Tuesday, May 8, 2012

ልበ ሰፊ


ለአንድ ክርስቲያን ልበ ሰፊ መሆን በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡ ልብ የሰውነትን፣ የአእምሮንና የስነ ልቡናን ክፍሎች የሚያመለክት እንደመሆኑ ሙሉ እኛነታችንን የሚገዛና የሚቆጣጠር ነው፡፡ ስለዚህ የአእምሮና የአሳብ፣ የስሜትና የፈቃድ እንብርት የሆነው ልባችን ሰፊ መሆን ይኖርበታል፡፡ የምንኖርበት ዓለም ለጥላቻ ምክንያት በሌላቸው፣ እንዲሁ ስመለከትህ ክፉ ትመስለኛለህ፣ ሳይህ ታስጠላኛለህ በሚሉ፣ ሰውን በሆነው ማንነቱ ሳይሆን ገና በይሆናል በሚጸየፉ የተከበበች ናት፡፡ የወደደ የሚጠላባት፣ የገፋ የሚያፈቅርባት፣ ያነባ ስቆ የሳቀ የሚያምጥባት፣ ያጣ አግኝቶ የጠገበ የሚራብባት ይችው የምንኖርባት ምድር ናት፡፡ ታዲያ የኑሮ ትግል ሲበረታ፣ እንደ እግዚአብሔር ያልሆነው ነገር ሲያይል፣ ነውር እንደ ክብር ዓመጽ እንደ ጽድቅ ሲቆጠር፣ ከስቃይ ወደ ባሰ ስቃይ መገላበጥ ሲበዛ፣ በጉድ ነግቶ በጉድ ሲመሽ ልበ ሰፊ መሆን በእጅጉ ያስፈልጋል፡፡ ኑሮን በአግባቡ ለመኖር፣ በሕይወት ውስጥ አመዛዛኝ ለመሆን፣ ከቅድም አሁን ከትላንት ዛሬ በተሻለ ለማደግ፣ ከራስ አልፎ ለሌሎች ለመትረፍ፣ በማዕበል ውስጥ ፀጥታን ለመተንፈስ አሳበ ሰፊነት በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡  

ዓለም አመጣሽ ለሆነው አዲስ ነገር የማይደነቅ፣ ለጥላቻ የማይበቀል፣ ሁሉን በፍቅር የሚያይ፣ ሰው ተስፋ የቆረጠበትን የሚታገሥ፣ ሁሉን ከሰጪው እግዚአብሔር የሚጠብቅ፣ ለመስማት የፈጠነ ለመናገር የዘገየ፣ ለፍርድ የማይቸኩል ለማቅናት የሚተጋ፣ በሁሉ የሚያመሰግን ልበ ሰፊ የሆነው ማንነት ነው፡፡ ሁላችንም እንደምንረዳው የጠላት ዲያብሎስ ዘመቻ፣ የኑሮው ፍላፃ ሁሉ የሚያነጣጥረው ልባችን ላይ ነው፡፡(ምሳ. 4÷23) በዓለም ትልቁ መቅደስ ንጹሕ ልብ ነው (2ቆሮ. 6÷16) እንደሚባል የእግዚአብሔርም ናፍቆት፣ የዓይኑም ማረፊያ ልባችን ነው፡፡ ጉዳት የሚጠነክረውም ከልባችን ሲጀምር ነው፡፡ ከልብ የጀመረውን እግዚአብሔር ካልተቆጣጠረው የሥጋና የደም ምክር አይቆጣጠረውም፡፡ በተለያየ ሁኔታ ውስጥ ሆነን ጥላቻን በአግባቡ ለማስተናገድ ልበ ሰፊነት ትልቅ መፍትሔ ነው፡፡ ልበ ሰፊ (አሳበ ሰፊ) በሆነ ሰው ሕይወት ውስጥ በዋናነት ሁለት ባሕርያትን እናያለን፡፡
1. የተዘጋጀ ነው
ያለ ዝግጅት ደስታም መርዶ ነው፡፡ በሕይወት ከምናስተናግደው ውጣ ውረድ በላይ ሊመጣ ላለው ነገር አለመዘጋጀታችን ዋጋ ያስከፍለናል፡፡ ክፉውን ለመቋቋም፣ በጎውን ለመፈጸም፣ ሁሉን እንደ እግዚአብሔር ቃል ለማስተናገድ በቂ ዝግጅት የእምነት አንዱ ገጽታ ነው፡፡ ክርስትና በራሱ ለዘላለም ሕይወት ለክርስቶስ ዳግም መምጣት  የምናደርገው ዝግጅት ነው፡፡ ታላቅቅ ከሚባሉት ጀምሮ አነስተኛ እስከሆኑት ተግባራት ድረስ ለሚከሰተው የውጤት ብልሽት ትልቁን ድርሻ የሚይዘው የዝግጅት ማነስ ነው፡፡ ክርስቲያን የልቡናውን ወገብ የታጠቀ፣ ኑሮን በመጠን የሚመራ ነው፡፡ “የልብ መዘጋጀት ከሰው ነው÷ የምላስ መልስ ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው” (ምሳ. 16÷1)፡፡ በክርስትና ዝግጅት የሚገለጽባቸውን ጥቂት ነጥቦች በእግዚአብሔር አጋዥነት በመንፈሱም መሪነት ለመመልከት እንሞክራለን፡፡  
ሀ. ያለማቋረጥ በእግዚአብሔር ላይ መደገፍ
ከእግዚአብሔር ጋር የምንገናኝበት አደባባይ፣ የምንግባባበት ቋንቋ፣ ስጦታውንም የምንቀበልበት እጅ እምነት ነው፡፡ ያላየነውን እግዚአብሔር እንዳየነው፣ ያልዳሰስነውን አምላክ እንዳገኘነው፣ ያልደረስንበትን ተስፋ እንደጨበጥነው የሚያስረግጥ ኃይል ነው፡፡ ያለማቋረጥ በእግዚአብሔር ላይ መደገፍ ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት ጤናማነት የምንፈትሽበት ሂደት ነው፡፡ ትልቅ እምነት ወደ ትልቅ ነጻነት ያመጣል፡፡ ዓለምን የምናሸንፍበት ኃይል ያለውም እምነት ውስጥ ነው፡፡ (1 ዮሐ. 5÷4)

በነቢዩ በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ በምዕራፍ ሦስት ላይ ያለ ማቋረጥ በእግዚአብሔር ላይ ስለ መደገፍ የሚያስረዳንን ታሪክ እናገኛለን፡፡ በባቢሎን ምድር ናቡከደነፆር ይገዛ በነበረበት ዘመን ኢየሩሳሌም ተቃጥላ ሕዝቡ ሲማረክ ሦስት ዕብራውያን ብላቴኖች አብረው እንደተጋዙ እናነባለን፡፡ አገራቸው ሰላም ሳለ በእምነት ያመለኩትን እግዚአብሔር በተሰደዱበት ምድርም ሆነው አመለኩት፡፡ እግዚአብሔር ለስሙ ያሳየነውን ፍቅር ይረሳ ዘንድ አመፀኛ አይደለምና የእነርሱ ባልሆነው አገር ርስት፣ በማያውቁት ንጉሥ ፊት ሞገስ ሆናቸው፡፡ እግዚአብሔር የእርሱ የሆኑትን የትም ያውቃቸዋል፡፡ ያመንበትን ነገር ምቾት የሚያስረሳን፣ መከራ የሚያስጥለን ከሆነ አደጋ ነው፡፡

ናቡከደነፆር ኢየሩሳሌምን ቢያቃጥል፣ ቤተ መቅደሱን ቢያፈርስ፣ ንዋያቱን ቢያወድም ለእግዚአብሔር የነበራቸውን ፍቅር፣ ለእምነታቸው የሚያሳዩትን ቅናት፣ እውነተኛ ኑሮአቸውን ግን ከልብ ከአእምሮአቸው ሊፍቅ ደግሞም በእግዚአብሔር ላይ ከመደገፍ ሊለያቸው አልቻለም፡፡ እነርሱ ቢሰደዱም እግዚአብሔር አይሰደድም፡፡ እነርሱ ቢታሰሩም እምነታቸው ግን አይታሰርም፡፡ እነርሱ በጠላት ቢከበቡም ጌታ ግን አይከበብም፡፡ ዕብራውያኑ በባቢሎን ምድር በዱራ ሜዳ ንጉሡ ባስቆመው ምስል (ጣዖት) ፊት በእግዚአብሔር ላይ የነበራቸውን እምነት ገለጡ፡፡ ከንጉሡ ቁጣ በኋላም ሰባት እጥፍ በሚነደው እሳት ውስጥ “ባያድነን እንኳን” በሚል ፍፁም እምነት የተፈተነ ኑሮአቸውን የማያቋርጥ መታመናቸውን ለእግዚአብሔር አሳዩ፡፡ በእርግጥ ጌታን ያለማቋረጥ እንደገፈው ዘንድ አይገባምን?     

ዓለም ላይ ወደ ሕይወታችን በሚመጣ ማንኛውም አሉታዊ ነገር ሳንሸበር በክርስቶስ ያለን ነፃነት የሚጠበቀው ትልቁ ኃይል እምነት በውስጣችን ሲኖር ነው፡፡ እግዚብሔርን ከተደገፍከው የተደገፍከው እውነተኛ ወዳጅ ነውና ደስ ይበልህ፡፡ (ት. ኢሳ. 26÷4) ተወዳጆች ሆይ እርሱ ጌታ እግዚአብሔር የዘላለም አምባ፣ እውነተኛ ወዳጅ፣ ማረፊያ ጥላ ነውና ለዘላለም እንመነው፡፡ በጉዳት ውስጥ ሆነን የእግዚብሔር እጅ ሲሠራ ማየት እምነት ነውና በወጀብና በአውሎ መንገድ ያለውን ጌታ እንደገፍ፡፡  
“እምነት ማለት ያላየኽውን ማመን ነው፡፡ የዚህም ሽልማቱ ያመንከውን ማየት ነው፡፡”
 /ቅዱስ አውግስጢኖስ/

ለ. በፍቅር መኖር

በዓለም ላይ እጅግ አደገኛው ነገር “ፍቅር አልባ” እምነት ነው፡፡ ክርስትና መሠረቱ ክርስቶስ፣ መገለጫው ፍቅር፣ ግቡም ሰላምና ዕረፍት ነው፡፡ አምነን የምናመልከውን አምላክ የምንገልጥበት አማራጭ የሌለው መንገድ ቢኖር በሥራና በእውነት የተቃኘ ፍቅር ነው፡፡ ቃሉ እንደሚል “በእናንተ ዘንድ ሁሉ በፍቅር ይሁን፡፡” (1ቆሮ. 16÷14) ፍቅር ከሌለው ብዙ ተግባር ይልቅ መውደድ በተሞላ ንግግር እግዚብሔር ይከብራል፡፡ ሁሉ የምትለው ቃል “ቃልና ተግባር” የሚል ፍቺ ይዛለች፡፡ በዚህ መሰረት ሙሉው አሳብ ቃላችሁም ተግባራችሁም በፍቅር ይሁን ማለት ይሆናል፡፡ ለዓለም የሚታየው ትልቁ ምስክርነት የእምነት አቋማችን ሳይሆን መውደድ የተሞላው ሕይወታችን ነው፡፡ (ዮሐ. 13÷35) በእግዚአብሔር ፊትም የምንጋፈጠው ጥያቄ የፍቅር ነው፡፡ (ማቴ. 25÷31-46)

ተወዳጆች ሆይ፡- የእድሜያችንን ሙሉ ክፍል መውደድ ላይ ካዋልነው የትኛውም ሚዛን ላይ አንቀልም፡፡ የመልካምነት መመዘኛው ፍቅር ነውና፡፡ አንባቢው ልብ ይበል! ልበ ሰፊ ሰው በፍቅር የተሞላ ነው፡፡ ለጥላቻም ያለው ምላሽ መውደድ ብቻ ነው፡፡ (ማቴ. 5÷43)
“ንስጥሮስ ሆይ አንተን እወድሃለሁ ትምህርትህን ግን እጠላዋለሁ”
/ቅዱስ ቄርሎስ/  

 ሐ. በደልን መናዘዝ

        አጥፍቶ በድያለሁ ማለት እውነተኛነት ነው፡፡ (ዮሐ. 1÷8) በደላችንን ስንናዘዝ ደግሞ ንስሐ ይባላል፡፡ በድለን ከእግዚአብሔር ይቅርታ የምናገኝበት ብቸኛው መንገድም ይኸው ነው፡፡ ኃጢአታችንን ብንሰውር ልማት አይሆንልንም፡፡ ብንናዘዝባትና ብንተዋት ግን ከሚምር ከእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረትን እናገኛለን፡፡ (ምሳ. 28÷13) እኛ በደለኝነታችንን አምነን ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት መንገድ ንስሐ ሲሆን ኑዛዜያችንን ተቀብሎ እግዚአብሔር ለኃጢአታችን መንፃትን የሚሰጥበት መንገድ ደግሞ ደም ነው፡፡ (1 ዮሐ. 1÷7)

ስለዚህ የሚያውቀውን መተላፋችንን እንዲተውልን ደግመንም ወደእዚያ ጥፋት እንዳንመለስ ጸጋውን እንዲያበዛልን ልባዊ ጸጸትና ሸክምን ይዞ መቅረብ ያስፈልጋል፡፡ መቆሸሽ ካለ መታጠብ ግድ ስለሆነ ንጹሕና የተቀደሰ ኑሮ እንድንኖር ዕለት ዕለት በምሕረቱ ባለ ጸጋ ወደሆነው አምላክ በንስሐ ልንቀርብ ይገባል፡፡ “በብዙኃ ምሕረትከ ደምስስ አበሳነ” በምሕረትህ ብዛት ኃጢአታችንን ደምስስ!

መ. የሕይወት ፀጥታ
ሕይወትን በፀጥታ የማትኖራት ከሆነ አይደለም ከእግዚአብሔር ከደህና ሰውም ሳትገናኝ ትሞታለህ፡፡ የሕይወት ቁምነገሯ፣ የኑሮ ትርፍና ኪሳራ የሚገባን፣ ድምፆች በበዙበት ዓለም መለኮታዊውን የእግዚአብሔር ድምጽ የምንለየው፣ የምንናገረውንና እግዚአብሔር የሚመልስልንን የምናስተውለው በፊቱ ፀጥታና ዕረፍት የሰፈነበት ከሁከትና ከጭንቀት የፀዳ የኑሮ ስርዓት ሲኖረን ነው፡፡ ፀጥታ በሌለበት ሁኔታ መደማመጥና መግባባት እደማይቻል ሁሉ ከፀጥታ የራቀችም ነፍስ የእግዚአብሔርን ፈቃድ መረዳትና ከአሳቡ ጋር መስማማት አትችልም፡፡ እግዚአብሔር የሰላም እንጂ የሁከት አምላክ ስላይደለ በፀጥታ ውስጥ ይናገራል፡፡

ክርስቲያን በፈጠረው ብሎም ባዳነው አምላክ ያረፈ፣ ከጭንቀት የራቀ፣ አሳቡም በዘላለማዊው ሕይወት የተሞላ ነው፡፡ ቃሉ “እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉ” (1ጴጥ.5÷7) ይላል፡፡ ግን ጥለናል ወይ? በአሳብህ ውጥረትህንና ጭንቀትህን ከሕሊናህ ደጃፍ አውጥተህ ጣላቸው፡፡ የሚቀበልህም እጅ በርህ ላይ ተዘርግቶአል፡፡ ቤትህን በእግዚአብሔር ሰላም፣ ሙቀትና ብርሃን ለመሙላት የተዘጋጀህ ሁን፡፡ በተሳሳተ መንገድ የሮጠ የሚደርሰው የተሳሳተ ቦታ ላይ ነው፡፡ ከጉዞአችን ይልቅ አሳሳቢው ጉዳይ መድረሻችን ው፡፡ የሕይወት ፀጥታ የመጣንበትን፣ ያለንበትንና የምንደርስበትን አጥርተን እንድናይ ይረዳናል፡፡ የሕይወትህ ግድግዳ ላይ የተሰቀለውን ማስጠንቀቂያ አንብበኸዋልን “ፀጥታ ይከበር” ይላል፡፡

“በልቤ ውስጥ አንድ ትንሽዬ ክፍል አለች፡፡ በሮችዋ ደስታንና ሀዘንን ለመሰብሰብ በሰፊው የተከፈቱ ናቸው፡፡ ፍቅርም ወደ ውስጧ ይገባል”
 / የልበ ሰፊዎች ንግግር/  
እነዚህ ሁሉ ከላይ የተመለከትናቸው ለልበ ሰፊነት የሚያስፈልጉ ነገሮች እንዲሁም መገለጫ ጠባያት ናቸው፡፡ እግዚብሔርን “በዓለም ላይ ትልቁ ሀብት የት ይገኛል” ስል ጠየኩት፡፡ እርሱም “ታላቅ ልብ (የልብ ስፋት) ካለህ አስቀድመህ አግኝተኸዋል” ሲል መለሰልኝ፡፡ አሜን! 

- ይቀጥላል -


2 comments:

  1. Kale hiwot yasemalin. Egziabher lehulachinm nitsu libonan yadilen!

    ReplyDelete
  2. kale hiwet yasemalen

    ReplyDelete