Wednesday, December 11, 2013

የንጉሡ ኢትዮጵያ

                                           Please Read in PDF: Yengusu etyopia

                             
                                    እሮብ ታህሳስ 2/2006 የምሕረት ዓመት

      ለመጀመሪያ ጊዜ የቅዱስ ጳውሎስን ሆስፒታል የረገጥኩበት ዕለት ነው፡፡ የሕዳር ወር መጨረሻ! እንደነዚህ ያሉ ስፍራዎችን በዋናነት ሦስት ሰዎች ማለትም ሕሙማን፣ አስታማሚ (ጠያቂ) እና የሕክምና ባለሙያዎች እንደሚገኙበት አስባለሁ፡፡ ታዲያ ከቀትሩ ለመሸሽ ማለዳውን እየተሽቀዳደምኩ ነበር ወደምጠይቀው ሰው ያቀናሁት፡፡ እኔ የምፈልገው ሰው ወደሚገኝበት ክፍል ስደርስ ጽዳት ላይ የነበሩ ሠራተኞች እንድታገስ ነገሩኝ፡፡ ከመቆም ብዬ ዘወር ዘወር ለማለት ወደ ታችኛው የቅጽሩ አካባቢ ወረድኩ፡፡ በግራና በቀኝ፣ በፊትና በኋላ ዙሪያዬ መፍትሔ ሽተው በዚያ የተገኙ ሕሙማንን ልማዳዊ ከሆነው ‹‹ይማራችሁ›› ባለፈ ስለ እነርሱ በልቤ እየጸለይኩ በእርጋታ በጥጋ ጥጉ ሳይቀር ተራመድኩ፡፡ ድንገት ዓይኔ አንድ ነገር አስተዋለና ይበልጥ ተጠግቼ ተመለከትኩት፡፡ ከዚህ ጽሑፍ በላይ የምታዩትን የንጉሡ የኃይለ ሥላሴን ስዕል ነበር ያየሁት፡፡ የመጣሁበትን ዓላማ የዘነጋሁ እስኪመስለኝ ድረስ ደጋግሜ በአግራሞት አስተዋልኩት፡፡ አሁንም ይበልጥ አስተዋልኩት፡፡
      ንጉሡን ከታሪክ ባለፈ በልደት አልደረስኩባቸውም፡፡ ዳሩ ግን ወድጄም ይሁን ሳልወድ፣ አስቤውም ይሁን በአጋጣሚ ስለ እርሳቸው በጎም ክፉም ሰምቻለሁ፡፡ አሁን ያየሁት ግን ብዙ ነገር እንዳወጣና እንዳወርድ ምክንያት ሆነኝ፡፡ ከስድስት ወር በፊት በማኅበራዊ ስነ ልቦና የድኅረ ምረቃ ትምህርቱን የሚከታተል ወዳጄ ‹‹የሕዝባችን ደግነት ምንጩ ምን ይመስልሃል?›› በማለት የጠየቀኝንና የተወያየንበትን አሳብ አስታወስኩት፡፡ ደግነትና ፍቅር መነሻቸው ብዙ ነው፡፡ ሊያጠፉ ያበሉ፣ ሊያጣሉ የወደዱ፣ ሊያከስሩ የቸሩ ብዙ ናቸው፡፡ ወዳጄ ያነሣው ከነበረው አሳብ አንዱ ‹‹አጥፋ ግደል በሚለው ሥርዓት ውስጥ የሰው ሥጋ የመብላት ያህል የከፉ፣ የተጎራበታቸውን በአደባባይ አውጥተው የገደሉ፣ ለአብራካቸው ክፋይ ያልራሩ እግዚአብሔር የለሾች እንደ አሸን በነበሩበት ባለፉት ዘመናት እየተጠፋፋ የኖረ ማኅበረሰብ የዛሬ ጸጥታው ምንጩ እምነት፣ ሕግ፣ ፍቅር፣ ስልጣኔ፣ ሥርዓት፣ አለመመቸት (ለዓመጽ) ወይንስ . . . የትኛው ነው?›› የሚል ነበር፡፡

      በእርግጥም አለመመቸት እስራት የሆነበት ማኅበረሰብ እንዳለ አያጠያይቅም፡፡ ቢችል የሚያጠፋ፣ አቅም ቢያገኝ የሰው ኑሮ በእንባና በደም የሚያቦካ፣ ጊዜ ቢገጥመው በሬሳ ላይ የሚረማመድ፣ ሥርዓቱ እንዳለፉት ዘመናት ሁሉ አመጽ መርኁ ቢሆን ከአውሬ የሚከፋ ሰው አይጠፋም፡፡ የአኗኗራችን ዘይቤ በእውነት የደፈጣ ነው፡፡ እዚህ ውስጥ ፍቅር የለም፡፡ ግን ፍቅር የሚመስል ነገር አለ፡፡ እዚህ ውስጥ ትእግስት ግን ለአንድ ቀን ጥፋት የቀጠረን ትእግስት አለ፡፡ እዚህ ውስጥ በአፍ የሚሸረድድ በልቡ የሚያርድ ትህትና አለ፡፡ እዚህ ውስጥ ወደ መቃብር እንኳ እየሸኘ የሚሸነግል ወዳጅነት አለ፡፡ የሕይወት አሳቻ መንገድ ላይ እስክንገናኝ የሚያጨበጭብ፣ አቅም እስኪያገኝ የሚጎናበስ፣ ሲመቸው ሸጦ ለውጦ እፍ የሚል ኑሮ አለን፡፡

       እግዚአብሔር ዘመን ሰጥቶአቸው በዚያ ንጉሣዊ ሥርዓት ስር በተለያየ ደረጃ የነበሩ ሰዎችን በእድሜ ደርሰንባቸው አይተናቸዋል፡፡ አንዳንዱ እድሜ ለንስሀ ብሎ፣ ሌላው ያለፈውን ሥርዓት በብርቱ እየናፈቀ ናፍቆት ከሰውነት ተራ አውጥቶት፣ ደግሞ ሌላው የዛሬው ሥርዓት ምቾት ነሥቶት እየተቁነጠነጠ ብቻ በልዩ ልዩ ሁኔታ ውስጥ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ መቼም እንዲህ በኃይል የምናገርበት ምክንያት ሳይገባችሁ የቀረ አይመስለኝም፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ሙት ወቃሽ፣ ነገር ጠንሳሽ፣ ጥላቻ አመላላሽ የሆነ አሳብ ማቅረብ አይደለም፡፡ በግልጥ የሚስተዋለውን ያለፈ ስህተት በፍቅር እንድንማርበት ማስቻል ነው፡፡

       አንዳንድ ጊዜ እንዲህ እላለሁ ‹‹ጥሩ የጀመሩ ሰዎችን በተለይ በአስተዳደር ላይ ያሉትን የብልሽታቸው ምንጩ ምንድነው? ደግነታቸውን አውርተን የማንጨርስላቸው ከፍታውን ሲቆናጠጡ ምነው ከፉ? በእውነት ምለው፣ በፍቅር ተማምለው በጎውን ሊሠሩ ቃል የገቡ ወገኖችስ ምነው መገለጫቸው እንክሻ ሆነ? . . . ››፡፡ በእርግጥም የመንጋደዳቸው ምንጭ እነርሱ ብቻ አይደሉም፡፡ ከምላስ መንሻ እስከ እጅ መንሻ የሚያቀርቡ፣ ክበው ክበው ቁልል የሚያሳክሉ፣ ከሰው ማነፃጸሪያ ጨርሰው እንደ አምላክ የሚመስሉ ለመኖራቸው የንጉሡ የኃይለ ሥላሴ ምስል እማኝ ነው፡፡ ስእሉ በ1970 (እንደ አውሮፓ አቆጣጠር ይመስለኛል) በአፈወርቅ ተክሌ (ማዕረግ ያልፃፍኩት የስም ሞክሼ ስሎት ከሆነ በሚል ነው) የተሳለ ነው፡፡ መቼም የዓለም ሎሬት ስለውት ከሆነ ብዬ ብዙ አሰብኩ፡፡ ይህንን ስእል በስንት ውለታ አልያም ዋጋ ይሆን የሳሉት? አሳቡን ያመነጨው አካልስ ማን ይሆን? እጆቻቸውን ወደ ኃይለ ሥላሴ ያነሡት የኢትዮጵያ ሕዝብስ ‹‹እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች›› የሚለውን ጥቅስ እንዴት ታግሰው ዝም አሉ? ብቻ አወጣሁ አወረድኩ፡፡ ለካ ስእል ላይም አመጽ አለ!

       የዚያን ጊዜ ኢትዮጵያና ሕዝቡ የማን ነበሩ? እናት ከነልጇ፣ በገጠሪቱና በከተማው መደብ ነዋሪ ወገኖች፣ አካል ጉዳተኛና ታማሚ ከየዓይነቱ ከደመና በላይ ወደሚታዩት ንጉሥ እጆቻቸውን አንስተው ይጮሀሉ፡፡ ዛሬም ድረስ ‹‹እግዜር እንኳ ከእጄ አያስጥልህም›› በማለት በድፍረት የሚናገሩ ሰዎች መኖራቸው የእግዚአብሔር መፈራት በተግባር ወዴት አለ? ያስብላል፡፡ ምግብ ያልቀመሰ ሆዴ ጮኸ፣ ዓይኖቼ ይበልጥ ፈጠጡ፡፡ ትኩስ ስእል ፊት የቆምኩ ያህል ብግን አልኩ፡፡ ሠዓሊው ልበልና ምን ነካቸው፣ እንዲህ በዚህ መንገድ እንዲስሉ ማን ቆነጠጣቸው፣ አላፊውን ሰው እንደ ፈጣሪ ማቅረብ እምነት ሳይሆን ሕሊና የሚዳኘው ተራ ነገር ነበር፡፡ ታዲያ ምክንያቱ ምን ይሆን? ለእኔ ያልገባኝ ለእናንተ የገባችሁ፣ እኔ ልብ ያላልኩት እናንተን የተረዳችሁ ነገር ካለ ፃፉልኝ፡፡ እይታና ወቀሳ ካላችሁ ቁጣችሁንም ቢሆን ንገሩኝ፡፡ ከመውደድ የተነሣ ይሆን? ብል እርሱም ፍቅር ለበስ አመጽ ሆነብኝ፡፡

       ሎሬቱ በተለያዩ አብያተክርስቲያናት መንፈሳዊ የሚባሉ ስእሎችን እንደሳሉ አውቃለሁ፡፡ ይህ ስእል ከነዚያ ጋር አለመቀላቀሉ ምን አልባት ንጉሡ ደግ ሆነው ይሆናል እንጂ የሞገተ ሰው ኖሮ አይመስለኝም፡፡ ለካ ይህንን የሳለ እጅ ነው ክርስቶስ ተሰቅሎም የሳለው! ፈጣሪን ለሰው አሳብ ያጎናበሰ ቅዥት፣ ከንቱን እንደተሸከመ አረፋ፣ ከፍ ብሎ ነፋስ እንዳንሳፈፈው ፊኛ ብኩን ተግባር፡፡ እንደዚህ ያሉ ስህተቶችን እና በእግዚአብሔር ላይ የተቃጡ ዝበታዎችን በተለያየ አጋጣሚ አስተውያለሁ፡፡ ሰይጣን በሰው ውስጥ የእግዚአብሔርን ክብር ለራሱ እንደሚወስድ የክርስትናውን ቋሚ ጠላት በአግባቡ የተረዳ ወገን ሁሉ ልብ ይለዋል፡፡ በዚህም ስእል ያስተዋልኩት እንደዚያ ነው፡፡ እኔ እንዳየሁ ላይታያችሁ፣ እኔ እንደቀናሁ ላያስቀናችሁ ይልቁንም ሊቀላችሁ ይችል ይሆናል፡፡ አንድ ጊዜ በቲዎሎጂ ትምህርት ቤት እየነበርኩ የክርስትናን ሥነ ምግባር የሚያስተምረን መምህር ‹‹ሕዝባችን ድኅነት ይዞት እንጂ እግዚአብሔርንም ቢሆን ለጠብ ፍለጋ ይሄድ ነበር›› ያለውን አስታውሳለሁ፡፡

       እውነት የብዙዎች መታመን ለእግዚአብሔርም ለክፉውም ይመስለኛል፡፡ እርግጥ ነው! ጠንቋይ ቤት አድረው ማለዳ ሰው አየኝ አላየኝ ብለው የሚያስቀድሱ ሰዎችን አይቻለሁ፡፡ ዛር ቤት ሄደው ግድግዳ ላይ የተሰቀለ የመልአክትን ስእል እየተሳለሙ፣ ጠበል እንዲነከሩ እየተመከሩ ያለ ምንም ጥያቄ የሚጎናበሱ ሰዎችን አስተውያለሁ፡፡ እንደነዚህ ያሉት ለሁለቱም ታምነው የሚሰለፉ፣ በሞቀበት ሞቀው፣ የተጨበጨበበት አጨብጭበው የሚኖሩ ናቸው፡፡ የእግዚአብሔር ሰዎች በተግባር የታመኑበትን እኛ በስእል እንኳ ካልታመንን፣ ልክ አይደለም ካላልን፣ እጃችንን ካልሰበሰብን፣ ትውልዱን የሚያደፋፍር፣ የሐሰት ሎሌ፣ የነውር ባሪያ የሚያደርግ ተግባር እየፈጸምን ሁሉን አቅሎ እንዲያይ ሕሊናውን ካለማመድን እውነትን ጨክኖ መታዘዝ ከወዴት ይኖራል?

      ተወዳጆች ሆይ የምናደርገው ነገር አልፎም ሐቅ አለው ወይ? ብለን ልንጠይቅ ይገባል፡፡ ሰዎች ራሳቸውን የሚያስቡበት መንገድ ብቻ ሳይሆን እኛም እነርሱን የምናይበት አተያየት በአስተሳሰብና በአኗኗራቸው ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ያስከትላል፡፡ ልጆቻቸውን ምንም እንደማያቅታቸው እየነገሩ ያሳደጉ ወላጆች እንደ ፈጣሪ ሁሉም ጋር ልክ እንደሆኑ እያሰቡባቸው ተቸግረዋል፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ‹‹ነገር ግን ከፍርድ በታች እንዳትወድቁ ነገራችሁ አዎን ቢሆን አዎን ይሁን፥ አይደለምም ቢሆን አይደለም ይሁን›› (ያዕ. 5፥12) እንደሚል የስልጣኔ መጀመሪያ፣ ሰዎችን የማክበር ቁንጮ፣ ለትውልድ የሚቆይ ጥሪት ይህ እውነት ነው፡፡ ንጉሡን የዘላለም ንጉሥ እግዚአብሔር እንዳለ በተግባር እንዳያስተውሉ፣ ተሳስቻለሁ ብለው ስህተታችውን እንዳያርሙ፣ እንደዚያ ባለ ውርደት ዘመናቸው እንዲጨረስ ማን ጎዳቸው? እውነታ እውነታውን ለመቀበል ለምን አሻፈረኝ አሉ? የውዳሴ ከንቱ ብዛት፣ ‹‹እርስዎ አይሳሳቱም›› አይነት ሽንገላ፣ የሃይማኖት አባቶች ግብር በላነት፣ የራስን ሙቀት እንጂ የውጪውን ቅዝቃዜ ዳባ ልበስ ማለት ብዙ ብዙ ምክንያቶች ተደማምረው ነው፡፡

     ንጉሡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶስ ቤተ ክርስቲያንን በተመለከት ከሀገር ወጪ ሳሉ የተሾሙ አምስት ጳጳሳትን ‹‹እኔ ባልፈቀድኩበትና በሌለሁበት የሾማችሁን ከጠላት ጋር አሲራችሁ ነው›› በማለት እንዲከለሱ ትእዛዝ ሰጥተው ሁለቱ እምቢታቸውን ገልጸው በግዞት ሲኖሩ ሦስቱ ግን ተከልሰው አገልግለዋል፡፡ እንደ ቤተክርስቲያኒቱ እምነት በመንፈስ ቅዱስ የሚባለውን በኃይለ ሥላሴ ፈቃድ አያሰኘውምን? እንዲያ ያለ ያላወራነው ስንት ብልሽት ዘመን ተሻግሯል፡፡ እውነትን ማእከል ያላደረገ ሰብእና ከነፈሰው ጋር ይነፍሳል፡፡ በጎ ተጽእኖ የመፍጠር አቅምና ጉልበቱ ቄጤማ ይሆናል፡፡ ይልቁና ‹‹የሺህ ዓመት ንገሥ›› ዜማ፣ የእንብላው ድግስ ወከባ፣ የጠጅ የጠላ ጠጡ ድንፋታ፣ ማብቂያ መቋጫ የሌለው የሽገላ ጋጋታ . . . ከንጉሥ እስከ ሎሌ ስንቱን ለገዛ ነፍሱ እንኳ ሳይሆን ወደ መቃብር ሸኘው፡፡

     እውነት እውነቱን ተነጋገሩ፡፡ ሐቅ ሐቁን ሥሩ፡፡ እውነት አርነት ያወጣችኋል፡፡ እንኳን በኑሮ ስእላችሁ እንኳን ትህትናን ይስበክ፡፡ ለሸንጋዮቻችሁ የማያዳግም እምቢታችሁን ግለጡላቸው፡፡ ብዙ አድርጋችሁ ጥቂትም እንደከበደው ኑሩ፡፡ በተለይ በተለይ ከእግዚአብሔር ጋር በተያያዘ አመጽን እጅግ አድርጋችሁ በነፍስ ተጸየፉት፡፡ እግዚአብሔር ደመናው ላይ የተሰየሙትን እንዴት ባለ አጨራረስ ምድሪቱንም እንደነፈጋቸው ከእኔ ይልቅ ወደኋላ እድሜያችሁ ረጅም የሆነ ሁሉ ታውቃላችሁ፡፡ የወዳጅ ፍቅር ለሚወደው ሁለንተናዊ ጤንነት ይጨነቃል፡፡ የፍቅር ትልቁ ኃይል እውነቱ ነው፡፡ እግዚአብሔር ባስቀመጣችሁ ቦታ ሁሉ ከፍታውን ለጌታ ስጡት፡፡ ራሳችሁን እንደማይጠቅም ባሪያ እየቆጠራችሁ ለልባችሁ ጌጥና ውበት ተጨነቁ፡፡ ከፍታና ዝቅታ ፈረቃ እንደሆኑ በማስተዋል ከላይ ስትሆኑ ታቹን እያያችሁ በጥበብና በማስተዋል፤ ታች ስትሆኑ ደግሞ ወደ ላይ እያያችሁ ለኃላፊነት ትከሻችሁን ማስፋት፣ በብዙው ላይ ለመሾም በትንሹ መታመን እጅግ አግባብ ነው፡፡

     ከዚህ የንጉሡ ስእል ስር ‹‹አፍቅር ቢጸከ ከመ ነፍስከ›› የሚል ጽሑፍ አነበብኩ፡፡ ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የሚል መልእክት አለው፡፡ መቼም ጌታ ከተናገራቸው የፍቅር ትእዛዞች መካከል አንዱ ሌሎችን እንደ ራሳችን እንድናስብላቸውና እንድንወዳቸው የሚያዝ ነው (ማቴ. 19፥19)፡፡ ሠዓሊው ለምን ጥቅስ (ምንጭ) እንዳልፃፈ ፊቴ አግኝቼ ብጠይቀው ደስታዬ ነበር፡፡ ይህንንም ያሉት ንጉሡ ናቸውን? ወይንስ ሰዓሊው አንዳች ቅያሜ በእግዚአብሔር ላይ አላቸው? በየዘመናቱ መልኩን በቀያየረ መንገድ የክፋት ሠራዊትና የጥልቁ ሎሌዎች እግዚአብሔርን እያጣቀሱ ትውልዱን ወደ ጨለማው ጥልቅ ይሰድዱታል፡፡ እዚህ ስእል ላይ ባልንጀራን እንደ ራስ መውደድን የሚያሳይ ምንም ነገር የለም፡፡ የበላይና የበታች መደብን የሚገልጽ፣ ሕዝብን የመለኮት ሳይሆን የሥጋና የደም ተስፈኛ የሚያደርግ፣ የኃይለኞችን ምቾት የምስኪኖችን መኮሳመን በግልጽ የገለጠ፣ በማን አለብኝነት ልክ ችንካር እንጎረሱት የክርስቶስ እጆች ምቾትን የጠገቡ እጆች የተዘረጉበት . . . ሌላም ሌላም ልክ እንደምታዩት፡፡ ይህ ጥሎ ማለፍን እንጂ መረዳዳትን አላሳየኝም (እኔን በተመለከተ ብቻ)፣ በዚህ ስእል ውስጥ አንድ የአእምሮ ችግር እንዳለበት እጁን በራሱ ላይ ካደረገ ምስኪን ጋር እያቀፈው ይሁን እየገፋው ግልጽ ካልሆነ ሰውዬ እና ተፈጥሮ የጣለባትን ኃላፊነት በታማኝነት ለመወጣት ከምትታትር፤ የተጎሳቆለ ልጇን ወደ ተስፋው ካመጣች እናት ውጪ ግልጽ የሥጋ እንኳ መቀራረብ የሚታይበት አይደለም፡፡ ግን አሉን ‹‹ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ››፡፡ ሰዓሊው ከሰሙኝ ‹‹ቦታ ያቀያይሩ››፡፡

     ምድራችን እንዲህ ባለ ግብዝነት መጥለቅለቁ እግዚኦ የሚያሰኝ ነው፡፡ የምንናገረውና የምንሠራው አልገጥምላችሁ ያለን እድለ ቢስ አፈኞች፡፡ ፈውስን የሚሰጥ ጌታ ልቦቻችንን ይፈውሳቸው፡፡ ግን እግዚአብሔር አይዘበትበትም፡፡ ከዚህ ስእል ጎን አንድ ሌላ ስእል አስተዋልኩ፡፡ እስካሁን ለተነጋገርንበት ስእል እንደ ማራከሻ የተሳለ ይመስላል፡፡ ንጉሡ የአንድ ሕፃን ጉንጭ ለመንካት ሂደታዊ ላይ ሆነው ሌላ ቀድሞ የተጎበኘ ልጅ ለምስጋና በሚመስል መልኩ እጆዙን አንሥቶ፣ የጠመጠሙ ቄስ፣ ልጅ የታቀፈች እናት፣ የቆረቡ የሚመስሉ ሴት፣ ዛፍ የተደገፈና መቋሚያ የያዘ ሁለት ወንዶች በዋናነት ይታያሉ፡፡ ልቤ ይህንን እንደማካካሻ ስላልተቀበለው ወደ ሌላ ጥያቄዬ ዘወር አልኩ፡፡

      ለመሆኑ ይህ ስእል እዚህ ምን ያደርጋል? ሆስፒታሉን ያስገነቡት እርሳቸው ናቸውን? ሕሙማንን ተመላልሰው ይጠይቁ ነበርን? ወይንስ ሰው ታሞም ያስባቸው ተብሎ ተሰቅሎ ይሆን? እያልኩ ገና ጥያቄዬን ሳልጨርስ አንድ ጽሑፍ በግልጽ የማይታይ ቦታ ላይ አነበብኩ፡፡ ‹‹በጀርመን አገር የሚገኘው ኤቫንጄሊካል ቤተ ክርስቲያን ለዚህ ሆስፒታል መሥሪያና በውስጡ ለተዘጋጁት የሕክምና መሣሪያዎችና ዕቃዎች ወጪ ከጠቅላላው ዋጋ ሰባ አምስት በመቶ ረድቷል›› የሚል በእንግሊዝኛ ቋንቋ ጭምር የተከተበ ጽሑፍ ደጋግሜ አነበብኩ፡፡
                                                                        


      አንድ ነርስ ስታልፍ ‹‹የእነዚህ ሰዎች ፎቶ የታለ?›› አልኳት፡፡ ተገርማ አየችኝና ጠጋ ብላ ፈገግ እያለች  ‹‹የመጣኸው ፎቶ ልትጠይቅ ነው እንዴ?›› ብላ መለሰችልኝ፡፡ ለሰው ያልኩትን ለራሷ ብላ መስማቷ ምን ያህል በተቃራኒ ፆታ ያለመጠየቅ (ያለ መፈለግ) ስነ ልቦናዊ ችግር እንዳለባት ስለጠቆመኝ፡፡ በጊዜ ሸኘኋትና የሥራ ድርሻው ግልጽ ያልሆነልጽ ስጠረጥር ጥበቃ የሆነ ፆታዬን ሲያልፍ አስቁሜ የጠየኳትን ጠየኩት፡፡ ተገርሞ በትህትና ‹‹የለም›› አለኝ፡፡ እርሱም እንደ እኔ የገባው ነገር ሳይኖር የቀረ አልመሰለኝም፡፡ እኔ ግን ሳይሰማ ጩኸቴን አቀለጥኩት፡፡ የታሉ ሰባ አምስት በመቶ የተጉት፣ የታሉ ረድተው የተዘነጉት፣ የታሉ ሰጥተው ፎቶ ያልሰቀሉት እኮ የታሉ ለነፍስ ብለው ለማያውቁን የቸሩት . . . ግብዝነታችን ፍንትው አለልኝ፡፡ ‹‹ትንሽ ይዘህ ካለው ተጠጋ›› የሚለው ቀማኛ ኑሮአችን አመመኝ፡፡    


      ጽድቅን የሚያደርጉ ለፎቶአቸው እንኳ ቦታና ክብር የላትም፡፡ ክርስቶስን መምሰል ክርስቶስ ባለፈበት ደግሞ ማለፍ መሆኑን ልብ አልኩ፡፡ ዓመተ ምሕረት እንኳ በአግባቡ ያልተፃፈበት፣ ተለምዶአዊ የሆነውን ሥርዓት እንኳ በአግባቡ ያላሟላ የይምሰል መረጃ በእርግጥ ንጉሡ ከፍ ብለው በተሰቀሉበት ክፍል ውስጥ ከዚህ በበለጠ የሚደምቅ ነገር ሊኖር አይችልም፡፡ ይህንን ሆስፒታል ትልቁም ትንሹም፣ ክርስቲያን ሙስሊሙም፣ ደሀ ሐብታሙም ይታከሙበታል፡፡  ኤቫንጄሊካል ቤተ ክርስቲያን የሚለው ግን የተወሰነ ወገንን ሊያሳይ ይችላል፡፡ ፍቅር ድንበር ይሻገራል፡፡ ሰውን ሳይሆን እውነትን ይታዘዛል፡፡ መታሰቢያው የጽድቅ ተግባሩ ነው፡፡ ፍቅር ይሰጣል አይቆጥርም፡፡ ያደርጋል ምላሽ አይጠብቅም፡፡ ፍቅር ወድዶ፣ ሰጥቶ፣ ረድቶ፣ አግዞ፣ አሻግሮ ዘወር ማለት ነው፡፡ ፍቅር እግዚአብሔርን የማሳየት ተግባር ነው፡፡ ፍቅር ራስን ሸሽጎ የሞተውን ደግሞም ከሙታን ተለይቶ የተነሣውን ክርስቶስን መግለጥ ነው፡፡ በአስራ አምስት በመቶ ድርሻ እንዲህ መካብ ያሳፍራል፡፡ ትንሽ ያላት እንቅልፍ የላትም አይደል፡፡ ጽሑፌን አንድ ድምጽ ገታው ‹‹ጽዳቶቹ ጨርሰዋል›› የሚል፡፡ እኔ ግን አልኩ ‹‹ምነው ይህንንም ባጸዱት››! ፍቅራችሁ ያለ ግብዝነት ይሁን፡፡ ጸጋ ይብዛላችሁ! 

3 comments:

  1. Always u touch my heart,&I don't know
    how many people visit that hospital
    day after day,week after week,year after year,but no one figures out what
    was wrong on that picture or whatever
    it's that is not there business ,u touch
    alot of things &u point out who &how
    made that kind of mistake,some where
    Some place some body screw-up,but
    for all this years no one says nothing,
    but finally u flash the light,good job
    Personally I do appreciate your comments u did outstanding and
    tangible work,l blame majesty also
    People surrounding them,they made
    a huge mistake through their legacy,
    Specially Ethiopian church,even at that
    time I don't know who was leading that
    Church still this period of time,the church needs stand by its own,

    ReplyDelete
  2. amazing vision with phenomenal lessons God bless you !!!
    but በአስራ አምስት(?25%) በመቶ ድርሻ እንዲህ መካብ ያሳፍራል

    ReplyDelete
  3. ብዙ አድርጋችሁ ጥቂትም እንደከበደው ኑሩ፡GOD bless ethiopia

    ReplyDelete