Wednesday, September 4, 2013

ዘመንሰ ለሊከ ውእቱ


 እሮብ ነሐሴ 29/ 2005 የምሕረት ዓመት
                                                 
        ተስዕለ አሐዱ እምነገሥት ወይቤ 
«እፎ ዘመን ሐለወት
         ወይቤልዎ «ዘመንሰ ለሊከ ውእቱ፤
          እስመ አንተ አሰነይካ ለሊከ ትሴኒ
             ወለእመ አንተ አህሰምካ ለሊከ ተሃስም፡፡
    ዘመንሰ ለሊከ ውእቱ . . . . »

ትርጉም፡-
ከነገሥታት አንዱ ለሊቃውንቱ እንዲህ የሚል ጥያቄ አቀረበላቸው፡-
ዘመን ማለት ምን ማለት ነው?”
ሊቃውንቱም፡- «ዘመን ማለት አንተ ነህ፣
አንተ ጥሩ ከሆንክ ዘመኑ ጥሩ ይሆናል፣
አንተ ክፉ ከሆንክ ዘመኑ ክፉ ይሆናል፡፡
ዘመን ማለት አንተ ነህ . . . »
      
       ጥሩ ዘመን ከተነሣ ጥሩ ሰዎች ይታወሳሉ፡፡ መጥፎ ዘመንም ከተወሳ መጥፎ ሰዎች ይዘከራሉ፡፡ ዘመኑ የትጋት ከሆነ ትጉ ሰዎች ይወደሱበታል፡፡ ዘመኑ የስንፍና ከሆነ ደግሞ ሰነፍ ሰዎች ይወቀሱበታል፡፡ ዘመን ጥሩም ሆነ ክፉ የሚሆነው ከእኛ ምግባር የተነሣ ነው፡፡ ጥሩ ከሆንን ጊዜው ጥሩ ሲሆን መጥፎ ከሆንን ግን ዘመኑ መጥፎ ይሆናል፡፡ ልክ እንደ መስታወት ራሳችሁን ይዛችሁለት ስትቀርቡ እድፉን እድፍ፣ ንጻቱን ንጹህ እንደሚለው ዘመን አደባባይ ነው፡፡ ገዥና ሻጭ፣ ትጉና ሰነፍ፣ አስተዋይና መሃይም፣ ብርቱና ድኩም፣ ዝንጉና ባለ ራዕይ . . . . ለሁሉም የእኩል እድል ዘመን ነው፡፡

ዘመን ሰውን ይመስላል
ሰውም ዘመኑን፡፡    
       ስለ ዘመን ስናስብ በውስጡ ያለው ዋናው ተዋናይ የሰው ልጅ ነው፡፡ ሰው ባይኖር ኖሮ ዘመን ትርጉም ባልኖረው ነበር፡፡ ዘመን ከሰው ጋር፣ ሰውም ከዘመን ጋር የተጣመረ ነውና፡፡ ሰው በዘመን ውስጥ ይኖራል፣ ይንቀሳቀሳል፣ ይሠራል እንዲሁም በዘመን ውስጥ ትውልድ ተክቶ ያልፋል፡፡ ዘመን ልክ እንደ ብእር ጫፍ ነው፡፡ ሰዎች ታሪካቸውን በመልካምም በክፉም በገዛ እጃቸው ይጽፉበታል፡፡ የሚመጣው ትውልድ ወይ ይማርበታል አልያም ባለ ታሪኩ ይወቀስበታል፡፡ ዘመን አይከፋም፡፡ ዘመኑን ግን ሰዎች ያከፉታል፡፡ ዘመን በራሱ በጎ አይሆንም፡፡ ሰዎች ግን ዘመኑን መልካም ያደርጉታል፡፡ እግዚአብሔር የዘመኖቻችን ጌታ ነው፡፡ ከስጦታዎቹ ሁሉ በላይ ለእኛ ጊዜን መስጠቱ ታላቅ ነው፡፡ ከትላንት ዛሬ የተሻለ፣ ከዛሬ ነገ ደግሞ የበለጠ የምናስተውልበትን ዘመን መጨመሩ አምላክ ምንኛ ድንቅ ነው፡፡ የሚዋደዱ ባልንጀሮች እቃ ይዋዋሱ ይሆናል እድሜ ግን አይዋስም፡፡ ሰው አዝኖ የማይረዳን እድሜ ነው፡፡ በእግዚአብሔር እጅ ተሰፍሮ የተሰጠን ነውና፡፡ ስጦታ ተንከባካቢ ይፈልጋል፡፡ ለተሰጠን ነገር እንደ ስጦታው መጠን መመለስ አቅማችን ባይሆንም ከእግዚአብሔር የተቀበልነውን በአግባቡ በመንከባከብ ደስ ልናሰኘው ግን እንችላለን፡፡

         ዘመን በመኖራችን የምንደነቅበት ነው፡፡ መቃብር ከወረዱት ይልቅ ከመቃብር በላይ በሕይወት የቆየነው እንገርማለን፡፡ እኛ በበቂ ምክንያት መኖር የማይገባን ነበርን፡፡ እግዚአብሔርም እኛን ላለማዳንና ይቅር ላለማለት ከበቂ በላይ  ምክንያት አለው ግን ኃይሉን ለማዳን አደረገው፡፡ ከዚህም የተነሣ የምንቆጥረው ዘመን ዓመተ ምህረት፣ ዓመተ ፍቅር፣ ዓመተ ይቅርታ፣ ዓመተ ቡራኬ . . . በማለት ነው፡፡ በተለይ በአዲስ ኪዳን ላለነው ዘመን ትርጉሙ ብዙ ነው፡፡ ደም ፈስሶበታልና! የእግዚአብሔር ልጅ የሰው ልጅ ሆኖበታል፡፡ ለብዙዎች ክብር አንዱ ተዋርዷል፡፡ የጨለማውን ዘመን ከሁለት የከፈለው፣ ዓመተ ኩነኔን በዓመተ ምህረት የተካው፣ በትላንት ስንሠጋ ለነገ ያሰበን ውዳችን ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፡፡  

       ዘመን ያለፈውን አወራርደን በታደሰ ኃይል ወደ ፊት የምንዘረጋበት ነው፡፡ ያለፈው ከያዘን ከሚመጣው ጋር ለመገናኘት እንዘገያለን፡፡  ወደ ፊት የመዘርጋት መርኅ የክርስትናው ቋሚ ተግባር ነው፡፡ ባለፈው ውስጥ ክፉም በጎም አለ፡፡ በሚመጣው ውስጥ ደግም ልትሆኑ የወሰናችሁት አለ፡፡ ባለፈው ውስጥ ትርፍና ኪሳራችሁ አለ፡፡ በሚመጣው ውስጥ ደግሞ የተግባራችሁ ፍሬ አለ፡፡ ልክ እንዳለፈ ውኃ ኃጢአትና በደል ሕሊናን ከሞተ ሥራ በሚያነፃው በኢየሱስ ደም መታጠብ አለበት፡፡ በንስሐ ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ሕብረት ማደስና ወደ ቀደመው ዓመጽ ላለመመለስ ብርታት ማሳየት ይኖርብናል፡፡  

ጊዜን ጊዜ ያስባለው
የሰው ልጅ ነው፡፡

       ጊዜ የሕልውናችን ጥሬ ሀብት ነው፡፡ በአንዲቷ ቀን ውስጥ በፋብሪካ የማይመረቱ፣ ከማንኛውም ሀብት የሚልቁ፣ የትኛውም ሌባ የማይዘርፈውና ለሁሉም ሰው እኩል የሆነ ሃያ አራት ሰዓታት አሉን፡፡ ጊዜ ለጠቢባኑም ሆነ ላልተጠበቡት፣ ለሠራተኛውም ሆነ ለሰነፉት፣ ለተማረም ሆነ ላልተማረው፣ ለታላቅም ሆነ ለታናሽ አንዲት ትርፍ ሰዓት አትለግስም፡፡ ሁሉም ሰው እኩል የሆነ ጊዜ አለው፡፡ ሃያ አራቱ ሰዓታት ለአንዱ አይበዛም፤ ለሌላውም አያንስም፡፡ ታዲያ ልዩነቱ ያለው አጠቃቀሙ ላይ ነው፡፡ የጊዜን ውድነት ተረድቶ እያንዳንዷን ደቂቃ በዋዛ ለማያባክናት፣ እንደ ገንዘብ ሁሉ ጊዜውን በበጀት መልክ ለሚጠቀምባት ጊዜ ታከብረዋለች፡፡ በጊዜያቸው የማይቀልዱ ሁሉ የማያፍሩበትን ኑሮ ኖረው ያልፋሉ፡፡

ይቅር የማይሉንን ሰዓታት ጥቅም ላይ ካዋልናቸው
ሰው እንሆናለን!”

       ጊዜን መግደል ራስን በራስ ማጥፋት (suicide) ነው፡፡ እንዲህ ላለው ስህተታችንም በፍፁም ምሕረት አይደረግልንም፡፡ ምክንያቱም ይቅርታ የማይደረግለት ጥፋት ነውና፡፡ በጊዜ አለመጠቀም ከሞትም ትልቅ ሞት ነው፡፡ የቀብር ስፍራ መቃብር ብቻ አይደለም፡፡ የሚሠራ ሕሊና ይዘው ሳይሠሩበት ለቀሩ ሙታን የገዛ ሥጋቸው መቃብራቸው ነው፡፡ ጊዜያቸውን በከንቱ የሚያባክኑ እነርሱ የሚንቀሳቀሱ ሬሳዎች ናቸው፡፡ ሰነፎች ሕይወታቸውን በቁም ነገር ላይ ማዋል ሲገባቸው ሥራ በመፍታት የሀሜትን መቀነት ታጥቀው የሰውን ሥጋ የሚቆራርጡ ሲሆኑ ብርቱውን በማዛል፣ ደካማውን በመኮነን፣ ሰውን ከሰው ጋር በማጋጨት የተካኑ ናቸው፡፡
       እንደ ጉልቻ በአንድ ቦታ በመቀመጥ ጊዜያቸውን የሚያጠፉ ናቸው፡፡ ጉልቻ እንኳ አይንቀሳቀስ እንጂ የተጣደበትን ነገር በመሸከም ያገለግላል፡፡ ዳሩ ግን እንዲህ ያሉ ሰዎች ተግባራቸው የሚሠራውን ሰው ሥራ ማስፈታትና መንገዱ ላይ እንቅፋት መሆን ነው፡፡ የጊዜ ዋጋ የገባቸው ስንፍናን ለመናገርና ለማድረግ ሰዓት አያባክኑም፡፡

«ትልቁ ቁም ነገር አዲሱ ዓመት ለእኛ የሚያመጣው
ሳይሆን እኛ ለአዲሱ ዓመት የምናመጣው ነው

       ብዙ ሰዎች ሕይወታቸውንና ኑሮአቸውን ከዘመን መለወጥ ጋር ያቆራኙትና እጅና እግራቸውን አጣጥፈው ይሰንፋሉ፡፡ መሥራትን ትተው የዘመንና የቁጥር መለወጥን ዝም ብለው ስለሚጠብቁ ድህነት ሠይፉን መዝዞና ገዝፎ ይመጣባቸዋል፡፡ በሥራ እስካልተዋጉትና እስካልተቋቋሙት ድረስ ቆራርጦ ይጥላቸዋል፡፡ ብዙዎች ከአድማስ ማዶ በመቃኘት ገና ወደ ፊት ጊዜ ሲያገኙ ለመለወጥ ያስባሉ፡፡ ዳሩ ግን ለውጥና ስኬት በቀጠሮ አይመጣም፡፡ ዛሬን ከሌሎች ቀናት ልዩ የሚያደርጋት አንድ እውነት አለ፡፡ እርሱም በእጃችን ላይ ያለች እንቁ መሆኗ ነው፡፡  
       ትናንት ታሪክ ነው፣ ነገም ምስጢር ናት፣ ዛሬ ግን የእግዚአብሔር ስጦታ ናት፡፡ ታዲያ ወደ ሕይወታችን በጸጋ የመጣችውን ዛሬን በአግባቡ ከተጠቀምንባት የተለወጠ ሕይወት፣ የተባረከ ኑሮና የማንቆጭበትን እድሜ እናሳልፋለን፡፡ በሰው መሐል ሰው ሆነን ይህችን ምድር የተቀላቀልንበትን ያንን ቀን አክብረነውና ወድደነው ማለፍ የምንችልበት ኃይል ያለው ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ ዘመን ለፍስሐ!      
-      ይቀጥላል -



1 comment: