መስቀል መደመር ነው፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ ያገኘነውን ሕይወት በፍሬ የምንገልጥበት መንገድ! ከትላንት ዛሬ፤ ከዛሬ ነገ
የተሻለና የበለጠ ሆነን የምንገኝበት ኃይል ነው፡፡ በክርስቶስ ያየነውን ርኅራኄ ለሌሎች የምንገልጥበት በረከት ነው፡፡ ጥልን ከመካከላችን
የምናስወግድበት እርቅ ነው፡፡ በዚህ ዓለም መከራና ፈተና ፊት ትምክህት ነው፡፡ ለምድሪቱ የምናቀርበው መፍትሔ ነው፡፡ እግዚአብሔር
ምን ያህል እንደሰጠን ብቻ ሳይሆን ምን ያህል እንደወደደን የፍቅሩን ብርታት፣ የቃል ኪዳኑን ጽናት፣ የተስፋውን ፍፃሜ የምናይበት
አደባባይ፤ ከምድር ከፍ ከሰማይ ዝቅ ያለ ቃል ኪዳን፣ ዘመንና ኑሮ ለሁለት የተከፈለበት ውለታ፣ ምሕረትና እውነት፣ ጽድቅና ሰላም
የተስማሙበት ማሰሪያ መስቀል (ድመራ) ነው፡፡
የክርስትናውን መልክ ከሚያደበዝዙ ነገሮች መካከል ዋናው በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ የተገለጡትን አሳቦች በትክክል አለመተርጎምና
አለመኖር ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ “የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሹ . . . የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን . . . (ማቴ.
28÷5፣ 1 ቆሮ. 1÷3)” ተብሎ ተጽፏል፡፡ ለሰዎች መሻት ምላሽ የሚሆነው መሻታችን ሳይሆን ትክክለኛውን እርካታ ማቅረባችን ነው፡፡
የክርስቶስ መለያው መስቀል እንደ ሆነ ሁሉ የክርስትናውም መለያ መስቀል ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ስለ ምቾታችን እየተሟገትን የምንኖርበት
ሳይሆን ክርስቶስን በመከራው የምንመስልበትና የመስቀሉን ኃይል በኑሮ የምንመሰክርበት ነው፡፡ ክርስትና ዛሬ ላይ እንዴት እንደደረሰ
ታሪክ ስንመረምር ብዙ እውነተኛ ክርስቲያኖች ዋጋ እየከፈሉ፣ የተሰጣቸውን የወንጌል አደራ በደም ጭምር እየተወጡ፣ በቃልና በኑሮ
እየታመኑ ነው፡፡ በረከት የምንደምረው ነው፡፡ እግዚአብሔር በመስቀሉ በኩል በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ የሠራው ሥራ ከንቱ በሆነችው
ዓለም ፊት የምንቆጥረው ብልጥግናችን ነው፡፡