሁሉ የሚያስመካውን ጌታ ታምነው ይጠብቁታል፡፡ ጨለማ ቢያስፈራችሁ እርሱ የማይጠፋ ብርሃን ነው፡፡ የእንጀራ ዋስትና ቢያሻችሁ እርሱ የሕይወት እንጀራ ነው፡፡ መከዳት ቢሰብራችሁ እርሱ የእስከ መጨረሻ ወዳጅ ነው፡፡ የጠላት ፍላፃ ቢከብባችሁ እርሱ የማይደፈር የበጎች በር ነው፡፡ የሞት ጣር ቢያስጨንቃችሁ እርሱ ትንሣኤና ሕይወት ነው፡፡ በእርግጥም ጌታ ለሚጠብቁት ከግምት በላይ ይሠራል፡፡ በእኛም ሕይወት ጌታ ከዚህ በላይ ይሠራል፡፡ በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ የእርሱን አሠራርና ጊዜ በጽናት መጠበቅን መለማመድ ይኖርብናል፡፡ ቢዘገይም የእግዚአብሔር ይበልጣል፡፡

    ReplyDelete