Wednesday, September 25, 2013

ድመራ (+)


                        
       መስቀል መደመር ነው፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ ያገኘነውን ሕይወት በፍሬ የምንገልጥበት መንገድ! ከትላንት ዛሬ፤ ከዛሬ ነገ የተሻለና የበለጠ ሆነን የምንገኝበት ኃይል ነው፡፡ በክርስቶስ ያየነውን ርኅራኄ ለሌሎች የምንገልጥበት በረከት ነው፡፡ ጥልን ከመካከላችን የምናስወግድበት እርቅ ነው፡፡ በዚህ ዓለም መከራና ፈተና ፊት ትምክህት ነው፡፡ ለምድሪቱ የምናቀርበው መፍትሔ ነው፡፡ እግዚአብሔር ምን ያህል እንደሰጠን ብቻ ሳይሆን ምን ያህል እንደወደደን የፍቅሩን ብርታት፣ የቃል ኪዳኑን ጽናት፣ የተስፋውን ፍፃሜ የምናይበት አደባባይ፤ ከምድር ከፍ ከሰማይ ዝቅ ያለ ቃል ኪዳን፣ ዘመንና ኑሮ ለሁለት የተከፈለበት ውለታ፣ ምሕረትና እውነት፣ ጽድቅና ሰላም የተስማሙበት ማሰሪያ መስቀል (ድመራ) ነው፡፡

       የክርስትናውን መልክ ከሚያደበዝዙ ነገሮች መካከል ዋናው በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ የተገለጡትን አሳቦች በትክክል አለመተርጎምና አለመኖር ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ “የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሹ . . . የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን . . . (ማቴ. 28÷5፣ 1 ቆሮ. 1÷3)” ተብሎ ተጽፏል፡፡ ለሰዎች መሻት ምላሽ የሚሆነው መሻታችን ሳይሆን ትክክለኛውን እርካታ ማቅረባችን ነው፡፡ የክርስቶስ መለያው መስቀል እንደ ሆነ ሁሉ የክርስትናውም መለያ መስቀል ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ስለ ምቾታችን እየተሟገትን የምንኖርበት ሳይሆን ክርስቶስን በመከራው የምንመስልበትና የመስቀሉን ኃይል በኑሮ የምንመሰክርበት ነው፡፡ ክርስትና ዛሬ ላይ እንዴት እንደደረሰ ታሪክ ስንመረምር ብዙ እውነተኛ ክርስቲያኖች ዋጋ እየከፈሉ፣ የተሰጣቸውን የወንጌል አደራ በደም ጭምር እየተወጡ፣ በቃልና በኑሮ እየታመኑ ነው፡፡ በረከት የምንደምረው ነው፡፡ እግዚአብሔር በመስቀሉ በኩል በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ የሠራው ሥራ ከንቱ በሆነችው ዓለም ፊት የምንቆጥረው ብልጥግናችን ነው፡፡

        ዛሬ በዚህ ቀን ብዙ ክርስቲያኖች የመስቀል በዓል ደመራ (ችቦ) ሊያበሩ ወደ አደባባይ የሚወጡበት ቀን ነው፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ ለምድሪቱ የመጣውን መፍትሔ፣ የዘላለም ተድላ፣ አእምሮን ሁሉ የሚያልፍ ሰላም እንድናስብ ከረዳን ደግሞም የእግዚአብሔር በግ በመስቀሉ መሠዊያ ላይ ስለ እኛ እንዴት የተቃጠለ መሥዋዕት እንደ ሆነልን ውለታውን ካዘከረን በእርግጥም ተጠቅመናል፡፡ ዳሩ ግን ከሥጋ ሞቅታና ፌሽታ ባላለፈ መንገድ እንደ አንድ አጋጣሚ ቆጥረነው  ከተለያየን በእውነት ይህ መደመር አይደለም፤ ብዙ ነገር ከስረናል ማለት ነው፡፡

        አንድ አባት ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ሲያጫውቱኝ “ብዙ ሰው ራዕዩን የሚያቃጥልበት ቀን ነው” አሉኝ፡፡ እኔም ግር ብሎኝ “እንዴት?” የሚል ቀጭን ጥያቄ አቀረብኩላቸው፡፡ “አየህ! አብዛኛው ሰው አዲስ ዓመት መምጣቱን አስመልክቶ አዳዲስ እቅድ፣ ልዩ ልዩ ዓላማና ራዕይ እንዳለው ይለፍፋል፡፡ ታዲያ ልክ የመስቀል በዓል ደርሶ፣ ደመራ ተደምሮ፣ ችቦው ተቀጣጥሎ፣ ደስታና ፌሽታው ተከናውኖ ልክ እንዳለፈ ስለ አዳዲስ ነገር ያወሩህን ሰዎች ባረጀ ነገር ውስጥ ታገኛቸዋለህ፡፡ ስለ ብዙ ዓላማቸው የተረኩልህ ሰዎች አንዱን ማድረግ ተስኖአቸው ታያለህ፡፡ ብቻ የቀደመ ኑሮአቸውን፣ የኮነኑት ታሪካቸውን ሲደግሙት፤ አይጠቅምም! ብለው የጣሉትን ሲያነሡት ልብ ማለት ቀላል ነው፡፡ እኔም ችቦ ሲለኩሱ አብረው ለኩሰውት፣ ደመራው ሲቀጣጠል አብረው አቃጥለውት፣ ወደ ቀኝ ወደ ግራ፣ ወደ ፊት ወደ ኋላ ሲሉ አብረው ከእንጨቱ ጋር ጥለውት፣ አንድ . . ሁለት . . ሲሉ እዚያው እረስተውት ይሆናል በማለት አንተንም ራዕይህን ልታቃጥል ነው ወይ? ብዬ የጠየኩህ፡፡” ብለው አስረዱኝ፡፡


       እኚህን አባት በሕይወት ባይኖሩም ሁሌ ምክራቸውን አስበዋለሁ፡፡ ከዚያም ውስጥ ይህኛው ምክራቸው ልቤን ይነካዋል፡፡ ብዙ ጊዜ አስተውላችሁ ከሆነ እርሳቸው ያሉት በግልጥ ይስተዋላል፡፡ ሰው ሊደምር (አንድም ችቦ ሊለኩስ፣ አንድም መንፈሳዊ ነገር ሊጨምር፣ አንድም . . . ) ወጥቶ እንዴት ሚዛኑን ስቶ፣ የያዘውን ጥሎ፣ ለሥጋው አምሽቶ፣ በየመንገዱ ወድቆ (ሰክሮ)፣ በየአደባባዩ ተዳርቶ፣ ከእውነተኛው ላይ መንትፎ (ሰርቆ)፣ ለአመጽ ተማምሎ፣ ርኩሰት አንሾካሽኮ ይመለሳል? ተወዳጆች ሆይ ለሚሰማ ጥቂት ቃል ብዙ ነው፡፡ እኔም በፍቅር እላችኋለሁ፡- መስቀል መደመር ነው! መልካምነት ጨምሩ፣ ፍቅር ጨምሩ፣ ትእግስት ጨምሩ፣ ርኅራኄ ጨምሩ፣ ይቅርታ ጨምሩ፣ ፆም ጸሎት ጨምሩ፣ ቸርነት ማድረግ ጨምሩ፣ የታመሙትንና የታሰሩትን መጠየቅ ጨምሩ፣ ያዘኑትን ማጽናናት ጨምሩ፣ ወንጌልን መስበክ፣ ለክርስቶስ ዋጋ መክፈል፣ በእውነትና በመንፈስ መኖር ጨምሩሩሩሩሩሩሩሩሩሩሩሩሩሩሩሩሩሩሩ!!

1 comment:

  1. Thanks outstanding work.can I share u
    Something,I got this long time ago.if u
    are interesting post on if not take it for u
    SEE THE BRIGHT FUTURE
    What has happened before has brought you to where you are.yet the past has no control over where you can go from here.
    Your past history does not create your future.the choice's you make right now are what create the substance of that future.
    Learn from your mistakes,but don't agonize over them.there is nothing you can do to change.the fact that may happened.yet there is much you can do to move positively beyond them.
    When you dwell the past it holds you prisoner.when you let it go,that allows you to go anywhere.you now chose.
    People change,circumstances change,and you can change too,with each moment comes the opportunity to shake off the old assumption and limitations,to give new purpose and meaning to life.
    Give new energy,new effort,new commitment and determination to this day that you have the good future to be living.see the bright future that can be,and you will make it so.
    Thanks again and God bless you.

    ReplyDelete