ማክሰኞ ሕዳር 25/2005
የምሕረት ዓመት
በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ከመልካምነት ይልቅ ክፋት ዓለምን እንደገዛ
እናስተውላለን፡፡ አለመታዘዝ ያመጣውን ውድቀት ተከትሎ የሰው ዝንባሌ “የማልወደውን ክፉን ነገር አደርጋለሁና ዳሩ ግን የምወደውን
በጎውን ነገር አላደርገውም” (ሮሜ. 7÷19) ወደሚል ሙግት ገብቶአል፡፡ ከመምረጥ ጀምሮ እስከ ድርጊት ድረስ ሰዎች በብርቱ ይፈተናሉ፡፡
አንዳንድ ጊዜም ከነ አካቴው ሁሉን እርግፍ አድርጎ የመተው ውሳኔ ላይ ይደርሳሉ፡፡ ማለትም በጎም መጥፎም ያለመሆንና ያለማድረግ!
ሰው ግን ከሁለት አንዱን ነው፡፡ ከእነዚህ ራሱን የሚያገልበት ሌላ ሦስተኛ ክልል የለም፡፡ ልክ እንደ አንድ ቀን ሁለት ገጽታ ብርሃንና
ጨለማ ነው፡፡ በብርሃን እንመላለሳለን ወይም በጨለማ እንመላለሳለን፡፡ ክርስትና ግን እንደ ብርሃን ልጆች መመላለስ ነው፡፡ ከክፉ
መራቅ ሰላማችንን የሚጸናበት ዋስትና ነው (ኢሳ. 48÷22)፡፡
በታሪክ ከተነሡ እጅግ ክፉና አምባገነን መሪዎች መካከል አንዱ
ሂትለር ነው፡፡ በየዘመናቱ ብዙ አስጨናቂዎችን ሰዎች ርደውና ተንቀጥቅጠው አስተናግደዋል፡፡ ብዙዎች ሞተው፤ አንዳንዶች ደግሞ አጉል
ነዋሪ ሆነው በዚያ አረመኔያዊ ሥርዓት ውስጥ አልፈዋል፡፡ አንዳንዴ ባለፈው የአገራችን ሥርዓት ውስጥ ጨካኝ የነበሩና የገዛ ጎረቤታቸውን
በቁም የቀበሩ ሰዎች በዚህኛው ሥርዓት ውስጥ ሲሽቆጠቆጡ ስናያቸው የሥርዓቱ ለውጥ ጭካኔያቸውን እንዳዳፈነው እንጂ እንዳጠፋው አይሰማንም፡፡
የዚያ አምባገነናዊነት ግርሻት ያየለበባቸው ደግሞ ለዚህኛው ሥርዓት ተቆርቋሪ መስለው በዚያኛው አመጽ ይገለጣሉ፡፡ እናም ራሳቸውን
ያረካሉ፤ ክፋት ያስገብራልና ዘመን ቢቀያየርም ክፉውን አያስረጀውም፡፡ እግዚአብሔር ግን ይለውጣል!
ለዚህ ጽሑፍ ርዕስ ያደረኩትን ቃል ያገኘሁት ለልቤ እጅግ ቅርብ
ከሆነ አባት (ከአንዱ እግዚአብሔር) ምክር መካከል ነው፡፡ ዘመኑ መካሪም ተመካሪም የሰለቸበት ነው፡፡ ከዚህ ይልቅ ሰው ሁሉ ወደ
ልቡ አሳብ ተጠምዷል፡፡ ምን አልባት “ደግሞ በዚህ ዘመን ምን በጎ መካሪ አለ?” ልትሉ ትችላላችሁ፡፡ ነገር ግን ሰው አያስተውልም
እንጂ እግዚአብሔር በአንድ በሌላም መንገድ ይመክራል፡፡ አንዳንዴ ሳት ብሏቸው እንኳ ጥሩ እንደማይናገሩ ከምናስባቸው ሰዎች ሕይወት
ያለባቸው ቃላት ሲወጡ እናስተውላለን፡፡
እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ ይረግምለት ዘንድ ባላቅ የከፈለበትን
የበልዓም አንደበት መርቆበታል (ዘኁ. 22)፡፡ በእርግጥ ተደላድለን ውሸት ከምንናገር እግዚአብሔር ጠምዝዞን ለእውነት ብንመሰክር
ይበልጣል፡፡ በየአደባባዩ የሚጠፋውን መብል እያሰቡ፣ ሕሊናቸውን አራቁተው ሆዳቸውን እየሞሉ በዚህ ዓለም ከንቱ መለፍለፍ የተጠመዱ
ሁሉ ከበለዓም ስሕተት (ይሁዳ 11) ሊማሩ ያስፈልጋቸዋል፡፡
የስነ ልቦና ባለሙያዎች እንደሚያስረዱት ልጆች እያለን ከቤተሰቦቻችና
ከማኅበረሰቡ ጋር የነበረን ግንኙነት (Attachment) ወደ ማወቅ ደረጃ ከመጣን በኋላ በቀጣይ ኑሮአችን ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ
(በጥሩም በመጥፎም) ያሳድራል፡፡ የአንድ ሰው ክፋት የብቻው ክፋት፣ የአንድ ሰው መልካምነት የብቻው መልካምነት አይደለም የሚል
መከራከሪያ የሚቀርበውም ለዚህ ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የምንመለከተው ወንጀል ተባባሪና አሰልጣኝ ያለው ነው፡፡ በጣም ጨዋ እንደነበሩ
የምናውቃቸውን አልባሌ ቦታ ስናገኛቸው አድራሻ ለመለወጥ ያበቃቸው ክፉ ባልንጀርነት እንደሆነ እናያለን፡፡
ሰውና ሁኔታ ያከፋው ካልሆነ በስተቀር ማንም ክፉ ሆኖ የተፈጠረ
የለም፡፡ ወድጄ መሰለህ እንዲህ ያለ ጠባይ የያዝኩት፣ አመል ያወጣሁት በማለት የሚናገሩ ወገኖች ብዙ ናቸው፡፡ ማንም በጥረት የተበላሸ
የለም፡፡ አንዳንዱ እንጀራ በልቶ ለማደር፣ ሌላው ከሰው ተመሳስሎ ለመኖር፣ አንዳንዱ የእጁን ላለማጣት ብቻ ሁሉም ለከፋበት ምክንያት
ያቀርባል (ምንም እንኳ ምክንያት ባይታደግም ግን እኮ ከፀሐይ በታች ባለው ኑሮ ምክንያተኝነት ስልጣኔ ነው እንጃ እንግዲህ አንዱን
ምረጡ)፡፡
በጭካኔውና በአረመኔነቱ ከምናውቀው ሂትለር ጀርባ ያለውን ታሪክ በአጭሩ
ለመመልከት ብንሞክር፤ እናቱ ክላራ ከእርሷ በ23 ዓመት እድሜ ለሚበልጣት ለአጎቷ የልጅ ልጅ ሦስተኛ ሚስት የነበረች ስትሆን በትዳር
በቆየችባቸው ጊዜያት ሁሉ ባለቤትዋን ትጠራው የነበረው “አጎቴ” እያለች ነበር፡፡ ግንኙነታቸው የተጀመረውም በአጎቷ ቤት በቤት ሠራተኛነት
ታገለግል በነበረበት ጊዜ ነው፡፡ ታዲያ ሂትለር ልጅ እያለ እናቱ ክላራ ብቸኛ ጓደኛው ነበረች፡፡
አስራ ስምንት ዓመት ሲሞላው እናቱ በካንሰር ሞተችበት፡፡ በዚህም
ምክንያት ለከፍተኛ የልብ ስብራትና ለበለጠ ብቸኝነት ተጋለጠ፡፡ አንዳንድ የታሪክ ምሁራን እንደሚያስረዱት ሂትለር በሴሜቲኮች በተለይም
በአይሁዶች ላይ ጥላቻና የበቀል ስሜት ያደረበት የሚወዳት እናቱ አይሁዳዊ በሆነ ዶክተር የተደረገላት ሕክምና ውጤት አልባ በመሆኑ
ነው፡፡ እንግዲህ በግፍና በሰው ሰቆቃ ራሱን ያረካ የነበረው አዶልፍ ሂትለር ወደዚህ የክፋት ጣሪያ የደረሰው በዚህ መንገድ ነው፡፡
እናንተስ እንዴት ታዩታላችሁ?
መልካም የምንሆነው ለራሳችን ብቻ ብለን አይደለም፡፡ ሌሎችንም ከእሳት
ነጥቆ ለማውጣት እውነተኛ መንገድ ስለሆነ ጭምር ነው፡፡ በጎ ነገር ዘር ነው፡፡ ዘር ደግሞ ከተዘራ በኋላ እንደ ዘራነው ልክ አይሆንም፡፡
ስለዚህ በጎነታችንም ሆነ ክፋታችን መሐን ሊሆን አይችልም፡፡ በጎ የዘራችሁ ደስ ይበላችሁ!
- ይቀጥላል -