Wednesday, May 1, 2013

የአብ ቤት ማብራሪያ (ጎጆዬ)


እሮብ ሚያዝያ 23/2005 የምሕረት ዓመት

“. . . በቀን ከሙቀት ለጥላ፤ ከዐውሎ ነፋስና ከዝናብም ለመጠጊያና ለመሸሸጊያ ጎጆ ይሆናል (ኢሳ. 4÷6)”

          የእግዚአብሔር ቃል በማይቋረጥ ዋስትናና በማይታጠፍ ቃል ኪዳን የተሞላ ነው፡፡ በሰው ታሪክ ዋስትናና ቃል ኪዳን ሲከተሉን የሚኖሩ ብርቱ ፍላጎቶቻችን ናቸው፡፡ እግዚአብሔር ከሰው ጋር ያለው ግንኙነት እነዚህን ብርቱ መሻቶች ያሟላ መሆኑ እርሱን የዘላለም መጠጊያ እናደርገው ዘንድ ያስችለናል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምድር ሰው ሆኖ በሰው መካከል በተመላለሰበት ጊዜ ሕሙማን እንደ ተፈወሱ፣ የተራቡ እንደ ጠገቡ፣ የተናቁ ወደ ክብር እንደ መጡ፣ የተጠሉ ኃጢአተኞች ወዳጅ እንዳገኙ፣ የታወሩ ዓይኖች እንዳዩ፣ የደነቆሩ ጆሮዎች እንደ ሰሙ፣ የሰለሉ አካሎች እንደ ተዘረጉ በቅዱሱ መጽሐፍ ውስጥ በግልጥ ተጠቅሷል፡፡ ዳሩ ግን በዚህ ምድር ለማንም መኖሪያ ቤት እንደ ሠራ አልተፃፈም፡፡ ራሱ ጌታ እንኳ ከአእዋፋት ባነሰ ሁኔታ ራሱን የሚያስጠጋበት ቤት የሌለው ሆኖ ነው የተመላለሰው (ማቴ. 8÷20)፡፡

          ሰው ተሰማርቶ መሰብሰብን ሲያስብ ቤትን ያስባል፡፡ ሰው ተከፍቶ ማልቀስ ሲፈልግ ቤቱ ማሳለፍን ይመርጣል፡፡ ደስታውንም ሀዘኑንም “የሚችለኝ ቤቴ ነው” ብሎ ለማሳለፍ በዚያ መሆን ይቀናዋል፡፡ ሰው ቢጥመውም ቢመረውም ዞሮ ዞሮ ቤቱ ይገባል፡፡ ቤቱ በጎም ይቆየው ክፉ ተመልሶ ይመጣል፡፡ ምክንያቱም ቤቱ ነው፡፡ አደባባይ ላይ በብዙ ወዳጅ የተከበበ ሰው፣ ባማሩ ሆቴሎች ሲጋበዝ፣ መናፈሻ ለመናፈሻ ሲዞር፣ አንቱታና ውዳሴ ሲጠግብ የዋለ ሰው ሲመሽ የሚሰበሰበው እንደ አቅሚቲ በሠራት ቤት ውስጥ ነው፡፡ ተማሪ ቤት እያለሁ የቅኔ ክፍለ ጊዜ መምህራችን “ይህ ሁሉ አደባባይ ላይ የምትመለከቱት ዘናጭ መሽቶ ቤቱ ሲገባ ተከትላችሁ ብታዩት አብዛኛው ጭቃ ቤት የሚኖር ነው፡፡ እዚህ “ጦጣ መጀመሪያ የመቀመጫዬን አለች” የሚለው አባባል ስለማይሠራ የአደባባይ ለባሽ፣ የቤት ውስጥ ቀማሽ (ጠግቦ የማያድር) የበረከተበት ነው፡፡ እናም በምታዩት አትወሰዱ ትምህርታችሁን ጠንክራችሁ ተማሩ፡፡” በማለት የመከሩንን አስታውሳለሁ፡፡ ታዲያ እርሳቸው የነገሩን ምን ያህል ትክክል ነው? በማለት አንዳንድ ጥሩ ለብሰዋል ያልናቸውን ሰዎች ሲመሽ ተከትለን ለማረጋገጥ በሞከርንባቸው ጊዜዎች መምህሩ የነገሩን እውነት እንደ ሆነ አመሳክረናል፡፡ በእርግጥም ሰው አደባባይ ላይ ቢያጌጥ ቢደምቅ፣ ቢከበር ቢወደድ መጨረሻው መጠለያው ናት፡፡ ብታዘምም ብትቆምም ቻዩ ያችው ቤቱ ናት፡፡    

          ጌታ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ብዙ ነገር አውርቶአል፡፡ እነርሱም የሕይወት ቃል ባለው በእርሱ ነፍሳቸው ሐሴትን አድርጋለች፡፡ ሥጋቸውም በሚፈፀም ተስፋ አድራለች፡፡ አንድ ጊዜ ግን ልባቸውን የሚያውክ ነገር ገጠማቸው (ዮሐ. 14÷1-7)፡፡ እርሱም ጌታ እንደሚሄድ ሲነግራቸው ነው፡፡ ለሰው ልጅ ከባድ ከሆኑ ነገሮች አንዱ ስንብት ነው፡፡ በተለይ ቁርጥ ሲሆን መለያየት ይከብዳል፡፡ መለያየትን ሊቃውንቱ በሦስት መንገድ ይከፍሉታል፡፡ የመጀመሪያው በቦታ መለያየት ሲሆን በዚህ ውስጥ የመንፈስ አንድነት አለ፡፡ ሁለተኛው መካካድ ሲሆን በዚህ ውስጥ ጠንካራ ቅራኔ አለ፡፡ ሦስተኛው ቀብሮ መመለስ ሲሆን በዚህ ውስጥ ደግሞ ብርቱ ሀዘን አለ፡፡ ጌታ ግን ደቀ መዛሙርቱን “ልባችሁ አይታወክ” በማለት አጽናናቸው፡፡ እርሱ ብቻ ስለ ሰው ልብ ይዞታ ሊናገር ድፍረት አለው፡፡ ሰው ከፊታችንና ከሁኔታችን ነገሮችን ለመፈረጅ ይቸኩላል፡፡ ጌታ ግን የልብ ነው፡፡ እርሱ ሲናገር ከልብ ይጀምራል፡፡  እርሱ ከጥርሳችን ፈገግታ ባለፈ፣ ከልብሳችን ንጽሕና በዘለቀ የተሰወረውን መታወክ ያውቃል፡፡ እርሱ ለአፋችን ቅርብ ሰሚ ሳይሆን ለልባችን የቀረበ አዳማጭ ነው፡፡ ለልባችን መታወክ ቅርብ መጽናኛ ኢየሱስ ነው!

          ደቀ መዛሙርቱ ስለ ልባቸው መታወክ ጌታን አላስረዱትም፡፡ ሊያስረዱትም አይጠበቅባቸውም፡፡ እርሱ ሁሉን የሚያውቅ ነው፡፡ ከእርሱ ማወቅ የተሰወረ ነገር የለም፡፡ የፀጉራችሁ ቁጥር በእርሱ ዘንድ የታወቀ ነው፡፡ ከዓይኑ እይታ ውጪ ሊሆን ማን አቅም አለው? ከማወቁስ ሊሰወር ማን ይቻለዋል? ሁሉን በሚችል በእርሱ ፊት ማን በኃይሉ ይበረታል? ልቦችን ሁሉ እርሱ ያውቃል፡፡ ይህንን እያነበባችሁ በዚህ ሰዓት በልዩ ልዩ ጉዳይ የምትታወኩ ወገኖቼ ሁሉ ጌታ የልባችሁን መታወክ ያርቅላችሁ፡፡ ሰሜን ከምስራቅ እንደሚርቅ ጌታ ጭንቀታችሁን ያርቅ፡፡ ሌላም ትኩረት  ልንሰጠው የሚያስፈልገንን ትምህርት በዚሁ ክፍል ላይ እናገኛለን፡፡ የአብዛኛው ሰው መታወክ ምክንያቱ ምን ሊሆን ይችላል? ለሚለው ጥያቄ ጌታ “በእግዚአብሔር እመኑ፤ በእኔም ደግሞ እመኑ” በማለት ለሁከት የምንጋለጥበትን ትልቅ ምክንያት “የአለማመን ጠንቅ” ይነግረናል፡፡ “እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ፣ ጽድቅን አደረጉ፣ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አገኙ፣ የአንበሶችን አፍ ዘጉ፣ የእሳትን ኃይል አጠፉ፣ ከሰይፍ ስለት አመለጡ፣ ከድካማቸው በረቱ፣ በጦርነት ኃይለኞች ሆኑ፣ የባዕድ ጭፍሮችን አባረሩ (ዕብ. 11÷33)” ተብሎ እንደ ተፃፈ ዓለምን የምናሸንፍበት ኃይል ያለው እምነት (ከእግዚአብሔር ለተወለዱ ብቻ) ውስጥ ነው፡፡ 

1. በእግዚአብሔር እመኑ፡- በእግዚአብሔር ማመን ማለት በአንድነቱና በሦስትነቱ ማመን ነው፡፡ በአካል ሦስትነት በግብር አንድነት የተገለጠ አምላክ እግዚአብሔር እርሱ ብቻ ፈጣሪ እንደ ሆነ በልብ መቀበልና ማመን ነው፡፡ ሁሉን አዋቂነት፣ በሁሉ መገኘትና ሁሉን መቻል የእርሱ ብቻ እንደ ሆነ መረዳትና ማመንም ይገባል፡፡ ልባችን ለዚህ እውነት በተሸነፈበት ዘመን ሁሉ እውነተኛ አማኞች ነን፡፡


2. በእኔም እመኑ፡- ከሦስቱ አካላት ማለትም አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ አንዱ አካል ወልድ ወደ ምድር መጥቶ ሰው መሆኑንና መከራ መስቀልን መቀበሉን  እንዲሁም በክርስቶስ ለእኛ የሆነልንን መረዳትና ማመን ማለት ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተወለደና እንደ ሞተ ብናውቅም ዳሩ ግን የእርሱ መከራ መቀበልና ሞት ለእኛ ያስገኘልን ትርፍ አይገባንም፡፡ እግዚአብሔር የሚጠይቀን ነገር ቢኖር የሚወደውን አንድያ ልጅ በመስጠቱና ልጁ እስከ መስቀል ሞት በመታዘዙ ምን እንደ ሆነልን ማስተዋላችንን ነው፡፡ ሰው በተሰጠው ነገር የሚጠቀመው የተቀበለውን ነገር በተረዳው መጠን ነው፡፡

3. ያለ መታወክ ምስጢር፡-  ምድራችን በብዙ መተራመስ የተሞላች ናት፡፡ ከትላንት ይልቅ ዛሬ የባሰ ሥጋት አለብን፡፡ ከሰው የሚመጣው ምክንያት ጋብ ቢል እንኳ ራሳችን የሁከት ምክንት እየሆነብን ብዙ ተንጠናል፡፡ ተወዳጆች ሆይ እመኑ! በዙሪያችሁ ካለው፣ ከረገጣችሁት ደግሞም ቀና ብላችሁ ከምታስተውሉት በላይ በሙሉ ኃይላችሁ እመኑ! እግዚአብሔር በመልኩ እንደ ምሳሌው የፈጠራችሁ ደግሞም በኃጢአት ምክንያት ለሞት ከተሰጠን በኋላ የልጁን መልክ እንድንመስል አብ እንዴት ባለ ፍቅር ወድዶ በክርስቶስ ሞት እንዳዳነን እመኑ! በለስ ባታፈራ፣ በወይንም ሐረግ ፍሬ ባይገኝ፣ የወይራ ሠራ ቢጎድል፣ እርሾችም መብልን ባይሰወጡ፣ በጎች ከበረቱ ቢጠፉ፣ ላሞችም በጋጡ ውስጥ ባይገኙ እግዚአብሔርን እመኑ! ቀኑ በመዓት መሽቶ በጉድ ቢነጋም ያለመታከት እመኑ!

         ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ስለ ስንብት ያወራበትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እየተነጋገርን ነው፡፡ ጌታ ልባቸው እንዳይታወክ መፍትሔው ምን እንደ ሆነ ከነገራቸው በኋላ ለምን? እና ወዴት? እንደሚሄድ ይነግራቸዋል፡፡ በአባቱ ቤት ብዙ መኖሪያ እንዳለ፣ ሄዶም ስፍራን እንደሚያዘጋጅልን ደግሞም ወዳዘጋጀልን ስፍራ ሊወስደን ዳግም ተመልሶ እንደሚመጣ ልብን በሚያሳርፍ መልኩ ነገራቸው፡፡ በአብ ዘንድ ብዙ መኖሪያ ካለ ጌታ ስፍራን ለእኛ ለምን ያዘጋጃል? የሚለው ጥያቄ ምላሽ የሚያስፈልገው ነገር ነው፡፡ የሰው ዘር በሙሉ ከአዳም የተነሣ ኃጢአትን በማድረጉ ደግሞም ሞት ለሰው ሁሉ ስለ ደረሰ ሰው ባለ መታዘዝ ምክንያት በአብ ዘንድ ካለው ስፍራ ኮበለለ (ስፍራን አጣ)፡፡ ከበደል በኋላ ሰው ዝም ብሎ በአብ ዘንድ ስፋራን የሚያገኝ አልሆነም፡፡ እግዚአብሔርም ለመዳናችን ምክንያት የሆነውን ክርስቶስን እስኪልክልን ድረስ ሰውን ዝም ብሎ አልተቀበለውም፡፡ እግዚአብሔር አሁን አደረገልን የምንለውን ለማድረግ የሰው የኃጢአት ዋጋ ይከፈል ዘንድ ግድ አስፈልጓል፡፡ ያለ መሥዋዕት ሥርየት የለም፡፡

          ከላይ በመግቢያችን ላይ በነቢዩ በኢሳይያስ የተጠቀሰው ጥቅስ እግዚአብሔር ራሱን ለሰው እንደ ጎጆ ያቀረበበት ክፍል ነው፡፡ ከሙቀት ለጥላ፤ ከዐውሎ ነፋስና ከዝናብም ለመጠጊያና ለመሸሸጊያ የሚያሳርፍ ጎጆ ሆኖልን እናየዋለን፡፡ ይህ ምንኛ ድንቅና ልብን በሐሴት የሚሞላ ነገር ነው? እርሱ እግዚአብሔር ራሱን ከሰው ግምት በተለየ መንገድ ከየትኛውም ዓይነት ሁኔታ የምናመልጥበት መኖሪያ አድርጎ አቅርቦልናል፡፡ በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር ራሱን በልዩ ልዩ መንገድ እንደ ገለጠ እናውቃለን፡፡ አርጅቻለሁ መውለድ አልችልም ብሎ በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ለነበረው አብርሃም ራሱን የገለጠለት በኤልሻዳይነቱ ነው፡፡ በእርግጥም አልችልም ላለ ሰው ሁሉን እኔ እችላለሁ ከማለት የተሻለ ምላሽ ምን ሊኖር ይችላል? የራበው ሰው በጆሮው ሳይሆን በሆዱ ነው የሚሰማህ እንደሚባለው ለተራበ ሰው ከመብል የተሻለ ምላሽ ምን ሊሆን ይችላል፡፡ ችግራችሁ የተራራቀ ቢሆንም አንዱ መፍትሔ ግን ለሁላችንም የቀረበ ነው፡፡ ዓይነቱ ቢለያይም መድኃኒታችን ክርስቶስ ነው፡፡

         በአዲስ ኪዳን የራዕይን መጽሐፍ ስናጠና የምናገኛቸውን ሰባት አብያተ ክርስቲያናት ጌታ የሚገናኛቸው ከየአብያተ ክርስቲያናቱ ሁኔታ አንፃር እንደ ሆነ እንረዳለን፡፡ ለምሳሌ የጴርጋሞንን ቤተ ክርስቲያን (ራዕ. 2÷12) ብንመለከት ጌታ ራሱን በሁለት ወገን የተሳለ ስለታም ሠይፍ ያለው አድርጎ ያቀርባል፡፡ እንዲህ ባለ መልኩ ራሱን እንዲገልጥ ምክንያቱ ምን ነበር? ብለን ስንጠይቅ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከዓለም ጋር ጋብቻ እንዳረገች እንመለከታለን፡፡ ቤተ ክርስቲያን ከጴርጋሞን ገጽታ አንፃር ስትታይ ወይም በጴርጋሞን ውድቀት ውስጥ ስትገኝ ሙሽራዋን ወደ ጎን ትታ ዓለምን የወሸመች ሚስት ትሆናለች፡፡ ከዚህም የተነሣ እውነተኛው ሙሽራ ስፍራውን ስለሚነፈግ ሐሰትና ዓመጽ በኃይል ይሠራሉ፡፡ እንግዲህ ጌታ ለዚህች ቤተ ክርስቲያን ከዚህ የተሻለ መፍትሔ አልነበረውም፡፡ ምክንያቱም ፍቺ የሚጸናው ሰማንያ ሲቀደድ ነው፡፡ በሁለት ወገን የተሳለው ሰይፍ (ቃሉ) ደግሞ ከዓለም ይለያል፡፡ ለሙሽራዋም ታማኝ ያደርጋታል፡፡ ዛሬም ጌታ ለዚያ ላለንበት ሁኔታ በሚያስፈልግ መልኩ ራሱን ይገልጣል፡፡  

         እግዚአብሔር ራሱን በተንጣለሉ ሕንፃዎች አልያም ባማሩ ሥፍራዎች አለማቅረቡ ምንኛ ድንቅ ነው? እስቲ በዚህ ዓለም ላይ ባሉ ውብ መኖሪያዎች መካከል ያለችን አንዲት ጎጆ አስቧት? ያላፊ የአግዳሚው ግልምጫ፣ የአፈኛ የኮልታፋው ሽሙጥ፣ የሕፃን የአዋቂው ንቀት . . . . ማን ትኩረት ይሰጣታል? ምን አልባት መኖሯንም ለማስታወስ ብዙዎች ይቸገሩ ይመስለኛል፡፡ ለብዙዎች እግዚአብሔር እንደዚህ ነው፡፡ ከጉብዝናቸው፣ ከሀብታቸው፣ ከማስተዋል ከእውቀታቸው፣ ከሥልጣን ከክብራቸው ያነሰ፤ ሊያስቡት የሚቸግራቸው፡፡ ከየትኛውም መኖሪያ ውበት በላይ የእግዚአብሔር ጎጆነት ውብ ነው፡፡ ከየትኛውም መጠለያ በላይ የእግዚአብሔር መጠጊያነት አስተማማኝ ነው፡፡ ከማንኛውም ስፍራ በላቀ ሁኔታ መኖሪያችን የዘላለም አምላክ ነው (ዘዳ. 33÷7)፡፡  

         እግዚአብሔር ከዚህም በላይ ራሱን በብዙ መልኩ ለእኛ ቅርብ አድርጓል፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ በሌላ ስፍራ “እግዚአብሔር በዚያ የሰፉ ወንዞችና የመስኖ ስፍራ ሆኖ ከእኛ ጋር በግርማ ይሆናል የሚቀዝፉ መርከቦች አይገቡባትም፥ ታላላቆችም መርከቦች አያልፉባትም። እግዚአብሔር ፈራጃችን ነው፥ እግዚአብሔር ሕግን ሰጪያችን ነው፥ እግዚአብሔር ንጉሣችን ነው እርሱ ያድነናል (ኢሳ. 33÷21)” በማለት ልባችንን በመተማመን ይሞላዋል፡፡ እግዚአብሔር እንደ ሰፉ ወንዞች ሆኖ ኑሮአችንን ያጥራል፡፡ ወደ እኛ የሚቀዝፉ ጠላቶች ሁሉ ለምርኮ ይሆናሉ፡፡ ፈራጃችን ጌታ በግርማና በሞገስ ከእኛ ጋር ነው፡፡

         ክርስቶስ ለእኛ ስፍራን የሚያዘጋጅ የሆነው እንዴት ነው? አስተውላችሁ ከሆነ በጎጆ ቤት የማይታጣ ነገር ቢኖር አጎዛ ነው፡፡ አጎዛ ደግሞ አንድ በግ ታርዶ ሥጋና ደሙ ከተወራረደ በኋላ ቆዳውን በማድረቅ ለመቀመጫነትና ለመተኛት ጥቅም ላይ የሚውል ነው፡፡ አንዳንዴ ግድግዳ ላይ ተሰቅሎ ሌላ ጊዜ ደግሞ መደብ ላይ ተነጥፎ ሰዎች ሲገለገሉበት ይስተዋላል፡፡ እኛ በአብ ዘንድ ሥፍራን እንድናገኝ ጌታ ቤዛችን ሆኖአል፡፡ እነሆም የእግዚአብሔር በግ ለእኛ ዕረፍት እንዲሆንልን ታርዷል፡፡ በማመን ክርስቶስ ምትክ ያልሆነለት ሁሉ በአብ ዘንድ ስፍራን ያገኝ ዘንድ አይችልም፡፡ ለሚያምኑ ሁሉ ግን ክርስቶስ ቀዳሚ ሆኖ ወደ አብ ገብቶአል፡፡ እንግዲህ ወንድሞች ሆይ በመረቀልን በአዲስና በሕያው መንገድ ወደ ቅድስት በኢየሱስ ደም በመጋረጃው ማለት በሥጋው በኩል እንድንገባ ድፍረት አለን (ዕብ. 10÷9)፡፡

         ጌታ ስለ መሄዱና ስፍራን ስለማዘጋጀቱ አውርቶ በፈፀመ ጊዜ ቶማስ ጌታ ሆይ፥ ወደምትሄድበት አናውቅም፤ እንዴትስ መንገዱን እናውቃለን? አለው። ኢየሱስም፦ እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም (ዮሐ. 14÷6) በማለት መለሰለት። በአብ ዘንድ ባለው ብዙ መኖሪያ ውስጥ ያለ ኢየሱስ ስፍራን ማግኘት አይቻልም፡፡ እርሱ ወደዚህ ስፍራ የሚያደርስና የሚያገባ መንገድ ነው፡፡ እርሱ እንዲህ ያለውን እረፍት የምንረዳበት እውነት ነው፡፡ እርሱ ለዘላለም በዚህ ስፍራ ላይ የምንኖርበት ሕይወት ነው፡፡ ለጌታ ወደ ምድር የመምጣቱ ብቻ ሳይሆን ወደ ሰማይ የመውጣቱም ርዕስ እኛው ነን፡፡ ነፍሳችን ትባርክህ (መዝ. 103÷)!!   
    

5 comments:

  1. ጌታ ስለ መሄዱና ስፍራን ስለማዘጋጀቱ አውርቶ በፈፀመ ጊዜ ቶማስ ጌታ ሆይ፥ ወደምትሄድበት አናውቅም፤ እንዴትስ መንገዱን እናውቃለን? አለው። ኢየሱስም፦ እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም (ዮሐ. 14÷6) በማለት መለሰለት። በአብ ዘንድ ባለው ብዙ መኖሪያ ውስጥ ያለ ኢየሱስ ስፍራን ማግኘት አይቻልም፡፡ እርሱ ወደዚህ ስፍራ የሚያደርስና የሚያገባ መንገድ ነው፡፡ እርሱ እንዲህ ያለውን እረፍት የምንረዳበት እውነት ነው፡፡ እርሱ ለዘላለም በዚህ ስፍራ ላይ የምንኖርበት ሕይወት ነው፡፡ ለጌታ ወደ ምድር የመምጣቱ ብቻ ሳይሆን ወደ ሰማይ የመውጣቱም ርዕስ እኛው ነን፡፡ ነፍሳችን ትባርክህ (መዝ. 103÷)!!

    ReplyDelete
  2. ክርስቶስ ለእኛ ስፍራን የሚያዘጋጅ የሆነው እንዴት ነው? አስተውላችሁ ከሆነ በጎጆ ቤት የማይታጣ ነገር ቢኖር አጎዛ ነው፡፡

    ReplyDelete
  3. 'kenu bemeat meshito begud binegam yalemetaket emenu"........Amen

    ReplyDelete

  4. Amen nefsachin lezelalem kidus simun tibark! tebareku!

    ReplyDelete