Friday, January 18, 2013

ከዚህም በላይ ደስታ!



                                     
                       

                                        ቅዳሜ ጥር 11/2005 የምሕረት ዓመት


       ከእያንዳንዱ ሰው ጥረት ጀርባ ያለው ጥልቅ መሻት ደስታ እንደሆነ ሁሉ በእግዚአብሔር አሳብ ውስጥ ያለው ከፍታም ደስታ ነው፡፡ እርሱ በሰው ታሪክ ውስጥ ያዘጋጀው ትልቁ ነገር ደስታ ነው፡፡ እግዚአብሔር ማንንም ለሀዘን፣ ለሮሮረ፣ ለመከራና ስቃይ አልፈጠረም፡፡ ዛሬ የምናልፍበት የተበላሸ ነገር ሁሉ የሰው መበላሸት ውጤት ነው፡፡ ነገር ግን ሰው በየዘመናቱ በራሱ መንገድ ደስታን ሲያስስ ኖሮአል፡፡ የደስታ መገኛ ሀብት እንደሆነ ያሰቡ ሰዎች ለዚህ እስከ መጋደል ኖረዋል፣ የሰላም ምንጩ እውቀት እንደሆነ ያሰቡ ወገኖችም የቻሉትን ያህል ለመጠበብ ሞክረዋል፣ ደስታ የሚገኘው ሥልጣን በመያዝ እንደሆነ የተሰማቸው ሰዎችም ለዚህ ታምነው ኖረው አልፈዋል፡፡ ሁሉም በየተሰማራበት ተግባር ለመደሰት ዘወትር ይሻል፡፡

       ደስታን ስለ መፈለግ ስናስብ የጠቢቡ ሰሎሞንን ፍለጋ እናስታውሳለን፡፡ ብዙ ሰው ዝና ቢኖረው የማይቸገር፣ ሀብት ቢኖረው የማይርበው፣ ሥልጣን ቢኖረው የማያዝን ይመስለዋል፡፡ ከእነዚህ አንዱ እንኳ ቢኖረን እንባዎች ሁሉ ከአይኖቻችን እንደሚታበሱ እናስባለን፡፡ ዳሩ ግን ጠቢቡ ሰሎሞን እነዚህን ሁሉ ነገሮች በአንድነት ጠቅልሎ የያዘ ንጉሥ ነበር፡፡

       ኢትዮጵያዊቷ ንግሥተ ሳባ ዝናና ጥበቡን ሰምታ፣ ብዙ ጓዝና እጅ መንሻ ይዛ፣ ቀይ ባህርን አቋርጣ ነፍስ እስከማይቀርላት ድረስ የልቧን ሁሉ የገለጠችለት የእስራኤል ገዥ ነበር(1ነገ. 10÷1-10)፡፡ ለክብሩ የማይንበረከክና በጥበቡ የማይደመም ያልነበረለት ሰሎሞን የሕይወት ትርጉም የጠፋበት የደስታ አድራሻ ግር ያለው ሰው ነበር፡፡ መጽሐፈ መክብብ ምዕራፍ ሁለትን በመንፈስ ሆነን ስናጠና ጥበበኛው እንዴት ባለ ድካምና ጥረት ውስጥ እንዳለፈ የፍለጋውንም ከንቱነት እናስተውላለን፡፡


1. ልቡን በደስታ ፈተነው፡- ጠቢቡ በምሳሌው መጽሐፍ ውስጥ ከነገረን ቃል ጋር “ልጄ ሆይ ልብህን ስጠኝ አይኖችህም መንገዴን ይውደዱ” ሲጣላ እናየዋለን፡፡ ልቡን ራስን በመግዛት ደግሞም የእግዚአብሔር የሆነውን ነገር በማድረግ ሳይሆን መልካም መስሎ የታየውን በፊቱ በመፈጸም ባከበረው አምላክ ፊት እንደ ልቡ ተመላለሰ፡፡ ልባችን የምንፈትንባቸው ልዩ ልዩ ደስታዎች በኑሮአችን ውስጥ ይፈራረቃሉ፡፡ አንዱ ውስጥ ያጣነውን ሌላው ውስጥ እንፈልጋለን፡፡ ደስታ አልባ ከሆነው ነገር ወደ ሌላ ደስታ አልባ ነገር እንገላበጣለን፡፡ ጥበበኛው ልቡን ያስደስታሉ ላላቸው ነገሮች ሁሉ ልቡን ሰጠ፡፡ ዳሩ ግን

ውጤት፡- የከንቱ ከንቱ

2. ልቡን በሳቅ ፈተነው፡- ጥርስ ለማኘክ ብቻ እንደተፈጠረ ልናስብ እንደማንችል ሁሉ ጥርስ መሳቁ እውነተኛ ደስታ ነው ማለትም አንችልም፡፡ ሲናደዱ የሚስቁ፣ እየሳቁ ጉድ የሚያደርጉ ብዙ ሰዎችን ልናገኝ እንችላለን፡፡ ጠቢቡ በመሳቅ ውስጥ ያለውን ደስታና የሕይወት ትርጉም መረመረ፡፡ እንደ ሀብቱና እንደ ሥልጣኑ ሲስቅ ውሎ ሲስቅ ሊያድር እንደሚችል ልንገምት እንችላለን፡፡ ብዙ አስቂኝ የተባሉ ባለ ብዙ ቀልደኞችን ፊቱ ሊያቆም አልያም ሎሌዎቹ ሲኮረኩሩት አድረው ሊውሉ ኃይሉ ነበረው፡፡ በአጫዋች የሚንቀሳቀሱ፣ በብዙ አሻንጉሊት የተከበቡ፣ የቤታቸው መደርደሪያ በቀልድ ካሴት የተጨናነቀ ወገኖች ጠቢቡን እንዲገናኙት እመክራለሁ፡፡ ሰሎሞን ሆዱን እስኪያመው፣ ናላው እስኪዞር፣ ጥርሶቹ እስኪቆጠሩ ስቋል፡፡ ዳሩ ግን

ውጤት፡- የከንቱ ከንቱ

3. ልቡን በወይን ጠጅና በስንፍና ፈተነው፡- እዚህ ላይ ጥበበኛው በምሳሌው መጽሐፉ በነገረን “ወይን ልብን ደስ ያሰኛል” ነገር ሲያፍር እንመለከተዋለን፡፡ በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ስንፍናን መናገርና ስንፍናን መሥራት ኃጢአት እንደሆነ ተደጋግሞ ተገልጿል፡፡ ጠቢቡ ግን በስንፍና ውስጥ ራሱን አገኘው፡፡ እንደ ባለጠግነቱ ምርጥ የተባለውን የመጠጥ አይነት አስጠምቆ ሊጠጣ ደግሞም ስካር በሚያስከትለው ስንፍና ውስጥ ሊገኝ ይችላል፡፡ እንዲያውም ጠቢቡ ከአህዛብ ጋር እንዲያመነዝር ጉልበት የሰጠው ስካር እንደሆነ ልናስብ እንችላለን፡፡

        የወይን ጠጅ ለሆድ ሕመም መልካምነቱ እንዳለ ሆኖ ለክፋት የግፊት ኃይልነቱ ግን ያይላል፡፡ ብዙ አመጾች በመጠጥ ይታቀዳሉ በመጠጥም ይከወናሉ፡፡ በወይን ጠጅ ብዛት ደስታን ለመሸመት የሚጋፋው ወገናችን ቁጥሩ፤ ከዚህም የተነሣ ጉብዝናቸውን ስንፍና የተጠናወተው የትየለሌ ናቸው፡፡ ጠቢቡ ወይን ጠጅ ውስጥ ጥበቡ ትርጉም አጣበት፡፡ በመጠጥ እየቀዘፈ ከፀሐይ በታች የሰው ልጆች ሊሠሩት መልካም ነገር ምን እንደሆነ እስኪያይ ድረስ የልቡ ጥበብ እየመራው እስከ ቻለው ዞረ፡፡ ወይን ጠጅና ስንፍና ተቀይጠው ጠቢቡን አቀለሉት፡፡ በዚህም ፍለጋው ውስጥ ያለውን ፍሬ ለቀመ፡፡ ዳሩ ግን

ውጤት፡- የከንቱ ከንቱ

4. ልቡን በእጁ ሥራ ፈተነው፡- በጥረት ለማረፍ መሞከር ሰው ውድቀቱ ያመጣለት መፍትሔ ነው፡፡ ምን ጊዜም ኑሮን ከሚያንሻፍፈው ነገር አንዱ የሕይወትን ትርጉም፣ ደስታና ሰላም እጃችን ውስጥ መፈለግ ነው፡፡ ወደ ራሳችን ነገር ዘወር ባልን ቁጥር አለመርካት ፈጥኖ ይከብበናል፡፡ በራስ ብልሃት የእግዚአብሔርን ነገር ለማግኘት ደግሞም ከእርሱ የሆነውን ሁሉ ለመቀበል በፊቱ መጎናበስን ያሳየንባቸው እነዚያ የጨለማ ዘመናት አቅማችንን ለማየት ከበቂ በላይ ናቸው፡፡

          ቃሉ የሰውን ጽድቅ የመርገም ጨርቅ በማለት ይዘጋዋል፡፡ በእርግጥም ሠርቶ የሥጋውን ጥያቄ በአግባቡ መልስ ያልሰጠ ወገን ሠርቶ በነፍሱ ሊጸድቅ መፍጨርጨሩ እግዚአብሔር ባቆመው ጽድቅ ላይ እንደ መዘባበት ነው፡፡ ጠቢቡ በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ እንዳለችው ገነት በብዙ አትክልትና ፍራ ፍሬ የተከበቡ ቤቶችን ሠራ፡፡ በብዙ ወርቅና የከበሩ ድንጋዮች የተሽቆጠቆጡ ቤቶችን አቆመ፡፡ ደግሞም አትክልቶቹን የሚያጠጣበት የውኃ ማጠራቀሚያ አደረገ፡፡ በእያንዳንዱ ዛፍና በሕንፃው ውበት መሐል የቻለውን ያህል ተመላለሰ፡፡ በዚህ ውስጥ ያለውንም ምቾት አጣጣመ፡፡ ዳሩ ግን

ውጤት፡- የከንቱ ከንቱ

5. ልቡን በመብል ፈተነው፡- ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ አለመግባባት ያሳየው በመብል መሆኑን ስናስብ የሁል ጊዜ መደመም ይሞላናል፡፡ ዛሬም ሰው ከሰው ጋር ላለው መለያየትና መባላት ጥልቅ ምክንያቱ መብል (ጥቅም) ነው፡፡ እውነትና ወንጌል እየተገፉ የሚኖሩትም ለሆዳቸው ባደሩ ወገኖች ምክንያት ነው፡፡ ወንድም ከወንድሙ፣ አባት ከልጁ፣ ባልንጀራ ከወዳጁ ጋር ሆድና ጀርባ የሚሆንበት መንገድ ለሕሊና ቀርቶ ለሆድ ማደር ነው፡፡ ወደ ጠቢቡ ስንመጣ ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎችን እንደገዛ ደግሞም ብዙ የከብት መንጋዎች እንደነበሩት ይነግረናል፡፡

         በአገልግሎት ያገኘናት አንዲት ሴት በጭንቀት ተይዛ ሥራ መሥራት፣ እንደ ልቧ መውጣትና መግባት ባለመቻሏ ልንጠይቃት ሄድን፡፡ ወደ ቤቱ እንደደረስን በዘበኛ ቤት ተከፈተልን፡፡ ወደ ውስጥ እንደዘለቅን ወደ እልፍኝ የሚያደርሰን ሌላ አንድ ወጣት መጣና እጅ ነሥቶን ወደ ፊት መራን፡፡ የታሰሩ ድልብ ውሾች ድምጽ እያጀበን ወደ ፊት መራመድ ያዝን፡፡ ወደ ዋናው ቤት እንደዘለቅን ሌላ የደንብ ልብስ የለበሰ ዘበኛ ተመለከትን፡፡ ወደ ዋናው ቤት ገብተን ባለፍንባቸው አብዛኛውን ክፍሎች ውስጥ ባይሠሩ እንኳ የቆሙ የቤት ሠራተኞችን፣ ወንዶችና ሴቶች አገልጋዮችን እንዲሁም በእያንዳንዱ በር ላይ ያሉትን ትላልቅ ቁልፎች ብዛት ተመልክተን ተገረምን፡፡

         ይመራን የነበረው ወጣት ለአንዲት ሴት “ወደ ሳሎን አስገቢያቸው” ብሎ ትእዛዝ በመስጠት በመጀመሪያው እጅ መንሣት  ተሰናበተን፡፡ እኛም እንዲህ የተቀባበሉን “አክብረውን ነው” ብለን ራሳችንን ለመሸንገል ሞከርን፡፡ ልንጠይቃት የሄድንላትን ሴት ስናገኛት ግን ልባችን አዘነ፡፡ ዙሪያዋን ወዳጆች ከብበው ሊያዝናኗት ይሞክራሉ፡፡ ፊትዋ ትልቅ እስክሪን አፍጥጦ ቻናል እየተቀያየረ ፊልም ያማርጧታል፡፡ ልዩ ልዩ የምግብ አይነት ገበታውን ሞልቶታል፡፡ “እባክሽ ከዚህች እንኳ ቅመሽ” የሚል ማባበያ በየደቂቃው ልዩነት እናት ይናገራሉ፡፡ ልጅቱ ግን ፍንክች አላለችም፡፡ እኛም “እግዚአብሔር ይክበብሽ” ብለን መርቀን ወጣን፡፡ ተወዳጆች ሆይ እግዚአብሔር ይክበባችሁ!

         ጠቢቡ ሰሎሞን ብዙ ሎሌዎችና የቤት ውሉድ ባሪያዎች ከብበውት ነበር፡፡ በወጣ በገባ ቁጥር “ንጉሥ ሺ ዓመት ንገስ” እያሉ የሚጎናበሱ፣ ራበን ሳይሆን አይራብህ፣ ከፋን ሳይሆን አይክፋህ፣ ስማን ሳይሆን የልብህን ተናገረን የሚሉት ባሪያዎች ቤተ መንግሥቱን ሞልተው ነበር፡፡ ከእርሱ በፊት በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሁሉ ይልቅ ብዙ ከብቶች ስለነበሩት ከሥጋቸው ወስደው እንዳሻው ሊያሰናዱለት ይችሉ ነበር፡፡ ጥበበኛውም ቢፈልግ ከጥሬው፣ ቢፈልግ ደግሞ ከብስሉ ይበላል፡፡ በቀን ሦስቴ ጊዜ ሳይሆን በቀን ሃያ አራቴ ጊዜ ቢበላ ከልካይ የለበትም፡፡ ጥበበኛው በባሪያዎች ተከብቦ፣ በከብቶች መንጋ መሐል ተገኝቶ ደስታና እርካታን ፈለገ፡፡ ዳሩ ግን

ውጤት፡- የከንቱ ከንቱ

6. ልቡን በሴቶችና በአዝማሪዎች ፈተነው፡- አሁን ደግሞ ጥበበኛው በአዝማሪና በሴቶች ብዛት ሲከበብ እናየዋለን፡፡ አዝማሪዎቹ ስሙን እየጠሩ፣ ገድሉን እየተረኩ ያሞጋግሱታል፡፡ ምናልባትም በምድር በብዙ ባለጠጋ ስለነበር በሰማዩ ነገር የሚሸነግሉት ይመስለኛል፡፡ ዙፋኑን እንደ እግዚአብሔር ዙፋን፣ ክብሩን እንደ እግዚአብሔር ክብር፣ ግዛቱን እንደ እግዚአብሔር ግዛት . . . . አዝማሪ የእናንተ ኪስ ባዶ አይሁን እንጂ እንደ ገበሬ ክምር ሲቆልላችሁ አድሮ ሲቆልላችሁ ይውላል፡፡ ጥቁሩን እንደ ፀሐይ የሚያበራ፣ አጭሩን መለሎ፣ ቀጭኑንም ወፍራም ሊያደርገው ይችላል፡፡ ልክ እንደ ልጆቹ ሆያ ሆዬ፡፡ ሰሎሞን ስፍራውን ከእግዚአብሔር ሳይሆን ከአዝማሪ ሰማ፡፡ በአዝማሪዎች ብዛት ውስጥ የሚፈልገውን ደስታ ለማጣጣም ሞከረ፡፡

           ጠቢቡ ሚስትና እቁባቶቹ በጠቅላላ ቁጥራቸው ወደ አንድ ሺ እንደሚጠጋ እናውቃለን፡፡ ለንጉሥ እንደመሆናቸው ከነሙሉ ክብራቸው ተመልምለው እንደመጡለት ልናስ እንችላለን (አስቴር ለንጉሱ አርጤክስስ እንደተመለመለችው)፡፡ ከአንዷ ውበት ወደ ሌላዋ ውበት፣ ከአንዲቱ ወደ ሌላይቱ ይፋጠናል፡፡ ሲከብቡት አድረው ሲከብቡት ይውላሉ (እንዴት ይጨንቃል)፡፡ የአህዛብ ሴቶች ሳይቀር ሚስት ሆነውለት ነበር፡፡ የአዝማሪዎች ሽንገላና የሴቶች ውበት ተደማምረው የጠቢቡን ልብ ፈተኑት፡፡ አይኖቹን ማየት ከፈለጉት ሁሉ፣ ጆሮዎቹንም መስማት ከፈለጉት ሁሉ፣ እጆቹን መሥራት ከፈለጉት ሁሉ፣ እግሮቹንም መድረስ ከፈለጉት ሁሉ አልከለከላቸውም፡፡ በዚህ ውስጥ ያለውንም ደስታ ተጎነጨ፡፡ ዳሩ ግን


ውጤት፡- እነሆ ሁሉ ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነበር÷ ከፀሐይ በታችም ትርፍ አልነበረም!

         ጠቢቡ ልቡን ከደስታ ሁሉ አላራቀም፡፡ ከድካሙም ሁሉ ይህ እድል ፈንታው ሆነ፡፡ እጁ የሠራቻቸውን ሁሉ የደከመበትንም ድካሙን ሁሉ ተመለከተ፡፡ የፍለጋውንም መጨረሻ አስተዋለ፡፡ የከንቱ ከንቱ ሁሉም ከንቱ ነበር፡፡ በእርግጥም የሰው መንገድ ከዚህ ያለፈ ትርፍ ሊያመጣ አቅም የለውም፡፡ አዳምና ሄዋን ከእግዚአብሔር ቁጣ ለማምለጥ በገዛ እጃቸው የሰፉት ቅጠል እንዳላዋጣቸው ደግሞም ያሰቡትን ሰላም እንዳላመጣላቸው እናያለን (ዘፍ. 3)፡፡ እግዚአብሔር ግን አዘነላቸው፡፡ የቁርበት ልብስም አለበሳቸው፡፡ እግዚአብሔር በሰው ጥረት መሐል ስላቆመው መፍትሔ ሲናገር “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” (ማቴ. 3÷17) አለ፡፡ ሐዋርያው ደግሞ “እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ” (ኤፌ. 4÷24) ይለናል፡፡

         መጥምቁ ዮሐንስ “የዓለሙን ሁሉ ኃጢአት የሚያስተሰርይ የእግዚአብሔር በግ” ብሎ ያስተዋወቀውን ጌታ አብ ደግሞ “ደስታዬ” ብሎ ነገረን፡፡ በግ ለመሥዋዕት የሚቀርብ እንደመሆኑ አብን ደስ ያሰኘው መሥዋዕት ልጁ ነው፡፡ ወደ አብ ይህንን መሥዋዕት ይዞ የማይቀርብ ሁሉ አብን በእውነትና በመንፈስ ሊያመልከው ደግሞም ደስ ሊያሰኘው አይችልም፡፡ አብና መንፈስ ቅዱስ በአንድነት የመሰከሩለት ደስታ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ሰው ይህንን ገፍቶ በምንም ደስ ሊሰኝ አይችልም፡፡

        ጌታ ከሰሎሞን ፍለጋ የሚልቅ ፍለጋ እንዳለ ሲነግረን “ከሰሎሞን የሚበልጥ ከዚህ አለ” ይለናል፡፡ የጠቢቡ ፍለጋ ሁሉን በከንቱ ዘግቶታል፡፡ በክርስቶስ ግን ሁሉ አዲስ ሆኗል፡፡ መዳናችንም የተከናወነው ከፀሐይ በታች ነው፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ የሰው ልጅ ሆኖ ከዘላለም ሞት በደሙ ዋጀን፡፡ ንግሥተ ሳባ ነፍስ እስከማይቀርላት ድረስ የልቧን ለሰሎሞን አጫውታዋለች፡፡ እርሱም እንቆቅልሿን ፈትቶ ደስ አሰኝቷታል፡፡ እንዲህ የምናነብለት ሰሎሞን ግን ደስታና የሕይወት ትርጉም የጠፋው ይህንንም ከፀሐይ በታች ለማግኘት የዳከረ ነበር፡፡ ጠቢቡ ሁሉን የከንቱ ከንቱ ያደረገበት ደስታን ከፀሐይ በታች መፈለጉ ነው፡፡ ከፀሐይ በላይ ግን አብ ደስታዬ ያለው ደስታ ምድር ላይ ተገልጦአል፡፡ የትኛውም የሕይወት እንቆቅልሽ በእርሱ ይፈታል፡፡ ከእርሱ የሚያልፍ ጥበብ፣ እርሱን የሚሻገር እውቀት፣ ከእርሱም ባለፈ እረፍት የለም፡፡ ሁሉ እዚህ ጌታ ጋር ሲደርስ ታሪክ ይጠቀለላል (ኤፌ. 1÷10)፡፡

        ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ደስታ በፃፈው የፊልጵስዩስ መጽሐፍ “ሁል ጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ÷ ደስ ይበላችሁ” (ፊል. 4÷4) ይላል፡፡ ሐዋርያው “ደግሜ” ያለውን ቃል ማስተዋል ተገቢ ነው፡፡ ስለ ሌላ ደስታ ከጠየቃችሁኝ፣ ስለ አማራጭ ደስታ ከጠየቃችሁኝ ደግሜም የምላችሁ ደስታ “ጌታ ነው” እያለ ነው፡፡ ሰው ወደ አንድ ቦታ ለመድረስ በዚህ መንገድ ባይመቸው በዚያ መንገድ ሊሄድ ይችላል፡፡ የእግዚአብሔርን መንግሥት በተመለከተ ግን የግዴታ (በክርስቶስ) እንጂ የአማራጭ ጉዳይ አይደለም፡፡ በእውነትም በእግዚአብሔር የሚያምኑ ሁሉ ደስ የሚሰኙት እግዚአብሔርን ደስ በሚያሰኘው ነገር ነው፡፡ እርሱ ደግሞ ደስ የተሰኘው በልጁ ነው፡፡ በልጁ ያላመነ የዘላለም ሕይወት እንደማይኖረው ሁሉ ያለዚህም እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ደስታ ነው፡፡ አብ ደስ በተሰኘበት ደስ አለመሰኘት በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ላይ መበደል ነው፡፡

       በዚህ ዓለም የአንዱ ደስታ ለሌላው ሀዘን፣ የአንዱ እረፍት ለሌላው መባዘን፣ የአንዱ ምቾት ሌላውን ይቆረቁራል፡፡ ልቦች ሁሉ ከእውነተኛ ደስታ ርቀው በቆሙበት በዚህ ዘመን ደስታችን የአብ ደስታ ነው፡፡ ጌታ ሰውን ከእግዚአብሔር፣ ሰውን ከሰው ያስታረቀ ደስታ ነው፡፡ ክርስቶስ ከድቅድቅ ጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ በፍቅር የጠራን ደስታ ነው፡፡ እርሱ የቤተክርስቲያን መሠረት፣ የማዕዘን ድንጋይና ጉልላት የሆነ ደስታ ነው፡፡ ኢየሱስ በበደላችንና በኃጢአታችን ሙታን ከነበርንበት ታሪክ የታደገን ደስታ ነው፡፡ ስለ በደላችን የደቀቀ፣ ስለ ጽድቃችን ከሙታን መካከል ተለይቶ የተነሣ ደስታ ነው፡፡ ወልደ እግዚአብሔር ስፍራን ሊያዘጋጅልን የሄደ፣ ወዳዘጋጀልንም ስፍራ ሊወስደን ዳግም የሚመለስ ደስታ ነው፡፡ ጌታ የተናቁትን ሊያከብር የተዋረደ ደስታ ነው፡፡ እርሱ ጥበበኛ ደሀ፣ ባለ ርስት መፃተኛ፣ የተገፋ እውነት፣ በስተ ውጪ የሚያንኳኳ የሕይወት ደስታ ነው፡፡ እንባዎች ሁሉ ከአይን የሚታበሱበት ብቸኛው ደስታችን የእግዚአብሔር ልጅ ነው፡፡ ተወዳጆች ሆይ ከዚህም በላይ ደስታ የለም!!! 
    

2 comments:

  1. ርስቶስ ከድቅድቅ ጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ በፍቅር የጠራን ደስታ ነው፡፡ እርሱ የቤተክርስቲያን መሠረት፣ የማዕዘን ድንጋይና ጉልላት የሆነ ደስታ ነው፡፡ ኢየሱስ በበደላችንና በኃጢአታችን ሙታን ከነበርንበት ታሪክ የታደገን ደስታ ነው፡፡ ስለ በደላችን የደቀቀ፣ ስለ ጽድቃችን ከሙታን መካከል ተለይቶ የተነሣ ደስታ ነው፡፡ ወልደ እግዚአብሔር ስፍራን ሊያዘጋጅልን የሄደ፣ ወዳዘጋጀልንም ስፍራ ሊወስደን ዳግም የሚመለስ ደስታ ነው፡፡ ጌታ የተናቁትን ሊያከብር የተዋረደ ደስታ ነው፡፡ እርሱ ጥበበኛ ደሀ፣ ባለ ርስት መፃተኛ፣ የተገፋ እውነት፣ በስተ ውጪ የሚያንኳኳ የሕይወት ደስታ ነው፡፡ እንባዎች ሁሉ ከአይን የሚታበሱበት ብቸኛው ደስታችን የእግዚአብሔር ልጅ ነው፡፡ ተወዳጆች ሆይ ከዚህም በላይ ደስታ የለም!!!

    ReplyDelete
  2. ewinet new kersu belay desta yelem! enbawoch hulu ke ayin yemitabesubet bichegnaw destachin ye Egziabher lij new! kezihm belay desta yelem!

    ReplyDelete