ቅዳሜ ጥቅምት 9/ 2006 የምሕረት ዓመት
ከሻ-ይ መልስ
ያላችሁ ተሳስታችኋል፡፡ ከሻሸመኔ ማለዳው ይዞት የመጣውን የሚያስደንቅ ብርሃን በተመስገን ቃል ተቀብዬ ጉዞዬን ወደ መጣሁበት አዲስ
አበባ ለማድረግ አረፋፍጄ ተነሣሁ፡፡ ትራንስፖርት እንደ ልብ ማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን ለእናንተ መንገር ለቀባሪው ማርዳት ይሆናል፡፡
ስለዚህ አማራጭ የለኝምና ቢሆንም ባይሆንም ወደ መኪና መናሃሪያ ሄድኩ፡፡ ልክ እዚያ እንደ ደረስኩ ገና ከባጃጅ ሳልወርድ አዲስ
አበባ መሆኔን ለደንቡ የጠየቀኝ አንድ ወጣት መልሴን ሳይታገስ ለሹፌሩ ትእዛዝ ሰጥቶ አንድ አንቡላንስ ጋር አደረሰኝ፡፡ እኔም ለሥራ
መድረስ ነበረብኝና የውድ ግዴን ተስማማሁ፡፡
ከእኔ ጋር አንድ የሰማይ ስባሪ የሚያህሉ፣ ራሳቸው ፀጉር አልባ
የሆነ፣ ዓይናቸው ጎላ፤ ሻኛቸው ወደል ያሉ ሰውዬ ከእኔ ሻል ያለ አንድ ወጣት ጎን ተቀምጠዋል፡፡ ከእኔ በስተ ቀኝ ደግሞ ደጋግማ
የኢየሱስን ስም የምትጠራ አንዲት ጎልማሳ ሴት ቁጭ ብላለች፡፡ ሻንጣዎቻችንን የበሽተኛ ማስተኛው ላይ ቁጭ አድርገን እኛ አራታችን
በሕክምና ባለሙያዎችና በአስታማሚዎች ቦታ ተቀምጠናል፡፡ ሁላችንን እዚህ መኪና ውስጥ ያገናኘን የጋራ ነገር ምንድነው? ብዬ ለማሰብ
ሞከርኩ፡፡ እርሱም “መንገድ” በሚል ተመለሰልኝ፡፡
መንገድ ያገናኛል፡፡ ከማያውቁት ጋር ያግባባል፡፡ እኔ ግን ለመግባባት
ጊዜ ከመውሰድ ይልቅ እንደ በሽተኛ እያክለፈለፈ፣ መንገድ ሲዘጋበት የአደጋ ድምጽ እያሰማ፣ አናታችን ላይ ቀይ ለኩሶ ስለሚነጉደው
አምቡላንስ ማሰብ ጀመርኩ፡፡ ይገርማል! የታመመ ለመርዳትና ለማድረስ ቀርቶ ለመመልከት እንኳ አምቡላንስ ውስጥ ገብቼ አላውቅም፡፡
ምናልባት ትኩረቴን የሳበው ያም ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ከእያንዳንዱ ነገር ውስጥ ጥቂት ትምህርት የሚፈልገው አእምሮዬ ተማር
. . ተማር . . አለኝና ከዚህ ሁኔታ ምን እማራለሁ? ብዬ ራሴን ጠየኩት፡፡ አምቡላንሱ ውስጥ ከተቀመጥነው አራት ተሳፋሪዎች ሌላ
ጋቢና ከሾፌሩ ጋር አንዲት ወጣት ቢጤ ሴትና አንድ ጎረምሳ ተሸካክመው ተቀምጠዋል፡፡ መቼም ሹፌሩ ከማርሽና ከመሪ በስተቀር ሌላ
ምንም የያዘ አይመስልም፡፡
በነዳጁ ላይ የማዘዝ መብት የነበራት ሴቲቱ ናት፡፡ አንዴ በሳቅ
ቀልቡን ስትገፈው ነዳጁ ይተኮሳል መኪናዋ ምድሪቱን እየለቀቀች ለሰማይ ቅርብ ትሆንብናለች፡፡ ከዚያማ ምን ልበላችሁ ሾፌሩ ወሬም
ማርሽም ማቀናነሱን ይረሳዋል፡፡ ወቼው ጉድ! ይሉኝታ የለውም እንዴ? እላለሁ በሆዴ፡፡ አልፎ አልፎም ድምፃችንን በምታስተላልፈው
የውስጥ መስኮት ተጠቅሜ ድምጼን ከፍ በማድረግ “ከምንከፍልህ ሂሳብ ላይ የማሳጅ ትቀንሳለህ” እለዋለሁ፡፡ ግን እርሱ ምን ገዶት
ብቻ “ጌታ ሆይ ለሰው ማትረፊያ በሚያገለግለው መኪና እኛ እንዳንሞት” እያልኩ እጸልያለሁ፡፡ ከእኔ በስተቀኝ ያለችው እህት ደግሞ
በፍርሃት የጸለይኩትን ኃይልን በሚሰጠው ስም ትሸኝልኛለች፡፡ መቼም ሲጨንቅ “ወላሂም” ይባላል ያሉኝ አባት ፊቴ ድቅን አሉብኝ፡፡
ታመን ነው? ወይስ በጤናችን? እስክንል ድረስ አምቡላንሱ ይፈጥናል፡፡
ከውጪ የሚያየን ሰው ሁሉ በ“ያትርፋችሁ” አይነት አስተያየት ሲመለከተን እኛ “አሜን . . አሜን” እንደሚል ምርቃት ተቀባይ ተጣጥፈን
ቁጭ ብለናል፡፡ በየመንገዱ መኪኖች ዳር ይይዙልናል፡፡ ቆየት ብዬ እረሳውና ከመካከላችን በሽተኛ እፈልጋለሁ፡፡ ግን ምንም የሚያቃስት፣
የሚገላበጥ፣ የእርዱኝ ሲቃ የሚያሰማ፣ አቅሉን የሳተ፣ የሰው ክንድ ድጋፍ፤ የሐኪም እርዳታ የሚፈልግ አይታየኝም፡፡ ግን ቦርሳችን
የተቀመጠበት የበሽተኛ ማሳረፊያ ፊት ለፊታችን ተቀምጧል፡፡ ለቀልድና ለጨዋታ ያለንበት ስፍራ አይመችም፡፡ ቦታው የተጨነቀን፣ ድንገተኛ
ያጣደፈውን፣ በድቅድቅ ጨለማ በሽታ ቤቱን ያንኳኳበትን፣ ገፋ ሲልም የሞተ ሬሳን . . . የሚያስታውስ ነው፡፡ ሻሸመኔ ላይ ስነሣ
የገዛሁትን ውኃ የመጠጣት አቅም እስካጣ ድረስ መኪናይቱ ከእኛ በፊት ያሳፈረቻቸውን በሽተኞች እያሰብኩ አዝን ነበር፡፡
በመሐል ከወደ ጋቢና “ተጫወቱ” የሚል ድምጽ ተሰማ፡፡ አልዋሽም
አሁን ፈገግ አልኩ፡፡ “የማያስተኛ ነግረው ተኛ ይላሉ” የሚለኝ ወንድሜን አስታወስኩት፡፡ እንዴት እንጫወት ፋሻና ከፈን፤ የበሽተኛ
አልጋና ጉሉኮስ ማንጠልጠያ እያየን እንዴት ይሳቀን - ያሳቀን እንጂ፡፡ ከፍዬ የተሳቀኩበት ቀን ያውም በአምቡላንስ ሂሳብ ታሪፍ
አንጠይቅ ነገር እንዴት? ተከራክረን ትራፊክ ብንጠራ እንኳ በሽተኛ ምን ድምጽ አለው፡፡ የተጫንበትን ርእስ ደግሜ እያሰብኩት ዝዋይ
ደረስን፡፡ ለሾፌሩ ለራሱ በሚገርመው ሰዓት ደረስን፡፡ ምሳ ሰዓት ያለፈ ቢሆንም ምሳ እንብላ ብሎን መኪና ቆመ፡፡ ሾፌሩ ከጋቢና
ወርዶ ለእኛ በር ሲከፍት ሆቴል በር ላይ መሆኑ አቀዘቀዘው እንጂ የሰዉ ሰፍታ ያሸማቅቃል፡፡ ብቻ በዚህም በዚያ ወረድን ያስቻላቸው
ምግብ በሉ እንቢ ያለን ደግሞ እንቢ አልን፡፡ ጉዞ ምእራፍ ሁለት በበለጠ ኃይል ተጀመረ፡፡ እኔን የቱጋ ነው የያዙኝ? እያልኩ በሰውነታቸው
ግዝፈት የተደነኩባቸው አዛውንት ረዣዥም ጫት ይዘው ገቡ፡፡ ሾፌሩማ ከሲጋራና ከጫቱ ጋር ገላግለናቸው በስንት ግርግር መሰላችሁ ወደ
መኪና የገባው፡፡ ከምሳ በኋላ ጫት መቃሚያ ቤት ገብቶ ኖሮ ብዙ አስጠበቀን፡፡ አሁን መስሚያዬ ጥጥ ነው! አይነት መኪናው ተነዳ፡፡
እኔ
ወደ አሳብ አለሜ ተመለስኩ፡፡ በሽተኞች ተገኙ፡፡ ከስንት የአሳብ ውጣ ውረድ በኋላ በሽተኞች ተገኙ፡፡ ከረጅም አድካሚ ጉዞና ጥረት
በኋላ ሕመምተኞች ተደረሰባቸው፡፡ ሴቲቱና ወጣቱ ልጅ በማያነታርከው መነታረክ ጀመሩ፣ አልፎም ተርፎ ገላግሉን አስፈለጋቸው፣ የኔን
ታፋ ሻኛቸው ላይ የቆለሉት ሰውዬ እግራችንን በገራባ ሞሉት፣ ያ ሳያንስ የጫት ቁንጣን ይዟቸው በመቁነጥነጥ ወገባቸውን ፈተሸብን፣
ጋቢና ሮማንስ ይሠራ ጀመር፣ ሹፌሩ ዓይኖቹ ቀልተው በደመ ነፍስ የእልህ ይነዳዋል፡፡ አሁን በብርቱ መጸለይ ጀመርኩ፡፡ በእርግጥም
ያቺ አምቡላንስ በሽተኛ ጭና ነበር፡፡ ወደ ውስጤ ማየት ጀመርኩ፡፡ እዚህ ያለነው በሽተኞች ችግራችን የውስጥ ደዌ ነው! ያውም የነፍስ
አልኩ፡፡ የሚያቃስት፣ አልጋ የያዘ፣ ጉሉኮስ ያስተከለ በሽተኛ የለም፡፡ ነገር ግን የአመል በሽተኛ፣ የስነ ምግባር በሽተኛ፣ የጸብና
የቂም በሽተኛ፣ ያለመታገስና የስሜታዊነት በሽተኛ . . . እነዚህ ከጉበትና ከኩላሊት ችግር ቢበልጡ እንጂ አያንሱም፡፡
ለእንደነዚህ
አይነት ችግሮች አምቡላንስ ጮሆ፣ ነርሶች ተሰብስበው፣ ጉሉኮስ ተተክሎ፣ ሐኪሞች ደፋ ቀና ብለው አያውቁም፡፡ ግን የሰዎች ትልቁ
ችግር መንፈሳዊና ስነ ልቦናዊ ነው፡፡ ኩላሊቱ ያጣራለት ሰው ጆሮው እያቆሸሸ ከሰማ፣ ጨጓራው የፈጨለት ሰው አሳቡ የላመ የጣመ ካልሆነ
በእርግጥ ይሄ ሰው ሥጋና ደም ብቻ ነው፡፡ በሰማይና በምድር ሐኪም እግዚአብሔር ፊት የምናቃስትበት፣ እቀፉኝ ደግፉኝ የምንልበት፣
እሹኝ አገላብጡኝ የሚያሰኘውን ችግራችንን ኩልል ብሎ አየሁት፡፡ ጌታ ሆይ በአንተ ፊት እዚህ አምቡላንስ ውስጥ፣ በዚህ የበሽተኛ
አልጋ ላይ የሚያስተኛ ያውም በባሰ ሁኔታ ስንት ነገር ነበረን? “ሰው ውጪውን ያያል አንተ ግን ልብና ኩላሊትን ትመረምራለህ” አልኩ፡፡
አሁን ተቃውሞዬን አነሣሁ፡፡ እንደውም ሲፈጥን አሳቤ ፍጠን ይላል፡፡ የአደጋ ድምጽ ሲያሰማ በለው በደንብ ይጩህ ይላል፡፡ ግን ግራ
ገባኝ ይህን በሽታ የት ሆስፒታል ይዞት ይሄዳል፡፡
እንዲህ ያለውን የምድሪቱ ሥጋት፣ የሰው ልጆች መናጥ፣ ያለ ውዴታ
ግዴታ እንግልት፣ የነውር መዓት፣ የኃጢአት ሸክም፣ ሞትን የተላበሰ ማንነት . . . የትኛው ሐኪም ዘንድ ይወስደዋል? በመፍትሔው
ላይ እየተሟገትኩ እኔ የምወርድበት ቦታ በሰላም ደረስኩ፡፡ ግን አእምሮዬ በሽታችንስ መፍትሔው ምንድነው? እያለ ሞገተኝ፡፡ ልክ
ከመኪናው ወርጄ ቀና ስል አምቡላንሱ ላይ ቀይ መብራት ቦግ . . ቦግ ይላል፡፡ እኔም ይህ ቃል ትዝ አለኝ፡- “የልጁም የኢየሱስ
ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል (1 ዮሐ. 1፥7)።” ለካስ መፍትሔው ከላይ ነው፡፡ ሁሉን ከሚችል አምላክ፣ እግዚአብሔር
ከላከው ከአንድያ ልጁ፣ ለካስ መፍትሔያችን ሲከተለን ነበር፡፡ አሁንም ሌላ ቃል ትዝ አለኝ፡- “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ
ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ (ማቴ. 11፥28)።” ለነፍሳችን እረፍት ያለው ጌታ ብቻ ነው፡፡ ሻንጣዬን በትከሻዬ ላይ
እንዳንጠለጠልኩ አምቡላንሷ የስንብት ድምጿን፣ የደህና ሁን ፈገግታዋን ሰጥታኝ ካይኔ ራቀች፡፡ ጎኗ ላይ የተፃፈው ጽፈት ግን እንዲህ
ይላል፡- “በጤና ተቋም ሲወልዱ፤ እናት ጤና ልጅም ደህና” ደህና . . . ደህና . . ደህና . ደህና!
No comments:
Post a Comment