Thursday, January 16, 2014

ከዛፉ ውረዱ


                                  Please Read in PDF: Kezafu Weredu


                     
                                         ሐሙስ ጥር 8/ 2006 የምሕረት ዓመት

        ለአገልግሎት ወደ አንድ ከተማ ሄጄ ካሰብኩበት ቦታ እንዲያደርሰኝ በፈረስ ተጎታች ጋሪ ላይ ተሳፈርኩ፡፡ እስቲ እኔም ወግ ይድረሰኝ፣ ኮንትራት ልያዝ ብዬ ሙሉ ሂሳቡን ልከፍለው ተስማምቼ መንገድ ቀጠልን፡፡ ትንሽ በሄድን ቁጥር ሾፌሬን ሰዎች በተደጋጋሚ ሰላምታ ይሰጡታል፡፡ ታዲያ ማን ብለው እየጠሩ መሰላችሁ ‹‹ዶክተር›› በጣም ተገርሜ ‹‹ያሉት እውነት ነው?›› ብዬ ጠየኩት፡፡ እርሱ ግን እየሳቀ ‹‹ቆጥረውኝ ነው›› አለኝ፡፡ እኛ ማኅበረሰብ ውስጥ እየተቆጠረላቸው ከሆኑት በላቀ፣ ከጨበጡት ባለፈ የሚታሰቡ ብዙ ሰዎችን አስተውያለሁ፡፡ ይህ ግን አግራሞቴን አገሸበው፡፡ ሰዉ ለዓመታት ቀን ከሌሊት ደክሞ የሚደርስበትን ሙያ እርሱ እያፌዘ ሲጠራበት ተደነኩ፡፡ በሙያ ስሞች የሚደረጉ ማጭበርበሮችን ሰምቻለሁ፡፡ ቢያንስ እንደዚህ የሚጠራው ጋሪ ነጂ (ዶ/ር) ማኅበረሰቡን ልብላው፣ ላጭበርብረው፣ ላምታታው፣ ቀን ልውጣበት ብሎ አለመነሣቱ፤ ያለውን ኑሮ ተቀብሎ ለሥራ መልፋቱ በልቤ መደነቅ፣ ከንፈሬ ላይ አግራሞት፣ ኮንትራቱ ላይ ደግሞ ተጨማሪ አንድ ብር አስገኘለት፡፡

        መንደሮቹን ስናሳብር ‹‹ዶክተሬ›› ብላ አንዲት መልከ መልካም ሸንቃጣ ወጣት ‹‹ስትመለስ›› አይነት እጇን አወዛወዘች፡፡ ደግሞ እሷን ‹‹ምኗን አክመሃት ነው?›› አልኩት፡፡ እንደ ማፈር ሲል ‹‹ግድ የለም ንገረኝ ያለው ጋሪና ፈረሱ ነው፡፡ ይታዘበኛል ካልክ ያለ ሰው ምስክር እኔን ነው›› ብዬ አደፋፈርኩት፡፡ ከጠየከኝማ ብሎ ነው መሰል ያስነወራቸውን፣ ሲያልፍም ልጅ ያስወለዳቸውን፣ እንደ ሕመምተኛ ተቅለስልሰው የቀረቡትንና የፈወሳቸውን (በሱ ቤት) ዘረዘረልኝ፡፡ እጅብ ያለ ማሳ የመሰለ ጠጉሩን፣ በሻርብ የተጠቀለለ ፊቱን፣ አቧራ የተኳለ ዓይኑን አፍጥጬ አየሁት፡፡ እሺ! ዶክተር በሚል ስሜት ራሴን ወዘወዝኩለት፡፡ ብዙ እንደ ሰማሁ የማልጽፈውን ቀዶ ጥገና ነገረኝ፡፡ በገባው ላናግረው ብዬ ‹‹ለመሆኑ የካርድ ይከፍላሉ›› አልኩት፡፡ ተያይተን ተሳሳቅን፡፡
       ወደ መዳረሻዬ ስቃረብ ‹‹ውይ! ሞት ይርሳኝ›› ብሎ ‹‹ዛፍ ላይ ትወጫለሽ›› አለኝ፡፡ እውነቱን ለመናገር ‹‹ምን አስቦ ነው›› ብዬ ደነገጥኩ፡፡ በአገልግሎት የረገጥኳቸውን ብዙ ቦታዎች አስታውሳለሁ፡፡ በተለይ ጠንቋይ አስካዳችሁ ተብለን ለሞት የተገለገልንበትን አጋጣሚ ሁሌም የምስጋና ርእሴ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ እዚህ የተራቆተ እሾሃማ ዛፍ መሀል ስንደርስ ‹‹ምን ነካው?›› ብዬ አሰብኩ፡፡ ምድር ላይ እንዳሉት አየር ላይ ሆኜ ዶ/ር ስላላልኩት ይሆን? ወይስ እንዲህ ያለውን ማዕረግ ነጣቂ መጣብኝ ብሎ አስቦ ይሆን? አልኩ፡፡ ትካዜዬን በሚገፍ መልኩ በድጋሚ ‹‹እህ! ዛፍ ላይ አትወጪም›› አለኝ፡፡ ግብዣውን ተከትዬ እጁ ያረፈበትን ጥቅልል ጫፉን አየሁት፡፡ ሳቅ በሳቅ . . አሁንም ሳቅ . . ለካ ጫት ትቅማለህ ወይ? ማለቱ ነው፡፡ የልቤን ትከሻ እየነቀነቅሁ ሥጋቶቼን እርግፍ አድርጌ ወደ ጨዋታችን ተመለስን፡፡ ባለማወቄ በተራው እርሱ እየተደነቀ ‹‹በዚህ እድሜህ ዛፍ ላይ እንዴት መውጣት አልቻልክም?›› በማለት የሞያተኛ ደንብ ልብስ የመሰለ የማዳበሪያ ኮቱን ኮሌታ እያስተካከለ (ዶ/ር) ጠየቀኝ፡፡

      ወጣቱ ከልቤ አሳዘነኝ፡፡ የማኅበረሰቡ ሽንገላና የገዛ ራሱ ፌዝ መጫወቻ መሆኑ ተሰማኝ፡፡ ሱስና ሴሰኝነት የገዛው አካሉን መድኃኔዓለም እንዲወርሰው ተመኘሁ፡፡ በየክፍለ ሀገሩ እንደዚህ ባክነው ኖረው የሚያልፉ ጎበዞችን፣ ለሰውም ለራሳቸውም ያልሆኑ ብኩኖችን አሰብኳቸው፡፡ ያንን የዛፍ ላይ ሰው ‹‹አንተ ግን ሐኪም አለህ?›› ስል በትህትና ጠየኩት፡፡ እየሳቀ ‹‹ለዶ/ር ደግሞ ምን ሐኪም ያስፈልገዋል›› ብሎ መለሰልኝ፡፡ ችግሩ ያልገባው መፍትሔው ያጥረዋል፡፡ ከሚረባው ጋርም መገናኘት ለእርሱ ጭንቅ ነው፡፡ መንፈሳዊ ሕመሙን፣ ሥጋዊ ኪሳራውን እንዲያስተውል የቻልኩትን ያህል አስረዳሁት፡፡ የእኔን ዶ/ር ላስተዋውቅህና አብራችሁ ሥሩ አልኩት፡፡ ‹‹ቀልድ ነው ወይስ ቁምነገር›› በሚል መንፈስ ወደ ጎን ገርመም አደረገኝ፡፡ እኔ ቀጠልኩ፡፡ ከዛሬ ሁለት ሺህ ዓመት በፊት እንደ አንተ ላሉ ኃጢአተኞች እግዚአብሔር የሚወደውን አንድ ልጁን ለሞት ሰጥቶአል፡፡ እርሱም የዓለም መድኃኒት ነው፡፡ ክርስቶስ ኢየሱስ! ‹‹እርሱ መድኃኒት የሚያዝልህ ሳይሆን አንተው የምትወስደው መድኃኒት ነው፡፡ ለችግሮችህ መፈታት፣ ለሸክሞችህ መቅለል፣ ለአእምሮህ ሰላም ፍቱን መልስ ነው፡፡ እንዲህ ያለውን ዶ/ር አትፈልግምን?›› አልኩት፡፡ ጽድቅ ይሁንህ ልበሰው፣ ትምክህት ይሁንህ ታጠቀው፣ ቅድስና ይሁንህ አጊጥበት አልኩት፡፡ አብረኸው ሥራ ማለቴ ፈቃድህን ለፈቃዱ አስረክብ ማለቴ ነው፡፡

       ለመንኩት ‹‹እኔ ከዚህ ጋሪ ሳልወርድ ከዛፉ ላይ ውረድ›› አልኩት፡፡ እንደ ቀድሞው ሊቀልድ አቅም አጣ፡፡ ትርፍና ኪሳራ እንሥራ ተባባልን፡፡ እስከ ዛሬ የቃምከው ዳቦ ቢሆን ስንት ምስኪኖችን ያጠግባል? እስከ አሁን ያጨስከው ሲጋራ እንጨት ቢሆን የስንት ሠርግ ወጥ ያበስላል? አሁንም እንኳ ሴቶች ላይ የምታባክነው አቅም ስንት ያቀና ነበር? ተባባልን፡፡

       ከዚህ ስትወርድ የምትወጣበትን ሌላ ዛፍ ላሳይህ ብዬ ‹‹እውነተኛ የወይን ግንድ እኔ ነኝ፤ ገበሬውም አባቴ ነው። ፍሬ የማያፈራውን በእኔ ያለውን ቅርንጫፍ ሁሉ ያስወግደዋል፤ ፍሬ የሚያፈራውንም ሁሉ አብዝቶ እንዲያፈራ ያጠራዋል።›› (ዮሐ. 15÷1-2) የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ነገርኩት፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከዛፍ ጋር የተያያዘ ነገር እንዳለ አስቦት እንደማያውቅና ክርስቲያን ያለ ግንዱ ምንም ማድረግ የማይችል በዛፉ ላይ ያለ ቅርንጫፍ መሆኑን እንዳላስተዋለ ተነፈሰልኝ፡፡ አእምሮን የሚገዛ፣ ለፍሬያማነታችን የሚጨነቅ፣ በጎነታችን ግድ የሚለው፣ አብዝቶ የሚያጠራ እርሱ ጌታ እንደ ሆነ ገለጥኩለት፡፡ የልቡን ባላውቅም ምላሱ ግን ከዛፍ ላይ ወረደ፡፡ የብክነት ኑሮው ቆጨው፡፡ ሸክም ሲቀልለት፣ እድፍ ሲጸዳለት፣ ብርሃን ሲበራለት በመንፈስ አስተዋልኩ፡፡

      ተወዳጆች ሆይ የትኛው ዛፍ ላይ ናችሁ፡፡ ብዙ አመፆች ወደ ተግባር የሚሻገሩት በሱስ ኃይል ግፊት እንደ ሆነ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ ሰዎች በሚያዙት ማንነታቸው የሕሊናም የሕግም ተጠያቂነትና ኃላፊነት እንዳለባቸው ስለሚገነዘቡ ይህንን ሽሽት የብዙ ነገር ሱሰኛ (ባሪያ) ይሆናሉ፡፡ ለዚህ ጽሑፍ ጫት አብዛኛውን ወሰደ እንጂ ሱስ ልዩ ልዩ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ቴክኖሎጂው እያደገ፣ የትውልዱ ስልጣኔ ጥማት እየጨመረ በመጣበት በዚህ ዘመን ሱሰኝነት በየፈርጁ ነው፡፡
-      ይቀጥላል -


2 comments: