‹‹ለሰብእ ሰብእ
ዘየዐብዮ በምንት፤
አምጣነ ኩሉ ዕሩይ
በጊዜ ልደት ወሞት፡፡››
ትርጉም፡ -
‹‹ሰው ከሰው በምን
ይበልጣል፤
ልደትና ሞት አንድ
ያደርገዋል፡፡››
(አለቃ ጥበቡ ገሜ)
ወደዚህ ምድር መምጣት ቀላል እንዳልሆነ
የነገረችኝ እናቴ ናት፡፡ ያማጠ ያውራ፡፡ የወለደ ይናገር፡፡ መወለድ ጸጋ ነው፡፡ ወላጅ፣ ስፍራ፣ ሕዝብ፣ ሁኔታ መርጠን አልተወለድንም፡፡
ዳሩ ግን ወደ ማስተዋል ስንመጣ ራሳችንን እዚህ አግኝተነዋል፡፡ ተመስገን! እንደ አሳቡ ሁሉን የሚፈጽም፣ ለአድራጎቱ ከልካይ የሌለበት
አምላክ ስሙ ብሩክ ይሁን፡፡ የአርያም ደጆች ተከፈቱ፡፡ ያበጃጀኝን መዳፍ አየሁት፡፡ ከምድር አፈር የሠራኝን፣ የሕይወት እስትንፋስ
እፍ ያለብኝን፣ ለእኔ ተጠቦ ገነትን ስፍራ የሰጠኝን፣ መልክና ምሳሌው ያደረገኝን፣ ቢስት እመልሰዋለሁ፣ ቢጠም አቀናዋለሁ፣ ልጅነቱን
አሳድጋለሁ፣ አለማወቁን አስተምራለሁ ብሎ ኑር ያለኝን ልብ አልኩት፡፡
መጪውን እያየ፣ መዳረሻዬን እያወቀ የፈጠረኝን የአባቶች አባት፣
የወላጅ ጥግ፣ የመውደድ ዳርቻ ኤሎሂም ወሰን መስፈሪያ በሌለው ክብር በዙፋኑ ሆኖ አስተዋልኩት፡፡ የልቤን ዓይኖች ወደ ጸጋው ዙፋን
ዘረጋሁ፡፡ አባባ እንዲህ አለኝ ‹‹አሳብ ሳለህ ያሰብኩህ፣ ጽንስ ሳለህ ሰው ያልኩህ እኔ ነኝ›› ገጹ በማይቆጠር እጥፍ ያበራል፡፡
ሁሉን የሚችል ብርታቱ፣ ደከመኝ ሳይል የሚሸከም ፍቅሩ፣ ያለመጥፋት ዋስትና ምህረቱ፣ የማይናድ የማይፈርስ ኪዳኑ፣ አመጽን የማያውቅ
ጽድቁ በግልጥ ይነበባል፡፡