Monday, December 30, 2013

ለልደቴ

                      Please Read in PDF: Lelidete

‹‹ለሰብእ ሰብእ ዘየዐብዮ በምንት፤
አምጣነ ኩሉ ዕሩይ በጊዜ ልደት ወሞት፡፡››
ትርጉም፡ -
‹‹ሰው ከሰው በምን ይበልጣል፤
ልደትና ሞት አንድ ያደርገዋል፡፡››  

                           (አለቃ ጥበቡ ገሜ)

       ወደዚህ ምድር መምጣት ቀላል እንዳልሆነ የነገረችኝ እናቴ ናት፡፡ ያማጠ ያውራ፡፡ የወለደ ይናገር፡፡ መወለድ ጸጋ ነው፡፡ ወላጅ፣ ስፍራ፣ ሕዝብ፣ ሁኔታ መርጠን አልተወለድንም፡፡ ዳሩ ግን ወደ ማስተዋል ስንመጣ ራሳችንን እዚህ አግኝተነዋል፡፡ ተመስገን! እንደ አሳቡ ሁሉን የሚፈጽም፣ ለአድራጎቱ ከልካይ የሌለበት አምላክ ስሙ ብሩክ ይሁን፡፡ የአርያም ደጆች ተከፈቱ፡፡ ያበጃጀኝን መዳፍ አየሁት፡፡ ከምድር አፈር የሠራኝን፣ የሕይወት እስትንፋስ እፍ ያለብኝን፣ ለእኔ ተጠቦ ገነትን ስፍራ የሰጠኝን፣ መልክና ምሳሌው ያደረገኝን፣ ቢስት እመልሰዋለሁ፣ ቢጠም አቀናዋለሁ፣ ልጅነቱን አሳድጋለሁ፣ አለማወቁን አስተምራለሁ ብሎ ኑር ያለኝን ልብ አልኩት፡፡

        መጪውን እያየ፣ መዳረሻዬን እያወቀ የፈጠረኝን የአባቶች አባት፣ የወላጅ ጥግ፣ የመውደድ ዳርቻ ኤሎሂም ወሰን መስፈሪያ በሌለው ክብር በዙፋኑ ሆኖ አስተዋልኩት፡፡ የልቤን ዓይኖች ወደ ጸጋው ዙፋን ዘረጋሁ፡፡ አባባ እንዲህ አለኝ ‹‹አሳብ ሳለህ ያሰብኩህ፣ ጽንስ ሳለህ ሰው ያልኩህ እኔ ነኝ›› ገጹ በማይቆጠር እጥፍ ያበራል፡፡ ሁሉን የሚችል ብርታቱ፣ ደከመኝ ሳይል የሚሸከም ፍቅሩ፣ ያለመጥፋት ዋስትና ምህረቱ፣ የማይናድ የማይፈርስ ኪዳኑ፣ አመጽን የማያውቅ ጽድቁ በግልጥ ይነበባል፡፡

      መለስኩ ‹‹ዛሬም ልታወራኝ በናፍቆት ያለህ አንተ ብቻ ነህ፡፡ መከፋቴን እንደ በር ከፍተህ የገባህ፣ የዘመኔ ፈቃጅ፣ ለጉዳቴ ፈራጅ፣ ክብርን ሁሉ ወሳጅ አዎ አንተ ነህ፡፡ ለልደቴ ኬክ ሳይሆን ልጅህን የቆረስክ፣ ሻማ ሳይሆን ደም የለኮስክ ስምህ ይቀደስ›› የአእላፍ መልአክት አሜንታ ተሰማ፡፡ ለታረደው በግ ‹‹ክብር ይሁን›› እንደ ብዙ ውኃዎች ድምጽ አስተጋባ፡፡ ለዘላለም መወለዴን፣ ለበለጠው መታሰቤን፣ ታማኝ ሆኜ መቆጠሬን እያሰብኩ ቀጠልኩ ‹‹ጌታ ሆይ ባሪያህ ምን አቅም አለው፡፡ እንዳደረክልኝ ላደርግልህ፣ እንደ ወደድከኝ ልወድህ፣ እንዳሰብክልኝ ላስብህ ምን አቅም አለኝ? የሰጠኸኝን የምቀበልበት ጉልበት አንተው አይደለህምን? እንደ ፍጡር ያየኝ ፈጣሪነትህ ይባረክ፡፡ እንደ ልጅ ያደረገኝ አባትነትህ ይቀደስ፡፡ ከልቤ እንባ . . ››

       ለልደቴ ያሰፋውን ጽድቅ እያየሁ ግሩም ድንቅ አልኩ፡፡ በስስት እያየ በፍቅር ያለበሰኝን ደጋግሜ እየተመለከትኩ መገረም ሞላኝ፡፡ ችንካር ያለፈባቸውን የጌታ እጆች፣ የእሾህ አክሊል የደፋ ራሱን፣ ምራቅ የተተፋበት ፊቱን፣ በቁስል የተገመደ ጀርባውን፣ እንደሚታረድ በግ በሸላቾቹ ፊት ዝም ያለ አንደበቱን፣ እርቃኑን የቀረ አካሉን ትኩር ብዬ አሰብኩ፡፡ የተወለድኩበት ምጥ፣ እኔ እኔን የሆንኩበት መከራ ድቅን አለብኝ፡፡ ሰው ከሰው በምን ይበልጣል፣ ልደትና ሞት አንድ ያደርገዋል፡፡ ኢየሱስ ግን ይበልጣል፡፡ ሰውም በክርስቶስ ሲሆን ይበልጣል፡፡ ለልደቴ አባባ እንዲህ አለኝ ‹‹ስጦታዬ ይኸው፡- ልጄን ሰጠሁህ›› አሜን!   

3 comments:

  1. Yehien Mastewal Yesteh Fetari Yimesgen, Lekbru wesen yelelew Fikru ejig yebeza Medhanealem Yemezgen, Kale hiwot Yasemalegn, berta.

    ReplyDelete
  2. ‹ስጦታዬ ይኸው፡- ልጄን ሰጠሁህ›› አሜን!

    ReplyDelete
  3. egziabher tsegawin yabzalih

    ReplyDelete