Tuesday, March 4, 2014

ማረፍን ማን ይሰጠኛል?

                                   Please Read in PDF: Marefn man yesetegnal?
                                                    

                              
                                            ማክሰኞ የካቲት 25 ቀን 2006 የምሕረት ዓመት

            ጌታ ሆይ÷ አንተ ታላቅ ነህ÷ ውዳሴም ያለ ገደብ ይገባሃል፤ ኃይልህ ታላቅ÷ ጥበብህም የማይለካ ነው፡፡ የፍጥረትህ ደካማ ክፍል የሆነው የሰው ልጅ÷ ሟችነቱንም ከራሱ ጋር የተሸከመው የሰው ልጅ÷ የኃጢአቱን ምስክርነት÷ የአንተንም የትዕቢተኞችን መቃወም ማስረጃ የተሸከመው የሰው ልጅ÷ አንተን ነው ማወደስ የሚፈልገው፡፡ እንግዲህ ይህ የፍጥረታት ደካማ ክፍል የሆነው የሰው ልጅ ሊያወድስህ ይፈልጋል፡፡

            ‹‹ከጌታ ከራሱ በስተቀር ማን ነው ሌላ ጌታ፤ ወይስ ከእግዚአብሔር ውጭ እግዚአብሔርስ ማን ነው?›› እጅግ ታላቅ፣ እጅጉን የላቀ፣ እጅግ ኃያል፣ እጅግ ሁሉን ቻይ፣ እጅጉን መሐሪ፣ እጅግ ጻድቅ፣ እጅግ የተሰወርክ እጅግ የቀረብክ፣ እጅግ ውብና እጅግ ብርቱ፣ ጽኑና የማትጨበጥ፣ የማትለወጥና ሁሉን የምትለውጥ፣ አዲስ ሆነህ የማታውቅ፣ የማታረጅ፣ ሁሉን የምታድስ፣ እነርሱ ሳያውቁት ትዕቢተኞችን የምታስረጅ፣ ምንጊዜም የምትሠራ፣ ምንጊዜም የምታርፍ፣ የምትሰበስብ፣ ምንም የማያሻህ፣ እየደገፍክ የምትይዝ፣ የምትሞላ፣ የምትከላከልም፣ የምትፈጥር፣ የምትመግብ፣ የምታጠናቅቅ፣ የምትፈልግ፣ ምንም ሳይጎድልህ፡፡

             አንተ ታፈቅራለህ ነገር ግን ያለ ስሜት ነው፤ ቅናትህ መሥጋት የለበትም፡፡ ጸጸትህ ቁጭት አያውቅም፡፡ ቁጣህም የተረጋጋ ነው፡፡ ሥራዎችህን እንጂ እቅድህን አትቀይርም፤ ፈጽሞ ሳይጠፋብህ፤ ያገኘኸውን ትጨብጣለህ፡፡ ምንም ባያሻህም በማግኘትህ ትደሰታለህ፡፡ ስስትን ባታውቅም፤ ብድርን ከነወለዱ ትፈልጋለህ፡፡ ባለእዳ እስክትሆን አብዝተው የሚከፍሉህ፤ ለመሆኑ ያንተ ቢኖረው ካንተ ያልሆነ ሊኖረው የሚችል ማን ነው? ለማንም ባለ እዳ ሳትሆን እዳህን ትከፍላለህ ስትመልስም ምንም አይጎድልብህም፡፡ ኦ አምላኬ ሕይወቴ ቅዱሱ ትፍስሕቴ ሆይ ምን እያልን ይሆን? ስለ አንተ ሲናገር ሰው ምን ማለት ይችላል? ስለ አንተ አብዝተው እንኳን የሚናገሩ እንደ ዲዳ ናቸው - ስለ አንተ የማይናገሩ ወዮላቸው!

            በአንተ ማረፍን ማን ይሰጠኛል? ልቦናዬ ይጥለቀለቅ ዘንድ፣ ክፋቴን እረሳ ዘንድ፣ አንተን ብቸኛው ሀብቴን አቅፍ ዘንድ! ወደ እኔ መግባትህን ማን ይሰጠኛል? አንተ ለእኔ ምንድነህ? እንድናገር በርኅራኄህ አንደበቴን ዳስሰው እንዳፈቅርህ ግድ የምትለኝ፤ ምላሽ ባልሰጥህ ቁጣህ የሚነደውና ከለላ የሚያሳጣኝ፤ እኔ ለአንተ ምንድነኝ? አንተን አለማፍቀር ራሱ ጉስቁልና አይደለምን? ኦ! አቤቱ ጌታዬ አምላኬ፤ በርኅሩኅነትህ መልስልኝ፤ አንተ ለእኔ ማን ነህ? ‹‹ለነፍሴ፤ እኔ መድኃኒትሽ ነኝ፤ በላት›› እሰማህ ዘንድ ተናገረኝ፤ እነሆ በፊትህ የልቦናዬ ጆሮዎች ተከፍተዋል፤ አቤቱ ጌታዬ፤ ክፈትና ‹‹ለነፍሴ እኔ መድኃኒትሽ ነኝ፤ በላት›› ይህን ድምጽ በሩጫ ተከትዬ በመጨረሻ አንተን ልይዝህ እፈልጋለሁ፤ ሰምቼ ወደ አንተ ልሩጥ÷ በአንተም ላይ ራሴን ልጣል÷ እባክህን ፊትህን ከእኔ አትሰውር፤ ላለመሞት ልሙት፤ ብቻ ፊትህን ልይ፡፡

             አንተ ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ ነፍሴ ለማደሪያህ እጅግ ጠባብ ናት፡፡ ታድርባት ዘንድ÷ በአንተው ትስፋ፤ እየፈራረሰች ነው÷ አንተው መታደስ ሁናት፡፡ ውስጤ የሚያስከፋህ መቃብር ነው፤ መተላለፌን አውቃለሁ፤ ኃጢአቴንም እናዘዛለሁ፤ ነገር ግን ከዚህ ሁሉ ማን ያነጻኛል? ወይስ ካንተስ በቀር ጌታ ሆይ ወደ ማን ልጩኽ? ‹‹ከማላስተውለው ስውር ኃጢአቴ አንጻኝ›› ጌታ ሆይ ‹‹ከማያውቀውም ኃጢአት አገልጋይህን ጠብቅ›› ‹‹አምናለሁም÷ ስለዚህ እናገራለሁ›› ሆኖም ግን ጌታ ሆይ ከአንተ የተሰወረ የለምና በአንተ ላይ የፈጸምኩትን መተላለፍ አልተናዘዝኩ ይሆን? አቤቱ አምላኬ÷ የልቤንስ ኃጢአት አልተውክልኝም? ከአንተ ጋር በፍርድህ አልጣላም÷ አንተ እኮ እውነት ነህ ራሴን አላታልልም፤ በደለኛነቴ ከአረማመዴ ይታወቃልና ከአንተ ጋር በፍርድህ አልጣላም፡፡ አቤቱ አንተ ኃጢአትንስ ብትቆጥር ኖሮ÷ ጌታ ሆይ÷ ፊትህ ማን ይቆማል?

            ጌታ ሆይ÷ ጸሎቴን ስማ፤ ነፍሴ በሕግህ ስር አትራድ፡፡ ከበዛውም የስሕተት መንገዴ÷ ስከተለው ከነበረው የሚያማልል ነገር ሁሉ በላይ ጣፋጭ ሆኖ በመለሰኝ በምሕረትህ ስር ስናዘዝም÷ በሁለንተናዬ አንተን ማፍቀር እንድችል÷ በሙሉ ልቤም እጆችህን እንድጨብጥ÷ ከሁሉም ፈተና እስከ ፍጻሜው ድረስ ታወጣኝ ዘንድ፤ በፍርሃት አልራድ፡፡ አቤቱ÷ ንጉሤና አምላኬ የሆንክ ጌታ ሆይ÷ ለአንተ አገልግሎት ማንኛውም በልጅነት የተማርኩት ማንኛውም ነገር ጠቃሚ ቢሆን . . . የምናገረውን÷ የምጽፈውን÷ የማሰላውን÷ ለአንተ አገልግሎት አቀርባለሁ፡፡

            ታዲያ÷ አንተ የምትሞላቸው÷ ሰማይና ምድር ይችሉህ ይሆን? ወይንም ሞልተሃቸው÷ ሊሸከሙህ ስለማይችሉ÷ የሚተርፍ የአንተ ክፍል ይኖራልን? ሰማይና ምድር ከሞላ በኋላስ ካንተ የሚቀረውን ክፍል ወዴት ለይተህ ታስቀምጠዋለህ? የምትሞላውን እየተሸከምክ ስለምትሞላው÷ አንተ ሁሉን የምትይዝ÷ ምንም ምን እንዲይዝህ አያስፈልግም አይደለምን? አንተ የሚላሃቸው የሸክላ እቃዎች አይደሉም ላንተ ጽናትን የሚሰጡት፡፡ ቢሰበሩም አንተ ወደ ውጪ አትፈስም፡፡ በእኛ ውስጥ ስትሰራጭ አንተ ወደ ምድር አትወድቅም፤ ይልቁንም ታነሣናለህ እንጂ፤ አንተ አትበታተንም÷ ይልቁንም ትሰበስበናለህ እንጂ፡፡

           ምነው ዘግይቼ አንተን ማፍቀሬ! ኦ ጥንታዊም አዲስም የሆንክ ውበት÷ ምነው ዘግይዜ አንተን ማፍቀሬ! እነሆ አንተ በውስጤ እያለህ እኔ ከራሴ ውጭ ነበርኩ፡፡ የማስጠላው እኔ፤ ውብ አድርገህ በፈጠርካቸው ነገሮች መካከል ያለ ማስተዋል ስጣደፍ አንተ ከእኔ ጋር ነበርክ፤ እኔ ግን ከአንተ ጋር አልነበርኩም፡፡ እነዚህ ነገሮች ከአንተ አርቀውኛል፤ ሆኖም እነርሱም ባንተ ባይሆኑ ኖሮ መኖር ባልቻሉ ነበር፡፡ ድምጽህን ከፍ አድርገህ ጮህክልኝ፤ ጠራኸኝም፡፡ ድንቁርናዬንም በኃይልህ ከፈትከው፡፡ ጸዳልህን ልከህ ሸፈነኝ፤ አበራህልኝም፤ ዓይነ ሥውርነቴንም ገፈፍከው፡፡ መዓዛህን ለእኔ ተነፈስክ፤ ተንፍሼም ሳብኩት፤ ተከትዬህም ቃተትኩ፡፡ ቀመስኩህ፤ ተራብኩ፤ ተጠማሁም፡፡ ዳሰስከኝ፤ ለሰላምህ ተቃጠልኩ፡፡ 


                   /ዘካርያስ ደበበ፤ ቅዱስ አውግስጢኖስ ኑዛዜ (አዲስ አበባ፤ 2006 ዓ.ም)/  

4 comments:

  1. ድንቁርናዬንም በኃይልህ ከፈትከው፡፡ ጸዳልህን ልከህ ሸፈነኝ፤ አበራህልኝም፤ ዓይነ ሥውርነቴንም ገፈፍከው፡፡ መዓዛህን ለእኔ ተነፈስክ፤ ተንፍሼም ሳብኩት፤ ተከትዬህም ቃተትኩ፡፡ ቀመስኩህ፤ ተራብኩ፤ ተጠማሁም፡፡ ዳሰስከኝ፤ ለሰላምህ ተቃጠልኩ፡፡ let God bless u!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!

    ReplyDelete
  2. ድምጽህን ከፍ አድርገህ ጮህክልኝ፤ ጠራኸኝም፡፡ ድንቁርናዬንም በኃይልህ ከፈትከው፡፡ ጸዳልህን ልከህ ሸፈነኝ፤ አበራህልኝም፤ ዓይነ ሥውርነቴንም ገፈፍከው፡፡ መዓዛህን ለእኔ ተነፈስክ፤ ተንፍሼም ሳብኩት፤ ተከትዬህም ቃተትኩ፡፡ ቀመስኩህ፤ ተራብኩ፤ ተጠማሁም፡፡ ዳሰስከኝ፤ ለሰላምህ ተቃጠልኩ፡፡ endet yale erkata new! Egziabher yebarkachehu!

    ReplyDelete