ሐሙስ መጋቢት 11 ቀን 2006
የምሕረት ዓመት
‹‹ልጆች ሆይ፥ ኃጢአታችሁ ስለ ስሙ ተሰርዮላችኋልና እጽፍላችኋለሁ። አባቶች
ሆይ፥ ከመጀመሪያ የነበረውን አውቃችኋልና እጽፍላችኋለሁ። ጎበዞች ሆይ፥ ክፉውን አሸንፋችኋልና እጽፍላችኋለሁ።›› (1 ዮሐ.
2÷12-14)፡፡
መንገድ እየሄድኩ ግርግር ተፈጠረና ፈንጠር ብዬ የሚሆነውን በአንክሮ እከታተል
ጀመር፡፡ አንድ ወጣት እጅ ከፍንጅ አንዲት ጉብል ቦርሳ ውስጥ ተገኝቶ ኖሮ የጸጥታ አስከባሪዎች ከብበው ያናዝዙታል፡፡ ታዲያ በተጠየቅ
ሂደቱ አንድ የሚያውቀው ሌላ መንገደኛ ድምጹን ከፍ አድርጎ ‹‹እንዴ! እኔ አውቀዋለሁ፡፡ እርሱ ሌባ አይመስለኝም፤ እንዲያውም የሚጥል
በሽታ አለበት›› ብሎ መሰከረ፡፡ በዚህ ጊዜ ከጸጥታ አስከባሪዎቹ አንዱ፤ በበሰለ ነገር ላይ ደርሶ አስተያየት ለሰጠው መንገደኛ
‹‹ታዲያ ሴት ቦርሳ ውስጥ ነው እንዴ የሚጥለው?›› ብሎ ሲጠይቅ፤ በዙሪያው የቆመ ሰው ሁሉ ሳቀ፤ አንዳንዱም እኔን ጨምሮ ተሳቀቀ፡፡
ዶ/ር ኢዮብ ማሞ ‹‹እይታ /Mindset/›› በሚል መጽሐፋቸው ‹‹ስለምታስበው
ነገር ተጠንቀቅ፤ አሳቦችህ ወደ ቃላት ይለወጣሉና፡፡ ስለምትናገረው
ነገር ተጠንቀቅ፤ ንግግሮችህ ወደ ተግባር ይለወጣሉና፡፡ ስለምትተገብረው
ነገር ተጠንቀቅ፤ ተግባሮችህ ወደ ልማድ (ባህርይ) ይለወጣሉና፡፡
ስለ ልማድህ ተጠንቀቅ፤ ልማድህ የሕይወት ፍፃሜህን ይወስናልና›› (ዶ/ር ኢዮብ ማሞ፤ 2005 ዓ.ም፤ እይታ (Mindset)፤ አዲስ
አበባ) በማለት፤ አሳብና አመለካከት በእያንዳንዳችን ሕይወት ላይ ያለውን ጉልህ ተጽእኖ ይናገራሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔርን
አሳብ የያዘ መጽሐፍ ነው፡፡ የፈጠረን አምላክ እንዴት እንድንኖር መመሪያ የሰጠንም በዚሁ ቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ ነው፡፡ ሰው አሳቡን፤
ንግግሩን እና ተግባሩን የሚያነፃው በመለኮት አዋጅ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር የጠበቀ ግንኙነት ከሌለን የእግዚአብሔርን ፈቃድ
ልንረዳና ልንታዘዘው አንችልም፡፡