Wednesday, May 29, 2013

እየሆነ ያለው . . . (ክፍል ሁለት)


                                            እሮብ ግንቦት 22/2005 የምሕረት ዓመት

       ተወዳጆች ሆይ እንደምን ለዛሬ ደረሳችሁ? ዛሬ ብዙ ናት፡፡ በእጃችን እንዳሉ ከምናስባቸውና በብዙ ዋጋ ከማይተመኑ ነገሮች ሁሉ በላይ ናት፡፡ ለዛሬ ክብር ያልሰጡ በትላንት እየተጸጸቱ፣ በነገ ደግሞ እየሠጉ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል መዳንን የሚያህል ስጦታ ያኖረው “ዛሬ” ላይ ነው (2 ቆሮ. 6÷2)፡፡ ዛሬ ለምትወዷቸው ፍቅራችሁን፣ ለበደሏችሁ ይቅርታችሁን፣ ለዕለቱ ትጋታችሁን፣ ለሚፈልጓችሁ ቸርነታችሁን የምታሳዩበት ዕድል ነው፡፡ ጌታን ለማመስገን ይህ ምንኛ የላቀ ምክንያታችን ይሆን?

      በፍቅር የምወዳችሁ ሆይ ስለ ዘላለም የሚያወራን እግዚአብሔር ነው፡፡ የዘላለም ወሬም ተግባርም የእርሱ ብቻ ነው፡፡ ሰው እንኳ ተግባሩ ንግግሩም አይጸናም፡፡ ዘመናችን ሰው በሰው ከመቼውም ይልቅ ያዘነበት፣ የተዛዘበበትና ለክፉ የተሰጣጠበት ነው፡፡ ጊዜያዊው ነገር የዘላለም ያህል ተስሎብናል፡፡ ለሚያልፈው እየተጣላን ለቋሚው መሽቶብናል፡፡ እንደ ልባችን የሆኑ ነገሮች የማያፈናፍኑ እሾህና አሜኬላ ሆነውብናል፡፡ እርሱ ጌታ ግን የዘላለም መሠወሪያ ነው፡፡ ስለ ዘላለማዊው መኖሪያ የነገረን የዘላለም መጠጊያችን ነው፡፡ ብዙ ሰው እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ያለው ግንኙነት በሚታየውና በሚያልፈው ነገር ላይ እንደተመሠረተ በተግባር ያስባሉ፡፡ እግዚአብሔር ግን የዘላለም አምላክ ነው፡፡ ምክርና ተግባሩም እንደዚሁ ነው፡፡ እርሱ ለእኛ ያለው አሳብ ጊዜያዊ ቢሆን ሰውን እንደ ሆነ ባሰብነው ነበር፡፡ ዳሩ ግን ለእኛ ያለው አሳብ ዘላለም ነው፡፡ የእርሱ ነገሮች ሁሉ ይህንን ያህል ዋጋ የተሸከሙ ናቸው፡፡

       በጌታ የተወደዳችሁ ሆይ ከሚናፍቃችሁ ልብ ሰላም ይብዛላችሁ፡፡ ዛሬ ዋጋዋ የዘላለምን ያህል እንደ ሆነ ተረድታችሁልኛል ብዬ በጌታ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ዛሬ ጀርባ ላይ ከዘላለም ሞት ወደ ዘላለም ሕይወት ሰዎች ሁሉ የሚሻገሩበት እድል መኖሩ ነው፡፡ እስቲ ደግሞ እግዚአብሔር ከበትሩ ጋር በበጎች መሐል ዱር ያገኘውን ብላቴና ከኑሮአችን ጋር አያይዘን እንማርበት፡፡ ስለ ነቢዩ ዳዊት መጠራትና ለእግዚአብሔር ዓላማ በተግባር ወደ መለየት የመጣበትን መንገድ ብዙዎቻችሁ ወይ ተሰብካችሁ አልያም አንብባችሁ እንደማትስቱት ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ እግዚአብሔር ይህንን ብላቴና በአባቱ መረሳትና በወንድሞቹ ቸል መባል (በሚጠሉት) መሐል ራሱን እንዴት ባለ ሁኔታ በዘይት እንደቀባ ለእናንተ መንገር ለቀባሪው እንደማርዳት ነው፡፡ በመሐል የሚገርመኝ አንድ ነገር አሳቤን ወደ ፊት አላራምድ አለውና ላካፍላችሁ ታዘዝኩት፡፡ ምን መሰላችሁ! ብዙ ጊዜ በየምሕረት አደባባዩ ሰዎችን እልል ስለሚያሰኛቸው አገልግሎት ሳስብ ዳዊትና ጎልያድ፣ ጠጠርና ሰይፍ ይታወሱኛል፡፡


       ብዙ ዘመን ሰዎች ከዳዊት ጋር ወግነው፣ ጎልያድን ጥለው፣ በአንገቱ ላይ ሰይፍ አሳርፈው፣ ተግባሩን በእልልታና ጭብጨባ አጅበው ወደየቤታቸው ሲመለሱ አስተውለናል፡፡ የብዙ ሰው ደስታ ከዚህ የዘለለ አይሆንም፡፡ የመጽሐፍ ቅዱሱ ጎልያድ ስንቴ ሞተ፡፡ የመጽሐፍ ቅዱሱ ዳዊት ስንቴ አሸነፈ፡፡ የእኛ ጎልያድ ግን ተሸክመነው እየዞርን በሕይወት አለ፡፡ ስለ ወደቀ አውርተን ያልወደቀልን ብዙ ነገር እንዳለ ላይመለሱ ያለፉት ዘመናት ምስክር ናቸው፡፡ በወንጌላቱ እንደተተቀሰው “ወደ ጥልቁ” ፈቀቅ ማለት ግን ያስፈልጋል፡፡ ጆሮ ያለው ይስማ!

       አሁን የፊቱ አሳቤ ማለፊያ አግኝቶአል፡፡ ታዲያ የዳዊትን መቀባት ተከትሎ የመጣው መከራና ስደት ነው፡፡ ከቤተሰቦቹ ንቀትን የጠገበ፣ በሳኦል ምድረ በዳ ለምድረ በዳ የተንከራተተ ነበር፡፡ መራብና መጠማት፣ እንቅልፍ ማጣትና እንግልት ነበረበት፡፡ ዳሩ ግን ከእነዚህ ሁሉ ነገሮች በላይ ለዳዊት ትልቁ ነገር መቀባቱ ነበር፡፡ ከመከራው በላይ በራሱ ላይ ያለው ዘይት ዋጋ ነበረው፡፡ ከስደቱ በላይ እግዚአብሔር ልብ ውስጥ የነበረው ስፍራ የላቀ ነበር፡፡ በሕይወት ውስጥ የምናልፍባቸው ውጣ ውረዶች ተደማምረው እግዚአብሔር ለእኛ ካደረገው ጋር አይስተካከሉም፡፡ ቀኖች ሊጨልሙ፣ ደስታ ሊደፈርስ፣ ሰዎች ሊሸሹ፣ ነገሮች ባሰብነው መንገድ ላይሄዱ ይችላሉ፡፡ ከምድሪቱ የጠበቅንባት ቀርቶ ከራሳችን የጠበቅነውን ያህል እንኳ ሚዛን የሚደፋ ኑሮ አልኖርን ይሆናል፡፡ ግን እስቲ ቁጠሩ፡፡ የሆነላችሁን፣ እግዚአብሔር ወደ ሕይወታችሁ ያመጣውን፣ በዙሪያችሁ ካሉ የተቀበላችሁትን . . . ይህ እየሆነ ያለውን የሚያስረሳ የሆነልን ድል ነው፡፡ ተወዳጆች ሆይ ያኔ ነብዩ ዳዊትን ምድረ በዳ ብታገኙትና እየሆነብህ ያለው ምንድነው? ብላችሁ ብትጠይቁት መልሱ ከሆነልኝ አይበልጥም የሚል ነበር፡፡

      እግዚአብሔር እረኛው፣ ማጣት የሌለበት ዋስትናው የሆነለት፣ ለምለም መስክና የዕረፍት ውኃ የከበቡት፣ በጽድቅ መንገድ ምሪትን ያገኘ፣ በሞት ጥላ መካከል እንኳ በሕይወት ያለ ፍርሃት የሚሄድ፣ መጽናናት የከበበው፣ ፊቱ ገበታ የተዘረጋለት፣ ጽዋው የተትረፈረፈ፣ ቸርነትና ምሕረት እድሜውን በሙሉ የተከተሉት ሰው የተደረገለት ባይገባውና ልቡን በምሬት አፉ በስንፍና ቃል ቢሞላ ከዚህ ሰው በላይ ምስኪን ማን ሊሆን ይችላል? የእግዚአብሔር ሰው ዳዊት ግን በረከቶቹን በመቁጠር የሆነበትን ሁሉ በእምነት የታገሰ ነው፡፡ ክርስቲያን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃን የመጣ፣ የጌታን በጎነት ለመመስከር የተመረጠ ትውልድ፣ ጌታን ለማገልገል የንጉሥ ካህናት፣ ከእርሱ ጋር ለመኖር ቅዱስና ለርስቱ የተለየ ሕዝብ ነው (1 ጴጥ. 2÷9)፡፡ ትክክለኛ ስፍራችንን ስንረዳ ትክክለኛ ምስጋና ለእግዚአብሔር ይኖረናል፡፡ በእርግጥም የሆነልን ሲገባን የሆኑብንን መቁጠር እንተዋለን፡፡ እኛስ ልክ እንደ ዳዊት ሁሉ ከሙሽራችን ከክርስቶስ ጋር እስክንነግስ ድረስ በዚህ ዓለም የኤልያብ ጠባይና የሳኦል ቅናት መከራን የምንቀበል አይደለንምን?

                                              . . . ከሆነልን አይበልጥም፡፡

2 comments:

  1. Tsegaw Abezeto yebezalachu. Geta beneger hulu ke'enanet gar yehun. Amennnnnnnnnnnnnnnn

    ReplyDelete
  2. Yetetemahut endezih aynet mekari kal new.
    egziabhar ybarkachu zaran emndnbet, emnwadedbet, mhretemnaregbet, gatan emnamesegnbet yhunln
    Amen!! Egziabhar ykber

    ReplyDelete