ማክሰኞ ጥቅምት 12/2006 የምሕረት
ዓመት
‹‹ . . . ዳዊትም በራሱ ዘመን የእግዚአብሔርን አሳብ ካገለገለ በኋላ
አንቀላፋ፣ ከአባቶቹም ጋር ተጨምሮ መበስበስን አየ፤ ይህ እግዚአብሔር ያሥነሣው ግን መበስበስን አላየም›› (የሐዋ. 13፥36-39)
ወዳጆች ሆይ ከሁሉ አስቀድሞ የጌታችንና የአምላካችን የመደኃኒታችንም የኢየሱስ
ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ፡፡ በዚህ የጽሑፍ አገልግሎት የእግዚአብሔርን አሳብ ማገልገል ማለት ምን እንደ ሆነ የእግዚአብሔርን
ቃል መሠረት በማድረግ እንካፈላለን፡፡ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ጸሐፊ በዚህ ክፍል ላይ ሁለት አገልጋዮችን በንጽጽር ያሳየናል፡፡
ይኸውም ነቢዩ ዳዊትንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ነው፡፡ ስለ ዳዊት የእግዚአብሔርን አሳብ አገልግሎ መበስበስን እንዳየ ሲፃፍ፤
ስለ ክርስቶስ ደግሞ የእግዚአብሔርን አሳብ አገልግሎ መበስበስን እንዳላየ ያስረዳናል፡፡ በዚህ ክፍል የእግዚአብሔርን አሳብ ማገልገል
ምን እንደ ሆነ እንመልከት፡፡ ከዚያ በፊት ግን ጥቂት ጥያቄዎችን ለመንደርደሪያ እናንሣ፡፡
አገልግሎት ምንድነው?
የእግዚአብሔር አሳብስ ምን ማለት ነው?
የሚያገለግለው ማን ነው?
ሁሉ ሰው አገልጋይ ነውን?