Saturday, October 12, 2013

ይህን ሰምተዋል?

                   ጥቅምት 2/ 2006 የምሕረት ዓመት




ቤተ ፍቅር መጽሔት

እጅግ የተወደዳችሁ ወዳጆች ሆይ ጸጋና ሰላም ከእናንተ ጋር ይሁን!

       ቤተ ፍቅር ብሎግ ከአዳዲስ አሳቦች ጋር በመጽሔት መልክ መታተሟን እያበሰርናችሁ በዚህ መንገድ የሚኖረንን አገልግሎት በስርጭት፣ በብርቱ ጸሎት፣ ከፍቅር በመነጨ ምክር (አሳብ) እንዲሁም በልግስና እንድታግዙን እንጠይቃችኋለን፡፡

      ቤተ ፍቅር በዚህ እትም በጉበኛው (በረኛ) አማካኝነት የወዳጅ አቀባበል ካደረገችልን በኋላ ወደ ግቢዋ እንድንዘልቅ የፍቅር ግብዣዋን ታቀርብልናለች፡፡ እርስዎ በር መክፈት አይጠበቅብዎትም፡፡ ጉበኛው በፈረጠመ ክንድ፣ በማይነጥፍ መስተንግዶ፣ እንደ ማር ወለላ በሚጣፍጡ ቃላት እጁን ዘርግቶ መንገድ ይጠርግልዎታል፡፡ ነገር ግን በፍቅር ልብዎን እንዲከፍቱ እንለምንዎታለን፡፡ በግቢው ሳር ላይ ዘና ብለው ከፍራፍሬው እየበሉ፣ ነፋሻማውን አየር በፍቅር እየሳቡ ይመከራሉ፡፡ ለመኖር እንዲጓጉ፣ ከጠባቡ የኑሮ ጉድጓድ አልፈው በተሻለ እንዲያዩ ትጋት ይበዛልዎ ዘንድ በተስፋ ትሞላዎታለች፡፡ በእያንዳንዱ እርምጃዎ “እንደ እግዚአብሔር ያለ አስተማሪ ማነው?” የሚሉበትን መደነቅ፣ በሁኔታዎች ውስጥ አግራሞትን የሚያጭሩ ቁም ነገሮችን ያስተውላሉ፡፡ የመኖር አቅሙ ተስፋ እንደ ሆነ፣ አልጫ የሆነብዎ ነገር ማጣፈጫ እንዳለው በፍቅር ይረዳሉ፡፡

       ጉበኛው አሁንም ስር ስርዎ እያለ እግር በእግር እየተከተለ ለእርስዎ ደስታ ይተጋል፡፡ ግቢውን አልፈው ወደ እልፍኙ እንዲዘልቁ ዝቅ ብሎ በእጁ ያመላክትዎታል፡፡ ቤተ ፍቅር ቁርጥ በሆነው ነገር ላይ መቁረጥ እንዲችሉ፣ መልፈስፈስ አቅም ያሳጣውን፣ ማመንታት ያሰቃየውን፣ አሳብ ያንገዳገደውን አካልዎን ጉበኛው ወንበር ስቦ፣ የሚጎነጩት አቅርቦ፣ በፍቅር ዓይን እየተመለከትዎ አንድ በአንድ ስለ ፍቅር ሕይወትዎ ያጫውትዎታል፡፡ በብርቱ ቃላት እያዋዛ ወደ ውሳኔ የሚደርሱበትን አቅም ይፈጥርልዎታል፡፡ በእልፍኙ ካሠርዎት ይሉኝታ፣ የማስመሰል ኑሮ፣ እውነት ከሌለው ግብዝነት ተፈተው ዘና ይላሉ፡፡ ይህም በፍቅር ሲከወን ያስተውላሉ፡፡

       አሁን ወደ ቤተ መፃህፍት ክፍል ዘልቀዋል፡፡ መደርደሪያውን ባጨናነቁት መጽሐፍቶች ነፍስዎ ሐሴት ታደርጋለች፡፡ የቱን አንሥተው የቱን እንደሚጥሉ ግራ እስኪገባዎት ድረስ በንባብ ክፍሉ ውስጥ በነፃነት ይመላለሳሉ፡፡ ጉበኛው ከሁለት መፃህፍቶች ጥቂት ቁም ነገሮችን እንዲያነቡ በፍቅር ያቀርብልዎታል፡፡ የማፍቀር ጥበብንና የሚዛናዊነትን ጥቅም በውል እንዲረዱ ቤተ ፍቅር ትረዳዎታለች፡፡ ከጊዜ በጀትዎ ለንባብ የሚያጠፉትን መቼም እንደማይቆጩበት በፍቅር ይገነዘባሉ፡፡  

       እንኳን ወደ ማረፊያ ክፍላችን በደህና መጡ፡፡ ለእርስዎ ምቾት ቤተ ፍቅር ትጨነቃለች፡፡ ቤተ ፍቅር ማኅበራዊ ኑሮዎን፣ ይቅርታ ያለ ማድረግ ፈተናዎን፣ አብሮ የመኖር ተግዳሮቶችንና መፍትሔዎቻቸውን በግልጽ ፍቅርን በተሞሉ አሳቦች ሕይወትዎን ትዳስሳለች፡፡ ሸክም እንዲቀልልዎ፣ ከመቁነጥነጥ እንዲላቀቁ፣ የማይጠቅምዎን አስወግዱ ትልዎታለች፡፡ ጭንቀትዎን በአስቸኳይ እንዲያስወግዱ ይጠየቃሉ፡፡ ቤተ ፍቅር ልክ እንደ ጥሩ እናት ፀጉርዎን እየዳበሰች የእውነት እንቅልፍ (ዕረፍት) እንዲያንቀላፉ አልጋ አንጥፋ፣ የሌሊት ልብስ አሰናድታ፣ ራስጌዎን በብርሃን አድምቃ ትቀበልዎታለች፡፡ ለደኅንነትዎ ጉበኛው ከተዘጋው ደጅ በስተውጪ ይቆማል፡፡ ለኮሽታ እንኳ ምላሽ በሚሰጥ ዝግጅት፣ ለእንጥሻዎ አቤት በሚል ንቃት እርስዎ ያርፋል እርሱ ይቆማል፡፡

        ጉበኛው በእርስዎ ደስታ ደስ እየተሰኘ፣ ልብዎ ባገኘው ጥቂት ቁም ነገር ምስጋና እያቀረበ ወደ ማዕድ ቤት ይመራዎታል፡፡ ርሀብና ጥም ላዛለው አካልዎ ምላሽ ለመስጠት ማዕድ ቤታችን ሙሉ ናት፡፡ ከብዙ ቃላት ይልቅ ጥቂት ድርጊት ብዙ እንደሚናገር፣ ለሌሎች ማድረግ ለራስ ማድረግ እንደ ሆነ፣ በእግዚአብሔር ዘንድ ውብ ስለሆነው ነገር እያወራንዎ ተመስገን ብለው ጠግበው ይነሣሉ፡፡ በማዕድ ቤታችን ለምድሪቱ ሰላም የእርስዎን አስተዋጽዎ ከፍተኛነት እንነግርዎታለን፡፡ የመጣውን ዘመን፣ እግዚአብሔር የሰጠንን እድሜ፣ እያንዳንዱን ዕለት እንዴት ማሳለፍ እንዳለብዎ አሳብ እናካፍልዎታለን፡፡

         አሁን ወደ ጓዳ ዘልቀናል፡፡ ስሜትዎን በሚጋራ፣ ችግርዎን በሚፈታ፣ መከፋትዎን በሚያጽናና አሳብ ጓዳው ስንዱ ነው፡፡ ያለዎትን እንዲያስተውሉ፣ ከምሬት ወጥተው ለጥቂቱ እንኳ እንዲያመሰግኑ በብርቱ እንሞግትዎታለን፡፡ ለጨላለመብዎ ነገር የብርሃን ወጋገን፣ በምርጫ ለተቸገሩበት ነገር የተሻለውን እንጠቁምዎታለን፡፡

         ተወዳጆች ሆይ ጎጆአችንን በፍቅር ስለጎበኛችሁልን፣ በቀጣይም ደጋግማችሁ ልታዩን ፈቃደኛ ስለሆናችሁ፣ ብርታትና ድካማችንን ያለ መሸንገል ልትነግሩን ታማኝ ስለሆናችሁ ጉበኛው ይላል፡- እናመሰግናለን!  

                                              መጽሔቷን ለማግኘት፡- 0912- 926616


5 comments:

  1. wowwwwwwwwwwwwww simegnew ina sitebikew neber igziabiher amalak zeminachun yibark tebarekulign be inante betam be bizu iyetebareku new geta agelegilotachun yibarkew beziw ketilu irgitegna negn ye mestihetachu denbegna ihonalew

    ReplyDelete
  2. Good job one step at a time,keep moving.blessing.thanks.

    ReplyDelete
  3. can i get the magazine in Jimma?

    ReplyDelete
  4. am rly happy for hearing zis gud news frm u........God bless u!

    ReplyDelete
  5. Bete feker wunetem feker kezih belay men feker ale?egziabher yabertachu ketechalachu ene south Africa newena yemenorew yemetebaberew kale zegeju negn.my e mail sewbe2000@yahoo.com

    ReplyDelete