Tuesday, September 4, 2012

የተወጋ ሲረሳ (ክፍል ሦስት)


                
“ . . . . ዮፍታሔን፡- የልዩ ሴት ልጅ ነህና በአባታችን ቤት አትወርስም ብለው አሳደዱት፡፡ ዮፍታሔም ከወንድሞቹ ፊት ሸሽቶ በጦብ ምድር ተቀመጠ ምናምንቴዎችም ሰዎች ተሰብስበው ዮፍታሔን ተከተሉት” (መ. መሳ. 11÷2)፡፡
          በድህነት ውስጥ ባለጠግነት፣ በመዋረድ ውስጥ ክብረት፣ በመሰደድ ውስጥ ዕረፍት እንዳለ ማመን ለአብዛኛው የሰው ልብ ከባድ ነው፡፡ ነገር ግን በልቶ ጠጥቶ መራብ መጠማት፣ ለብሶ አንቀላፍቶ ሥጋት እርዛት ካለ፤ እየተራቡ መጥገብ፣ እየተጠሙ መርካት፣ እየተሰደዱ ማረፍ፣ እየተዋረዱ መክበር፣ እየሞቱም መኖር እንዳለ እናስተውላለን፡፡ በእምነት ስንኖር በመከራ ውስጥ ምቾትን የምናስተውልበት ኃይል እናገኛለን፡፡ በዮፍታሔ ሕይወት ውስጥ የምናየው ነገር ይህንን ይመስላል፡፡ የልዩ ሴት (የጋለሞታ) ልጅ ቢሆንም ነገር ግን ጽኑዕ ኃያል ሰውም ነበረ፡፡
          ሐዋርያው “ያልታወቁ ስንባል የታወቅን ነን፣ የምንሞት ስንመስል እነሆ ሕያዋን ነን፣ የተቀጣን ስንሆን አንገደልም፣ ሀዘንተኞች ስንሆን ዘወትር ደስ ይለናል፣ ድሆች ስንሆን ብዙዎችን ባለጠጎች እናደርጋለን፣ አንዳች የሌለን ስንሆን ሁሉ የእኛ ነው (2 ቆሮ. 6÷9)” እንዳለ ክርስትና በምድራዊው ልደት የምንብራራበት ሳይሆን በመንፈሳዊው ልጅነታችን የምንታይበት ኃይል ነው፡፡ በሰው ዘንድ አለመታወቅ ቢሆንም በሰማያዊው ስፍራ በሕይወት መዝገብ ላይ ስማችን ተጽፎአል፡፡ በሥጋ ከሚሆንብን ልዩ ልዩ መከራ የተነሣ ቀኑን ሁሉ ብንገደልም ነገር ግን ሕያዋን ነን፣ በሰው ፊት ዘወትር ሀዘን ቢከበንም በእግዚአብሔር ፊት ካለን መጽናናት የተነሣ ግን ሁል ጊዜ በጌታ ደስ ይለናል፡፡ በድህነታችን ውስጥ ለሌሎች የሚተርፍ ባለጠግነት አለ፣ አንዳች እንደሌለን ብንኖርም ሁሉ ግን የእኛ ነው፡፡
          ዮፍታሔ በሰው ፊት ያለውን እሳቤ ስንመለከት “የጋለሞታ ሴት ልጅ” ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ዘንድ የነበረውን ምስክርነት ስንመለከት ደግሞ “ጽኑዕ ኃያል ሰው” ነበር፡፡ ምን ጊዜም ከራስ ጋር ጸብ የሚጀመረው ሰውና ልባችን ከሚነግረን ነገር ጋር ስንቆም ነው፡፡ እግዚአብሔር ከሚለው ጋር መስማማት ሲኖረን ግን ልካችንን የምናስተውልበት እድል ይኖረናል፡፡ ሰዎች የሚሉን፣ የሚያስታውሱን እንዲሁም እኛን የሚዳኙበት መንገድ ልባችንን የሚያደማ፣ ዓይናችንን የሚያስነባ ሊሆን ይችላል፡፡ ዳሩ ግን መቼም ቢሆን እግዚአብሔር ፊት ጌታ እግዚአብሔር ስለ ኢዮብ የሚናገረው እንጂ የሰይጣን ክስና ሙግት ልክ አይሆንም (ኢዮ. 1÷6)፡፡ የሚወራው ሁሉ እውነት አይደለም! እግዚአብሔር ያለው ግን የሰውን ልክ ይዳኛል፡፡
        ዮፍታሔ የልዩ ሴት ልጅ መሆኑ ከአባቱ ቤት ሊያገኝ የሚገባውን ውርስ አስከለከለው፡፡ ጌታ ከነገድ፣ ከቋንቋ፣ ከወገንና ከሕዝብ ዋጅቶ ለእግዚአብሔር ልጆች አድርጎናልና ወራሾች ነን፡፡ በእርሱ ዘንድ የቤትና የእንጀራ ልጅ የሚባል ልዩነት የለም፡፡ ዮፍታሔ እናቱን መርጦ አካባቢውን ወስኖ አልተወለደም፡፡ ነገር ግን እርሱ መርጦ ባላመጣው መጡበት የገዛ ወንድሞቹም አሳደዱት፡፡ ልክ እንደ እርሱ ሁሉ ሰላምታ የሚያስከለክሉ፣ በጎ ቃል የሚያስነፍጉ ብዙ ጉዳዮችን በኅብረተሰባችን መካከል እንታዘባለን፡፡
        ሰው ከተፈጥሮ በተቀበለው ነገር አይፈረድበትም፡፡ እንደ እውነት ከሆነም የዮፍታሔን ጽኑዕ ኃያልነት የጋለሞታ ሴት ልጅነቱ ሊሸፍነው አይገባም ነበር፡፡ ሰው ግን በሥጋና በደም ማስተዋል ውስጥ ብቻ ሲሆን ከዚህ ተሻግሮ ጽናትና ኃይልን ሊመለከት አይችልም፡፡ የዮፍታሔ ታሪክ ግን የልዩ ሴት ልጅ መሆኑ ብቻ አልነበረም፡፡ እርሱ ጽኑዕ ኃያል ሰውም ነበር፡፡ ስለ ሰዎች የድካም ታሪክ ስንሰማ የምንጠብቀው የበለጠ ድካምን ከሆነ ጨለምተኞች እንሆናለን፡፡ ሰው የኃይልና የጽናት ክፍልም አለው፡፡ ስለወደቀ ስናወራ መነሣትን እያሰብን፣ ስለተቸገረ ስንናገር ማግኘትን እያስተዋልን፣ ስለ ሞት ስንነጋገርም ትንሣኤን እያወጅን ከሆነ ለተስፋ መቁረጥ የእግር እሳት ነን፡፡
        ከጠላትህ አንድ ጊዜ ከወዳጅህ ደግሞ ሺህ ጊዜ ተጠንቀቅ እንደተባለ ሰምተናል እኔ ግን ልጠይቃችሁ “ከወንድምስ” ስንት ጊዜ እንጠንቀቅ? ሰዎች ጭንቅላታቸውን ይዘው፣ አፋቸውን ከፍተው፣ እንባቸውን እየረጩ የልባቸውን በአንደበት ሲጮኹ ምን እንደሆኑ ለመስማት ጓጉተን ስንጠጋቸው የወንድም ባዳ፣ የወገን ምድረ በዳ እንደገጠማቸው አምርረው ያወጉናል፡፡ ዮፍታሔ ወንድሞቹ ናቸው ያሳደዱት፡፡ እርሱም ከፊታቸው ሸሸ!
        ዘመናችንን ስንዋጀው ሰው ከወንድሙ ፊት የሚሸሽበት ነው፡፡ ጌታ ወንድሞች ብሎ ሊጠራን አላፈረምና ወንድምነት ብርቱ ቅርበት ነው (ዕብ. 2÷13)፡፡ ደስታን እንደ ራስ ደስታ መቁጠር ብቻ ሳይሆን መከራንም እንደ ራስ መከራ የመቁጠር ሂደት ነው፡፡ ከሚያዝኑ ጋር የምናዝንበት ከሚደሰቱ ጋር የምንደሰትበት ምክንያትም ሌሎችን እንደ ወንድም መቁጠር ነው፡፡ ለዮፍታሔ ከወንድሞቹ ፊት ይልቅ የጦብ ምድር መሸሸጊያ ነበር፡፡ ወንድም ፊት ለነሳችሁ፣ ወዳጅ ለጎዳችሁ፣ ቀን ለጨለመባችሁ ሁሉን የሚችል ልዑል እግዚአብሔር የሚሸሽግ አምባ የሚያሳድር ጥላ ነው፡፡ እኛ ብንገፋም ጌታ ግን አይገፋም፡፡ እኛ ብንሰደድ እግዚአብሔር አይሰደድም፡፡ እኛ ብንታሠር ቃሉ ግን አይታሰርም (2 ጢሞ. 2÷9)!!
                                              - ይቀጥላል -  

No comments:

Post a Comment