Tuesday, September 11, 2012

እቅድ በአረቄ


  
         ዘመን የማይቆጠርለት እግዚአብሔር የዘመኖቻችንን ርዝማኔ ወስኖ ለእድሜያችን ዳርቻ አበጅቶ ሁሉን በሚችለው ኃይሉ ፍጥረትን ያኖራል፡፡ ታዲያ ከዘመን ለውጥ ጋር ተያይዞ ሰዎች ኑሮአቸውን ሲፈትሹ የጎደለውን ለመሙላት፣ ያረጀውን ለማደስ፣ የጠመመውን ለማቅናት፣ የሚናፍቁትን ለመያዝ ያለፈውን ገምግመው ለወደፊቱ እቅድ ያወጣሉ፣ ያንንና ይህንን ለመሥራት ይወጥናሉ፡፡ ሰው እንስሳ ስላልሆነ በዘፈቀደ ሊኖር አይችልም፡፡ መብላት መጠጣት፣ መንቃት ማንቀላፋት፣ መውለድ ማሳደግ እግረ መንገድ እንጂ የተፈጠርንበት ብቸኛ ምክንያት አይደለም፡፡ ስለዚህ በእቅድና በዓላማ መኖር እንደ አማኝ መኖር ሳይሆን አንደ ሰው የመኖር ጥበብ ነው፡፡  
         ዘመን ስጦታ ነው፡፡ የምንፎክርበት ሳይሆን የምንሠራበት፣ የምንዝናናበት ሳይሆን የምንዘጋጅበት፣ የምንበድልበት ሳይሆን በንስሐ የምንታጠብበት ነው፡፡ እግዚአብሔር በእድሜ በረከት የሚጎበኘን የሥጋን አሳብ ወደ ፍፃሜ እንድናደርስ ሳይሆን ሥጋን ከነመሻቱ ሰቅለን ስለ በደላችን የሞተውን ደግሞም እኛን ስለማጽደቅ የተነሣውን የእግዚአብሔር ልጅ በማመን የዘላለም ሕይወት እንዲሆንልን ነው፡፡ ዘመንን እግዚአብሔር በእኛ ላይ ካለው ዓላማ አንፃር ማየት መቻል በብዙ ማትረፍ ነው፡፡ ዘመንን እንደ ስጦታ ካሰብነው በየትኛውም ጊዜ ሊወሰድ ይችላል ማለት ነው፡፡ ሙሉ ሥልጣኑም በሰጪው ዘንድ ነው፡፡ ስለዚህ የተሰጠንን ዕድሜ በእግዚአብሔር አሳብ፣ በፍቅር፣ በጤና፣ በይቅርታ፣ በለጋስነት . . . . ልንከባከበው ይገባል፡፡ በእድሜአችን ምሽት ላይ የማናፍርበትን ነገር ለማየት ቀን ሳለ እንደሚገባ ልንሠራና እንደ ታማኝ ሎሌ ልንተጋ ያስፈልገናል፡፡
         በሌላ ጎን የአዲስ አመት መምጣትን ለሞት ከፊት ይልቅ መቅረብ እንደሆነ ልናስተውል ይገባናል፡፡ ሃምሳ ዓመት የሚኖር አንድ ሰው አርባኛ አዲስ አመቱን ቢያከብር የቀረው አሥር ዓመት ይሆናል፡፡ ይህ ሰው በሕይወት ዘመኑ ሊሠራው የሚገባውን በቀልድ ቢያሳልፍ አሥሩ ዓመት ቀልዱን ለማረም እንኳን አይበቃውም ማለት ነው፡፡ ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆኑኝ ሰው እቅድን ከአረቄ ጋር ያያዙ ሰው ናቸው፡፡ ለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የተናገረውን ምክር ይጠቅሳሉ፡፡
          ብዙ ጊዜ የሚስተዋለው ችግር ከራስ አሳብና ፈቃድ ተነሥቶ ወደ እግዚአብሔር ቃል የሚደረግ ጉዞ ላይ ነው፡፡ ምክንያቱም የምናጣቅሰው ሁሉ የራሳችንን አሳብ እንዲደግፍልን በመሻት ስሜት ውስጥ ሆነን ነው፡፡ ይህ ቃሉን ከልባችን ምክር ጋር እንዲስማማ በግድ መጠምዘዝ ነው፡፡ ነገር ግን ከቃሉ ተነሥተን ወደ ራሳችን ሕይወት ብንመለከት እንደ ቃሉ ራሳችንን ማስተካከልና መታዘዝን እናሳያለን፡፡ ለእነዚህ ሰው አረቄ ከሌለ እቅድ የለም፡፡ አዲስ አመት ያለ አረቄ እርሳቸው ጋር ትርጉም የለውም፡፡ ሲጠጡ የማያፈርሱት ጎጂ ነገር፣ የማይገነቡት በጎ ነገር የለም፡፡ ከጠጡ ሰፈራቸው ኒዮርክ፣ መዝናኛቸው ባንኮክ ነው፡፡
         የማይሰጡት ተስፋ፣ ቃል የማይገቡት ነገር የለም፡፡ የድህነት ወሬአቸው እንኳን የሀብትን ያህል ያስፈነድቃል፤ ልክ እንደ አመት በዓል ሆያ ሆዬ ለአንዱ መኪና ለሌላው መርከብ፣ አንዱን ዘፋኝ ሌላውን መሪ፣ አንዱን ዶክተር ሌላውን መሃንዲስ ብቻ የሚሰጡት እንደ ቸርነታቸው ነው፡፡ መመረቅ ከፈለጋችሁ መለኪያ አረቄ በተኮማተሩት እጆቻው ማስያዝ ነው፡፡ ለአሜንታ እንኳን ክፍተት ለምናችሁ ካልሆነ በቀር ፍንክች የለም፡፡ አንዳንዴ እንዲህ ያለውን እቅድ ሳይሰክሩ ቢያቅዱት ኖሮ ብዬ እቆጫለው፡፡ ሲጠጡ ባለ ብዙ ራዕይ ባለ ብዙ ዓላማ፤ ከመለኪያው ሲርቁ ከስካር ሲነቁ ደግሞ ቀልደኛ ነዋሪ ናቸው፡፡ (አንድምታው ቁጭ ሲል ይነፋዋል ሲቆም ይጠፋዋል እንዲል) የአረቄ ዕቅድ ይሏችኋል እንግዲህ ይህ ነው!
         ለብዙ ሰው አዲስ ዓመት ከእቅድ አንፃር ብቻ ሳይሆን ከመጠጣት፣ ከመልበስ፣ ከዝሙት እንዲሁም ከብዙ ምድራዊ ክፉ ነገሮች ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ለመኖር ብቻ ሳይሆን ለማጥፋትም ይታቀዳል፡፡ አዲስ ዓመትን ሕሊናዊ ከሆነ ነገር ጋር እንጂ ቁሳዊ ከሆነ ነገር ጋር ማያያዝ ትርፉ በጣም ትንሽ ነው፡፡ እኛም ልክ እንደ ዳዊት “በጎ ዘመንን ለማየት የሚወድድ ማነው?” (መዝ. 33÷12) ብልን እንጠይቅና በጎ ዘመንን ለማየት፡-
1. ላለፈው ስህተት ይቅርታ ማድረግ፡- አብሮን መሻገር የሌለበት ነገር ቢኖር በደል ነው፡፡ እኛ በሰው ላይ የሠራነውን ይቅርታ በመጠየቅ፣ ሌሎች በእኛ ላይ ላደረጉብን ደግሞ ይቅርታ በማድረግ እንዲሁም በእግዚአብሐር ላይ ላሳየነው አመጽ ንስሐ በመግባት ያለፈውን የዘመን ምእራፍ በመዝጋት አዲሱን መጀመር ይኖርብናል፡፡ ቤታችንን ስናድስ ቀለም ስንቀባ ቁሻሻውን ስናስወግድ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የሆነው ሰውነታችን ቅድሚያ ሊሰጠውና ሊታለፍ የማይገባው ነው፡፡  
2. እንደ ዘመኑ ሳይሆን እንደ ጌታ አሳብ መኖር፡- በየዘመኑ በኑሮአችን  ውስጥ የምናስተውላቸው በበጎም ይሁን በመጥፎ ለየት ያሉ ነገሮች አሉ፡፡ የሩጫ ሰሞን ሁሉም ለሩጫ በሚሆን መንገድ ትጥቁን አሟልቶ ሲሮጥ፣ የኳስ ወቅት ደግሞ ሁሉም መንደሩን በኳስ ሲያጥለቀልቀው ደግሞ ጊዜው የዘፈን እንደሆነ ሲታሰብ ሁሉም ሲያንጎራጉር እናስተውላለን፡፡ ብዙ ሰው እንደ ዘመኑ መኖርን ቋሚ የሕይወት መመሪያው አድርጓል፡፡ ሲሞቅ ሞቅ፣ ለብ ሲል ለብ፣ ሲቀዘቅዝ ደግሞ ቅዝቅዝ ማለት ለብዙኃኑ አልከበደም፡፡ ዘመንን በጎ ለማድረግ ግን በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ እንደ እግዚአብሔር አሳብ መኖርን መለማመድ ያስፈልጋል፡፡
3. ተግባራዊ መሆን፡- በጎ ቃል ለመናገር ከምናሳየው ትጋት በበለጠ የተናገርነውን ተግባራዊ ለማድረግ ቆራጥነት ማሳየት ይኖርብናል፡፡ ሕይወት ጥልቅ ትርጉም ስለምትጠይቅ እያንዳንዱ ሰው በእድሜው ሁሉ ዓላማዬ ምንድነው? ማለት አለበት፡፡ ስለዚህ አስተዋይና ጥበበኛ ሰው በሕይወቱ ሊያሳካው የሚፈልገው ዓላማ ይኖረዋል፡፡ ነገር ግን መፈለግ ብቻውን በቂ አይሆንም፡፡ ተግባራዊ መሆንም ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ምድር ላይ ሕይወት በጣም አጭር ናት፡፡ ቀኖቻችንን በማለም ብቻ ልናሳልፋቸው አግባብ አይደለም፡፡ ስለዚህ አጫጭር እቅዶቻችሁን ከረጅም ጊዜ ዓላማዎቻችሁ ጋር ለማዛመድ ሞክሩ፡፡ ሕይወት እናስተውላትና ሙሉ ትኩረታችንን እንሰጣት ዘንድ ከእግዚአብሔር የተቀበልናት አጭር፣ ውድና ድንቅ ስጦታ ናት፡፡ ስጦታ ደግሞ የተቀባዩን እንክብካቤና ትኩረት ይሻል፡፡ አማኝ፣ ብልህ፣ አስተዋይና ንቁ ሰው ደግሞ ዘመኑን ሙሉ ተግባራዊ ነው፡፡ በዘመን በረከት የተቀበለን ለእርሱ ዘመን የማይቆጠርለት ጌታ ስሙ ብሩክ ይሁን!
          

No comments:

Post a Comment