Sunday, January 19, 2014

ልዩ፡ በመለኮት ጃን ሜዳ

                                       Pleas Read in PDF: Yemelekot Janmeda
                                                                     
      ‹‹የዚያን ጊዜ እኔ በእርሱ ዘንድ ዋና ሠራተኛ ነበርሁ ዕለት ዕለት ደስ አሰኘው ነበርሁ፥ በፊቱም ሁልጊዜ ደስ ይለኝ ነበርሁ፥ ደስታዬም በምድሩ ተድላዬም በሰው ልጆች ነበረ።›› (ምሳ. 8፥30-31)፡፡

       ቅዱሳት መጻሕፍት የዘላለም አባት፣ የዘላለም ልጅ እና የዘላለም መንፈስ እንዲሁም የዘላለም አሳብ እንዳለ በግልጥ ይናገራሉ (ዘዳ. 33፥27፣ ዮሐ. 1፥1-2፣ ዕብ. 9፥14፣ ኤፌ. 3፥11)፡፡ ፍጥረት በመለኮት ጉባኤ ውሳኔ ወደ ሕልውና ሳይመጣ፣ ሰው በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ ሳይሆን፣ ሰማያትና ምድር ሳይከናወኑ፣ ከዘመን መቆጠር አስቀድሞ ባልተፈጠሩ ሰማያት፣ ባልተቆጠሩ ዘመናት የአብ፣ የወልድና የመንፈስ ቅዱስን አኗኗር ስንመለከት በአካል ሦስትነት የባሕርይ አንድነታቸውን እናስተውላለን፡፡ ሦስት አካላት የሚደሰቱበት አንድ የመለኮት ደስታ ወደ ሕሊናችን ይመጣል፡፡ በጉባኤው መካከል የእርስ በእርስ ተድላቸውንም ልብ እንላለን፡፡  

      አባት በልጁ ደስ ሲሰኝ ልጅም በዚያው ልክ ያለመቀዳደምና መበላለጥ በአባቱ ደስ ይሰኛል፡፡ መንፈስ ቅዱስም እንዲሁ፡፡ ሕብረትን የሚሻ እግዚአብሔር ከፍቅሩ የተነሣ ደስታው በምድሩ፣ ተድላውም በሰው ልጆች መካከል እንዲሆን ወደደ፡፡ እግዚአብሔርም አለ፦ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ (ዘፍ. 1÷26)። ሰው እግዚአብሔር ያሰበለት አሳቡ፣ ያየለት ዕይታው፣ ያዘዘው ኑሮው አልሆን ብሎት ባለመታዘዝ አምላኩን በደለ፡፡ ጥንቱንም በምክሩ ቢበድል አድነዋለሁ፡፡ ለኃጢአቱም ቤዛ እከፍላለሁ ያለ ፈጣሪ ለሰው የመዳንን ተስፋ በበደለበት ሥፍራ ነገረው፡፡ እግዚአብሔር በመልኩ እንደ ምሳሌው የፈጠረው ሰው በመልኩ እንደ ምሳሌው ኃጢአተኛ እየወለደ ሁሉ ኃጢአትን ሰርተዋል ተባለ (ሮሜ. 3)፡፡ የእግዚአብሔርም ክብር እንደ ጎደለን የጎደለን እግዚአብሔር ነገረን፡፡

       የእግዚአብሔር ልጅ በሥጋ ተገለጠ፡፡ በመለኮት አስቀድሞ ማወቅ ለታየው የሰው በደል ‹‹እኔ ቤዛ እሆናለው›› ያለው ወልድ ከድንግል ተወለደ፡፡ የዚህችም ድንግል ስሟ ማርያም ነው፡፡ ‹‹ኮነ ወልደ እጓለ እመሕያው ዘበአማን ወውእቱ ፍኖት ዘይመርሀነ ኀበ አቡሁ ቅዱስ /እርሱም በእውነት ሰው የሆነ ወደ ቅዱስ አባቱ የሚመራን መንገድ ነው/››፡፡ በዘላለማዊ ልደት የአብ የዘላለም ልጅ የእግዚአብሔር ቃል ወልድ የሰው ጠባይዕ የሆኑትን ነፍስን ሥጋን መንፈስን ተገንዝቦ ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እኛን መሰለ፡፡ እኛም ፍጹማንና ምሉዓን የሆኑት መለኮቱና ሰውነቱ የባሕርይ መደባለቅና መለወጥ የአቅዋም ሽረትና ፍልሰት ሳይኖርባቸው ጭራሹን ያለመለየትና ያለመከፈል በአንዱ የአካል ተዋሕዶ አንድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን እናምናለን፡፡

     የሰው በደል በመለኮት ላይ የተሠራ በመሆኑ ሰውን የሚያድነው አካል ግድ መለኮታዊነት ያለው ሊሆን አስፈልጓም፡፡ የፍትህ ጥያቄ የተበዳይ ነውና፡፡ እግዚአብሔር ወልድ በሥጋና በደም ከእኛ ጋር ተካፍሎ በሰው መካከል ሰው ሆነ፡፡ እርሱ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው ነው፡፡ የሰው ልጆች መዳን የጠየቀው ዋጋ የእግዚአብሔርን አንድያ ልጅ ነው፡፡ የኃጢአት ክፋቱ በዚህ ይለካል፡፡ ውድ የሆነውን የእግዚአብሔር ልጅ ለመስቀል ሞት አድርሶታልና፡፡ በሥጋ በመገለጡ ከኃጢአት በቀር ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ፡፡ ሀዘናችንን የሚያዝን፣ ስደታችንን የሚሰደድ፣ ስቃያችንን የሚሰቃይ፣ ድካማችንን የሚደክም፣ በደላችንን የሚሸከም የሕማም ሰው ደዌንም የሚያውቅ ክርስቶስ (ኢሳ. 53)፡፡ ‹‹የእስራኤል ሥርዓተ ማኅሌትና የምጣኔ ሀብት መሠረት የነበረው የዚህ ሥርዓት እንቅፋትና አጥፊ ነው ተብሎ ሊገመት ነው፡፡ በሲና ተራራ ላይ ሕግን ያወጀው አሁን የሕግ ተላላፊ ነው ተብሎ ሊኮነን ነው፡፡ የሰይጣንን ኃይል ለመደምሰስ የመጣው ብዔልዘቡል ሊባል ነው፡፡ በምድር ላይ የእርሱን ማንነት የተረዳ አልነበረም፤ ስለዚህ በአገልግሎቱ ዘመንም ብቻውን መሆን ነበረበት›› /አበበ ብዙነህ፣ የዘመናት ምኞት፣ ገጽ 94፣ 1988 ዓ.ም አ.አ/

       ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አማራጭ በሌለበት ሁኔታ ምርጫችን ‹‹አዳኝ›› ሆኖ መጣ፡፡ በሰው ልጆች መካከል የተገኘ ደስታ፣ ለምድሪቱ የመጣ ተድላ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ በምንኖርበት ዓለም ላይ ስለ ብዙ ነገሮች እጥረት ይወራል፡፡ የምግብ፣ የመጠለያ፣ የትምህርት፣ የሰላም፣ የፍቅር . . እነዚህ ሁሉ ነገሮች ለሰባት ነጥብ አምስት ቢሊየን ሕዝብ ተሸራርፎ የሚደርስ የቤት ሥራ ነው፡፡ የዜና አውታሮች የሚያወጉን፣ እርስ በርሳችን የምንቀባበለውን ወሬ ጨምሮ መረጃው እንኳ ሥጋት ነው፡፡ መድኃኒት የለሽ በሽታዎች ቁጥራቸው በተበራከተበት በዚህ ዘመን የታመሙ ወገኖች ስለ እውነተኛ ፈውስና መድኃኒት መስማት ይሻሉ፡፡ ያለ ወንጀላቸው እንኳ እስራት የጸናባቸው፤ በነፍስ በሥጋ የሚሰቃዩ ሰዎች ስለ ፍጹም አርነት መስማት ይፈልጋሉ፡፡

       በባለጠጎች እልፍኝ ለውሻ የሚወረወረው ፍርፋሪ ቅንጦት የሆነባቸው ወገኖች በልቶ ማደር፣ ጠግቦ መሠማራትን መስማት በብርቱ ይናፍቃሉ (በተለይ ክርስትናችን እንዲህ ያለው ነገር ላይ እያፌዘ ይመስለኛል፡፡ በየአብያተ ክርስቲያናቱ ጉባኤ ላይ የእረኞች መወስለት፣ ጽኑ ዓመጽ የክፋት ሁሉ ሥር በሆነው ገንዘብ ነው፡፡ በክፉ ቀን ቀን የወጡበትን ወጪት እየሰበሩ በእግዚአብሔር ስም በተሰበሰበው ላይ እየፋነኑ በድህነቱ ባለ ጠጋ ያደረገንን ጌታ አደብዝዘውብናልና መለኮት ይገስፃቸው፡፡ የዛሬ ምቾት ለጌታ ጅራፉ ነውና ለልባቸው መደንደን በኃይል ይመልሳል)፣ ለዛሬ ኑሮ እጥፍ እጥፉን እየተጨነቁ እንደ አውታር ውጥረት የከበባቸው አእምሮን ስለሚያልፍ ሰላም መስማት ይፈልጋሉ፡፡

      ዓይኖቻቸው ዕንባን ያጋቱ፣ ፊታቸው ፍም የመሰለ፣ የልብ ስብራታቸውን፣ ከሰው የጨረሰ አካላቸውን የሚያስጠጉበት ጥላ፣ ሸክም የሚያቀልላቸው ብርቱ ክንድ አብዝተው ይሻሉ፡፡ ብዙ ማለዳዎች ለመርዶ እንቅልፍ አጥተው ባደሩ ወገኖች ዓይናቸውን ይገልጣሉ፡፡ የምሽቱም ዓይን ምሬት ተኩሎ፣ አስኳሉ ደፍርሶ ይጨፈናል፡፡ ሲመሽ መቼ በነጋ፣ ሲነጋ መቼ በመሸ በሚል የሸማኔ መወርወሪያ ፍጥነት የሚቅበዘበዙ ‹‹የምስራች ያለህ›› ይላሉ፡፡ ከዓለም የሆኑት የዓለምን ይናገራሉ፡፡ ለሰዎች ፍላጎትም ልዩ ልዩ አቅርቦት አላቸው፡፡ ግን በዚያ ውስጥም ሰዎች ማረፍ አልተቻላቸውም፡፡ ደስታና ተድላ ለሰው ልጆች ተንጠራርተው ያልደረሱበት የተሰቀለ ዳቦ ሆኖባቸዋል፡፡ የምስራች ያለህ!

       ‹‹ኢየሱስ ከሰላሳ ዓመታት ዝምታ በኋላ በውጭ ሥራ የሚጀምርበት ጊዜ ደረሰ፡፡ ይህም ዓለምን ሁሉ የሚነካ ጉዳይ ስለነበረ ሉቃስ የዮሐንስን መገለጥ ከሮሜ ገዥ ከጥቤርዮስ ጋር አያይዞአል (ሉቃ. 3÷2)፡፡ ዮሐንስ ተጋድሎን ያስተምር ስለ ነበረ ራሱም ተከተለው፣ ንስሐ ግቡ እያለ ሰበከ፡፡ ከሮማውያን ቀንበር ሳይሆን ከኃጢአት ባርነት ነፃ መውጣት አስፈላጊ መሆኑን አስረዳ፡፡ ስለዚህ ንስሐ መግባት ወይም ‹‹መመለስ›› ያስፈልጋል ብሎ አስተማረ፡፡ የአብርሃም ዘር በመሆን መመካት፣ እግዚአብሔር ከፈለገ ከድንጋይም ለአብርሃም ልጅ እንዲገኝ ሊያደርግ ይችላል (ሉቃ. 3÷7-9)፣ ነቢዩ ኢሳይያስ የተናገረው ይፈጸማል (ማር. 1÷2-4)፣ ኢሳ. 40÷3-5፣ ሚል. 4÷5-6)፡፡ አጥማቂው ዮሐንስ የኢየሱስን የበላይነት አልረሳም (ዮሐ. 1÷26-27፣ ማር. 1÷7-8)፡፡ ኢየሱስና ዮሐንስ በተገናኙ ቀን በዮሐንስ ትልቅ የትሕትና ስሜት ተገለጠ፣ መድኃኒት የሚያስፈልገው ለእርሱ መሆኑን ተረዳ (ማቴ. 3÷14-15)፡፡

       ጌታችን በመጠመቁ ራሱን ከኃጢአተኞች ጋር አንድ አደረገ (ኢሳ. 53÷12)፣ ወደ ዮሐንስ የመጣ ሁሉ ኃጢአቱን እየተናዘዘ ተጠመቀ (ማቴ. 3÷16)፣ ኢየሱስ ግን አልተናዘዘም፣ ኃጢአት የለውምና (ዮሐ. 8÷46፣ ዕብ. 4÷15)፡፡ ጌታ ራሱን ከሰው ዘር ጋር አንድ አድርጎአል፤ እርሱም ‹‹የሰው ልጅ ነውና››፣ የዮሐንስ ጥምቀት ደግሞ ከሰው ዘር ክፋት ጋር አንድ አደረገው፣ ጻድቅ ከኃጢአተኛ ጋር አብሮ ይቸገራል፡፡ ከብዙ ዓመታት በፊት በአባቴ ሥራ ላይ መሆን ይገባኛል ብሎ ነበር፣ አሁን የአባቱ ሥራ ምን እንደ ሆነ ይገልጣል፣ ሥራው የሰውን ዘር ማዳን ነው፡፡ በኋላ ሲናገር ሕግና ነቢያት እስከ ዮሐንስ ነበሩ ይላል (ሉቃ. 16÷16)፡፡ በብሉይ ኪዳን ሦስት ዓይነት ጥምቀት ነበረ፡- የውኃ፣ የዘይትና የደም (ዘጸ. 29÷4፣7፣ 20-21)፡፡ ዮርዳኖር፣ በተራራ ላይ መልክ መለወጥና ቀራኒዮ ሦስቱን ዓይነት ያመለክታሉ (ማቴ. 3÷15፣ ማር. 9÷7፣ ሉቃ. 23÷23)፡፡

      የኢየሱስ በውኃ መጠመቁ በደም የሚጠመቅ መሆኑን (ሕማማቱን) ያመለክታል፣ ዮርዳኖስ ወደ ቀራንዮ እንደሚመራው ገልጦ ነበርና፣ ‹‹የምጠመቃት ጥምቀት አለችኝ፣ እስክትፈጸም ድረስ እንዴት እጨነቃለሁ›› (ሉቃ. 12÷50)፡፡ የመድኃኒታችን ቅዱስ ሰውነት የሰማይና የምድር መገናኛ ነበረ (ዮሐ. 1÷52)፡፡ በብሉይ ኪዳን ተጀምሮ የነበረ የቅድስት ሥላሴ ምስጢር መገለጥ ይጀምራል፤ አንተ ልጄ ነህ (መዝ. 2÷7)፣ ጌታ ከኒቆዲሞስ ጋር ሲናገር አዲስ ልደት ያስፈልጋል አለ (ዮሐ. 5÷6)፡፡ ኢየሱስ ወደ ዮርዳኖስ ሲወርድ ብዙዎች ያወቁት የማርያም ልጅ መሆኑን ነው፡፡ ከዚያ ወጥቶ ግን ከዘላለም ያለውን ባሕሪውን ማለት የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን መግለጥ ይጀምራል፡፡›› /የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት፣ አባ ወ/ጊዮርጊስ ማቴዎስ፣ ገጽ 18-19፣ 1986 ዓ.ም አ.አ/

      ‹‹ኢየሱስም ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው ከውኃ ወጣ፤ እነሆም፥ ሰማያት ተከፈቱ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድ በእርሱ ላይም ሲመጣ አየ፤ እነሆም፥ ድምፅ ከሰማያት መጥቶ። በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው አለ።›› (ማቴ. 3÷16-17)፡፡

      እግዚአብሔር አብ ስለ አንድያ ልጁ የተናገረው ምስክርነት ምንኛ ድንቅ ነው፡፡ ‹‹በእርሱ ደስ የሚለኝ›› በመለኮት ጃን ሜዳ የተሰማ እንደ ብዙ ውኃዎች ድምጽ በደመና የተነገረ ‹‹የምድሪቱ ተድላ››፤ ጌታ በተወለደ ጊዜ መልአኩም እንዲህ አላቸው፦ እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ (ሉቃ. 2÷10) ተብሎ እንደተፃፈ አብ የመልእክተኛውን ምስክርነት ከምንጩ አመሳከረው፡፡ አብና መንፈስ ቅዱስ በአንድነት ሰምተነው የምናርፍበትን፣ አምነነው የምንድንበትን፣ ተከትለነው የምንባረክበትን ‹‹ወልድ›› እነሆ አሉን፡፡ ሰው ከመለኮት ባሕርይ ተካፋይ ሆነ (2 ጴጥ. 1÷4)፡፡ አስቀድሞ ዓለም ሳይፈጠር በመለኮት ጉባኤ ያለው ደስታ የሰው ልጆችም ደስታ ሆነ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የአብ ደስታ የሆነው ዮርዳኖስ ወንዝ ላይ አይደለም፡፡ ከዘላለም ጀምሮ ለአባት ልጁ ደስታው ነው፡፡ ሐዋርያው ዮሐንስ ‹‹መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው።›› (ዮሐ. 1÷18) በማለት ወልድ በሥጋም ተገልጦ በአባቱ እቅፍ እንዳለ ያስረዳናል፡፡ ልብ ልንል የሚገባን ‹‹ነበረ›› አለማለቱን ነው፡፡ በአብ እቅፍ ያለው ጌታ በሥጋ እቅፍ ሆነ፡፡ ወደ ምድር ዝቅ ብሎ ወደ መለኮት ደስታ አደረሰን፡፡ ስሙ ይቀደስ!

      እግዚአብሔር አብ ስለ ልጁ በተናገረበት ክፍል ‹‹ደስታዬ›› የሚለው ቁልፍ ቃል ነው፡፡ ሰው በመለኮት ጉባኤ የደስታ ርእስ የሆነው ኢየሱስ የኑሮው ርእስ ካልሆነ ከሰው ሁሉ ይልቅ ምስኪን ነው፡፡ አብ በእርሱ ደስ የሚለኝ ካለ እኛም ‹‹በእርሱ ደስ የሚለው›› ልንል ግድ ነው፡፡ እግዚአብሔርን ደስ የምናሰኝበት እምነታችን ክርስቶስ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ዘመን ያስቆጠረ ‹‹በክርስቶስ ክርስቲያን የተሰኛችሁ›› የሚል ቋሚ ሰላምታ አላት፡፡ ክርስቲያን መሰኘት በክርስቶስ ነው፡፡ አትናቴዎስ ‹‹ሞተ በሞተ ዚአነ በእንተ ኃጢአትነ ከመ ያጥፍዖ ለሞት በሞቱ ቤዛነ /ቤዛችን በሚሆን መሞቱ ሞትን ያጠፋው ዘንድ ስለ ኃጢአታችን በእኛ ሞት ሞተ/›› እንዳለ የክርስትናው እምብርት የጌታችን ሞትና ትንሣኤ ነው፡፡

      የምስራች እጥረት ላለበት ዓለም ከእግዚአብሔር የሆኑቱ አቅርቦት ‹‹የናዝሬቱ ኢየሱስ›› ነው፡፡ ችግር፣ ሰቆቃ፣ ርሀብ፣ ጦርነት የየዕለቱ ዜና በሆነባት ምድር ተድላና ደስታችን ክርስቶስ ነው፡፡ ኃጢአት ለራት የማይበቃ ልጅ ያቦካው ሊጥ ያስመሰላትን ዓለም ጨው ሆነን የምናጣፍጥበት፣ ብርሃን ሆነን የምንደምቅበት፣ መልስ ሆነን የምንታይበት ዝርግፍ ጌጣችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ሐዋርያው በመልእክቱ ‹‹ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ፥ ደስ ይበላችሁ።›› (ፊል. 4÷4) ይለናል፡፡ ተወዳጆች ሆይ እኔም በዚያው መንፈስ እላችኋለሁ ‹‹በጌታ ደስ ይበላችሁ››!  

      ኢየሱስ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር ወልደ እጓለ እመሕያው ዘትማልም ወዮም በክመ ውእቱ እስከ ለዓለም አሐዱ ህላዌ ሎቱ ንስግድ ወንሰብሕ!!!!!!


No comments:

Post a Comment