Tuesday, January 7, 2014

እንኳን አልደረሳችሁ

                        Please Read in PDF: Enkuan Alderesachw

                             ታህሳስ 29 ቀን 2006 የምሕረት ዓመት

         ከሚታየው በሌላኛው ጎን መመልከት፣ ግዙፉን አልፎ ረቂቁን ማስተዋል ከበዓላቶቼ መካከል አንዱ ነው፡፡ ቃሉም ‹‹የሚታየው የጊዜው ነውና የማይታየው ግን የዘላለም ነው›› (2 ቆሮ. 4÷17) ይለናል፡፡ ሰዎች በተስማሙባቸው የተለዩ ቀናቶች ውስጥ ደስታ ብቻ ሳይሆን ሀዘን፣ እረፍት ብቻ ሳይሆን ሁከት፣ ሰላም ብቻ ሳይሆን ክርክርም ይስተዋላል፡፡ የመመገብ ሽር ጉድ እንዳለ ሁሉ ያለመብላት ፍላጎት፣ የመንቀሳቀስና ወዳጅ ዘመድን የመጠየቅ ዝንባሌ እንደሚስተዋል ሁሉ እግርና እጅን አጣጥፎ ከቤት ያለመውጣት ሲያልፍም የመተኛት ሁኔታ ይታያል፡፡ ሰዎች ሁሉ እንደዚህ ያሉት ቀናት የደስታ እንደሆኑ ቢስማሙም እንኳ ሁሉ ግን አይደሰትም፡፡

          ለዚህ ርእሰ ጉዳይ መነሻ የሆነኝ ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ለአገልግሎት ሄጄ ቤታቸውን ማረፊያ አድርገው በእንግድነት በተቀበሉኝ ቤተሰቦች ዘንድ ያስተዋልኩት አሳዛኝ ታሪክ ነው፡፡ እማወራዋ ከተቀመጡበት ለመነሣት፣ ከሰው ጋር ብዙ ለማውራት፣ የቀረበላቸውን ምግብ ለመብላት አቅሙም ሆነ ፍላጎቱ የላቸውም፡፡ አብዝቶ መተከዝ፣ ሲያልፍም ማንባት፣ ብቻ መቀመጥ፣ ስልቹነት የቀን ውሏቸው ነው፡፡ የልጆች ከበባ፣ የአባወራው ቁልምጫ፣ የእኛ የእንግዶቹ ማባበያ የሀዘናቸውን ክምር፣ የትካዜያቸውን ቁልል አልፎ ሊዘልቅ አልቻለም፡፡ አልፎ አልፎ ከሚቀምሱት ምግብ ውጪ ቀለባቸው መቆዘም ነው፡፡

        ለዚህ የዳረጋቸው የበዓልን ዋዜማ ለሥራ ወጥቶ፣ ከሽፍቶች በተተኮሰ ጥይት ጭንቅላቱን የተመታ ሬሳ (ልጃቸው) በዚያው ምሽት መኖሪያ ቤታቸው ድረስ መጥቶላቸው ነው፡፡ ከዚያን ቀን ጀምሮ ለእርሳቸው በዓል የሚባል ነገር ትርጉም አይሰጣቸውም፡፡ እርሳቸውን ‹‹እንኳን አደረሰዎ›› ማለት ለትካዜ ርእስ መስጠት፣ ላለፈ ሀዘናቸው ግርሻት መሆን ነው፡፡ እንደ ትኩስ ሬሳ ብቸኛ ወንድ ልጃቸውን ስላጡበት ክፉ አጋጣሚ ይተርኩላችኋል፡፡ ዓመታት ቢያልፉም እርሳቸው መቃብሩ ስር ያሉ ያህል በአሳብ ያምጣሉ፡፡ አለማልቀስ እርሳቸው ፊት አይቻልም፡፡ እንኳን ዕንባ ከዓይናቸው ፈስሶ ፍም የሚመስለው ፊታቸውንም ማየት ለወዮታ ይጋብዛል፡፡ ከብዙ ዓመታት በኋላም ፊቴ ላይ ድቅን ይሉብኛል፡፡


        ኑሮአችን መድረስ በምንፈልግባቸው ብዙ ፍላጎቶች የተጨናነቀ ነው፡፡ በተለይ መፎካከር ለእድገት እንደ አንድ ማሳያ ሆኖ በሚታይበት ዘመን ውስጥ እንኳን ቆመን ተንጠራርተንም ያልነካናቸው ነገሮች ይበዛሉ፡፡ ዳሩ ግን ልብ ለሚል ልብ ‹‹እንኳን አልደረስኩ›› ‹‹እንኳን አልደረሳችሁ›› የምንልባቸው ብዙ ነገሮች በኑሮአችን ውስጥ አሉ፡፡ ‹‹ሁሉ ተፈቅዶልኛል ሁሉ ግን የሚጠቅም አይደለም፤ ሁሉ ተፈቅዶልኛል ነገር ግን ሁሉ የሚያንጽ አይደለም›› (1 ቆሮ. 10÷23) ተብሎ እንደተፃፈ ሰውን እንኳን አልደረስኩበት የሚያሰኙት ነገሮች አሉ፡፡

        የአማራጭ መብዛት ሁሉንም ምረጥ የሚል መልእክት አይኖረውም፡፡ እግዚአብሔር ሲያደርስ ብቻ ሳይሆን ሲያስቀርም ጻድቅ ነው፡፡ መሻታችን ሲሟላ ብቻ ሳይሆን ሲቀርም እርሱ እውነተኛ ነው፡፡ አምላካችንን ለማመስገን ርእስ ሊሆኑን የሚችሉት የደረስንባቸው ነገሮች ብቻ አይደሉም፤ ያልደረስንባቸውም ጭምር እንጂ፡፡ ጌታ በቀጠለውም ባቋረጠውም ሕይወት አይከሰስም፡፡ ሙገሳንም አይሻም፡፡ ግን ሰው ነንና በተለይ ልንደሰትባቸው የተለዩ እንደሆኑ በምናስባቸው ቀናቶች በመሄድ፣ በክህደትና በሞት ያጣናቸውን ወገኖች በብርቱ አስበን እናዝናለን፡፡ ‹‹ምነው ዛሬን አብሮኝ/ አብራኝ ባሳለፈ፣ ምን አለ ይህንን ቀን እንኳ ከእኔ ጋር በታደመ›› የምንልበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡

       እግዚአብሔር ያየውን ብናይ፣ ያሰበውን ብናስብ፣ ያደረገው ቢገባን እንደዚህ ለማዘን ምክንያት የሆኑንን ሰዎች ‹‹እንኳን አልደረሳችሁ፣ እንኳን ያየሁትን አላያችሁ፣ እንኳን የገጠመኝ አልገጠማችሁ›› እንላቸው ነበር፡፡ የእግዚአብሔር አሳብ ከአሳባችን፣ መንገዱም ከመንገዳችን እጅግ የራቀች መሆኗ ከምናስበው የእኛ አሳብ በተለየ፣ ፊት ለፊት ከምንመለከተው በላቀ መንገድ ነገሮችን እንድናስተውል ይጋብዛል፡፡ በሕይወት ባለነው መካከል እንዲህ ያለው አሳብ አለ፡፡ ‹‹ባልደረሰኝ›› እና ‹‹ባልደረስኩበት›› የምንልባቸው ጉዳዮች፡፡ በጊዜ እግዚአብሔር ባይሰበስባቸው ኖሮ የሚረክሱና የሚያረክሱ፣ የሚጠፉና የሚያጠፉ፣ ለምድሪቱ ጭንቅና ተጨማሪ የቤት ሥራ የሚሆኑ ወገኖችን አስቧቸው፡፡ በድናቸው ነፍስ ቢዘራና በእናንተ ፊት ቢቆጩ ምን ትሏቸዋላችሁ? በእርግጥም ‹‹እንኳን አልደረሳችሁ›› ዓለማችን ላይ በስም ብንዘረዝራቸው የሚታክቱንን ክፉዎችና ዓመፀኞችን አስቡ፡፡ እንኳንም እግዚአብሔር የወደደውን አደረገባቸው፡፡

       ቢቆዩ ኖሮ ቆመው በሥጋ ከሞቱት በባሰ የመንፈስ ሞት ተከራተው ዘመናቸው የሚጨረሰውን፣ አሳብም መጠጥም እየተሳከረባቸው እንቅፋት ሆነው የሚያልፉትን፣ ቢቆዩ ኖሮ የጀመሩትን የክፋት አብዮት ከማቀጣጠል ባለፈ የከበረ ራእይ የማይኖራቸውን ሊሆኑ ያለውን አስቀድሞ አይቶ ጌታ እንኳን ለባሰ ቅሌት አላደረሳቸው፡፡ ደግሞ በአጭር የቀሩትን ለረጅም ዘመን የሚሆን በጎ ሥራ ያበረከቱትን አስቧቸው፡፡ እንኳንም እግዚአብሔር የወደደውን አደረገላቸው፡፡ ማቱሳላ ረጅም እድሜ ኖሮ ስለ ሕይወቱ ነጭም ጥቁርም አልተፃፈም፡፡ ዳሩ ግን ከእርሱ ያነሰ እድሜ የኖረው አባቱ ሄኖክ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር እንዳደረገና ወደ ሰማይ እንደተወሰደ ተጽፏል፡፡ እግዚአብሔር በሥራው ሁሉ ፍትሐዊ ነው፡፡ ሲያለሙ ቆይተው አፍርሰው ያጠናቀቁ፣ በመንፈስ ጀምረው በሥጋ የፈጸሙ፣ ለሰው ተርፈው ራሳቸውን የከሰሩ መድረስ ያበላሻቸው ናቸው፡፡

       ገናን አስመልክቶ ወገኔ እንዴት እንዳሳለፈ የቻልኩትን ተጉዤ ያልቻልኩትን ደውዬ መጠነኛ ዳሰሳ አድርጌ ነበር፡፡ እንኳን አደረሰህ ቀርቶ እንኳን አደረሰዎ የሚባሉ አዛውንቶች እንኳን በቁጥር ናቸው፡፡ ሥጋቸውን ድል አድርገው የሞሸሩ ሽማግሌዎች፣ በተለይ አመሻሹ ላይ ቃሪያ ሱሪያቸው ሰፍቶአቸው በስካር የራሱ ወጣቶች የየመንገዱ ዳርና የየመጠጥ ቤቱ ውስጣ ውስጥ ማዳመቂያ ናቸው፡፡ ነውሩን ክብሩ ያደረገን ሰው እንዴት ‹‹እንኳን አደረሰህ›› ትሉታላችሁ? ራሱን ችሎ ወጥቶ በመስቀያ የተመለሰውን ሰካራም ምን ብላችሁ ‹‹እንኳን አደረሰህ›› ትሉታላችሁ? በሱስና በዝሙት ዝሎ ቀፎው የሚፎክረውን ምስኪን እንዴት ሆኖ ‹‹እንኳን አደረሰህ›› ይባላል? እግዚአብሔር ለዚህ አያደርስም፡፡  

       የውጪ እድል ቢደርሳችሁ ሕይወትን ትከስሩ ከነበረ እንኳን አልደረሳችሁ፡፡ ሎተሪ ቢደርሳችሁ ሰውን እንደፋቃችሁት የዕጣ ወረቀት የምትቆጥሩ ከነበረ እንኳን አልደረሳችሁ፡፡ የመምራትና የማስተዳደር እድሉ ለእናንተ ቢደርስና ደሀ መበደያ፣ ትከሻ ማሳያ፣ እውነትን መደለያ፣ ከሀሰት ጋር መታያ ታደርጉት ከነበረ እንኳንም እድሉ ለእናንተ አልደረሳችሁ፡፡ ስኬት ላይ አለመድረሳችሁ እንደ እግር እሳት የሚያንገበግባችሁ ጌታ እናንተ ያላችሁት ላይ ባለመድረሳችሁ ያለውን ጥቅም አሳምሮ ያውቃል፡፡ የደረስንበት ሁሉ ልክ፣ ያገኘነው ሁሉ በረከት፣ የተሽቀዳደምንበት ሁሉ ድል አይደለም፡፡ ጸሎት ‹‹ክፈትልኝ›› ብቻ አይደለም፡፡ የሚረባኝ ካልሆነ ‹‹ዝጋብኝ››ም ተብሎ ይጸለያል፡፡

       ተወዳጆች ሆይ እኔ ግን የሚያስቆጨውን አለመድረስ እነግራችኋለሁ፡፡ ‹‹ወደ ጽዮን ተራራና ወደ ሕያው እግዚአብሔር ከተማ ደርሳችኋል፥ ወደ ሰማያዊቱም ኢየሩሳሌም፥ በደስታም ወደ ተሰበሰቡት ወደ አእላፋት መላእክት፥ በሰማያትም ወደ ተጻፉ ወደ በኵራት ማኅበር፥ የሁሉም ዳኛ ወደሚሆን ወደ እግዚአብሔር፥ ፍጹማንም ወደ ሆኑት ወደ ጻድቃን መንፈሶች፥ የአዲስም ኪዳን መካከለኛ ወደሚሆን ወደ ኢየሱስ፥ ከአቤልም ደም ይልቅ የሚሻለውን ወደሚናገር ወደ መርጨት ደም ደርሳችኋል›› (ዕብ. 12÷22)፡፡

ለሚመለከታችሁ ‹‹እንኳን አደረሳችሁ››

2 comments:

  1. ‹‹ወደ ጽዮን ተራራና ወደ ሕያው እግዚአብሔር ከተማ ደርሳችኋል፥ ወደ ሰማያዊቱም ኢየሩሳሌም፥ በደስታም ወደ ተሰበሰቡት ወደ አእላፋት መላእክት፥ በሰማያትም ወደ ተጻፉ ወደ በኵራት ማኅበር፥ የሁሉም ዳኛ ወደሚሆን ወደ እግዚአብሔር፥ ፍጹማንም ወደ ሆኑት ወደ ጻድቃን መንፈሶች፥ የአዲስም ኪዳን መካከለኛ ወደሚሆን ወደ ኢየሱስ፥ ከአቤልም ደም ይልቅ የሚሻለውን ወደሚናገር ወደ መርጨት ደም ደርሳችኋል›› (ዕብ. 12÷22)፡፡.........Amen!!!!!!!!!!!

    ReplyDelete
  2. ጸሎት ‹‹ክፈትልኝ›› ብቻ አይደለም፡፡ የሚረባኝ ካልሆነ ‹‹ዝጋብኝ››ም ተብሎ ይጸለያል፡፡......it's a blessing to make Jesus the lord of our life!

    ReplyDelete