‹‹የዚያን ጊዜ እኔ በእርሱ ዘንድ ዋና ሠራተኛ ነበርሁ ዕለት ዕለት
ደስ አሰኘው ነበርሁ፥ በፊቱም ሁልጊዜ ደስ ይለኝ ነበርሁ፥ ደስታዬም በምድሩ ተድላዬም በሰው ልጆች ነበረ።›› (ምሳ. 8፥30-31)፡፡
ቅዱሳት መጻሕፍት የዘላለም አባት፣
የዘላለም ልጅ እና የዘላለም መንፈስ እንዲሁም የዘላለም አሳብ እንዳለ በግልጥ ይናገራሉ (ዘዳ. 33፥27፣ ዮሐ. 1፥1-2፣ ዕብ.
9፥14፣ ኤፌ. 3፥11)፡፡ ፍጥረት በመለኮት ጉባኤ ውሳኔ ወደ ሕልውና ሳይመጣ፣ ሰው በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ ሳይሆን፣ ሰማያትና
ምድር ሳይከናወኑ፣ ከዘመን መቆጠር አስቀድሞ ባልተፈጠሩ ሰማያት፣ ባልተቆጠሩ ዘመናት የአብ፣ የወልድና የመንፈስ ቅዱስን አኗኗር
ስንመለከት በአካል ሦስትነት የባሕርይ አንድነታቸውን እናስተውላለን፡፡ ሦስት አካላት የሚደሰቱበት አንድ የመለኮት ደስታ ወደ ሕሊናችን
ይመጣል፡፡ በጉባኤው መካከል የእርስ በእርስ ተድላቸውንም ልብ እንላለን፡፡
አባት
በልጁ ደስ ሲሰኝ ልጅም በዚያው ልክ ያለመቀዳደምና መበላለጥ በአባቱ ደስ ይሰኛል፡፡ መንፈስ
ቅዱስም እንዲሁ፡፡ ሕብረትን የሚሻ እግዚአብሔር ከፍቅሩ የተነሣ ደስታው በምድሩ፣ ተድላውም በሰው ልጆች መካከል እንዲሆን ወደደ፡፡
እግዚአብሔርም
አለ፦ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም
ሁሉ ይግዙ (ዘፍ. 1÷26)። ሰው እግዚአብሔር ያሰበለት አሳቡ፣ ያየለት ዕይታው፣ ያዘዘው ኑሮው አልሆን ብሎት ባለመታዘዝ አምላኩን
በደለ፡፡ ጥንቱንም በምክሩ ቢበድል አድነዋለሁ፡፡ ለኃጢአቱም ቤዛ እከፍላለሁ ያለ ፈጣሪ ለሰው የመዳንን ተስፋ በበደለበት ሥፍራ
ነገረው፡፡ እግዚአብሔር በመልኩ እንደ ምሳሌው የፈጠረው ሰው በመልኩ እንደ ምሳሌው ኃጢአተኛ እየወለደ ሁሉ ኃጢአትን ሰርተዋል ተባለ
(ሮሜ. 3)፡፡ የእግዚአብሔርም ክብር እንደ ጎደለን የጎደለን እግዚአብሔር ነገረን፡፡
የእግዚአብሔር
ልጅ በሥጋ ተገለጠ፡፡ በመለኮት አስቀድሞ ማወቅ ለታየው የሰው በደል ‹‹እኔ ቤዛ እሆናለው›› ያለው ወልድ ከድንግል ተወለደ፡፡
የዚህችም ድንግል ስሟ ማርያም ነው፡፡ ‹‹ኮነ ወልደ እጓለ እመሕያው ዘበአማን ወውእቱ ፍኖት ዘይመርሀነ ኀበ አቡሁ ቅዱስ /እርሱም
በእውነት ሰው የሆነ ወደ ቅዱስ አባቱ የሚመራን መንገድ ነው/››፡፡ በዘላለማዊ ልደት የአብ የዘላለም ልጅ የእግዚአብሔር ቃል ወልድ
የሰው ጠባይዕ የሆኑትን ነፍስን ሥጋን መንፈስን ተገንዝቦ ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እኛን መሰለ፡፡ እኛም ፍጹማንና ምሉዓን የሆኑት
መለኮቱና ሰውነቱ የባሕርይ መደባለቅና መለወጥ የአቅዋም ሽረትና ፍልሰት ሳይኖርባቸው ጭራሹን ያለመለየትና ያለመከፈል በአንዱ የአካል
ተዋሕዶ አንድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን እናምናለን፡፡