Thursday, March 20, 2014

የጉብዝና ወራት /ክፍል ሁለት/

                    Please Read in PDF: Yegubzna Werat

                       ሐሙስ መጋቢት 11 ቀን 2006 የምሕረት ዓመት


     ‹‹ልጆች ሆይ፥ ኃጢአታችሁ ስለ ስሙ ተሰርዮላችኋልና እጽፍላችኋለሁ። አባቶች ሆይ፥ ከመጀመሪያ የነበረውን አውቃችኋልና እጽፍላችኋለሁ። ጎበዞች ሆይ፥ ክፉውን አሸንፋችኋልና እጽፍላችኋለሁ።›› (1 ዮሐ. 2÷12-14)፡፡

         መንገድ እየሄድኩ ግርግር ተፈጠረና ፈንጠር ብዬ የሚሆነውን በአንክሮ እከታተል ጀመር፡፡ አንድ ወጣት እጅ ከፍንጅ አንዲት ጉብል ቦርሳ ውስጥ ተገኝቶ ኖሮ የጸጥታ አስከባሪዎች ከብበው ያናዝዙታል፡፡ ታዲያ በተጠየቅ ሂደቱ አንድ የሚያውቀው ሌላ መንገደኛ ድምጹን ከፍ አድርጎ ‹‹እንዴ! እኔ አውቀዋለሁ፡፡ እርሱ ሌባ አይመስለኝም፤ እንዲያውም የሚጥል በሽታ አለበት›› ብሎ መሰከረ፡፡ በዚህ ጊዜ ከጸጥታ አስከባሪዎቹ አንዱ፤ በበሰለ ነገር ላይ ደርሶ አስተያየት ለሰጠው መንገደኛ ‹‹ታዲያ ሴት ቦርሳ ውስጥ ነው እንዴ የሚጥለው?›› ብሎ ሲጠይቅ፤ በዙሪያው የቆመ ሰው ሁሉ ሳቀ፤ አንዳንዱም እኔን ጨምሮ ተሳቀቀ፡፡  

        ዶ/ር ኢዮብ ማሞ ‹‹እይታ /Mindset/›› በሚል መጽሐፋቸው ‹‹ስለምታስበው ነገር ተጠንቀቅ፤ አሳቦችህ ወደ ቃላት ይለወጣሉና፡፡ ስለምትናገረው ነገር ተጠንቀቅ፤ ንግግሮችህ ወደ ተግባር ይለወጣሉና፡፡ ስለምትተገብረው ነገር ተጠንቀቅ፤ ተግባሮችህ ወደ ልማድ (ባህርይ) ይለወጣሉና፡፡ ስለ ልማድህ ተጠንቀቅ፤ ልማድህ የሕይወት ፍፃሜህን ይወስናልና›› (ዶ/ር ኢዮብ ማሞ፤ 2005 ዓ.ም፤ እይታ (Mindset)፤ አዲስ አበባ) በማለት፤ አሳብና አመለካከት በእያንዳንዳችን ሕይወት ላይ ያለውን ጉልህ ተጽእኖ ይናገራሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔርን አሳብ የያዘ መጽሐፍ ነው፡፡ የፈጠረን አምላክ እንዴት እንድንኖር መመሪያ የሰጠንም በዚሁ ቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ ነው፡፡ ሰው አሳቡን፤ ንግግሩን እና ተግባሩን የሚያነፃው በመለኮት አዋጅ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር የጠበቀ ግንኙነት ከሌለን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ልንረዳና ልንታዘዘው አንችልም፡፡
         የአሳብን ብርታት ለመረዳት በዙሪያችን ያሉ፤ ሰው ያለማቸውንና ሰው ያበላሻቸውን ነገሮች መመልከት ብቻ በቂ ነው፡፡ ከነዚህ ነገሮች ያጨድነውን ደስታም ሆነ ሀዘን መለስ ብሎ ማሰላሰሉ ደግሞ ለመፍትሔ ከበቂ በላይ ማነሳሻ ይሆናል፡፡ በክፍል አንድ ጽሑፋችን ‹‹አሳብ›› ምን ያህል ጉልበት እንዳለው ለማየት በጥቂቱ ሞክረናል፡፡ ጥሩ እየበሉ ካደጉ ልጆች በላይ ጥሩ እያሰቡ ያደጉ፤ በምቾት መካከል ከተቀመጡ ሰዎች በላይ በበጎ አመለካከት የኖሩ፤ ለምድሪቱ እንደ መፍትሔ ናቸው፡፡ አሳብ በበጎም ሆነ በክፉ አንድን ሰው የመቅረጽ አቅም አለው፡፡ ክፉ የሚያስብ ያማረ ቤት ውስጥ ቢቀመጥ መልካሙን ስፍራ ያከፋዋል፡፡ በጎ ሕሊና ያለው ሰው ግን ሣር ቤት ውስጥ ቢኖር፤ ያንን የገነት ያህል ያለመልመዋል፡፡ የአስተሳሰብ ተጽእኖ ከሀገር ሀገር፤ ከወገን ወገን፤ ከሰው ሰው ልዩነቱ ጎልቶ የሚታይ ነው፡፡      

        የእግዚአብሔር ቃል (አሳብ) ለአሳባችን፤ ለንግግራችን እንዲሁም ለተግባራችን የሚጠነቀቅልን ነው፡፡ እንዲህ ያለው ጥንቃቄም ለልጆች፤ ለወጣቶችና ለአዛውንቶች በእኩል ፍቅር ነው፡፡ እግዚአብሔር ልጆችን ‹‹የሥጋ ወላጅ አላቸው›› ብሎ ለሥጋና ለደም እንክብካቤ ብቻ አይተዋቸውም፡፡ ቃሉ ‹‹እነሆ ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው፤ የሆድም ፍሬ የእርሱ ዋጋ ነው›› (መዝ. 126÷3) እንደሚል፤ እግዚአብሔር ስለ ልጆች አስተዳደግ የሚጠነቀቅ አባት እንደ ሆነ ልብ እንላለን፡፡ የሥጋ ወላጆች በልጆቻቸው ላይ ባለ መብት ሳይሆኑ ባለ አደራ ናቸው፡፡ ሰጪው እግዚአብሔር ስለ ሆነ፤ ስጦታውን በቃሉ እንደ ቃሉ የመንከባከብ ኃላፊነት የወላጆች ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር በዚህም ጉዳይ ስለሚጠይቀን ወላጆች እንደ ‹‹ባለ አደራ›› ልጆቻቸውን በእግዚአብሔር አሳብ ማሳደግ አለባቸው፡፡ ‹‹ልጅን በሚሄድበት መንገድ ምራው፥ በሸመገለም ጊዜ ከእርሱ ፈቀቅ አይልም›› (ምሳ. 22÷6) ተብሎ እንደ ተፃፈ ልጅነት ትኩረታ ችንንና እንክብካቤያችንን የሚፈልግ መሠረት ነው፡፡

        ማስተማር፤ መምከርና መገሰጽ ወላጆች ለልጆች የሚያደርጉት ቋሚ እንክብካቤ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ልጆችን በተመለከተ ልዩ ጥንቃቄና ብርቱ እንክብካቤ እንደሚያሻቸው ይጠቁማል፡፡ ልጆቻችን ልክ እንደ ሳሙኤል ‹‹ተናገር ባሪያህ ይሰማል›› እያሉ እንዲሰሙት ወላጆች ድርሻቸውን በታማኝነት ሊወጡ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ተግባራዊ ሊሆን የሚችል አንድ ነገር ላካፍላችሁ፡፡ ልጆቻችሁ ማታ ማታ ሲተኙ የምታስተኙባቸው ተረቶች በእግዚአብሔር ቃል ቢቀየሩ፤ ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪካዊ የሆኑ ክፍሎችን ለልጆቻችሁ ጆሮ በሚጥም አቀራረብ ብትነግሯቸው ትጠቅሟቸዋላችሁ፡፡ በእኛ ቤተ ክርስቲያን በልጆች ላይ የተፃፉና በስእል የተደገፉ ጽሑፎች እምብዛም ባይታዩም፤ ቅዱስ ቃሉ ግን ለልጆቻችንም በቂ እንክብካቤ አለው፡፡ ልጆቻችንን የተለያየ ክፉ ነገር ውስጥ ወድቀው ሳናገኛቸው በፊት ለእግዚአብሔር እንጂሸነፉ እንርዳቸው፡፡ ሐዋርያው ‹‹ልጆች ሆይ እጽፍላችኋለሁ›› ሲል ቃሉ ለልጆች በቂ መልእክት እንዳለው ማስተዋል እንችላለን፡፡

       ተወዳጆች ሆይ፤ ጉብዝና (ወጣትነት) በአብዛኛው የልጅነት መከር ነው፡፡ ልጅነት ላይ የዘራነው፤ ወጣትነት ላይ የሚታጨድ ነው፡፡ በስነ ልቦና ወላጆች አቅማቸውን ሁሉ ልጆች ላይ እንዲጠቀሙ ይመከራል፡፡ አንድን ሐረግ ስታስቡ ወደ ፈለግነው አቅጣጫ ልናስይዛቸው የምንችለው ወደ ግንድ ደረጃ ሳይደርስ ነው፡፡ ጠሞ የጠነከረን ግንድ እንዳንቆርጠው እንሳሳለን፤ እንዳናቀናው ደግሞ አቅም እናጣለን፡፡ ዛሬ የምናዝንባቸው ወጣትነቶች አብዛኛን በልጅነት የመልካም እንክብካቤ እጥረት ውጤቶች ናቸው፡፡

       የአንድ ሰው ጠባይና አመለካከት ከሁለት ነገሮች እንደሚቀዳ በስነ ልቦና ይታመናል፡፡ ቤተሰብ (Gene) እና ማኅበረ ሰብ (Environment) ናቸው፡፡ ይህ በሌላ አገላለጽ Nature and Nurture ይባላል፡፡ ቤተሰብ ልጁን በመልካም ክትትል በማሳደግ ልጆችን ከማኅበረሰቡ ክፉ ተጽእኖ መታደግ ይቻላል፡፡ አንድ ገበሬ ያለ ዘር ቡቃያ፤ ያለ ቡቃያ አበባ፤ ያለ አበባ ፍሬ ሊያገኝ አይችልም፡፡ መከሩ ላይ በብዙ ፍሬ መደሰት የሚችለው ዘሩ ታርሶ በለሰለሰ መሬትና ተስማሚ በሆነ ቦታ ሲዘራ ነው፡፡ በልጆቻችሁ ላይ ባለ አደራ ናችሁ፡፡ ልክ እንደ ሳሙኤል ‹‹ብላቴናውም ሳሙኤል እያደገ ሄደ፤ በእግዚአብሔርም በሰውም ፊት ሞገስ እያገኘ ሄደ›› (1 ሳሙ. 2÷26) የሚባልላቸው ልጆችን በመካከላችን ለማየት ከምሬትና ምኞት ያለፈ መንፈሳዊ ተግባር ያሻናል፡፡    

        እግዚአብሔር ወጣቶችን በተመለከተም እንደ ማኅበረሰቡ ‹‹አሁን ደርሰዋል፤ ቢሮጡ ያመልጣሉ፤ ቢመቱ ይጥላሉ›› ብሎ ለራሳቸው ብልሃት አይተዋቸውም፡፡ ለጉብዝና ያለን አመለካከት ከብዙ፤ በጎ ያልሆኑ ነገሮች ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የወጣቶች ሕይወት ጥያቄ ውስጥ እየወደቀ መጥቷል፡፡ ዳሩ ግን የዚህም ሰብሳቢና አሳቢ እግዚአብሔር ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ወጣቶች ‹‹በመለኮት አሳብ›› ሐሴት እንዲያደርጉ ይጋብዛል፡፡  ‹‹እግዚአብሔርን ማሰብ›› ማለት ለእግዚአብሔር ቦታ መስጠት ነው፡፡ ወጣትነት ብዙ ነገሮች የሚናጠቁት የእድሜ ክፍል ነው፡፡ ሦስቱ የመንፈሳዊ ሕይወት ባላንጣዎች ማለትም ሥጋ፣ ሰይጣንና ዓለም (ጠባዩ)፤ ጉብዝናችንን ታጥቀው ይዋጉታል፡፡ ወጣትነት ከብርታት ጋር የተያያዘ ስለሆነ ለብዙ ነገሮች መጠቀሚያ ይሆናል፡፡ ዳሩ ግን ከሁሉ በላይ ዋጋ የከፈለ፣ በረት ተወልዶ፣ የሕማም ሰው ሆኖ፣ በመከራ ተንገላቶ፣ መስቀል ላይ ሞቶ የተቤዠን መድኃኔዓለም ወጣትነታችንን ይፈልገዋል፡፡

       ነፃነት ማለት የምንም ነገር ባሪያ አለመሆን ማለት አይደለም፡፡ ሰው ወይ ላነሰው አልያም ለበለጠው ተገዢ (ባሪያ) ነው፡፡ ሰው ቢገዛ እንኳን እየተገዛ ነው፡፡ ገዢ የሌለበት ሉዓላዊ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡  ብዙ ወጣቶች በነፃነት ሰበብ ብዙ ነገር ያደርጋሉ፡፡ በብዙ ነገሮች ላይም ውሳኔ ያሳልፋሉ፡፡ ዳሩ ግን ለዚያ ለሚያደርጉት ነገር ባሪያ መሆናቸውን ልብ አይሉም፡፡ ከላይ እንደመግቢያ በተጠቀምነው ገጠመኝ፤ ወጣቱ ‹‹ሴት ቦርሳ ውስጥ›› በስርቆት ወድቆ ተገኝቷል፡፡ በእግዚአብሔር አሳብ ላይ ያልወደቀ ወጣትነት፤ ያገኘው ሁሉ ይጥለዋል፡፡ ትርፉም ፍዳ ነው፡፡ ጎበዞች ዘመናዊነትንና ንቃትን ያያያዙበት ነገር ርካሽ ነው፡፡

       ‹‹አራዳ›› እየተባባሉ በነውር የሚተራረዱ፤ ‹‹ነፍሱ›› እየተባባሉ በነፍስ የሚሻሻጡ፤ በቁልምጫ እየተጠራሩ በተግባር የሚካካዱ ወጣቶች ከልብ ያሳዝኑናል፡፡ ያ ደም ግባት፣ እንደዚያ ያለው ጉልበት፣ ያ ቅልጥፍና ጣፋጭ አንደበት፣ እንደዚያ ያለው እውቀት ብርቱ መራቀቅ፣ ያ ልብስ ሁሉ የሚያምርበት ቁመና፣ እንደዚያ ያለው አፍ የማያስከድን የጨዋታ ለዛ ‹‹እግዚአብሔር አሳብ›› ላይ ቢወድቅ፤ በእርሱ መዳፍ ውስጥ ቢያዝ፣ መጠበብ ለበለጠው ጠቢብ፣ ማወቅ ለበረታው አዋቂ ቢሸነፍ ወጣትነት ልክ በውኃ ዳር እንደተተከለች፤ ፍሬዋም ያለማቋረጥ እንደሚሆን ዛፍ በሆነ ነበር፡፡

       ጎበዞች ሆይ፤ በቅዱሳት መጻህፍት ውስጥ ‹‹ እግዚአብሔር ይግዛን›› (መሳ. 8÷23) እንደ ተባለ አሳባችሁ ለእግዚአብሔር አሳብ፤ ዘመናችሁ ለእግዚአብሔር ፈቃድ የተሰጠ ይሁን፡፡ እውቀት ሕይወት ጋር ካላደረሰን፣ ጥበብ ከርኩሰት ካልሰወረን፣ ዘመናዊነት ለሕልውና ዋስትና ካልሆነን ምን ይረባናል? ወጣትነታችን የሚኳለው ኩል፣ የሚደምቅበት ቀሚስ፣ የሚጫማው ጫማ፣ የሚያጠልቀው ቀለበት፣ ከጠራራ የምንጋረድበት ኩፌት ጌታ እግዚአብሔር ነው፡፡ ከጎበዞች ምሬት አንዱ ‹‹የት ወደቅሽ/ህ የሚለኝ አጣሁ›› የሚል ነው፡፡ እኔ ግን አልኳችሁ ‹‹የት ወደቃችሁ?››፤ በእግዚአብሔር አሳብ ላይ መውደቅ (መሸነፍ) ለእኛ ከምንም በላይ ይሻለናል፡፡

        ለሕይወት የሆነው የእግዚአብሔር አሳብ በክርስቶስ ኢየሱስ ይግዛችሁ፡፡ ሐዋርያው ‹‹ጎበዞች ሆይ፤ እጽፍላችኋለሁ›› ሲል እግዚአብሔር ስለ ወጣቶች የሚገደውና መልእክት ያለው አምላክ እንደ ሆነ እንረዳለን፡፡ ነቢዩ ዳዊት ‹‹እጅግ ተጨንቄአለሁ፤ ምሕረቱ ብዙ ነውና በእግዚአብሔር እጅ እንውደቅ፤ በሰው እጅ ግን አልውደቅ›› (2 ሳሙ. 24÷14) እንዳለ፤ የጭንቅ ቀን ሳይመጣ፣ ጉብዝናችንን ሳንከስር፣ ደስ የማያሰኙ ዓመታት ሳይከቡን በእግዚአብሔር እጅ እንውደቅ፡፡  

        እንዲሁ በእድሜ የገፉ አዛውንቶችን ስንመለከት እግዚአብሔር ለእነርሱም አሳቢ ሆኖ እናየዋለን፡፡ ‹‹ብዙ አመት የሕይወት ተሞክሮ አላቸው፤ ከማንም የተሻለ ያውቃሉ›› ብሎ ለሽምግልናቸው እንደማይተዋቸው ከቃሉ እንረዳለን፡፡ ሽምግልናን ስንመለከት የወጣትነት መከሩ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ተወዳጆች ሆይ፤ ሽምግልና የጉብዝና መከር እንዴት ሊሆን እንደሚችል ለማገናዘብ ሞክሩ፡፡        


2 comments:

  1. ሕይወት የክርስቶሰ ባሪያApril 7, 2014 at 5:19 AM

    ወጣትነትን በአገባቡ ካልተጠቀሙበት፣ በተለይም ዕድሜን ከጤና ጋር ለሚሰጠዉ ጌታ በችሮታዉ ብቻ ከተለገሰዉ ዘመን አስራት ማዉጣት ካልተቻለ፣ ሲመሽ በቁጭት መንገብገብ ይሆናል። እኔ ብዙ ወዳጆቼ (እራሴንም ጨምሮ) ቃሉን ድሮ አለመማራቸዉ እንደጌታ ፈቃድ ሕይወታቸዉን ባለመምራታቸዉ በፈተና ቅብብሎሽ ዉስጥ ማለፋቸዉ፣ ትናንትን በጸጸት ሲተርኩና የጠፋዉ ጊዜ የዉስጥ እግር ሲሆንባቸዉ አይቻለሁ። ከዚህ ዓይነት ጸጸት ለመዳን ጊዜዉ አሁን ነዉ ።ወጣቶች ሆይ! በቀን ለኳስ ከምታጠፋት አያሌ ሰዓታት ለቃሉ 5 ደቂቃ ብትመድቡ ጌታችን አብዝቶ የባረካችኋል።

    ReplyDelete
  2. ‹‹አራዳ›› እየተባባሉ በነውር የሚተራረዱ፤ ‹‹ነፍሱ›› እየተባባሉ በነፍስ የሚሻሻጡ፤ በቁልምጫ እየተጠራሩ በተግባር የሚካካዱ ወጣቶች ከልብ ያሳዝኑናል፡፡ ያ ደም ግባት፣ እንደዚያ ያለው ጉልበት፣ ያ ቅልጥፍና ጣፋጭ አንደበት፣ እንደዚያ ያለው እውቀት ብርቱ መራቀቅ፣ ያ ልብስ ሁሉ የሚያምርበት ቁመና፣ እንደዚያ ያለው አፍ የማያስከድን የጨዋታ ለዛ ‹‹እግዚአብሔር አሳብ›› ላይ ቢወድቅ፤ በእርሱ መዳፍ ውስጥ ቢያዝ፣ መጠበብ ለበለጠው ጠቢብ፣ ማወቅ ለበረታው አዋቂ ቢሸነፍ ወጣትነት ልክ በውኃ ዳር እንደተተከለች፤ ፍሬዋም ያለማቋረጥ እንደሚሆን ዛፍ በሆነ ነበር፡፡

    wow zis is really an amazing perception and let God bless all those who contribute for this spiritual blog.

    ReplyDelete