Saturday, March 8, 2014

የጉብዝና ወራት /ክፍል አንድ/

                                        Please Read in PDF: yegubzna werat 1
                                                            
      መግቢያ
                          ቅዳሜ የካቲት 29 ቀን 2006 የምሕረት ዓመት

        በአንድ አጋጣሚ ያገኘሁት ከሀገር ውጪ የሚኖር ሰው ስለ ሕይወት እየጠየኩት እንጨዋወታለን፡፡ ምን ዓይነት ውጥረት ውስጥ እያለፈ እንዳለና ከዚህ የተነሣ ትዳር ለመመስረት እንዳልቻለ ከወሬው መካከል ትኩረት ሰጥቶ፤ ስለዚህ ጉዳይ እየደጋገመ በቁጭት ይነግረኛል፡፡ እኔም ኑሮውን ባልካፈለው እንኳ ወሬውን ልጋራው ብዬ እህ . . እህ . . እያልኩ፤ አናቴን እየወዘወዝኩ አደምጣለሁ፡፡ ታዲያ በገረመኝ ሁኔታ በየጨዋታው መሐል ‹‹ተው እንጂ›› ስለው ‹‹ወጣትነቴን አያስጨርሰኝ እልሃለሁ›› እያለ መሐላ ቢጤ ጣል ያደርጋል፡፡ የፀጉሩን ለውጥ፣ የፊቱን ሽብሻብ፣ የወገቡን ጉብጠት፣ የትንፋሹን ቁርጥ ቁርጥ፣ ቢያቀኑት የሚንቋቋ ማጅራቱን፤ የእድሜውን የትየለሌነት እንኳን እኔ፤ በመነጽር ታግዞ የሚመለከትም አዛውንት ልብ እንደሚለው ግልጥ ነው፡፡ ልቤ ‹‹ምን ነካው?›› ለምዶበት ወይስ ያለፈ ናፍቆት ጸንቶበት ይሆን? እላለሁ፡፡ ልቡ ‹‹እስከ ዶቃ ማሠሪያው ንገረው›› አለው መሰል፤ እየደጋገመ ‹‹ወጣትነቴን አያስጨርሰኝ›› ይላል፡፡ እንደ መንደር ሰው ‹‹አይሻልህም ሕፃንነቴን›› ሊለው ሥጋዬ ዳዳ፤ መንፈስ ግን ልጓም ሆነበት፡፡

       እኔን ወንድሜ! አልኩኝ፡፡ ዛሬ ላይ ቆሞ ለትላንት መኖር፣ የያዙት ደብዝዞ ያለፈውን መከጀል፣ የተሸቃቀጠ ኑሮ፣ እድሜን የማያሳይ ድንግዝግዝ፤ ባልንጀራዬ አሳዘነኝ፡፡ እንደሚገባ ያልኖረበት፣ ተላላ ሆኖ ያለፈበት፣ በጭንቅ የሰበሰበውን በፌዝ የበተነበት፣ ምክር ሬት፣ ተግሳጽ ሞት የሆነበትን ለዛሬ መራራ የዳረገውን ወጣትነቱን ትኩር ብዬ ወደኋላ አየሁት፡፡ በኋላ በእንባ የነገረኝን ቀድሜ በመሐላው ደረስኩበት፡፡ ሙከራ ቅኝቱ፣ ስሜት መዘውሩ የነበረውን ወጣትነቱን አወጋኝ፡፡ የሽምግልና እድሜ ሸክም ማቅለያ ሳይሆን፤ ዕዳ ማቆያ የሆነውን የኑሮ እስታይል /ዘይቤ/ እንደሚገለጥ መጽሐፍ አስነበበኝ፡፡ ‹‹ብትችል ሰርዘው፤ ባትችል እለፈው›› እያለ አገላበጠልኝ፡፡ እንባ ያጋቱ ዓይኖቹ፣ የቁጭት ፍም የተከመረባቸው ጉንጮቹ፣ በጥርሱ መጅ የላመ ከንፈሩ፣ ደግፈኝ . . ደግፈኝ የሚለው አፍንጫው፣ በእጆቹ መዳፍ ልምዥግ የሚያደርጋቸው ጢሞቹ፣ የመፍትሔ ያለህ! የሚመታው ልቡ ሁሉም ፊቴ ተራቆተ፡፡

        ለካ የምናምር ተሸፋፍነን ኖሯል? እናንተ! ይህንን ‹‹የአደባባይ ሽቅርቅር የጓዳ ምንቅርቅር›› ጌታ ለኔ መስታወት አደረገው፡፡ ሃሌ ሉያ! የጭንቅ ቀን ሳይመጣ ለሰበሰብከኝ፡፡ ሃሌ ሉያ! ደስ የማያሳኙ ዓመታቶችን ሳልገናኝ ላገኘኸኝ፡፡ ሃሌ ሉያ! የሚያሳዝነው ጋር ሳልደርስ ቀድመህ ላዘንክልኝ፡፡ ሃሌ ሉያ! ለመፈራገጤ ሰፊ ትከሻ፣ ለመንቀዥቀዤ የተንጣለለ ቅጥር ላለህ፡፡ ሃሌ ሉያ! ‹‹ልጅ ነው›› ብለው ሊያስነውሩኝ፤ ባነሰው ባሪያ ሊያደርጉኝ የቀረቡኝን አዋቂ ሆነህ ለተጋፈጥክልኝ፡፡ ሃሌ ሉያ! ያለማሁ መስሎኝ ሳጠፋ፣ ያወኩ መስሎኝ ስከፋ ጥበብ ሆነህ ላረምከኝ፡፡ ሃሌ ሉያ! ሽሽቴን ቀርበህ፣ ድብቄን ፈልገህ፣ ስጠም አቅንተህ፣ ስዝል አስታመህ፣ ሳዝን አባብለህ አንተን ለመተው ምክንያት ላሳጣኸኝ፡፡ ሃሌ ሉያ! የፍቅር ጥግ፣ የእረፍት ዳርቻ፣ የጥበብ ወሰን፣ የሰላም ማሠሪያ፣ የኃይል ሁሉ ምንጭ፣ የፍለጋዬ መጨረሻ ለሆንከው ኢየሱስ፤ እልልልልልልልለልልልልልልልልልልልልል!!

       እግዚአብሔር ለሚያስተውሉ ‹‹በየአደባባዩ ሰሌዳ፣ በየአጋጣሚው ጠመኔ›› አለው፡፡ እንደ ያህዌ ኤሎሂም አስተማሪ ማነው? ልቤን ክታብ አድርጌ መምህሩ እግር ስር ቁጭ አልኩ፡፡ ከእውቀቱ ውቅያኖስ የማንኪያን ያህል ማስተዋል ጨለፍኩ፡፡ ድንግዝግዙን የምቀዝፍበት፣ ምስቅልቅሉ መሐል አጥርቼ የማይበት ቃል ያለው እግዚአብሔር ይባረክ፡፡ ከጊዜው ፈተና አንዱ ‹‹አለመተያየት›› ነው፡፡ ሰው ሁሉ ኑሮው በስልክ ሽቦ ውስጥ በሚደረግ የቃላት ልውውጥና በማኅበራዊ ድረ-ገፆች መፃፃፍ ላይ እየተመሰረተ መጥቷል፡፡ አንድ ቤት ውስጥ፤ በአንድ ቤተሰብ መካከል የሚኖሩ ወንድማማቾች ዕለት ዕለት ቤት እያደሩ ከተያየን ሳምንት ሞላን እያሉ ነው፡፡ ይህ ይገርመን ይሆናል፡፡

        እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ሰው ከራሱም ጋር ከተያየ ቆይቷል፡፡ ከዚህም በላይ ሰው የእግዚአብሔርን ፊት ለመፈለግ ታክቷል፡፡ ብዙ ሰዎች በተለይ ወጣቶች እንደ አዲስ ማንነታቸውን ‹‹አስተዋውቁኝ›› የሚሉ ይመስላሉ፡፡ ይህንን ጽሑፍ ከመፃፌ ሁለት ቀናት ቀደም ብሎ የምክር አገልግሎት /Counseling/ ፈልጎ አንድ ወጣት መጣ፡፡ ልክ እንደተገናኘን ፈገግ እያለ ‹‹አስተዋውቀኝ›› አለኝ፡፡ ብቻዬን እንደሆንኩ እርግጠኛ ስለነበርኩ ዙሪያዬን መመልከት አላስፈለገኝም፡፡ ፈገግታውን በፈገግታ መለስኩ፡፡ እየቆየን ስናወራ ግን ይህ ወጣት ከራሱ ጋር ‹‹አለመግባባቱን›› ተሸክሞ የሚዞር ምስኪን ነበር፡፡

        ከሰው ጋር ሳይሆን ከራሱ ጋር የሚሸመግለው፤ ውጪውን ሳይሆን ውስጡን የሚያስረዳው ይፈልግ ነበር፡፡ ያልተጨባበጡ አሳቦችን እየነገረኝ እጆቼን ወዘወዛቸው፤ ኑሮአችን እንዲህም አይደል? በሄድኩባቸው ከተሞች በፍቅር የምመለከታቸው ወጣቶች ደቦ ተጠራርተው ፊቴ ድቅን አሉ፡፡ በውስጤ ‹‹ብቻህን አይደለህም›› አልኩ፤ እነዚያ ሰብሳቢ አጥተው የባዘኑ፣ መካሪ አጥተው የጠመሙ፣ ምቾት ሲዖል የሆነባቸው፣ ሱስን ዋሻ ያደረጉ፣ ከራሳቸው እየሰረቁ የሚፈነድቁ፣ በወይን ጠጅ ‹‹አስጡኝ›› የሚል ጨርቅ የመሰሉ፣ ‹‹አራዳ›› የሚል ከረሜላቸውን እየመጠጡ የሚቦርቁ፣ እስፒል ሱሪያቸውን እየጎተቱ ግማሽ ተራቁተው የሚነጥሩ፣ ጉድጓዳቸውን አርቀው የማሱ፣ ሞት በደጅ የሚያደባባቸው፣ ማኅበረሰብና መንግሥት ተቆርቁሮ ያልታደጋቸውን ጎበዞች ሕሊናዬ ዘረዘራቸው፡፡ ግን የወጣቱ ኑሮ ‹‹ሾላ በድፍን›› እንደ ሆነ ማንም ልብ ይለዋል፡፡  

       የማንነት ችግር /ግጭት፣ ክስረት /Identity Crisis/ የአብዛኛው የዓለም ክፍል የወጣቶች ፈተና ነው፡፡ በሕይወት ውስጥ ያለንን አስተዋጽዖ /ልናበረክት የምንችለውን/ ነገር እርግጠኛ አለ መሆን እና ትክክለኛውን እኛነታችንን አለማወቅ፤ ወደ ማንነት ግጭት ውስጥ ይከተናል፡፡ ኤሪክ ኤሪክሰን /ኤሪክ የኤሪክ ልጅ (ይህ ሰው አባቱ ማን እንደ ሆነ ሳያውቅ ስላደገ ራሱን የራሱ ውላጅ፤ ልጅ አድርጎ ይጠራል)/ በማኅበረሰብ ስነ ልቦና እድገት ጥናቱ የሚታወቅ ሲሆን፤ ሰዎች feelings of identity versus role confusion የሚያስተናግዱበት የእድሜ ክልል ብሎ በሚጠራው ከ12 እስከ 18 ባለው ጊዜ  ውስጥ የማንነት ግጭት እንደሚፈጠር ያስረዳል፡፡ በዚህ እድሜ ሰዎች ራሳቸውን ለመቻል፣ በራሳቸው ለመቆምና ከሌሎች የአስተሳሰብ ተጽእኖና ጥገኝነት ለመላቀቅ በሚያደርጉት መፍጨርጨር ሚዛንን መሳት ሊከሰት፣ በራሳቸው ምርጫ እርግጠኝነት ማጣት፤ ደኅንነት አልባነት ስሜትን ማስተናገድ እንዲሁም በነገዎች ላይ የጠራ እይታን ማጣት ሊያስተናግዱ ይችላሉ፡፡ ከዚህ የተነሣ ያልጠራ የደፈረሰ፣ ያልተለየ ድብልቅ ሕይወታቸውን የሚፈትን ይሆናል፡፡ በወጣቶች ሕይወት እየተንከባለለ የመጣው ነገር ዛሬ ለሚተገብሩት የግፊት ኃይል ይሆናል፡፡

       ለወጣቶች የዛሬ ማንነት አልፈው የመጡበት የሕይወት መንገድ ተጽእኖው ብርቱ እንደ ሆነ ብዙ የስነ ልቦና እንዲሁም የማኅበረሰብ ጥናቶች ይነግሩናል፡፡ የጉብዝና ወራት የልጅነት መከሩ እንደ ሆነ ይታሰባል፡፡ ሽምግልና ደግሞ የወጣትነት ኑሮ መከሩ ይሆናል፡፡ የልጅ አስተዳደግ የወጣቶችን ሰብእና የመወሰን አቅም እንዳለው ሁሉ፤ የጉብዝና ወራት አያያዝም ሽምግልናን የደስታ አልያም የእንባ መደምደሚያ ሊያደርገው አቅም አለው፡፡ የወጣትነትን ወራት ተከትሎ የመጣውን ከንቱ ልማድ የምናስወግድበት፤ ለመጪው ሽምግልና ደግሞ በጎውን የምንሰበስብበት እንዲሁም በእነዚህ በሁለቱ መካከል ሚዛናችንን ጠብቀን የምንሰማራበት ሕይወት ይኖረን ዘንድ ‹‹ብርቱ አሳብ›› ያስፈልገናል፡፡   

        በአንድ ሰው ውስጥ ያለው በጎም መጥፎም ኃይል ‹‹አሳቡ›› ነው፡፡ በአእምሮአችን ውስጥ ቦታ የያዘ፤ አመለካከት የምንለውን ስፍራ የተቆጣጠረ አሳብ በውድ ባይሆን እንኳ በግድ ባሪያ ያደርገናል፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ ‹‹የጭንቀት ቀን ሳይመጣ በጕብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ›› (መክ. 12÷1) ይላል፡፡ እናንተ የምታስቡትን ያንን ናችሁ፡፡ ተግባር ከአሳብ የሚቀዳ ሲሆን፤ መራራውን የማጣፈጥና ጣፋጩን የማምረር አቅም አለው፡፡ ዓለም በአሳባውያን ተጽእኖ ስር እንዳለች በግልጥ እናያለን፡፡ በየእለቱ የምንመለከታቸው የፈጠራ ሥራዎች፣ የሳይንስ ግኝቶች፣ የመጠበብ ጥማቶች፣ ወደ እውቀት የሚደረጉ ሩጫዎች ሁሉም የአስተሳሰብን ክቡርነትና ጉልበት ይመሰክራሉ፡፡ ሰዎች ‹‹አጥፍተው እንዲጠፉ›› ሌሎችን የሚያሳምኑት፤ አሳማኝ አሳብ የማቅረብ፣ የሰውን አተያይ በበለጠ አሳብ የመቃኘት ጉልበት ሰላላቸው ነው፡፡ ጡንቻ ከጠመዘዘው፤ አሳብ የጠመዘዘውን ማቅናት ጭንቅ ነው፡፡  

                                     /ተከታታይ ትምህርት/

2 comments:

  1. ሕይወት የክርስቶስ ባሪያApril 7, 2014 at 5:21 AM

    ወጣትነትን በአገባቡ ካልተጠቀሙበት፣ በተለይም ዕድሜን ከጤና ጋር ለሚሰጠዉ ጌታ በችሮታዉ ብቻ ከተለገሰዉ ዘመን አስራት ማዉጣት ካልተቻለ፣ ሲመሽ በቁጭት መንገብገብ ይሆናል። እኔ ብዙ ወዳጆቼ (እራሴንም ጨምሮ) ቃሉን ድሮ አለመማራቸዉ እንደጌታ ፈቃድ ሕይወታቸዉን ባለመምራታቸዉ በፈተና ቅብብሎሽ ዉስጥ ማለፋቸዉ፣ ትናንትን በጸጸት ሲተርኩና የጠፋዉ ጊዜ የዉስጥ እግር ሲሆንባቸዉ አይቻለሁ። ከዚህ ዓይነት ጸጸት ለመዳን ጊዜዉ አሁን ነዉ ።ወጣቶች ሆይ! በቀን ለኳስ ከምታጠፋት አያሌ ሰዓታት ለቃሉ 5 ደቂቃ ብትመድቡ ጌታችን አብዝቶ የባረካችኋል።

    ReplyDelete
  2. በአንድ ሰው ውስጥ ያለው በጎም መጥፎም ኃይል ‹‹አሳቡ›› ነው፡፡ በአእምሮአችን ውስጥ ቦታ የያዘ፤ አመለካከት የምንለውን ስፍራ የተቆጣጠረ አሳብ በውድ ባይሆን እንኳ በግድ ባሪያ ያደርገናል. dat is rly true nd let God bless u!

    ReplyDelete